Tidarfelagi.com

Connecting the dots

ልጅ እያለሁ ነጥቦችን በማዋደድ ጨዋታ እዝናና ነበር… በአንዳንድ ጋዜጣና መጽሔቶች የጀርባ ገጽ ላይ በተንተን ያሉ ጥቂት ነጠብጣቦች ይቀመጡና አንባቢያን በነጠላ መስመር ሲያገናኟቸው አንዳች ትርጉም ያለው ቅርጽ እንዲሰጡ ሆነው ይታተማሉ… ነገሩ መዝናኛ ቢሆንም አስተውሎ ላየው አንዳች እውነት ሹክ ማለቱ አይቀርም… ትላልቅ ጉዳዮች የትናንሽ ነገሮች ውህደት የመሆናቸውን እውነት… እና ደግሞ ትንሽ በስርዓት ሲዛነቅ ትልቅ በጥንካሬ የመቆሙን ሃቂቃ…
~
ትልቀት በደቃቃ ስምረት በወግ ካልተቃኘ እንደ ኩይሳ ነው… ግዝፈት እንጂ መሰረት የለውም…
~
የብዙ ችግሮቻችን ጥነት ከነጠብጣብ የማዋሃድ ክህሎት ማነስ እንደሚወለድ ይሰማኛል… ትላልቅ ምስሎች የትናንሽ ነቁጦች ተዳምሮ ውጤት ናቸው… በሂደቱ ውስጥ ስለ አንድ ነጥብ እንኳ ግድ ባይልህ ግዙፉን ምስል አታይም…
~
እዚህ መንደር የምጋራቸውን ብዙዎቹን ጽሑፎች በዚህ መርህ ነው የምቃኛቸው… አንዳንድ የሃሳብ ዘለላዎች [በተለይ Science & Spirituality] ከኑረት እውነት ጋር እንዴት እንደሚዛነቁ ማሰላሰል ያስደስተኛል…
~
ትናንት ከሁለት ዓመት በፊት ፖስት ያደረግሁትን የነገረ ድምጽ [Cymatics] ጽሑፍ በፌስቡክ አስታዋሽነት ለጥፌ እንደነገሩ አንብበው በኢንቦክስ “መዓት” ያወረዱብኝ ሁለት ወዳጆቼ [እዚህ ጋ በደንብ ፈገግ በሉ…] አንዱ ከሐይማኖት ሌላው ከኤቲይስት እሳቤ ተወግነው ሲያንቆራጥጡኝ ነበር… ‘ሁለት ጽንፍ ላይ ያሉ ሰዎችን በዚህ ደረጃ ካነታረክ በቃ The middle way ያንተ ናት ማለት ነው’ አልኩት እራሴን… ሃሃሃ
~
ምን ለማለት መሰላችሁ… አንዳንዴም ነጠብጣቦችን ማያያዝን መልመድ በጎ ነገር ነው… መሰል ልምዶች እንደ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን እንደ ማሕበረሰብም ለገጠሙን ፈተናዎች መፍትሔ ይመስሉኛል… ፖለቲካችን – ማሕበራዊ መስተጋብራችን – ግለሰባዊ መረዳታችንና ሌላው ሁሉ ነገር በ Connecting the dots መርህ ቢቃኝ አንዳች የብርሃን ሽራፊ የሚያሳይ አይመስላችሁም?…
~
ጽሑፉ ከ ‘መጫኛ የረዘመብሽ’ ልጅ “Twitter አካውንት አለህ ግን?” ብለሽ አስገባሽልኝ ኣ?… ሃሃሃ
~
ሰላም ለምድራችን ይሁን!!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...