Tidarfelagi.com

ስለ ያ ቡዳ

“እንጫወት እንጂ የምን ማፈር ማፈር
ያ ቡዳ ሳይመጣ ሳይጫነን አፈር ‘
-(የማንኩሳ ዘፈን )-

ስለሞት ሁለት አይነት አመለካከት አውቃለሁ ፤
የመጀመርያው ከሃይማኖታዊ መገለጥ የመነጨና ብዙ ህዝብ የሚያምንበት ነው፤
ሰው የእግዚያብሔር አምሳያ ፍጡር ነው፤ ሲሞት ነፍሱ ወደ ሰማይ ትሄዳለች፤ ምግባረ ሰናዮች የዘላለም ደስታ ይቀበላቸዋል ፤ ሓጥአን ደግሞ” እሳቱ የማይጠፋበት ትሉ የማያንቀላፋበት “ የስቃይ ቦታ ይጠብቃቸዋል፤

አለማውያን ከዚህ የተለየ አሳብ አላቸው፤ ይሄ ህይወት ብቸኛው ህይወት ነው ፤ ደስታህንም ፍዳህንም እዚችው ትቀበላለህ ፤ እፍርታምና መድልኦ የበዛበት አለም ውስጥ እንደምንኖር ባይካድም መልካም መልካም ሰዎች ጥሩ ጥሩ ፀጋዎችም ይገጥሙናል ፤

ከትልቁ ህዋው እድሜ አንፃር ሲመዛዘን ፤ የሰው ህይወት ሚጢጢ ብልጭታ ናት ፤ ካምፋየር ሲነድ ወደ ጨለማ የሚተኑ ደቃቅ የእሳት ብናኞችን አይተሻል? እንደዚያ ነን! ወይም ዘፋኙ እንዳለው ፤

Dust in the wind
all we are dust in the wind

ስለትንሳኤ ያለኝ አመለካከት እንደ ሰዱቃውያን ነው ፤ ከሞት በሁዋላ እንደመኪና ጎማ የሚቀየር ህይወት ያለ አይመስለኝም፤ ግን ደግሞ ሙሉ በሙሉ ርግጠኛ አይደለሁም! ልቤ መጠማቱን አላቆመም፤ ከዚህ አለም በብዙ እጥፍ የተሻሻለ አለም ውስጥ የመኖር እድል ቢሰጠኝ አይኔን አላሽም፤ አይመረመሬዋ ተፈጥሮ “ ቦታ አይፈጅም ብየ ብታገስህ ሁለተኛ ዙርም ለመኖርም ያምርሃል? “ ብላ ከገገመችብኝ ደግሞ ምን አረጋለሁ ! ሁኔታውን በፀጋ እቀበላለሁ ! “ በህይወት መኖርን የመሰለ ብርቅ ነገር በነፃ የሚገኝ አይደለም! እና የመኖር ክፍያ ሞት ነው፤” ይላል ስሙን የረሳሁት ሊቅ፤ ግጥጥም አርጌ እስማማለሁ! ይሄንን የውሰት ጥቅስ በውሰት ግድግዳ ላይ ለጥፌዋለሁ!

ካልዋሸን በቀር ፤ሁላችንም ሞትን በየጣቢያው እየሸወድን በዚህ ምድር ዘለግ ያለ እድሜ መቆየት እንፈልጋለን፤ አገሬ በሰማይ ነው የሚለው ሰባኪ ከኔ ያነሰ የመኖር ጉጉት አለው ብየ አላስብም ፤ ለዚያ ነው፤ እንኩዋን ቫይረስ ፤እሾህ እማይዘልቀው ጉዋንት አጥልቆ የማየው፤ ለዚያ ነው ከአፍንጫው ተርፎ አፍንጮ በርን መሸፈን እሚችል ማስክ አድርጎ የሚውለው፤

እኔም እንሆ ሞትን መቀበል የምችልበትን ስልጠና ለመቅሰም መፃፍትን መረመርኩ! አእምሮየንም በዘበዝኩ፤ ጆሮየንም በአረጋዊያን ዲስኩር አስጠለዝኩ ! ከሚከተለው ያገሬ ገበሬ ግጥም በስተቀር የመሰጠኝ የለም!

“ጎሽ አይጠመድም
ሞት አይለመድም”

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...