የደርግ መንግሥትን ለመደምሰስ ሲታገሉ የነበሩ ከደርዘን በላይ የሚሆኑ ድርጅቶች ነበሩ። ኢህአዴግ፣ ኦነግ እና ኢህአፓን የመሳሰሉት የታጠቀ ሰራዊት አስከትተው ሲዋጉ ነበር። አንዳንዶቹ ግን ሰራዊት ሳይኖራቸው በደርግ መንግሥት ላይ አደገኛ ፕሮፓጋንዳዎችንና ስውር የውስጥ ጥቃቶችን ሲያካሂዱ ነበር። ከነዚህም ውስጥ በብዙዎች ዘንድ ልዩ ትዝታን ጥሎ ያለፈው ድርጅት “የኢትዮጵያ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ትብብር” (በእንግሊዝኛው ምህጻር EPDA) ይባላል። ይህ ድርጅት በሲ.አይ.ኤ. ድጋፍ የተቋቋመ መሆኑ በደንብ ይታወቃል። የአሜሪካ መንግሥት በጊዜው ከፍተኛ የተባለ በጀት በመመደብ ይደጉመው ነበር።
ኢፒዲኤ ይበልጥ የሚታወሰው መሰረቱን በካርቱም ከተማ ባደረገው Radio Free Ethiopia ሲያሰራጨው በነበረው ፕሮግራም ነው። በዚህ ፕሮግራም የተነሳ የደርግ መንግሥት ከሱዳን መንግሥት ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ለጎብኝት ወደ ውጪ በሚሄዱበት ወቅት በልዩ ልዩ ዘዴዎች እያባበለ ደርግን እንዲከዱ ያደርግ ነበር። እነዚህ ባለስልጣናት ደርግን አውግዘው ከስርዓቱ ጋር መለያየታቸውን ሲያስታውቁ ድርጅቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለደህንነታቸው አስተማማኝ ወደ ሆኑት የምዕራብ ሀገራት ያሸጋግራቸው ነበር። በሌላም በኩል ኢፒዲኤ ህዝቡ በደርግ መንግሥት ላይ እንዲነሳሳ የሚቀሰቅሱ በራሪ ጽሑፎችን በድብቅ ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባ ያሰራጭ ነበር። ይሁንና በአንድ ወቅት ለዚህ ተግባር መልምሎአቸው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት እነ ደጃዝማች አሰጋኽኝ አርአያ ያሉበት ቡድን በደርግ የደህንነት ሃይሎች በቁጥጥር ስር በመዋሉ የቡድኑ አባላት ተይዘው ተረሽነዋል።
ኢፒዲኤ ግንቦት 8/1981 ተካሂዶ የከሸፈውንም መፈንቅለ መንግሥት በማቀናባር ረገድ ከፍተኛ ሚና ነበረው። በተጨማሪም “የኢትዮጵያ ነጻ ወታደሮች ድርጅት” የተባለ እና እነ ኮሎኔል እምሩ ወንዴ እና ሻለቃ ዮሴፍ ያዘው የነበሩበት የራሱን ወታደራዊ ክንፍ ለመፍጠር ችሎ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን በድርጅቱ አመራር እና በወታደራዊ ክንፉ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት የተነሳ ወታደራዊ ክንፉ ከኢፒዲኤ ተገንጥሎ በራሱ ይንቀሳቀስ ነበር (ኮሎኔል እምሩ ወንዴ እስከ 1980ዎቹ መጨረሻ ድረስ የከፋኝ የኢትዮጵያ ህዝብ ንቅናቄ የተሰኘ ታጣቂ ቡድን ነበራቸው፤ አሁን ግን እርሳቸውም ሆኑ ድርጅታቸው የት እንዳሉ አናውቅም)።
