ከክርስቶስ ልደት በኋላ ፡ በአንደኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በንግሥት ህንደኬ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የገባው የጥምቀት ዜና በአራት ኛው ክፍለ ዘመን በኦብርሃና አጽብሐ ዘመነ መንግሥት በአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ስብከት ተስፋፍቶ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስብከተ ወንጌልን አምኖ ጥምቀትንና ክርስትናን ተቀበለ፡፡ እጅግ በጣም ጥቂት የሆኑ የአይሁድ (ጁዳይዝም) ሃይማኖት አማኞች በወንጌል አናምንም ክርስቲያን አንሆንም ፣ ሕገ ኦሪትን አንለቅም በማለት በ፱፻፹፪ (982) ዓ. ዓለም ግደማ በቀዳማዊ ምኒልክ ዘመን የመጣውን እምነተ እሥራኤል መከተልን ቀጠሉ፡፡
የክርስትና ሃይማኖት አንቀበልም ብለው በአይሁድ (የኦሪት) እምነታቸው የፀኑት ሕዝቦች በነገሥታቱ ትእዛዝ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ከሆነችው ከአክሱምና ከዙሪያዋ አየለቀቁ በመውጣት በወልቃይት፣ በሰሜንና ፥ በወገራ ፣ በደምቢያ ፥ ዛአገው ፥ በላስታ ፥ በሰቆጣና በመሳሰሉት ሊኖሩ እንደሚችሉ ስለ ተገለጸላቸው አክሱምንና አካባቢዋን እየለቀቁ በመሔድ ተበታትነው ይኖሩ ጀመረ ። በዚህ ምክንያት ፈላሻ ተባሉ ፡፡ ፈላሻዎች እምነታቸው ሕገ ኦሪት ቢሆንም ኢትዮጵያዊነታቸው የተረጋገጠ ስለሆነ ፥ በመንግሥት ትእዛዝ በተፈቀደላቸውና በሚኖሩባቸው በሰሜንና በላስታ እንዲሁም በተለያዩ ሥፍራዎች ለረዥም ጊዜ በመኖር ቁጥራቸው እየበዛ ሔደ ፡፡ የሕዝቡ ቁጥር አየበዛ ሲሄድም ለአክሱም መንግሥት ግብር እየክፈለ በሰላም ይኖር ጀመር፡፡
በዘጠነኛው ምዕተ ዓመት ፰፻፶፪ (852) ዓ.ም ገደማ ዮዲት የተባለችው የጌዴዎን ልጅ ንግሥት ዘሯ ከፈላሻ ውስጥ በመሆኑ ፈላሾችን ይዛ ተነሣች። በላስታ የሚኖር የክርስትያን ሃይማኖት ተከታይና የቡግና ባላባት በዮዲት ውበትና ኃይለኛነት ስለተማረከ ሃያማኖቱን ለውጦ አገባት። በዚህም ምክንያት ተጨማሪ ኃይል ለማግኘት ቻለች ፡፡ በዚህ ዘመን በአክሱም ዙፋን ላይ የተቀመጠው የንጉሥ ድግናዣን ልጅ አንበሳ ውድም ነበር ። አንበሳ ውድም አባቱ ሲሞት ገና የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ቢሆንም የንግሥና ሥልጣኑን ያዘ፡፡ ዮዲትም ንጉሡ ገና ሕፃን ስለሆነ የሧን ጥቃት የሚቋቋም ኃይል ሊያሰባስብ እንደማይችል በመገመት አጋጣሚውን ተጠቅማ ልትወጋው አሰበች፡፡
