Tidarfelagi.com

ሴት እና ትዳር – ‹‹እርቃን›› (ክፍል 1)

ፀሃፊ፡ ቢኮዙሉ ‹‹The Emperor’s Naked”
ትርጉም፡ ሕይወት እምሻው

የሶስት ወንዶች እና ሁለት ሴት ልጆች እናት ነኝ። ይህ ማለት፣ ከእንቅልፌ ከምነሳባት ሰከንድ አንስቶ መሽቶ የቤታችን የመጨረሻዋ መብራት እስክትጠፋ ድረስ ቀኑን ሙሉ ስተራመስ ነው የምውለው። ሌሊቶቼ አጭርና ቶሎ የሚያልቁ ናቸው።
ንጋት ጠላቴ ነው፣ ያልጠገብኩት እንቅልፌን ቀምቶ ለማያባራ የቤት ውስጥ ስራ አሳልፎ ይሰጠኛል። ቀኖቼ እረፍት አልባ ናቸው። ቀኖቼ በጩኸት የተሞሉ ናቸው። ሁሌም አንድ ነገር እንደተሰበረ ነው። መአት ብርጭቆ እገዛለሁ ግን ሁሉንም አንድ በአንድ ሰብረዋቸው አሁን ሁላችንም በፕላስቲክ ኩባያ ነው የምንጠጣው።

ሁሌም አንዳቸው እንዳለቀሱ ነው።
ሁሌም አንዳቸው ካንዳቸው እንደተጣሉ ነው።
አንዳቸውም ደብተራቸው የት እንዳለ አያውቁም፡
ወይ ደግሞ ካለሲያቸው ይጠፋባቸዋል። ወይ ደግሞ ፓንታቸው። ወይ ሸራ ጫማቸው።
ሁሌም የሆነ ነገር ላይ እንደተንጠለጠሉ ነው። ‹‹ውረድ…ውረዱ…!›› እያልኩ ከጣራ በላይ ብጮህም እነሱ እቴ! እንደ ሰው በመሬት ላይ ከመሄድ እንደ ጦጣ ባገኙት ነገር ላይ መንጠላጠልን ይመርጣሉ።

ቲቪው ከተከፈተ- ማለት ቲቪ በሚፈቀድላቸው ሰአት- ድምፁ ከጣራ በላይ ነው። ግን ማንም በጨዋ ደምብ ቁጭ አያየውም። ሁሌም ይሄኛውን እንይ…ይሄኛውን አናይም እያሉ ጣቢያ ለመቀየር የኔ ተራ ነው በሚል እንደተናቆሩ ነው።

ጠብ መገላገል፣፡ አንዳቸውን ማባበል፣ አንዳቸውን ማስፈራራት የነጋ ጠባ ስራዬ ነው። ሁሌም እህትና ወንድም እኮ ናችሁ…መዋደድ አለባችሁ እያልኩ እመክራለሁ። ወይ የሆነ ነገር ሸርክቶት የሚደማ እጅ ይዤ ኡፍፍ እያልኩ ፕላስተር አደርጋለሁ ።

እስከዛሬ የከፋ ነገር ገጥሞኝ ሃኪም ቤት ሮጬ የሄድኩት ለሁለት ነገር ነው። አንድ ጊዜ ያንዳቸው እጅ ተሰብሮ፣ አንዴ ደግሞ አንደኛው ሳንቲም ውጦ።
አምስት ልጆች ስላሉኝ የልደት በአል ቶሎ ቶሎ፣ ተከታትሎ ነው የሚመጣው። እንደገና ሌላ መአት ሻማ፣ እንደገና ሃው ኦልድ አር ዩ ናው እያሉ መዘፈን፣ እንደገና ኬክ መግዛት (የምገዛው ኬክ ሁሌም መጠኑ አንድ አይነት ነው። አንዱን ካንዱ ያስበለጥኩ እንዳይመስል)። በዚህ ሁሉ ትርምስ መሃከል አንደኛው ልጄ ሁልጊዜም ጡሩምባውን እንደነፋ ነው። ትንፋሽ እስኪያጥረው፣ ከመጠን በላይ ጮህ አድርጎ ነው የሚነፋው። (ወይ ትኩረት እንድንሰጠው ወይ ደግሞ ሊያናድደን)። የሚያወጣው ‹‹ሙዚቃ›› ጭራ እና ቀንድ የሌለው ታምቡር የሚፍቅ ድምፅ ነው። ያናድደኛል ግን ልጄ ነውና ሳምባው እስኪፈነዳ መንፋት ይችላል። ምናልባት ከልምምድ ብዛት ችሎታው ሊሻሻል ይችላል። ለጊዜው ግን የምሰማው ነገር ስሪያ ላይ ያለች ዝሆን የምታወጣው አይነት ነው።

