“በቃ ሂድና ትንሽ ጊዜ ስጭኝ ምናምን እስኪወጣልኝ አንጎዳጉጂኝ ምናምን በላታ?” ያለግጣል። አልሳቅኩለትም። ብቻውን ይገለፍጣል። ተነስቼ ወደቤቷ በሩጫ ረገጥኩ። 199″አንተ የምር አደረግከው እንዴ?” የአብርሽ ድምፅ ከጀርባዬ አጀበኝ። በሩን ከፍቼ ስገባ ደርቄ ቀረሁ።..
የሄድኩት ምን ልላት ነበር? ለምንድነው የምናቆመው ልላት? አይደለም። እኔ ምንሽ ነበርኩ? ልላት ነበር የፈለግኩት። ደስ ባለሽ ሰዓት የምትጠሪኝ ደስ ባለሽ ሰዓት የምታባርሪኝ ከአሻንጉሊትነት ያለፈ ልብ እና ስሜት ያለው ሰው መስዬሽ አውቃለሁ ወይ ልላት……
በርዋን ከፍቼ ስገባ ከአፌ የወጣው እሪታ ብቻ ነበር። ማመን አልፈልግም። ያቺ ጨረቃን ነይ እስኪ በርከክ ብለሽ ስቶኪንጌን አውልቂ ብትላት ጨረቃ ሳታመነታ ያን ሁሉ ማይል ስትንደረደር ፣ አልበላ አልጠጣ ብላ ያጠራቀመችውን ብርሃኗን አሟጣ ፣ ለምርምር የመጠቁላትን መንኩራኩሮች አፍንጫችሁን ላሱ ብላ ህዋ ላይ አሽቀንጥራ ጥላቸው ስትንደረደር አንድ ከጁፒተር ሳተላይት ጋር ተጋጭታ ሁለት ከሳተርን ሳተላይት ጋር ተላትማ እያላበች እግርዋ ስር የምትፈጠፈጥላት የምትመስለኝ ሴት በህይወት ለመኖር እንጥፍጣፊ ተስፋ አጥታ ራሷን አጠፋች ብሎ ማመን ከበደኝ።
እራቁቷን ሆና ከሲጋራ ጭሷ ጋር እየተጫወተች ቁልቁል ስታየኝ ሳያት ዓለምን በንቀት የምታያት የምትመስለኝ ሴት ነገን የመጋፈጥ ብርታት አጥታ መርዝ ተጋፈጠች ብዬ ማሰቡ እንኳን ከበደኝ።
ሰው ተሰብስቦ ሬሳዋን አፋፍሰው ሲያነሱ፣ ሲለቀስ፣ድንኳን ሲጣል፣ ቀብርም ሲሆን…… እዛው ነበርኩ። በጣም ማልቀስ እፈልጋለሁ ግን እንባ የለኝም። ከአብርሽ በስተቀር ማንም ልብ ብሎ ያየኝ የለም። አብርሽም አያዋራኝም በአይኑ ብቻ ይከታተለኛል።
“ማውራት ከፈለግክ ታውቃለህኣ አለሁ።” ይለኛል የባሰብኝ ሲመስለው።
“አይናለም እኮ ሞተች አንቺዬ… ”
“አይናለም? አይናለም?”
“አይናለም አጫሿ፣ አይናለም እንኳን ትንባሆ የምትስበው?…” ይባባላሉ። አያውቁም እንጂ “ያቺ የወዳጅዋን ልጅ የምታባልገው” ይሏት ነበር።
“ምነው አንችዬ ምን ጎደለባትና ነው ራሷን ያጠፋችው? ከሃብት ሃብት ከልጅም ወርቅ ልጅ ሰጥቷታል። ከባልም መሬት የሆነ ባል አላት ምን ሰይጣን ነው ያሳታት ባክሽ?” ይባባላሉ።
ሰውኛ አይደል? ርሃብተኛው አንጥንቱ ካልገጠጠ ቦርጫም ቦርጩ እንዴት ይገናል? ባለሀብቱ እንዲደምቅ ደሃውኮ ጉስቁልቁሉ መውጣት አለበት። ምግባረ ሰናይ ግብሩ እንዲዘመር ምግባረ ብልሹ መጠልሸት አለበት። ካለዚያማ ልዩነት የታል?