በዚያን ጊዜ አክሱም የእስልምናን ሃይማኖት ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት የተነሣ ጠረፎቿ በመወረራቸው በቀይ ባሕር የነበራትን የበላይነት ያጣችበት ወቅት ነበር ፡፡ ይህች የክርስቲያን ባላጋራ የሆነች ንግሥት ፈላሾች የሆኑትን ሁሉ በአንድነት አስባስባና አሥተባብራ የአክሱም ንጉሥ አንበሳ ውድምን ለመውጋት ተነሣች ፡፡ ከላስታ ፣ ስሜንና ወልቃይት የተሰበሰቡትን ፈላሾችና ሌሎችም ቀሥቅሣና አስፈራርታ በማሥነሣት ብዙ ሠራዊት እየመራች ወደ አክሱም ዘመተች ፡፡ ወደ አክሱም በምትጓዝበት ጊዜ ያለፈችበትን ሥፍራ ሁሉ ሠራዊቷ ይመዘብርና ያጠፋ ነበር ። አብዛኛዎቹ አብያተ ክርስቲያናትና ሌሎችም ውድ የሆኑ የባህል ቅርሶች የተቃጠሉትና የወደሙት በዮዲት ጭካኔ የተሞላበት ወረራ ነበር ፡፡ ብዙ ጊዜ አምረውና ደምቀው ግርማ ሞገስ የነበራቸው አብያተ ክርስትያናትና ሐውልቶች፡ ጭራሽ ከወደሙት ሌላ ለታሪክ ምሥክርነት በእሳት ጋይተው ፍርስራሻቸው ብቻ የሚታየው ብዙ ናቸው፡፡
ብዙ ክርስትያኖች ሲጨፈጨፉና የቀሩትንም በታላቅ አደጋና ሥጋት ተውጠው የመከራ ዘመናት አሳልፈዋል፡፡ የዮዲት ፍላጉት የክርስትና ሃያማኖትንን አጥፍታ የአይሁድን እምነት ለማስፈን ነበር፡፡ ይህን በስፋት ይካሄድ የነበረውን ጭፍጨፋ ለመቋቋም የተሳናቸውና በሥጋት ላያ ወድቀው የነበሩት የአክሱም መሳፍንትና መኳንንት ፋታና ጊዜ አግኝተው መልሰው ለማጥቃት እስኪችሉ ድረስ ሕፃኑን ንጉስ ይዘው ሸዋ ውስጥ ወደሚገኘው ወደ መንዝ ሸሹ፡፡ መንዝ የተመረጠበትም ዋናው ምክንያት የመልክዓ ምድሩ አቀማመጥ ገደላማና ዋሻ በመሆኑ ጠላት ስለማይደፍረው ፥ ገፍቶም ቢመጣ ለመከላከል አመቺ በመመሆኑ ነበር፡፡
ዮዲት የክርስትናን ሃይማኖት አጥፍታ የፈላሻን ሃይማኖት በሰፊው እንዲሰበክና እንዲስፋፋ ስለፈለገች በአክሱም ሕዝቦች የተገነባውንና ሁለት ሺህ ዓመታት ያህል አብቦ የቆየውን ሥልጣኔና የሥልጣኔ ውጤት የሆኑትን ታሪካውያን ሥራዎች ማፈራረሷን ተያያዘችው፡፡ አብያተ ክርስቲያናትን ማቃጠልና ካህናትን መግደል የዕለት ሥራዋ ሆነ፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከተረፉትና እስካሁን ድረስ ካሉት ጥቂቶች በስተቀር ሐውልቶችን ውብ የሆኑ የሥነ ጥበብ ቅርሶችንሞ አፈራርሳለች፤ አብያተ ክርስትያናትን አቃጥላለች ። የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ተራው ሕዝብና ቄሶች ተሰየፉ ። የመንግሥት ዘርነት የነበራቸው የመሳፍንት ልጆችም መንግሥቱን አንዳይቀናቀኑና አንዳይሸፍቱ ሕዝቡንም እንዳያነሣሡ ተብሎ ወደ ደብረ ዳሞ ተራራ አየተወሰዱ በእስር እንዲቀመጡ ይደረግ ነበር።
