ምስጢሯን ለማወቅ የነበረኝ ጉጉትን ክብደትና ጥልቀት የተረዳችው ቅድስት አንድ ሰአት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ሁሉን ነገር ዘርዝራ ነገረችኝ። ግን ወሬውን የጀመረችው በአንድ ጥያቄ ነበር።
‹‹ለምንድነው ክብደት መቀነስ የምትፈልጊው?››
ሁሌም የማስበው ነገር ስለሆነ በቅደም ተከተል ነገርኳት። ‹‹በፊት በፊት የሚያምረኝን ልብስ ለመልበስ…ፋሽን ለመከተል…ቅልል እንዲለኝ. ነበር። አሁን አሁን ግን ጤናዬም እያሳሰበኝ ነው…በተለይ በዚህ ሁኔታ ከቀጠልኩ እነ ስኳር ምናምን ስላለመምጣታቸው እርግጠኛ አይደለሁም…ራሴን ቶሎ ቶሎ ያመኛል..አንገቴ አካባቢ ይጨመድደኛል…የምወደው የእግር ጉዞ ከባድ እየሆነ ነው…ባለፈው የመስሪያ ቤት ‹‹ሪትሪት›› ሄጄ ሁለት መቶ ሜትር ሮጬ ሳለከልክ ነበር…አሁን የሚያሳስበኝ ጤናዬ ነው…›› አልኳት።
‹‹ከዚህ በፊት ዳይት ምናምን ሞክረሽ ነበር?››አለችኝ
‹‹ያው ታውቂያለሽ…አልሞከርኩም…ስኳር ግን ቀንሻለሁ…ቅባትና .ስጋ …እንቁላል ቺዝ ምናምን ጭራሽ አልበላም…›› አልኩ ኮራ ብዬ።
ፈገግ አለችና፤ ‹‹እና ምንድነው በብዛት የምትበይው?››
‹‹ቁርስ በየቀኑ ገብስ ዳቦ በኦቾሎኒ ቅቤ እና ሙዝ… በአብዛኛው…አንዳንዴ ፓንኬክ እና ጨጨብሳ…ኦትሚል››
‹‹ምሳስ?›››
‹‹ምሳ እንጀራ በሽሮ በምስር…ሰላጣ…ምስር በሃይል እንደምወድ ታውቂያለሽ….ጎመን አንዳንዴ ግን በብዛት ምስር እና ሽሮ…››
‹‹እራት›››
‹‹ሩዝ…ፓስታ…እንጀራ በምስር….አንዳንዴ ድንች ወጥ….ታውቂያለሽ ብዙ አልበላም…በጣም ትንሽ ትንሽ ነው የምበላው…እና በጣም ብዙ ቆሎ እበላለሁ…አንድ ብርጭቆ ወይን እጠጣለሁ›…ኬክ አንዳንዴ እበላለሁ እንጂ ስኳር ያለው ነገር ትቻለሁ ማለት ይቻላል…ስጋም…ግን ክብደት እንደመቀነስ እጨምራለሁ…›
በረጅሙ ተነፈሰች።
‹‹ሂዊ…አሁን የምነግርሽ ነገር ለማመን የሚቸግር ነው ግን ታምኚኛለሽ አይደል?›› አለችኝ አትኩራ
እያየችኝ።
‹‹ምን ጥያቄ አለው…እንዲህ አበባ መስለሽ እያየሁሽ…›› አልኩኝ በጉጉት።
‹‹ያው ታውቂያለሽ…ለሶስት ሳምንት አሜሪካ ሄጄ ነበር….አሁን የምነግርሽን ሁሉ የተማርኩት እዛ ነው….ላሳጠርረውና አንቺም ልክ እንደኔ እና እንደ ሌላው መአት ህዝብ መረጃሽ የተዛባ ነው…ቅባት ትተሸ ካርብ ትበያለሽ….ለማንኛውም ዋናዎቹ ነገሮች ሶስት ናቸው….›› ብላ ጀመረች።
ለማመን ይከብዳሉ ብላ የነገረችኝ ሶስት ነገሮች ምንድን ናቸው?