ማሰቢያዬ የሆነ ጠርዝ ላይ ምክንያቷ ውስጥ እኔ መኖሬን ማሰቤን ማቆም አቃተኝ። ከቀናት በኋላ
“እማ አይናለም ምን ሆና ይመስልሻል ራሷን ያጠፋችው?” አልኳት እማዬን
“ኧረ ምኑን አውቄው ልጄ?”
“ባሏ ጥሩ ሰው አይደል? ”
“ኧረ ሞገስ? መሬት የሆነ ባል አይደል እንዴ? አንዲትም ቀን አስከፋኝ የሚል ከአፏ ወጥቶ አያውቅም። እንደው እህቴን እንደው……… እህቴን አላወቅኩላትም እንጂ አንድ ነገርማ ሆድ ሆድዋን ሲበላት ነበር ። ” እንባዋ ተግተለተለ።
“ኧረ እማዬ…… ”
“መርዝ ከመጠጣትዋ አንድ ቀን በፊት ትዝ አይልህም?… ” ጭንቅላተን ነቀነቅኩ። “እዚህ ጋር ተቀምጣ…… “በእጇ ሶፋችንን እየጠቆመች “ያን ሲጋራዋን እየሳበች አስካል 40 አመት ጓደኛሞች ስንሆን በድዬሽ አውቃለሁ?” ብላ ጠየቀችኝ። እያባባኋት እንደሆነ ባውቅም ነገሩ መስማት ያለብኝ ጉዳይ መሆኑ ገባኝ።
“እሺ? ” አልኩኝ
“ውይ አይንዬ አንቺ ሰው ይደርስብሻል እንጅ ማንጋ ደርሰሽ ሰው ታስቀይሚያለሽ?” አልኳት
“አስክዬ እባክሽ ማሪኝ ምንድነው ብለሽ አትጠይቂኝ ይቅር ብዬሻለሁ በይኝ በድዬሻለሁ አለችኝ። ምንም ሳይገባኝ እሺ ምሬሻለሁ ምንም ቢሆን አልኳት። ምናለ ምን ሆነሻል ብያት በነበር?እኔ ምን አይነት ወዳጅ ነኝ? ” እሷ ከመንሰቅሰቋ በላይ እኔ ውስጤ የፈረሰ ነገር ስለመሰለኝ
“እማዬ ተይው በቃ እሺ ዝም በይ” ብዬ አባበልኳት።
ትዝታ የተንጠለጠለበት ጫፍ ላይ የታሰረ ስሜት፣ ጠረን፣ ምስል አብሮ ይጎተታል አላልኳችሁም? ወንፊታም ስቶኪንግ፣ የሲጋራ ጭስ ( ሽታውም ምስሉም) ፣ የነከሰ ዚፕ፣ የተቆላ ቡና ሽታ የደባለቀው የሚጣፍጥ ሽቶ ጠረን፣ ትዕዛዝ የተለወሰ የስሜት ማቃሰት……… እሷ አይናለም ናት። ይሄን ተከትሎ መሬት ላይ የተዘረረ ሰውነቷን ማስታወስ ተጎታቹ ጫፍ ነው።
******* ********* ******** ********
“ልክ እኮ ነሽ እዚህ ሀገር መሪም ተመሪም የለም። ሁሉም ራሱን ነው የሚመራው።” ሰርኬ ናት። እነኚህ ደግሞ ከደቂቃ በፊት ክተት ሊያውጁ አስመስለውት አልነበር እንዴ? ተስማሙ ማለት ነው? መቼ ነው እህሉ የታዘዘውና ተበልቶ ያለቀው? ስንተኛ ቢራዬ ነበር?