በቆየው ሥርዓት በዚህ ገዳም ውስጥ የመሳፍንት ልጆች በቁም አስረኛነት አየተጠበቁ ይቆዩና ንጉሡ ሲሞት ከመሳፍንቱ ውስጥ ሕዝቡ የመረጠው ይነግሥ ነበር ፡፡ በዚሁ ምክንያት የተሰበሰቡበትን ፬፻ (400) የሚሆኑ የመሳፍንት ልጆች በጅምላ አሳረደቻቸው። ዮዲት በፈጸመችው ጭካኔ ሥራና ከፍተኛ ጥረት የተነሣ ተግባሯንና ክፋትዋን የሚገልጹ የተለያዩ ቅጥያ ስሞች ተስጥቷታል። በትግራይ ሕዝብ ጉዲት (ጉደኛ) በአፋር ሕዝብ ጋፅዋ (አስፈሪ አውሬ) በመባል ስትታወቅ በአማራ ሕዝብም እሳቶ (የምታቃጥል) ብለዋታል፡፡ ጉዲት ሕፃኑን ንጉሥ አንበሳ ውድምን በመንዝ የመደበቁን ዜና በሰማች ጊዜ ኃይሉን ሰብሮ እሱን ማርኮ እንዲያመጣ ጦር ልካ ነበር ነገር ግን የላከችው ሠራዊት በመሸነፉ ሐሳቧ ሳይሰምር ቀረ ፡፡ ስለዚህ አንበሳ ውድምንና ተከታዮቹን አጥፍታ እርካታ ለማግኘት በማሰብ ራሷ ሠራዊቷን እየመራች ወደ መንዝ ዘመተች። አንበሳ ውድምና ተከታዮቹ ግን ለማጥቃት ይበልጥ አስቸጋሪ ወደ ሆነውና እዚያው ሸዋ ውስጥ ወደሚገኘው ወደ መርሐቤቴ ሸሹ። ዮዲትም በዚሁ ሳትገታ ልትከታተለው ሞክራ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከመሬቱ አቀማመጥ አስቸጋሪነት ሌላ የንጉሡ ወታደሮች የመንዝና የመርሐቤቴ ሕዝብ በየጊዜው ያደርሱባት የነበረው ጥቃት አንድ ላይ ተዳምረው ስሳደክሚት ዓላማዋ ሳይሳካላት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ እንደገና እንድትመለስ ተገደደች ፡፡ ከዚህ በሇላ ለ፲፫ (13) ዓመታት ስትገዛ ቆየች፡፡
ይህች ጨካኝ ንግሥት አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ቅርሶች ያጠፋችበትን የ፵ (40) ዓመታት ዕድሜ ገዝታ ማክተሚያ ላይ የእብርሃ ወአጽብሐን ቤተክርስቲያን አቃጥላ በምትመለስበት ጊዜ እግዚአብሔር መንገዷን አሳስቶ አዲንፋስ ከሚባለው ቦታ ከፍተኛና አስፈሪ አውሎ ነፋስ አስነሥቶ ወርውሮ አደካውህ ከሚባለው ቦታ ላይ አንደ ጣላትና በዚሁ ምክንያት አንደ ሞተች ብዙ ሊቃውንት ይናገራሉ። መቃብሯም ከውቅሮ ከተማ በታች በሚገኘው አደካውህ አጠገብ የድንጋይ ምልክት ተቀምጦበት ይገኛል፡፡
ምንጭ:-
1) “የኢትዮጵያ ሥልጣኔ” ፣ በላይ ግደይ፣ መጋቢት ፲፱፻፹፫
2) “ቅዱሳን መካናት በኢትዮጵያ”፣ ዘመድኩን በቀለ፣ የካቲት ፩፱፱፪
3) “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ታሪክ”፣ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ ሴኔ ፲፱፻፸፬
One Comment
በጣም ደስ የሚል ታሪክ ማወቅ የሚገባን ታሪክ ነው::