1ኛ- ቅባት ነክ ምግብ እና ስጋ አያወፍርም። ቅቤ አያወፍርም።
2ኛ- የሚያወፍረው ካርቦሃይድሬት እና ስኳር ነው።
3ኛ- ክብደትን ለመቀነስ የሚፈልግ ሰው በስመ ፍራፍሬ እና አትክልት ሁሉንም ሊመገብ አይገባም። የሚያወፍር ፍራፍሬ፣ የሚያፋፋ አትክልት አለ።
ናላዬ ዞረ። ስጋ አያወፍርም? ቅቤ አያወፍርም?
ጠየቅኳት። ‹‹እየቀለድሽ ነው አይደል?›› አልኳት።
ፊቷ እንዳይደለ ነገረኝ።
‹‹ አይደለም….ሰው ስጋ እና ቅቤ አወፈረኝ ብሎ የሚማረረው በዳቦ እየበላ ነው…ይሄን የአመጋገብ ዘዴ የደረሱበት ሰዎች ምን የሚል ቀልድ አላቸው መሰለሽ…‹‹ዳቦው ላመጣው ውፍረት ቅቤውን አትውቀስ!››
ይሄን ካለችኝ በኋላ ሳይንሱን በግርድፉ ልታስረዳኝ ሞከረች። ሰውነታቸን ካርቦሃይድሬት እና ስኳር የበዛበት ምግብ ሲያገኝ ወደ ስጋ እና ስብ እንደሚቀይር፣ ስጋ እና ቅባት፣ ፕሮቲንን ሲያገኝ ግን ወደ ሃይል እንደሚቀይር የሚያስረዳ ውስብስብ ነገር ነበር። በኋላ በብዙ የዩቲዮብ ሃኪሞች ተደግፌ ነገሩን እስክረዳው ግር ብሎኝ ነበር ግን እውነት ነው።
ሳይንሱን ካወራችኝ በኋላ አመጋገቤን እንዴት ማስተካከል እንደምችል ነገረችኝ።
ከ70-20-10 ጋር አስተዋወቀችኝ።
70-20-10 ማለት ምንድነው? ምግባችንን 70 በመቶ ቅባትና ቅባት ነክ ምግብ፣ 20 በመቶ ፕሮቲን የቀረውን 10 በመቶ ደግሞ ካርቦሃይድሬት ማድረግ ነው።
ከዚህ በላይ ጠቃሚ ሆኖ ያገኘሁትና በቅድሰት መረጃ ላይ ተመስርቼ፣ የራሴን ጥናት ተከትዬ ያዘጋጀሁት የሚመከሩና የማይመከሩ የምግብ አይነቶች ግን ቁልፉ ነገር ነበር።
ልብ በሉ…ይሄ የ‹‹መራብ›› ‹‹ዳይት›› አይደለም።
እንደ ለመድነው ቁርስ ምሳ እራት እንበላለን….እምብርታችን እስኪገለበጥ እንጠግባለን….በራበን ጊዜ እንመገባለን…አዲስ የምናደርገው ነገር ግን 70-20-10ን ማእከል አድርገን አስቤዛ እንገዛለን።
ይህን በማድረግ ሰውነታችን የምንበላውን በማጠራቀም ፈንታ ለጉልበት እንዲጠቀምበት፣ ተርፎ የሚያስቸግረንን ውፍረትም ‹‹ለችግር ጊዜ›› በማስቀመጥ ፈንታ ‹‹አውጥቶ እንዲጥለው›› እናስተምረዋለን።
ይሄን ለማድረግ ምን ምን እንብላ…ምን ምን እንተው ልትሉ ትችላላችሁ? ዝርዝሩ ራሴው ለኢትዮጵያውያን በሚስማማ መልኩ በአማርኛ ካዘጋጀሁት ፅሁፍ ቀጥታ መጥቶ መጨረሻ ላይ ተቀምጦላችኋል።
እኔ ያወቅኩትን፣ እኔን የረዳኝንን ይህንን መረጃ ለማካፈል አመት የቆየሁት ዘላቂነቱን ሳላረጋግጥ አላወራችሁም ብዬ ነው…አሁን ይህንን አረጋግጫለሁ…ይህ የአመጋገብ ዘዴ አያሰቃይም….አያስቸግርም…ክብደትን ከመቀነስ በላይ ያነቃል፣ ቆዳን ያጠራል.፣ ፀጉርን ያሳድጋል፣ ተላላፊ ካልሆኑና የሃገራችን ፈተና እየሆኑ ከመጡት በሽታዎች ይከላከላል…(ሌሎች ሰው ፊት የማይወሩ ጥቅሞችም አሉት…ሃሃሃ)
መጀመሪያ ላይ አዲስ ነገር ስለሆነ ግር ይላል…በአንድ ሳምንት ግን ተዋህዷችሁ ውጤቱን ማሳየት ይጀመራል….
