Tidarfelagi.com

‹‹ምን አጠፋ?››

መነሻ ሀሳብ This is Harassment አጭር ፊልም (ዴቪድ ሽዊመር)

ሃምሌ ላይ በማእረግ ተመርቄ እስከ ግንቦት ስራ ስፈልግ ነበር።
ቀኑ በገፋ፣ ወሩ በተባዛ ቁጥር- ትላንት በድግስ ዲግሪ ጭኜ ዘጠኝ ወር ሙሉ- ዛሬ ልክ እንደተማሪነት ዘመኔ በየቀኑ ከአባቴ የትራንሰፖርት ተቀብዬ ስራ ፍለጋ በወጣሁ ቁጥር- ሃያ ቦታ አመልክቼ አንዳቸውም ለማነጋገር እንኳን ባልጠሩኝ ቁጥር፤ ሰውነቴ መሳቀቅ፣ መንፈሴ መድቀቁን ቀጠለ።

የምበላው ባይቸግረኝ፣ ጎኔን ማሳረፊያ አልጋ ቢኖረኝም ተምሬ ግን ስራ ላገኝ አልቻልኩም።
መሳቀቄን ያዩ እናትና አባቴ ዘወትር ያፅናኑኛል።
እማማ እግዜርን ምርኩዝ አድርጋ ነጋ ጠባ ታበረታኛለች። ‹‹እሱ ባለው ቀን ይሆናል…አትሳቀቂ››፣ አባቴ ቅሬታውን ለመደበቅ እየታገለ በ‹‹አይዞሽ›› ይደልለኛል።

ክፉኛ መረረኝ።
በመጨረሻ፣ አንዲት ሴት አርግዛ፣ ወልዳ ልጅ አቅፋ የምትስምበትን ጊዜ ፈጅቼ- የእማ ቃል ሰምሮ እግዜር ባለው ቀን ካሳ የሚሆን ምርጥ ስራ-ፍጥንጥን ባለ መልኩ አገኘሁ። ፈረንጅ የሚበዛበት የእርዳታ ድርጅት ውስጥ ጀማሪ የአይቲ ባለሙያ ብለው ቀጠሩኝ። ጀማሪ ተባልኩ እንጂ ደሞዜ ግን ሃያ ዘጠኝ አመት ያገለገለውን አባቴን በሶስት እጥፍ ይበልጣል።

ልጅ አባቱን አይቀድምም ይላሉ። እኔ ግን በደሞዝም ቢሆን ቀደምኩት።
ፈነጠዝኩ። እነሱም ተገላገሉ።

ስራው የሚቆረቁር ነገር አልነበረውም። እግዜር የእስካሁኑን እንግልቴን ቆጥሮልኝ ነው መሰለኝ የማውቀውን የምሰራበት፣ የማላውቀውን የምማርበት እና በብዙ መልካም ሰዎች የተሞላ ቦታ ነው የወደቅኩት።

አለቃዬ አቶ ብሩክ ሰላሳዎቹ መሃል የሚገኝ ዘመነኛ-ደስ የሚል ሽቶ ተቀቢ-ቄንጠኘኛ ሸራ ጫማ ተጫሚ-ጂንስ በኮት አድራጊ ቀላልና ግሩም ሰው ነው። ምኑም አለቃ አለቃ አይሸትም።
ከአቶ ብሩክ ጋር በስራ ቀን-በቀን አንገናኝም- ነገር ግን አለቃዬ እሱ ነው። ልቀጠር ስመጣም ከፈታኞቼ አንዱም እሱ ነበር።
ፈገግ እያለ የስራ ቃለ መጠየቅ የሚያደርግ፣ መልስ ሲቸግር በአይዞሽ አይን የሚያይ፣ እንግሊዝኛ ሲያጥር ‹‹ግዴለም በአማርኛ በይው›› የሚል የመጀመሪያ ስራ ቀጣሪ እሱን ነው ያየሁት።
አልፌ መግባቴን- አለቃዬ እሱ መሆኑን የሰሙ እዚያ ቤት የሰነበቱ ሁሉ፣ ‹‹ታድለሽ›› ነበር ያሉኝ። ‹‹ጥሩ ሰው ነው›› ‹‹ብዙ ያስተምርሻል›› ‹‹ቶሎ ያሳድግሻል›› ነበር የነገሩኝ።
ታድዬ።

በስራ ጥቂት ወራት ከረምሁ።
ባለፈው ማክሰኞ አርብ ለሚደረግ ትልቅ አለም አቀፍ ስብሰባ ዲፓርተመንቱ ውስጥ ያለን ሁሉ ጠብ እርግፍ በምንልበት ሰአት- አምሽቶ መስራት መደበኛ ነገር በሆነበት ቀን እሱ በራሱ አሪፍ የአለቃ ቢሮው እኔና ኮሚኒኬሽን የምትሰራው ሳምራዊት ደግሞ በልቁ አዳራሽ ከሚገኙት ዴስኮቻችን ቁጭ ብለን የምንሰራውን እየሰራን ነበር።

