Tidarfelagi.com

Déjà Vu / ዲጃቩ !

ከቀናት በፊት አዋሬ አካባቢ …
ልክ ከታክሲ እንደወረድኩ ዝናብ ይዘንብ ስለነበር ተራሩጬ እግሬ እንዳመራኝ ተደርድረው ከተሰሩት ሱቆች ወደ አንዱ በረንዳ አመራሁ። የኮስሞቲክስ መሸጫ ሱቅ ነበር የተጠለልኩበት በረንዳ። ወደ ካሳንቺስ አዘውትሬ ብመላለስም አዋሬ ሚባለውን ሰፈር ግን አላውቀውም ነበር። መንገዱ ላይ ህዝቤ ዝናቡን ለማምለጥ ይራወጣል! ድንገት አጠገቤ በሰፊ ትሪ ሻይና ወተት የያዘች ሴት ገፋ አድርጋኝ ወደ ኮስሞቲክሱ ቤት ገባች! የልጅቷ ጥድፍ ጥድፍ ማለት ገርሞኝ በአይኔ ተከተልኳት የሆነ የካፌ አስተናጋጅ ሽርጥ አድርጋለች ትሪውን የኮስሞቲክሱ መደርደሪያ ላይ አስቀምጣ ሻዩን ከመደርደሪያው ጀርባ ላለች ወፈር ያለች ሴት አቀበለቻት ፣ ቀስ ብላ ደሞ ወተቱን ከመደርደሪያው ወዲህ በርጩማ ላይ ለተቀመጠ ወጣት ልጅ አቀበለችው ! የስኳር እቃ አቀበለቻቸውና እመለሳለሁ ብላ በመጣችበት ፍጥነት ጥድፍ ብላ ወጥታ አልፋኝ ሄደች ! ውስጤ ግን የሆነ ሃሳብ ይመላለስ ነበር ! የኮስሞቲክሶቹ አደራደር ፣ የአስተናጋጇ መጣደፍ ፣ በርጩማ ላይ የተቀመጠው ልጅ አቀማመጥ ፣ ወተቱን ወደ አፉ ሲያስጠጋው ጭሱ ከብርጭቆ በቀስታ ሲግተለተል ! አይኔን መልሼ ከአስፓልቱ ማዶ ወዳለ በላስቲክ የተሰራች ደሳሳ ቤት መሳይ ውስጥ አንዲት ሴት ልጇን በጀርባ አዝላ ከሰል ላይ በተጣደ ሰፊ ትልቅ ድስት ሁለት ቦታ በቆሎ እየሰባበረች ለመቀቀል ወደ ድስቱ ስታስገባ አየሁ ! እዛው ቤት ውስጥ ሁለት ወንዶች የተቀቀለ ድንች ሲበሉ ፣ ከነሱ ፈንጠር ብሎ አንድ ጎልማሳ ሰው የሆነ ጋዜጣ ወይ መጽሄት ነገር በትኩረት ሲያነብ ….. ይሄን ነገር ከዚህ በፊት ኖሬው አቃለሁ እንዴ ? ከአስተናጋጇ ጀምሮ ኮስሞቲክስ ቤት ውስጥ ያለው ክስተት ፣ ከዝናብ ለማምለጥ ሚጣደፉት ሰዎች ጭምር የሚተላለፉት መኪኖች ፣ በቆሎ ምትቀቅለዋ ልጅ ያዘለችው ሴት ፣ ድንች ሚበሉት ወጣቶች ፣ አንባቢው ሰውዬ ….. ክስተቱ ምንም ሳይዛነፍ ከዚህ በፊት የተከሰተ ያህል ፣ ኖሬው ማቀው ያህል ፣ ከየሆነ ግዜ በፊት የተመለከትኩት ያህል ተሰማኝ! ልቤ ክስተቱን እንደወረደ ታውቀዋለህ ብሎ ግግም አለብኝ ! እንዴት ሊሆን ይችላል ? ሰፈሩን እንኳን ያለ ዛሬ አላቀውም እኮ ? በህልሜ አይቼው አውቅ ይሆን ይሄን አጋጣሚ ? ምን ጉድ ነው ? ውስጤ ግን ይሄን ክስተት ታውቀዋለህ ብሎ ሰላሜን ነሳኝ !