ወዳጆቼ፣ ከዚያ በኋላ ስለዚህ አመጋገብ የምታወሩት እኔ ሳልሆን እናንተ ትሆናላችሁ ብዬ አስባለሁ….በአንድ ነገር ግን ጥርስ ልትነክሱብኝ ትችላላችሁ….ስትከሱ የድሮ ልብሳችሁ ሁሉ ስለሚሰፋባችሁ አዲስ ልብስ እና ጫማ የመግዣ ወጪው ከባድ ነው ፡)
በሉ እንግዲህ ….መልካም የመሸናቀጥ ጊዜ…..!
ዋናዎቹ ነጥቦች
1. ከተፈጥሮ እስከተገኘ እና በፋብሪካ እስካልተነካካ ድረስ ስጋ እና ቅባት ነክ ነገር አያወፍርም.
2. ከፍተኛ ካርቦሃይድሬት እና ስኳር ያላቸው ምግቦች እና የታሸጉ ምግቦች ያወፍራሉ
3. የሰው ልጅ ሲፈጠር ስጋን እንዲመገብ ሆኖ ነው
4. አላማችን ውፍረት መቀነስ ከሆነ ከአትክልትና ፍራፍሬዎች ውስጥ እንኳን ክብደትን ለመቀነስ የማይመከሩ አሉ
ለኢትዮጵውያን የሚመከር የአመጋገብ ዘዴ ( በርካታ ኪሎዎች ለመቀነስ ለሚፈልጉ ሰዎች ይህንን በትክክል መከተል በአንድ ሳምንት ውስጥ ልዩነቱን ያሳያል)
1. በቀን ከሶስት ጊዜ በላይ አይመገቡ። ነገር ግን የምግቡን መጠን አይገድቡ። እስኪጠግቡ ይመገቡ። በመሃል የሚበሉ ነገሮች ግን አይኑሩ (ሰናክስ)
2. ካልራብዎት አይብሉ።
3. የጎንዮሽ ጉዳት- ይህ አመገጋብ ሰውነታችን ሃይል የሚጠቀምበትን መንገድ በድንገት ስለሚቀይር ለሶስት ወይ አምስት ቀናት መድከም፣ መጠነኛ የራስ ምታት ሊያስከትል ይችላል። ከዚያ በሁዋላ ግን እጅግ ቀላልና ለረጅም ጊዜ የሚሆን ነው።
4. በአብይ ጾም ወይም በረጅም የፆመ ወቅት ጊዜ ለመተግበር ሊቸግር ስለሚችል የጤና ችግር ግፊት ከሌለ ከጾም ፍቺ በኃላ ቢጀምሩ ይመከራል።
መብላት የሚመከሩ
እንቁላል (በማናቸውም አይነት)
ስጋ (ፋብሪካ ያልነካው) ቀይ በተለይም የፍየል ወይ የበግ በማንኛውም መንገድ (ወጥ፣ ጥብስ፣ ክትፎ…)
አሳ (ማንኛውም ያልታሸገ እና ሌላ ተጨማሪ ማቆያ የሌላው)
ዶሮ
ቅቤ (የአበሻ፣ የፈረንጅ ጨው ያልበዛበት፣ ስኳር የሌለው)
ቺዝ/ አይብ (ማናቸውም አይነት) የፋብሪካ ባይሆን ይመረጣል (ጎት፣ የአበሻ፣ፈታ…ሞዜላ….ሁሉም አይነት )
ኦሊቭስ
የጤፍ እንጀራ
አቦካዶ
አትክልት (ከመሬት በላይ የሚበቅሉ በሙሉ በተለይ ቅጠላ ቅጠል)
ተልባ፣ ኑግ እና ሰሊጥ፣ ሱፍ
ቲማቲም
እርጎ
ኦቾሎኒ፣ ሻይ እና ቡና (ያለ ስኳር)
