ይሄን የእንግሊዝኛ ተረት በዚህ ዓመት ውስጥ ሺህ ጊዜ ሳልሰማው አልቀርም። ግን መደጋገሙ ሲበዛብኝ፤ አባባሉ እንዲወደድ ስልት ያለው የማለማመጃ ዘመቻ ወጣቱ ላይ እየተሰራ መሰለኝ።
ዘይቤውን የሚናገሩት ብዙ የጥቁር ሀበሻ (ሀበ) ፈረንጃዊያን ብቅ ብለዋል። እነሱም ʻየአገራችንን መልካም ታሪክ እንጥቀስʼ ስንል ዐይኖቻቸው ቀልተው (መቅላቱን እንዳናይ በመነፅር ጋርደው) ‘The past is a foreign country’ ይሉናል።
ዛሬ ተረሳ እንጂ፤ በአብዮቱ ጊዜ ወይም አብዮቱ ሲፈነዳ ለአለም አቀፋዊነት ሊሸቅሉን፣ አንዱን አገር ወዳድ በእጅ አዙር አዘፍነውታል
የድሮ ዝናሽ ላይጠቅምሽ
እንዲህ ነበርኩኝ ማለትሽ
ለአሁኑ ኑሮሽ ላይረባሽ
ኧረ ዝም በይ እባክሽሽ…… ተብሎ።
አንዳንድ የባዕድ ታሪክ ፀሐፊዎችም ይህቺን ጥበብ ይጠቀማሉ። እነዚህ የነጭና የጥቁር ተራቾች ግን ‘ታሪክ አስፈላጊ አይደለም…… ያውም ደብተራ የዘባረቀው’ ብለው እየሰበኩን ለምን የታሪከ ምሁር እንደሆኑ ግን አይነግሩንም።
የሚጠቅመኝ አይጠቅማችሁም ነው?
ፈረንጆች፤ የአገራቸውን ከተሞችና የሰፈሩባቸውን ቦታዎች በትውስታ ግንባታ እና በኪነጥበብ ሞልተዋቸዋል። የእኛን አንድ የአራዳውን ፈረሰኛ ግን እንድንጠላ ይገፋፉናል፣ እምቢ ስንል ደሞ ያጣጥሉታል።
ማጣጣላቸው አልገባን ካለ፤ በዓለም ያስቁብናል። ሳቂ ካጡ ታሪካችንን ይዘርፉናል። እሱም የእኛ ነው ብለን ከተሟዘዝን በተለይ ጥቋቁር ሽርኮቻቸውን (ሀበፈረንጃውያንን) ሰብስበው ወደ እኛ እየጠቆሙ የበለጠ ያስቁብናል። እንዲህም ይነዘንዙናል፤
አሁንስ በዛ (ባይበዛም)፣ ሁሉን ነገር እኛ ጀመርነው ልትሉ ነው? (አልወጣንም)።
እውነቱን እንዳንል፤ ባላልነው ነገር ቀድመው ያላግጡብናል።
የአገራችንን የጥንት ታሪክ እንመዘግባለን – አትመዘግቡም ንትርክ እና ጫጫታ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእረፍት ጊዜ ይመስላል። ተጠየቅ የራሱ ስልጣን ስላለው፤ ደወል መደወሉ ግን አይቀርም።
ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ፤ የእኛ ብቻ ሳይሆን የምዕራብ አውሮፓም ታሪክ የተፃፈው በደብተራዎች ነው። ቄስ ወይም ደብተራ ያልነካው የታሪክ መጽሐፍ የለም። ታሪካችንን ማጣጣል የፈለጉ ማርከሻ መረጃ ሲያጡ ይሄ የደብተራ ታሪክ ነው ብለው ያሽሟጥጣሉ (ከቴም ተሽሟጠጠ)።
በልቦናቸው ቢፈሩትም–የውሸት ይንቁታል፣ በአድማ ያጣጥሉታል።
በተቃራኒው የባዕድ ደብተራ (ዛሬ እንደሚባለው የʻባዴʼ ደብተራ) የፃፈውን ግን ያምኑታል። የባዴ ደብተራ ቀሽም ቢሆን እንኳን እንደ ደብተራ አይቆጠርም። ቢዋሽ እንኳን እንዲዋሽ አይደረግም። ክፉ ቢሆን እንኳን ክፉ አይደለም። ደብተራዎችን ለሁለት ልክፈል ብዬ ነው።
የለም ይሉናል እንጂ፤ ለማንኛውም አገር፤ ያለፈው በሆነ መልክ አለ። እኔ ታሪኬ ነኝ። ባሪያውም ጌታውም ታሪኩን ነው። ሰልጣኝና አሰልጣኝም ታሪክ አላቸው። ማንነት፤ (የሚባል ነገር ካለ) ከታሪክ የመጣ ነው። ከተመኙት ማለቴ አይደለም።
እንስማ ከተባለ፤ የማንም ታሪክ ውስጥ መበʼደል አለ። አበዳደል አለ። ይሄ አስገራሚ አይደለም። የሰው መልአክ የለውም። ሺህ እትዬ ትርሲቶች በአንድ ላይ ቢሰበሰቡ፤ አንድዋን ማርያምን አይወጣቸውም።
ከሆነ ብሎ ተሳሳች ጋር ግን ክርክር ማድረግ ይከብዳል። አውቆ የተኛን፤ ‘ዲቪ እንካ’ ቢሉት እንኳን አይሰማም።
ይሄ የሚያሳየን፤ በአገራችን በፍልስፍና ሙያቸው የሚያከብሩ፣ ትክክለኛ ማስረጃ ላይ የቆሙ የረቀቁ ልሂቃን ከድሮም በበቂ አለመኖራቸው ነው።
ልወደድ ባይነትን፣ በትምህርት ቤት የሰበሰቡትን መረጃ እንዳለ መድፋትን፣ ከፖለቲከኞች ጋር ተደጋግፎ ሆይ ሆይ ማለትን፣ ከባዴ መታከክን፣ ብልጣ ብልጥነትን፣ የማወናበድና የመዋሸት ተውህቦን ከምሁርነት ያምታቱታል…”
***
#የስንብት_ቀለማት