“ኧረ ብዙው ቆሟል ስልሽ? የሚሄድበት ስለሌለው መሪም አያሻው ራሱንም አይመራ። ቆሞ ትናንትን ይሰልቃል።” የኔዋ ጉድ ናት
“እንዲህኮ ነው የሚያደርጉን! “አልኩኝ ገርመውኝ
” እነማን?” አሉ ሁለቱም
” ዋናዎቹም፣ ተቃዋሚ ነን ባዮቹም፣ አክቲፂቪስት ነን ባዮቹም። በጎራ ተቧድኗው ጎራ ይመድቡንና ጉድጓድ ይከቱናል።”
“ማለት? “አለች ሰርኬ
“እንዲህ እንደእናንተ ነዋ! እነሱን አምነን በቡድን እንሰለፋለን፣ ግጠሙ ይሉናል እኛ ስንቧቀስ እነርሱ በጀርባ ተስማምተው እኛኑ ፣ደደብኮ ናቸው እያሉ ያሙናል። ታርቀዋል ብለን ደግሞ ቡና ስንጠራራ ድሮም ለፖለቲካው ድምቀት እንጂ እርቅ አይታሰብም በሉ እንክተት ይሉናል። አቦላችንን እንኳን በቅጡ ሳንጨርስ በስኒው ድብድብ እንገባለን።”
“ኧረ ትንታኔ አንተ ፖለቲካ አይመቸኝም አትንኩኝ ስትል አልነበር እንዴ? “ሰርኬ ናት
“ይሄ ሁሉ ህዝቤ የማይገባው ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ…… ውቅያኖስ ውስጥ የሚሮጠው፤ የብስ ላይ የሚዘፋቀው ወዶ መሰለሽ እንዴ? እንጀራውንም ውሃውንም፣ መንገዱንም ትዳሩንም ፖለቲካ አድርገውበት እንጂ ። ኧረ ተውኝ እስኪ ማነህ አስተናጋጅ ይሄ ቢራ እኮ ውሃ ማቆር ሆነብኝ እስቲ ጠንከር ያለ ነገር አምጣልኝማ።”
“ለምን ሙዚቃ ያለበት ቦታ ሄደን አንጠጣም?” የሰርኬ ሃሳብ ነው። ሁለታችንም ወደ አሚ ዞርን።
“እህ እሺኣ! ግን ለእማዬ ደውልላትና ካንተ ጋር መሆኔን ንገራት።”
“ማን ማን ናችሁ?” ትላለች እማዬ መስቀልኛዋን ስትጀምረኝ።
“ኧረ ወየው እማ ከኔ ሌላ ወንድ የለም እርምሽን አውጪ።” ብዬ ዘጋሁት።
“ባቢ ትንሽ አመሻለሁ አትጠብቀኝ እለዋለሁ አጎቴ ተደባድቦ ነው ወይ? ይለኛል። “ትለኛለች አሚ ስልኳን እያስቀመጠች።
ገና ከመውጣታችን አገለሉኝ። ዘመናት እንደከረመ ሰው እየተንሾካሸኩ ሁላ ሚስጥር ይቀባበሉ ጀመር። አሚ እንዲህ ናት ተወዳጅ ቀልብ ነው ያላት። ዛሬ ካገኘችው ሰው ጋር ድብልቅ አድርጋ ትጫወታለች። የምትገርመኝ ምንም ዓይነት ርዕስ ላይ ቢሆን የምታወራው ሀሳብ አታጣም። ጋግርታም የተባለ ሰው ታዋራለች። ፍቅረኛዬ ናት ብዬ ካስተዋወቅኳት ሴት ጋር ደግሞ ጭራሽ እሷ ፍቅረኛ መስላ ታርፈዋለች። ከአንዷ ጋር ይኧው እኔ ከተጣላኋት ዘመን የለኝም እሷ ግን ዛሬም ትደዋወላታለች።
“ትወድሃለችኮ ለምን የምርህን አብረሀት አትሆንም?” ትለኛለች ሰርኬን ሸኝተናት እየተመለስን ላዳ ውስጥ።
“እኔምኮ ተመችታኛለች። ይሄ በደህና ወሬ መሃል ወስዳ ፓርላማ የምትቀላቅለኝ ነገሯ ነው ቁርፍድ የሚለኝ። በረዶ ዘነበ መንግስት ይወገር፣ እንትን ክልል ሙቀት ጨመረ የእገሌ ብሄር ሙቀታም ስለሆነ ነው ከክልሉ ይውጣ፣ እገሌ የሚባል አክቲቪስት ቁርሱን አልበላም የብሄር አድሎ ነው።”
“ሃሃሃሃ ይልቅ ማጨስ ላቆም ነው አለችኝ ምን ተሻለህ?”