እናት ነኝ።
የእናትነት አለም ይሄ ነው። ለጤና ጥሩ አይደለም። ፀጥታ እና የጥሞና ሰአት ካገኘሁ ብዙ ጊዜ ሆኖኛል። የራሴ ጊዜ እና እረፍት ካገኘሁ አመታት ተቆጥረዋል። በባዶ እግር የሚሞቅ የባህር ዳርቻ አሸዋ ላይ መቆም የሚሰጠውን ስሜት አላውቀውም። መዋኛ ገንዳ አጠገብ አለሃሳብ በጀርባ ጋለል ብሎ ‹‹ልጆቼ የት ይሆኑ›› ከሚል ጭንቀት ተላቅቆ ዘና ማለት ምን ምን እንደሚል አላውቀም። እንደምንም ብዬ ከምሳ ሰአትe በኋላ ለጥቂት ደቂቃ አይኔን የመክደኛ ጊዜ ባገኝ እንኳን ለሳምንት ከእንቅልፌ የምነቃ አይመስለኝም።

አንዳንዴ 17ኛ ፎቅ ላይ ከሚገኘው ቢሮአችን ማታ አንድ ሰአት ላይ ወጥቼ ለብቻዬ ሊፍት ውስጥ ስገባ ጭንቅላቴን ከቀዝቃዛው የሊፍቱ ግድግዳ ላይ ደገፍ አደርግና፣ ይህቺን አጭር እና ጣፋጭ የፀጥታ ሰአት አጣጥማታለሁ።

መኪናዬ ውስጥ ሬዲዮ ከፍቼ አላውቅም።
ሁሌም የምነዳው በፍፁም ፀጥታ ታጅቤ ነው።
ይሄን ሁሉ ስላችሁ ግን እናት በመሆኔ እንደከፋኝ እና እየተማረርኩ እንደሆነ እንዳታስቡ።
እናት መሆኔን እወደዋለሁ።

ልጆቼን እወዳለሁ። ቤታችን በፍቅርና በበረከት የተሞላው በእነሱ ምክንያት ነው። እናትነት እጣ ፈንታዬ፣ አምላክ የሰጠኝ ፀጋ እና ማእረጌ ነው።
ልጆቼን መንከባከብ እና እድገታቸውን ማየት በምንም የማልቀይረው ደስታዬ ነው። አንዳንዴ እራት አቀርብላቸውና ዝም ብዬ ቁጭ ብዬ እያየኋቸው በልቤ፣ ‹‹እነዚህ ሁሉ ልጆች የማን ናቸው…ከየትስ መጡ?›› እያልኩ በደስታ እሞላለሁ።
—-
ለእናትና አባቴ ብቸኛ ልጅ ነበርኩ።
ቤታችን ትልቅ የድንጋይ ቤት ነበር። እናት እና አባቴ ቤቱን በፍቅር ሊሞሉት ቢሞክሩም እኔ ግን ብቸኝነት ያጠቃኝ ነበር። የራሴ ክፍል ነበረኝ። ገና ከልጅነቴ ጀምሮ።

በልብስ ወይ ደግሞ በቲቪ ሪሞት ኮንትሮል ከማንም ጋር ተጣልቼ አላውቅም።
የሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ ነበረኝ- ከወንድም ወይ ከእህት በስተቀር። የወንድም ወይ የእህት ፍላጎት ያንገበግበኝ ነበር።

የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ከወንድም እና እህቶቻቸው ጋር ተጠባብቀው ታክሲ ውስጥ ሲገቡ በሃይል እቀና ነበር። ምሳ እቃ ከፍተው አብረው ሲበሉ፣ እረፍት ላይ አብረው ለመጫወት አንዳቸው አንዳቸውን ሲጠብቁ ሳይ እቀና ነበር። ምንም ነገር ቢደርስብኝ ከሁሉም ሰው በፊት ሊያድነኝ እና ሊጠብቀኝ የሚችል፣ በደም የሚዛመደኝ ሰው ክፉኛ እናፍቅ ነበር። አስታውሳለሁ፤ አንዴ ትምህርት ቤታችን በከፊል ሲቃጠል ሁሉም ልጆች ወንድም እና እህታቸውን ፍለጋ ሲሯሯጡ እኔን ብሎ የመጣ ማንም ልጅ አልነበረም።

