Tidarfelagi.com

እንደሱ አይደለም

የምወዳቸውን ዘፈኖች ወደ ሙዚቃ ቪድዮ መቀየራቸውን ስሰማ ለማየት ፈራ ተባ እላለሁ ፤ በጣም የወደድኩትን ዘፈን በካሜራ አጉል ተርጉመው ሲያበላሹብኝ ይነደኛል ፤ በራሴም ደርሶብኛል ፤ ከጥቂት አመታት በፊት ነፍሱን ይማርና ኤልያስ መልካ አንድ ዜማ ሰደደልኝ፤ “ ዝምታየ” የሚል ግጥም አለበስኩና መልሼ ላክሁለት፤ ግርማ ተፈራ አሳምሮ ዘፈነው። ቆይቶ የሙዚቃ ቪድዮ ተሰርቶለት አየሁና በንዴት ጨስኩ። ወድያው አገጨ አካባቢ መሸበት ጀመርኩ። እንዲያውም ለቪድዮው ምላሽ የሚሆን ” ዝም አልልም” እሚል ዘፈን ደርሼ ላረጋኸን ወራሽ ልሰጠው ዳድቶኝ ነበር!

ሙዚቃ ቪድዮ የምትሰሩ ሰዎች ሆይ! የቁንጅና ሳሎን ያንድ እናት ልጅ ያስመሰላቸውን ሞደል ሴቶች ካልመለመላችሁ አይሆንላችሁም ወይ? ጥንቅሽ ሆድ(ሲክስ ፓክ) ያለው ሞዴል ወንድ የዘፈን ቪድዮ ውስጥ ማስገባት ግድ ነው ወይ? እዚህ ግባ ብቻ ሳይሆን እዚህ ውጣ እማንባል ወንዶች እኮ እንዳቅሚቲ ተወደን እናውቃለን ፡ ( ባየር ፀባያችን ምክንያት 🙂 ) “ላይን እማትሞላ” ሴት የሚወድ ወንድ ሞልቷል!

እናንተ የእፉኝት የልጅ ልጆች! ድሮ ህብረትርኢት ላይ ከሚቀርቡ የዘፈን ቪድዮዎች አትማሩምን? ያኔ ዘፋኙ አንድ ቦታ ቆሞ ይዘፍናል! በቃ! ሞዴል የለ! ምን የለ! የምንወዳትን ሴት በፊናችን እንድናስብ እድል ይሰጠናል ። እዚያ ድረስ ምን ወሰዳችሁ! ለመማር የፈለገ “ስቄ እሸኝሻለሁ” ከሚለው የሚካኤል በላይነህ ቪድዮ መማር ይችላል።

በሙዚቃ ቪድዮ ላይ ወዶ መለየትን የሚገልፅ ታሪክ ስታቀርቡ ተጠንቀቁ፤ ትንሽ ወደ እውነታው ይቅረብ እንጂ ፤ በሙዚቃ ቪድዮችእን ውስጥ ሴት እና ወንድ ይዋደዳሉ፤ በትራስ ይደባደባሉ፤ ኬክ የሚያጎርስ መስሎ ራሱ እየጎረሰ ያጫውታታል ፤ ከተረገሙ ቀናት ባንዱ ትጣላዋለች ፤ በሻንጣ ውስጥ ልብሶቿን ትሞላና “ቻው “ የሚል ቃል አልጋ ላይ ትታለት ትወጣለች፤እሱ ደጃፍ ላይ ቁጭ ብሎ እየተከዘ ይዘፍናል፤አለቀ !

በእውነታው አለም፤ ሴትና ወንድ ይገናኛሉ ፤ ይፋቀራሉ፤ የሆነ ጊዜ ላይ በቃኝ ትለዋለች፤ ማን ፈቅዶልሽ ነው የሚበቃሽ ይላታል፤ እሱ በፍቅረኝነት በነበሩ ጊዜ ሻወር ቤት ቁጭ ብላ የተነሳችውን ፎቶ ኢንተርኔት ላይ ይለቅባታል፤ እሱዋም “ እግዜር ይፍረድብህ “ እሚል ቴክስት ትልክለታለች፤ እግዜር እስኪፈርድ ጫኝና አውራጅ የሚሰራውን ወንድሙዋን ትልክበታለች፤ እሱም ጥርሱን ያራግፍለታል ፤ የሙዚቃ ቪድዮ የምትሰሩ ሰዎች ሆይ! I have an idea ተሰናባቹ ፍቅረኛ በጥርስ ኪኒክ ውስጥ የፊት ጥርሱን ሲያስበይድ የሙዚቃ ቪድዮውን መጀመር ይቻላል።

የ” ነዋሪ አልባ ጎጆዎች “ ደራሲ እንዳለው፤
“ፍቅር በባህሪው፥ እንዳስጨናቂ ህልም
ለመግባት ነው እንጂ፥ ለመውጣት አይቀልም “

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...