ማታ አንድ ሰአት ሊሆን ሲል ሳምሪ ብድግ አለችና
‹‹ልጄ ሳይተኛ ልደረስበት በቃ…በጠዋት እገባለሁ….ቻው ምልእትዬ ›› ብላኝ ውልቅ አለች።
ሳምሪ እንደሄደች እጄ ላይ ያለውን ስራ ከቀረኝ ጊዜ ጋር እያመዛዘንኩ ልውጣ አልውጣ ስል አቶ ብሩክ በውስጥ ስልክ ጠራኝ።
ለረጅም ሰአት ከወንበሬ ስላልተነቃነቅኩ ተጫጭኖኝ ነበር። ብድግ ብዬ በሃይል ተንጠራራሁና ወደ ቢሮው አመራሁ።
የእንጨት በሩን አንኳኳሁ።
‹‹ግቢ›› አለኝ።
ገባሁ።

‹‹ ሃይ ምልእተ…እንዴት ነሽ ?›› አለ ከትልቅ ኮምፒውተሩ ጀርባ እንደተቀመጠ ቀና ብሎ እያየኝ።
ቢሮው ሁልጊዜም ንጹህና በሽቶው የታወደ ነው።
‹‹ሰላም አቶ ብሩክ›› አልኩኝ በሩን ክፍቱን ትቼ እዚያው እንደቆምኩ።
‹‹ እባክሽ ያ የወርልድ ባንክ ፓወር ፖይንት ፋይል የመጨረሻው ቨርዥን እየጠፋ አስቸገረኝ….ነይ እስቲ ምን እንደሆነ እይልኝ›› አለኝ።
በፍጥነት ወደ ዴስኩ ሄድኩ።

ከመድረሴ እኔ ተቀምጬ ፋይሉን እንድፈልግለት በሚጋብዝ መልኩ አሳልፎኝ ቆመ።
‹‹ምንድነው የሚያጠፋው?›› አልኩና ወንበሩ ጫፍ ላይ ተቀምጬ ኮምፒውተሩን መነካካትና ፋይሉን ፍለጋ ማሰስ ስጀምር የምሰራውን የሚመለከተው አቶ ብሩክ አንዴ ኮምፒውተሩን፣ አንዴ እኔን፣ አንዴ የያዘውን ስልኩን ተመልክቶ አዛጋና፣
‹‹ወይ ጉድ…አንድ ሰአት አልፏል ለካ….ዛሬ ቁርስ የበላሁ ነኝ…በሃይል እርቦኛል›› አለኝ።
ምን ብዬ እንደምመልስ እያሰብኩ ሳለ ፋይሉን አገኘሁና፣ ‹‹ይሄውና….›› ብዬ ጠቆምኩት።
እኔ በተቀመጥኩበት ፣ እሱ ደግሞ በቆመበት በትከሻዬ ላይ ፋይሉ ያለበትን ለማየት አጎነበሰና፤
‹‹የት ነበረ?›› አለኝ።

አንገቴ ላይ ንፋስ ቢጤ ሽው ሲል ተሰማኝ። መስኮት ተከፍቷል ወይስ ትንፋሹ ነው?
‹‹እ…እዚህ ማይ ፋይልስ ውስጥ ካለ ፎልደር አስቀምጠኸው ነው….ችግር የለውም በቃ…አሁን ዴስክቶፕህ ላይ አደርግልሃለሁ—ከዚህ በሁዋላ አይጠፋብህም›› አልኩኝ ፋይሉን ያስቀመጠበት ቦታ ሊደበቅ የማይችልበት ቦታ መሆኑን ስረዳ ተገርሜም-ትንሽ አፍሬም።
እንዲህ ያለው ቀላል ነበር ግር የሚለው ሰው አይመስለኝም ነበር።
ከዚያ ብድግ አልኩኝ።

ወዲያው ወደ በር ለመሄድ መንገድ ስጀምር ፣
‹‹ አመሰግናለሁ ምልእቲ…ጎበዝ ልጅ ነሽ…›› አለኝ።
‹‹አይ ቀላል ነገር እኮ ነው›› አልኩና ዞር ብዬ አይቼው እርምጃዬን ልቀጥል ስል
‹‹መሄድሽ ነው?›› አለኝ
‹‹አዎ›› አልኩ ሙሉ በሙሉ ወደ እሱ ዞሬ።
‹‹ወዴት ነው የምትሄጅው?››
‹‹እ…ወደ ቤት…ወደ ቤቴ››
‹‹ትንሽ ጠብቂኝ…ኮምፒውተሬን ላጥፋና እሸኝሻለሁ››
‹‹አረ አያስፈልግም…ታክሲ በሽ ነው ወደኔ ሰፈር….አልመሸም እኮ›› አልኩኝ ባልጠበቅኩት ነገር ደንገጥ ብዬ።