ለዚህ ነው ብዙ ልጆች እንዲኖሩኝ እመኝ የነበረው።

የዛሬ ባሌን የማግባት እድሌ ሃምሳ በመቶ ነበር። አሜሪካ ለትምህርት የሄደውን እጮኛዬን የማግባት እድሌ ደግሞ ሃምሳ በመቶ ።
ልቤ ሁለቱንም ይወድ ነበር። በእርግጥ መጀመሪያ የወደድኩት የመጀመሪያውን፣ አሜሪካ የሄደውን እጮኛዬን ነበር። ልቤ ለሁለተኛው የተከፈተው አሜሪካ የሄደው እጮኛዬን መጠበቅ ከሰማይ መና የመጠበቅ ያህል ስለሆነብኝ ነው። እዚህ ሃገር ኢንጂነር መሆን የማይቻል ይመስል አሜሪካ ሄጄ ኢንጂነሪንግ ልማር ብሎ በጣም ረጅም ጊዜ ቆየ።

የዚያን ጊዜ ኢንተርኔት ጨጓራ የሚልጥና ቀርፋፋ ስለነበር በዚያ ጎታታ ኢንተርኔት በስካይፕ መገናኘት አቸከኝ። በቪዲዮ እያወራን አንድ አረፍተ ነገር ሳይጨርስ ምስሉ ስክሪኑ ላይ ደርቆ ይቀራል።

አንዳንዴ አፉ አጓጉል ተከፍቶ እያለ ነው እንዲህ የሚሆነው።
ታዲያ ይሄን ጊዜ ዝም ብዬ ይሄንን ምስሉን አይና ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነሳ ምን እንደሚመስል ማሰብ እጀምራለሁ። ጠዋት ሲነሳ ምን እንደሚመስል የማላውቀውን ሰው ለማግባት ማሰቤ ያስፈራኛል። ሴቶች የሚያገቡት ሰው ጠዋት እንደተነሳ ምን እንደሚመስል ማወቅ አለባቸው ባይ ነኝ።
ከእንቅልፋቸው ሲነሱ ነፍሰ ገዳይ የሚመስሉ ፍቅረኞቸ ነበሩኝ። በዚያ ምክንያት የተውኳቸው።

ባሌን የተዋወቅኩት ከግብርና ጋር የተያያዘ ስብሰባ ላይ ነው። ስለ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር ምናምን የሚያወራ ስልጠና ነገር ነበር። ወደፊት ገበሬ የመሆን ሃሳብ ነበረኝ። ከፕላስቲክ የተሰሩት ወንበሮች ላይ ጎን ለጎን ነበር የተቀመጥነው። ካሮት የሚመስሉ የእጆቹን ጣቶች ሰረቅ እያደረግኩ ሳይ ትዝ ይለኛል። ከዚያ ማውራት ጀመርን- ስለ እንጆሬ። የእንጆሬ እርሻ ነበር እንዲኖረኝ የምመኘው።

በኋላ ለሻይ ቡና ስንንናኝ አሜሪካ ስላለው እጮኛዬ ነገርኩት። ‹‹በዱር ካሉ ሁለት ወፎች በእጅ ያለ አንድ ወፍ ይበልጣል›› አይለኝም? ተረት እና ምሳሌያዊ አነጋገር፣ ፈሊጥ ምናምን የሚገባኝ አይነት ሴት አይደለሁም ግን እሱ ነው የሚያዋጣሽ ማለቱ መሰለኝ።
የሚገርመው ግን እንዲህ ማለቱ ልቤ እንዲፈልገው አደረገ። አለ አይደል…የሴት እልህ…‹‹ምናባቱ ቆርጦት ነው ለሌላ ወንድ አሳልፎ የሚሰጠኘኝ?›› አይነት ነገር።

ከአመት ተኩል በኋላ በሰርግ ተጋባን
አሜሪካ ያለው እጮኛዬን ልብ እንደ መስታወት ያደቀቀ እና መቶ ሰዎች ብቻ የተጋበዙበት ቀለል ያለ ሰርግ ነበር። ባሌ በጥቁር ሱፍ አምሮበት- ሰፊ ትከሻው ኮቱን ወጥሮት- የሚጣፍጥ የአፍተር ሼቩ መአዛ እያወደኝ። አፍተር ሼቭ የሚጠቀም ወንድ ደስ ይለኛል።
ከሰርጉ ጥቂት ወራት በፊት አርግዤ ነበር። ግን ሆዴ ስላልገፋ ብዙ አያስታውቅም ነበር። የእናቴን ውብ ሃብል አድርጌ. አባቴ እጄን ጥብቅ አድርጎ ይዞኝ…..ስለሰርጌ የማስታውሰው ይሄንን ነው። የአባዬ እጄን አጨማመቅ….