መብላት የማይመከሩ
ስኳር ወይም ማናቸውም ስኳር ያለው ነገር (የተፈቀደም ቢሆን)
ማር (የተፈጥሮም ቢሆን)
ማናቸውም አይነት ዳቦ (ገብስ፣ አጃ ጤፍም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ጤፍ ካልሆነ በስተቀር)
– ፒዛ
– ገንፎ
– ዳቦዎች
– አትሚል
ከአቡካዶ እና አንዳንዴም ከስትሮውቤሪ ውጪ ማናቸውም ፍራፍሬ ክብደትን ለመቀነስ አይመከርም። ሙዝን ይጨምራል
የእህልና የጥራጥሬ ዘሮች (ምስር፣ ሽሮ፣ ቆሎ፣ ….ባቄላ….) ቅንጬ)
ሩዝ
ወተት (ወተት ከፍተኛ የስኳር መጠን አለው) ሆድንም ይነፋል። የላም ወተትም ቢሆን አይጠቀሙ።
አልኮል መጠጦች ( ለሶስት ሳምንት ያቁሙ) በተለይ ቢራ
ከሶስት ሳምንት በኋላ ደረቅ አልኮሎችን መጠጣት ይቻላል (በጣም በትንሽ መጠን) ለምሳሌ ቮድካ፣ ውስኪ፣ ጣፋጭ ያልሆነ ወይን ግን ቢተው ይመረጣል
በአጠቃላይ አልኮል በብዛት መውሰድ አይመከርም
ከመሬት በታች የሚበቅሉ ማናቸውም አትክልቶች (ድንች፣ ቀይስር. ካሮተ…..) በሙሉ ከፍተኛ የስታርች መጠን ስላላቸው አይመገቡ
ተጨማሪ መረጃ
ማር ከስኳር ቢሻልም ኢንሱሊንን ከፍ በማድረግ እንድንራብ ያደርጋል። የጣፋጭ መጠንንም ይጨምራል። ማር አይጠቀሙ
የጤፍ ዳቦም ሆነ ገብስ ከስንዴ ጋር ነው የሚጋገረው። የሚፈልጉት ክብደት ጋር ሲደረስ ቀስ በቀስ መመለስ ይቻላል። የአበሻ ቅቤ ይመከራል። ክትፎ ሲበሉ በማንኪያ ይብሉ። እንጀራ አያብዙ። ቆጮም ሆነ ዳቦ አይጠቀሙ።
ፍራፍሬዎች ለጤና አስፈላጊ ቢሆኑም ከፍተኛ የስኳር መጠን ስላላቸው ክብደት ይጨምራሉ። የሚፈልጉት የክብደት ደረጃ ላይ ሲደርሱ ቀስ በቀስ መጨመር ይቻላል
እህልና ጥራጥሬዎች ከፍተኛ የካርቦሃይድሬት መጠን ስላላቸው ለጊዜው መገደብ ወይ መተው አለብን። በኋላ ላይ መጨመር እንችላለን። በተለይ ሽሮ አይመከርም
ምንም አይነት ሩዝ አይመገቡ
ከፍተኛ ኪሎ መቀነስ ለሚፈልጉ ሰዎች እንጀራ በቀን ከአንድ ቁርጥ በላይ ባይበላ ይመረጣል። የሚፈልጉት ደረጃ ሲደረስ ግን ወደ አንድ እንጀራ ከፍ መድረግ ይቻላል
አቦካዶ በብዛት ይመገቡ
One Comment
Eski degmo yanchi limokirew…gin ewunet yishalal…temechitognal.