ታክሲ እንኳን በዚህ ሰአት በጠራራ ፀኃይም መከራ እንደሆነ እያወቅኩ ነው እንዲህ ያልኩት።
‹‹ተይ ግዴለም እኔ እወስድሻለሁ..በዚህ ሰአት ሴት ልጅ…ሊያውም አንቺን የመሰለች ልጅ….ዱርዬ ያስቸግርሻል›› አለ ኮምፒውተሩን እያጠፋ።
ነገሩ ደስ አላለኝም። በተለይ ‹‹አንቺን የመሰለች ልጁ›› አልጣመኝም።
‹‹እውነት አቶ ብሩክ….ራሴ እሄዳለሁ…ችግር የለውም….›› አልኩኝ ጫን አድርጌ።
ፊቱ ላይ የመሸነፍ ምልክት ሳይ አሁንም መንገዴን ልቀጥል ዞር ስል ሌላ ወሬ ጀመረ…
‹‹በነገርሽ ላይ…ስራው እንዴት ነው? ቢሮውስ? ወደድሽው?›› አለኝ።
በወሬው ድንገተኛ አቀያየር ደንገጥ ብልም አፌ ላይ ያለውን መልስ ‹‹ውይ አዎ…በጣም አሪፍ ነው…በጣም ወድጄዋለሁ…›› አልኩት። አቋቋሜ ፣ ፊቴ ወደእሱ ይዙር እንጂ- ከበሩ ራቅ ይበል እንጂ- ለመሄድ የጓጓ- ልቡ የተንጠለጠለ አይነት ሰው ነው።
‹‹ቲሙም አሪፍ ነው? በደንብ እያገዙ እያለማመዱሽ ነው? ›› አለኝ
‹አዎ…ሁሉም ሰው አሪፍ ነው…በጣም እያገዙኝ ነው›…በእውነት በጣም እድለኛ ነኝ ይሄን የመሰለ ስራ በማግኘቴ › አልኩ መልሼ።
ይሄን ጊዜ ከዴስኩ ጀርባ ያለውን መለስተኛ ሻንጣ የሚያህል ቦርሳውን ይዞ ከፊትለፊት መጣና ዴስኩን ላይ እንደመደገፍም- እንደመቀመጥም ብሎ ከእኔ በቅርብ ርቀት ቆም ብሎ-
‹‹እኛ ነን እድለኛ…እንኳንም አንቺን መረጥንሽ……›› አለ
‹‹አረ እኔ ነኝ እድለኛዋስ….›› ብዬ ሳልጨርስ
‹‹ለነገሩ ስትቀጠሪ አብረውኝ ኢንርቪው ያደረጉሽ ሰዎች ልምድ ያለውና ትንሽ ጠና ያለ ሰው ካልመረጥን ብለው በጣም ታግለውኝ ነበር…እኔ ግን አይሆንም ብዬ ተከራከርኩ። እሷ መሆን አለባት ብዬ ድርቅ አልኩኝ…ያው ሃላፊነቱ ከባድ ቢሆንም አንቺን ነው የምፈልገው አልኩኝ…››
ምን እንደምለው ለማሰላሰል ጊዜ አጣሁና ቶሎ ብዬ፤
‹‹እውነት ነው ሃላፊነቱ ከባድ ነው…››
‹‹በዚያ ላይ ደሞዝሽም ላይ ኤች አር ቁምስቅሌን አሳይቶኛል..የምልሽ እዚህ ቤት ማንም ሰው ጀማሪ ሆኖ ባንቺ ደሞዝ አልተቀጠረም…እኔ ነኝ ይቺ ልጅ ፖቴንሻል አላት ብዬ ስንት ሚሞ ፅፌ ያፀደቅኩት…››
አሁንም የምለው ጠፋኝና ዝም ብዬ አየሁት።
‹‹በደሞዙ ደስተኛ ነሽ አይደል?›› አለኝ ድምጹን ምቾት በሚነሳ ሁኔታ ጎተት አድርጎ።
‹‹እህም…እንዴ በጣም ደስተኛ ነኝ…›› አልኩኝ ሁኔታውን ችላ ብዬ።
‹‹ጥሩ ዋናው እሱ ነው…ስለዚህ ባንቺ ስላለኝ መተማመን ይሄ ማስረጃ ይሆናል ብዬ አስባለሁ አይደል…ትልቅ ደረጃ የምትደርሺ ልጅ ነሽ….መበርታት አለብሽ…እሺ?›› አለኝ በዚያው ጎታታ ድምፅ።