ኢፒዴኤ እስከ ደርግ መውደቅ ድረስ በሰፊው ሲንቀሳቀስ ነበር። ከኢህአፓ፣ ከኢዲዩ እና ከመኢሶን ጋር በመሆን ኢዴኃቅ (የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ቅንጅት) የተባለውን ጥምረት መስርቷል። ሆኖም በደርግ ውድቀት ዋዜማ የድርጅቱ አመራር “የደረጄ ዴሬሳ ቡድን” እና “የክፍሌ ወዳጆ ቡድን” ተብሎ ለሁለት ተከፍሎ ነበር። በክፍሌ ወዳጆ የሚመራው ቡድን ስሙን ENDO በማለት ቀይሮ በሰኔ ወር 1983 በተካሄደው የሰላምና የዲሞክራሲ ኮንፈረንስ ተካፍሏል። የደረጄ ዴሬሳ ቡድን ግን እዚያው ውጭ ቀርቶ እነ ክፍሌ ወዳጆን ሲያወግዝ ነበር። ደረጄ ዴሬሳ በ1985 ከሞተ እና አቶ ክፍሌ ወዳጆ የህገ መንግሥቱ አርቃቂ ኮሚሽን አባል ከሆኑ በኋላ ግን ሁለቱም ቡድኖች በይፋ ትግል ማቆማቸውን ሳያስታውቁ በዚያው ጠፍተዋል።
ኢፒዲኤ በጊዜው በደርግ ላይ ያኮረፉ በርካታ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦችን ለማሰባሰብ ችሎ ነበር። ዛሬ የምናከብራቸው በርካታ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ታዋቂ ምሁራን ከዚህ ድርጅት ጋራ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ነበራቸው። ታዲያ እነዚህ ግለሰቦች በጊዜ ሂደት በአቋም ተለያይተው በተራራቀ የፖለቲካ ጽንፍ ውስጥ ይገኛሉ። አቶ ክፍሌ ወዳጆ፣ ዶ/ር ደጃዝማች ዘውዴ ገብረሥላሤ፣ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ፣ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ፣ ሻለቃ ዮሴፍ ያዘው፤ ዶ/ር አደም አብደላ፤ አቶ ነቢዩ ሳሙኤል፣ አቶ ብርሃኑ ዴሬሳ (የቀድሞው የአዲስ አበባ ከንቲባ) እና ሌሎችም በአንድ ወቅት በዚህ ድርጅት ታቅፈው ነበር። እናም “እገሌ ሲ.አይ.ኤ ነው” እየተባለ ሲወራ የነበረው ሰዎቹ በቀጥታ የሲ.አይ.ኤ አባል በመሆናቸው ሳይሆን ከዚህ ድርጅት ጋራ የነበራቸውን ግንኙነት የተንተራሰሰ ነው።
—–
ይህ ድርጅት እንደ ኢህአፓና ህወሓት እድሜ ጠገብ አልነበረም። ነገር ግን በአጭር ቆይታው የተጫወተው ሚና ቀላል አልነበረም። በተለይም በመጨረሻው ሰዓት በድርጅቱ ጠንሳሽነት የተካሄደው የግንቦት 8/1981 መፈንቅለ መንግሥት የደርግን መንግሥት ግብአተ መሬት ካፋጠኑት ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል። በርግጥም መፈንቅለ መንግሥቱ ከከሸፈ በኋላ ጓድ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ባካሄዱት ርሸናና እስራት ሳቢያ ሰራዊቱ ብቁ አመራር አጥቶ ባልተጠበቀ ፍጥነት ፍርክስክሱ ወጥቷል።