“ቆይ ምንድነው የምታደርጊያቸው? ለኔ ያልነገሩኝን ነገር የሚነግሩሽ?”
“አታስቀይስ ባክህ? ማጨስ አቆመች ብለህ ልትተዋት ነው?”
“በሽታዬን እያወቅሽው አሚዬ እንዳትጀምሪኝ ስወድሽ ይልቅ ለምን ትንሽ አናመሽም?”
“ምሽቱማ አለቀኮ ንጋት ጀምሯል ሃሃሃሃሃ”
“ይሁና ምን ይለናል! እሺ ትንሽ እናንጋኣ?”
እየሄድን የተለመደ ንዝንዟን ትነዘንዘኛለች።
“እስከዛሬ እኮ አፍቅረህ አታውቅም ማለት ነው። ብታፈቅራት እንኳን የሲጋራ ጭስ ቤቱ ተቃጥሎ ቢጨስ አይሸትህም። እነርሱን ሳይሆን ጭሳቸውን ነው አንተ የምታፈቅረው።…… ”
“ወይ ከጭሷ በላይ የደመቀችብኝ ሴት የለች ይሆናላ።” እላታለሁ ከላዳ እየወረድን።
ሞቅ ሲላትኮ ደስ ስትለኝ። ቤቱ ይጠባታል። ትንከተከታለች። በእንጥሻ ሁላ ትደንሳለች። እሷ እንደዛ ፈታ ስትል ማየት አለሜ ነው። ከኔ ጋር ብቻ ነው ይሄ ነፃነቷ። እንደምጠብቃት ታውቃለች። በግድ ይዣት ወጣሁና እኔ ቤት ሄድን።
“ዛሬ ያንተ ተራ ነው። እኔ አንተ ስትሰክር ተንከባክቤ አይደል የማስተኛህ? ደሞ ደሞ ስትዘባርቅ ሁላ እሰማህ የለ? ደሞ ደሞ……… ” ስትሰክር “ደሞ” ታበዛለች።
“እሺ! “እላታለሁ ደሞ ደሞ ስትለኝ። ልብሷን እየቀየርኩላት እንደልጅ ታስቸግረኛለች።
“ይሄ ከንቱ ሴክስ አትችይምኮ ነው ያለኝ።” የተጣላችውን ፍቅረኛዋን ነው። ለብዙኛ ጊዜ ነግራኛለች።
“አንቺ ግን የምር አትችይም እንዴ? ምኗ እንከፍ ነሽ? ” ለነገረችኝ ቁጥር ልክ አበሽቃታለሁ።
“ቆይ አንተ ግን የማልችል ይመስልሃል?”
“አሚዬ እሱ ነገርኮ በማየት አይታወቅም። በይ አርፈሽ ተኚ ሰክረሻል።”
“እኮ ሞክረኝና ንገረኛ? ”
“እርፍ! ይሄ ነበር የቀረሽ። በይ አትላዘዢ አርፈሽ ተኚ።”
“የምሬን ነው ባክህ። ደሞ አስቤሽ አላውቅም ለማለት ነው? ደሞ ደሞ ወንድምሽ ነኝ ምናምን እንዳትል አንተ የአብርሽ ወንድም ነህ እንጂ………
ከዛ ብዙ “ደሞ ደሞ” እና ብዙ ያስደነገጠኝን ነገር ተናግራ እንቅልፍ ወሰዳት። ስካሬ ለቀቀኝ። እሷ እቴ ጧ ብላ ተኛች።