‹‹እሺ…አመሰግናለሁ.›› አልኩኝ።
መሄድ ፈልጌያለሁ።
በድምፁ ቆፈኛል። መንፈሱ ረብሾኛል። ሁኔታው ጎረብጦኛል ግን ሌሎቹ አይሆንም ሲሉ እኔ ነኝ ተከራክሬ ያስቀጠርኩሽ የሚል አለቃን- ያውም ተከራክሮ በዚህ የሚያህል ደሞዝ ያስቀጠረነወ ጥሩ ሰው- ያውም ዘጠኝ ወር ሙሉ ያለስራ ሲንከራተቱ ተከርሞ ከዚያ ሁሉ ስቃይ ገላግሎ ለወግ ማእረግ-ቤተሰብን ለማገዝ ያበቃን ሰው- እንዴት ነው ኦኬ በቃ ደህና እደር ተብሎ የሚኬደው?

ይሉኝታ አስሮኝ እግሬ ከመሬቱ የተመረገ ይመስል ተገተርኩ።
‹‹አለባበስሽም ጥሩ ነው…ደህና ትለብሻለሽ…የደሞዙ ውጤት ነው መሰለኝ…›› አለ ራሱ ተናግሮ ራሱ እየሳቀ።
‹‹እህ…›› አልኩና ወፍራም የክረምት ሹራቤን – ከዚህ ቀድም አይቼው እንደማላውቅ ሁሉ- እንደአዲስ ጎንበስ ብዬ አየሁ። ቡትስ ጫማዬን ተመለከትኩ።
ድፍረቴን አሰባስቤ፣በትህትና ‹‹እሺ አቶ ብሩክ ታክሲ እንዳላጣ…›› ብዬ መሄዴ መሆኑን ላስታውስ ስነሳ ዳግመኛ አቋረጠኝና፤
‹‹ርቦኛል እያልኩሽ ብቻዬን ጥለሽኝ ልትሄጂ ነው?›› አለኝ።
አወራሩ በሚያስተዛዝን ድምፅ- ብልግናን ባዘለ አስተያየት የታጀበ ነው።
ኮሰኮሰኝ።
እህም።
‹እ?›› አልኩኝ ሌላ አረፍተነገር ማቀናጀት አቅቶኝ፣ ዝም ማለትም ከብዶኝ።
‹‹በሃይል እርቦኛል አላልኩሽም?….ከጋርደን ካፌ የሆነ ነገር ብናዝስ…?ቶሎ ያመጡልናል…›› አባባሉ ጥያቄም ትእዛዝም ይመስላል። መልስ ሳልሰጠው ቦርሳውን ዴስኩ ላይ አስቀምጦ ለእንግዳ የተሰናዳው ሶስት ሰው የሚያስቀምጥ የቆዳ ሶፋ ላይ ሄዶ ተዘረፈጠ።
‹‹አይ…እኔ እንኳን ብሄድ ይሻላል..ባይሆን አዝዤልህ ልሂድ›› አልኩ ቁልቁል እያየሁት።
ከበር ካለኝ ርቀት ለሶፋው ያለኝ ርቀት እንደሚቀርብ ሳሰላ ለምን ተረበሽኩ?
በሩን ክፍት መተዌን ሳስብ ለምን ተፅናናሁ?
ቢሮው ውሰጥ ከእኔና እሱ ውጪ ማንም እንደሌለ ሳስብ ለምን ፈራሁ?
‹‹አትድረቂ በናትሽ…ብቻዬን መብላት አልወድም…ቶሎ በልተን እኔው ራሴ አደርስሻለሁ›› አለኝ። ይሄኛው ትእዛዝ ብቻ ነው።
‹‹ይሄን በመሰለ ደሞዝ አስቀጥሬሽ ጥለሽን ስትሄጂ አይደብርሽም?›› ያለኝ ይመስል ዳግም በውለታ ታስሬ ቆምኩ፣ ምላሴም ተባበረ።
‹‹እሺ በቃ›› አልኩና ‹‹በስልክ ልዘዝ አይደል?›› ስለው
‹‹ተይው እኔ አዛለሁ…ምን ይሁንልሽ?›› አለና ከሶፋው ከቅድሙ ጋር በሚቃረን ቅልጥፍና ተነስቶ ስልኩን ጨብጦ ያየኝ ጀመር
‹‹እኔ? ግድ የለኝም…ያገኘሁትን ነው የምበላው›› አልኩ። አሁንም የቅድሙ ቦታ የቆምኩ ነኝ።
‹‹ተይ ባክሽ? እንደዛ ግን አትመስይም-ማለቴ…ሰውነትሽ…›› አለ ሊጎርሰኝ ይመስል በስግብግብ አይኖቹ ከላይ እስከታች እየቃኘኝ።
(ይቀጥላል)

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...