ይሁንና ከላይ እንደገለጽኩት ይህ በመጨረሻው ሰዓት መጥቶ ለደርግ መንግሥት የራስ ምታት ሆኖ የነበረ ድርጅት ለማንም ግልጽ ባልሆነ ፍጥነት ድራሹ ጠፍቷል። አንዳንዶች የድርጅቱ ሚና ደርግን መደምሰስ በመሆኑ ዓላማው ሲሳካለት በጸጥታ ከመድረኩ ተሰውሯል ይላሉ። አንዳንዶች ግን የድርጅቱ ሞተር የነበረው አቶ ደረጄ ዴሬሳ በ1985 ሲሞት እንደርሱ ሆኖ ድርጅቱን የሚያንቀሳቅስ ሰው በመጥፋቱ ድርጅቱ ተበትኗል ይላሉ።
የሆነው ይሁን!! ይህንን ታሪክ ያመጣነው የርሱ መኖርና አለመኖር አስጨንቆን አይደለም። በዚህ ጽሑፍ ለማሳየት የተፈለገው ሁለት ነገሮችን ነው። አንደኛ “በደርግ መንግሥት ላይ የተነሳ ህዝባዊ ተቃውሞ የለም፤ ደርግን እናጠፋለን በማለት የተነሱት የኢትዮጵያን መጥፋት የሚመኙ ጥቂት ሃይሎች ናቸው” የሚል ጭብጥ ይነገራል። እነዚህ ሰዎች የአሁኑን መንግሥት ስለሚጠሉት ብቻ ነው እንዲህ የሚሉት። ሆኖም ደርግን ሲታገል የነበረው አንድ ድርጅት ብቻ ሳይሆን ከሃያ የማያንሱ ድርጅቶች ናቸው። እነዚህ ድርጅቶች በዓላማ ቢለያዩም የሁሉም ግብ ደርግን ማጥፋት ነው። የድርጅቶቱ እንደዚያ መብዛት በህዝቡ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ጸረ-ደርግ ጥላቻና ተቃውሞ መኖሩን የሚያመላክት ነው። በወቅቱ ደርግን ይታገሉ ከነበሩት ድርጅቶች መካከል አንዳንዶቹ ከኢህአዴግ ጋር ፈጽሞ ስምምነት አልነበራቸውም። ከነዚያ ድርጅቶችም አንዱ ኢፒዲኤ ነው። ይህ ኢፒዴኤ በአንድ ወቅት “ከህወሓት ጋር የሚታገለው አማርኛ ተናጋሪው ቡድን ስሙን ኢህዴን (EPDM) ብሎ የሰየመው እኔን መስሎ ሌሎችን ለማሳሳት ነው” በማለት ክስ አቅርቦ ነበር። በተጨማሪም ሁለቱ ድርጅቶች በርዕዮተ ዓለም የተለያዩ ናቸው። ኢፒዴኤ የምዕራባዊያኑ ሊበራል ዲሞክራሲ አቀንቃኝ ሲሆን ኢህአዴግ ግን እስከ 1982 ድረስ ኮሚኒስታዊ ነበር። ቢሆንም ሁለቱም ድርጅቶች ደርግን ማስወገድ በሚለው ነጥብ ላይ ልዩነት አልነበራቸውም። ከዚህ እንደምንረዳው ትግሉ የጥቂት ሳይሆን የብዙዎች ነበር።
በሌላ በኩል ደርግን የደመሰስነው እኛ ብቻ ነን የሚል አነጋገር አለ። ይህም ስህተት ነው። ደርግን ሲታገሉ የነበሩት መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ነበሩ። በድርጅቶች መሪነት ሲካሄድ ከነበረው ትግል ኢህአዴግ በውጊያው መስክ የበላይነቱን እንደሚወስድ አያከራክርም። ሆኖም ኢህአዴግ ውጤታማ ለመሆን የበቃው ሌሎች ድርጅቶች በልዩ ልዩ መልኩ ሲያካሄዱት የነበረው ትግል ስለታከለበት ነው። ከላይ የቀረበው የኢፒዴኤ ታሪክም ለዚህ አስረጂ ነው። ስለሆነም ደርግ የተደመሰሰው ሁሉም ህዝቦች ባደረጉት ትግል መሆኑን ማመን አለብን።
——
ግንቦት 21/2007
——
ማስታወሻ፡
1. የኢፔዲኤን ታሪክ ሻለቃ ጌታቸው የሮም “ፍረጂ ኢትዮጵያ” በሚለው መጽሐፋቸው በሰፊው አቅርበውታል። ሆኖም የርሳቸው ትረካ የሚያቆመው እስከ በ1983 አጋማሽ ላይ ነው፤ ከዚያ ወዲህ ያለውን ታሪክ ያገኘሁት ከልዩ ልዩ መጽሔቶች ነው።
2. ይህ ጽሑፍ የተጻፈው ኢህአዴግ በስልጣን ላይ እያለ በ2007 ነው።