ብዙ ሳልቆይ ልጄን ወለድኩ።
ብዙ ሳልቆይ ስል ሰርጌ ላይ ኬኩ እንደተቆረሰ ማለቴ ሳይሆን ከጥቂት ወራት በኋላ።

ከዚያ በኋላ በተከታታይ መውለድ ቀጠልኩ። እንደ እኔ ፍላጎት ቢሆን ቤቴን ሆስፒታሉ ውስጥ አድርጌ መመላለሱ ይቀርልኝ ነበር። ዝም ብዬ መውለድ ቀጠልኩ።

ሶስተኛው ልጃችን እንደተወለደ ባሌ ‹‹አሁን ይበቃናል›› አለ።
ይበቃናል? ይቀልዳል እንዴ?
ከቁብ ሳልቆጥረው ሁለት ልጆችን ጨመርኩ።

ልጆች ድንቅ ስጦታዎች ናቸው፡፤ ግን ሰውነትን እንዳልነበር ነው የሚያደርጉት።
የመጀመሪያዎቹ ሁለት ልጆቼ ሰውነቴን ፈጽሞ ቀይረውት ነበር፡፤ ከዚያ በኋላ ግን ለውጡ እምብዛም ነው።

አሁን ሳስበው በሰርጌ እለት ከነበረኝ አቋም አሁን ሳልሻል አልቀርም። እንደዚያ ጊዜ ወደ ላይ አይለኝ።
ከዚያ ጊዜ ይልቅ አሁን ሞላ፣ ሰፋ ብያለሁ። ዳሌዬ ሰፍቷል። ከበፊት ይልቅ ያሁኑ ሰውነቴ ያኮራኛል። ያው ወገቤ አከባቤ ትርፍ ስጋ አይጠፋም ግን ለማስተካከል እየታተርኩ ነው። ደረጃ ስወጣ የሚንቀጠቀጥ ትልቅና የላላ መቀመጫዬ ሊኖረኝ ይችላል።
ግን ያም ሆኖ አማላይ ቢጤ ነኝ።

….ለምሳሌ መቼ እለት መስሪያ ቤታችን በተለማማጅነት የተቀጠረ የ ሃያ አንድ አመት ጎረምሳ፣ በእድሜ እጥፍ የምበልጠው ጉብል – ወደ ጠረጴዛዬ መጥቶ የባጡንም የቆጡንም ሲቀባጥር ቆይቶ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው?
‹‹ነገ…ከቢሮ ወጣ ብለን ሻይ ቡና ብንል ምን ይመስልሻል?››
እውይ።

‹‹በጣም ደስ ይለኝ ነበር …›› አልኩና ግራ እጄን አንስቼ የጋብቻ ቀለበቴን እየጠቆምኩ ‹‹ግን ባለትዳር ነኝ›› አልኩት።
‹‹ውይ…ይቅርታ…ግን በጣም ቆንጆ ነሽ›› አለኝ።
እውይ።

እድሜው ሰላሳ ሁለት ቢሆንና ከእናቱ ጋር የማይኖር ቢሆን ቡናውን እጋበዝለት ነበር። አሁን አሁን ከተማው ውስጥ እንደእሱ አይነቶቹ በዝተዋል- ከእናታቸው ወይ ደግሞ እንደ እናት ከሚሰራቸው ሴቶች ጋር የሚኖሩ ወጣት ወንዶች።
ግብዣውን እቀበል የነበረው ባለትዳር ብሆንም ላጤ ስለሆንኩ ነው።
ትዳሬ ጣእሙን መለወጥ የጀመረው ከአምስት አመታት በኋላ ነበር።
ትዳሬ የተለወጠው ባሌ ስለተለወጠ ነው።
ሁላችንም ተለውጠናል። ግን ለውጡ ቀ……ስ ያለ ነበር።
….አለ አይደል…ምን የመሰለ የአትክልት ስፍራ ውስጥ እንደሚታይ ትንሽ አረም….መጀመሪያ ስታዩት ያን ያህል ትልቅ ነገር አይመስልም። ቀስ በቀስ ተስፋፍቶ አትክልትና አበቦቻችሁን ውርር እስኪያደርግ እና አንድ በአንድ ማነቅ እስኪጀምር።
—ይቀጥላል—–

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...