ምኡዝ እንዲህ አለ
1
“ የሰው ልጅ ተገንጣይ እንስሳ ነው፤ ባለፈው አንዱ “ የአዲሳባ ልጅ” የሚል ፅሁፍ ያለበት ቲሸርት ለበሰ፤ ወድያው ብዙ ሰዎች እንደሱ መልበስ ሲጀምሩ ተገንጥሎ “ የሽሮ ሜዳ ልጅ “ የሚል ፅሁፍ ያለበት ቲሸርት ለበሰ፤ ብዙ የሰፈር ልጆች እንደሱ መልበስ ሲጀምሩ፤ ተገነጠለና “ የእኛ ቤት ልጅ “ የሚል ቲሸርት ለበስ ፤ በመጨረሻ ወንድሞቹ እንደሱ መልበስ ሲጅምሩ “ ታላቁ ልጅ “ የሚል ቲሸርት ለበሰ፤”
2
“ ከእማማ የወረስኩት አሪፍ ቤት ውስጥ እኖራለሁ፤ ግን ምን ዋጋ አለው? ለእኔ አይነት አኑዋኑዋር አይሆንም! በየቀኑ ሴት ይዠ ስመጣ ጎረቤቶቼ በየመስኮታቸው አንገታቸውን አሾልከው ያፈጡብኛል፤ ባለፈው አንድ ሰውየ ከሁለተኛ ፎቅ ላይ ሆኖ ሲያፈጥ ወድቆ ወገቡ ተሰበረ:: በማግስቱ በዊልቼር ላይ ተቀምጦ እንደገና ማፍጠጡን ቀጠለ፤
..አንዳንዴ ሳስበው አብርሃም በድንኩዋን ለመኖር የመረጠው ወዶ አይደለም፤ ጎረቤቶቹ ሲደብሩት ቤቱን በቦርሳው አጣጥፎ ከትቶ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ይችላል፤ እንዲህ አይነት ልዩ ነፃነት ስላገኘ ጤናው ተጠብቆ አምስት መቶ አመታት ኖረ፤ እኔ ግን የገዛ መንደሬ እስረኛ ነኝ፤ ትናንት ማታ እስኪጨላልም ድረስ ጠብቄ አንዱዋን ይዤ ወደ ቤት እየመጣሁ ነው፤ እና ድንገት በጨለማው መሀል አንድ ድንጋይ እንደ ሌሊት ወፍ ውልብ ብሎ ጀርባየ ላይ አረፈ፤ ማን የመታኝ ይመስልሃል? ሚስቱን ያባለግሁበት አባዋራ እንዳይመስልህ፤ ከጎረቤታችን ከሚኖሩ ጎረምሶች አንዱ ነው፤ ይህ ሰው በሴት ተዎዶ አያውቅም፤ የሴት ደስታን አያውቅም፤ የሴት ብልት እንኩዋ ያየው ፥የጎጂ ልማድ አስወጋጅ ኮሚቴ በሚያሳየው የግርዛት ቪድዮ ላይ ነው፤ ታድያ ቢወግረኝ ይገርማሀል’?
3
“…እግርዎትን ምን ሆነው ነው?”
ሽማግሌ፡- በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት አደጋ ደርሶብኝ ነው”
“ዘምተው ነበር? “
ሽማግሌ፡- አይ! አልዘመትኩም፤ ብቻ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የቤቴን ጣራ በመጠገን እያለሁ ተንሸራትቼ ወደቅሁ”