እንዲህ ገጥሟችሁ ያቅ ይሆን ? የሆነ ቦታ ፣ ክስተት ፣ ሁኔታ ከዚህ በፊት ሳይከሰት ግን የኖራችሁት ያህል ሚመስል አጋጣሚ ተፈጥሮባችሁ ያውቃል ? ምን ሊሆን ይችላል ይሄ የአይምሮ ጨዋታ ? ስም አለው ? ዲጃቩ !
እንደ ዶክተር ጁዲ ኦርሎፍ ገለጻ ( አሜሪካዊት የሳይካትሪ ፕሮፌሰር እና በዲጃቩ ላይ ጥናት ካደረጉ ባለሙያዎች አንዷ ) አብዛኞቻችን ይሄንን ስሜት እናስተናግደዋለን ስትል ስለዲጃቩ የጋራ ስሜትነት ገልጻለች ! ምንድነው ግን ዲጃቩ ? ከፈረንሳይኛ ስርወ ግንዱን ያገኘ ቃል ሲሆን ” Already seen ” የሚል አቻ የእንግሊዝኛ ትርጉም አለው ! ከመላምት የዘለለ ትንታኔ ባይሰጥበትም ነገር ግን ሰዎች ውስጥ አንድን ክስተት የኖሩት ያህል ፣ ከዚህ በፊት አጋጥሟቸው የሚያውቅ ያህል እርግጠኝነት ደረጃ ላይ የደረሰ ስሜት ወይም የውስጣዊ ሰውነታችንን ( ልቦናችን )ላይ የሚከሰት ረቂቅ ልምምድ ነው።

ዲጃቩ ልኩን ካልሳተና ከእለታት አንዳንድ ቀን ሚከሰት ከሆነ የጤና ነው። ዲጃቩ መንፈሳዊ ልምምድ ወይም የልእለ ሃያልነት ብልጭታ ነው ወይ ሚለው አከራካሪ ቢሆንም መንፈሳዊ ልምምድ ነው ብለው የሚያምኑ አጥኚዎችም አልታጡም። ዲጃቩ ይሄ ነው ብሎ የጠለቀና ለትክክለኛነት የቀረበ ትንታኔና መልስ የሰጠ አካል ወይም አጥኚ እስካሁን ባይገኝም አብዛኞቻችን ላይ የሚከሰት ውስጣዊ ልምምድ እንደሆነ ሁሉም በጉዳዩ ላይ አወቅን የሚሉ ሁሉ ይስማሙበታል። በዚህ ጉዳይ ላይ ከቀረቡ መላምቶች ቀልቤን የሳበኝ ግን ይሄ ነው :- እኛ ከምንኖርበት አለም ጋር ፍጹም ተመሳሳይ የሆነ አለም በሌላ ዩኒቨርስ ውስጥ እንደሚገኝ paradox :- እኛኑ የሆነ ሰው የእኛው ሌላ ማንነት /a parallel version of us / በዛ ኖሮት የነበረውን እየኖረ ያለው እሱን ጨረር ወደ ዩኒቨርሱ ሲልክ ሲጋጭብን /An alignment between the two universe / ሲከሰት ነው ዲጃቩ ምንለው የሚልም አስገራሚ መላምታዊ ትንታኔም አለ። ግራ ገብ ልምምድ ! ኖሬዋለሁ ወይስ አልኖርኩትም በህልሜ አይቼው ይሆንን ? የውዝግብ ውስጣዊ ድምጽ ! ዲጃቩ !

2 Comments

  • ኢሳይያስ አሰፋ መልካ commented on August 11, 2021 Reply

    በሚገርም ሁኔታ ስለ ክስተቱ የሚያረካ ትርጉም ያገኘሁበት ጽሁፍ ነው ።ይህ የውዝግብ ውስጣዊ ድምጽ ትርጉም ላገኝለት የምችለው ጉዳይ ባለመሆኑ ከአእምሮዬ በላይ ስለሚሆንብኝ ቀኑን ሙሉ እያሰብኩት እንዳልጨነቅበት የማደርግበት እና ውጤት ያገኘሁበት የግል ልምምዴ ክስተቱን አእምሮዬ ካስተናገደበት የጊዜ ርዝመት ያልበለጠ በዚያው ሰዓት የማደርገው አጭር ጸሎት ነው።በሥላሴ ስም አማትብና “ለመልካም ለበጎ ይሁን”ብዬ ታላቁን ጸሎት “አቡነ ዘበሰማያት” አደርሳለሁ።(እንደ እምነቴ ማለቴ ነው)።በሃይማኖት ፍልስፍና ወስጥ ለፈጣሪ መኖር አንዱ ማስረጃ የሰው ልጅ የማሰብና ለነገሮች መፍትሔ የመስጠት አቅም ውስንነት አንዱ መሆኑን የተማርኩበትን ጊዜ ያስታውሰኛል።

  • yonasbirhanu17@gmail.com'
    yonas birhanu commented on November 11, 2021 Reply

    ግሩም ነው ሳሚ ፋንታ፡ (ሪካርኔሽን )ብለው የሚያብራሩት አሉ የህይወት ድግግሞሽ፡ ዘላለማዊነት፡…..እናመሰግናለን፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...