Tidarfelagi.com

የፖለቲካ ቋንቋችን

እጄን በሳሙና ከመታጠብ በተረፈኝ ጊዜ ለንጀራ የሚሆን ስራ እሰራለሁ፤ ማታ ማታ ደግሞ አፌ ላይ ነጭ ሽንኩርት፤ ትከሻየ ላይ ነጭ ጋቢ ጣል አድርጌ ዩቲውብ ላይ እጣዳለሁ፤
ከፊልሙም ከዘፈኑም ቀማምሼ ያገሬን ቃለመጠይቅ ወይም ውይይት መመልከት እጀምራለሁ:: አልናደድም፤ አላዝንም፤ እንቅልፍ ደርሶ ከነዚህ ስሜቶች ይገላግለኛል : :
አይበልብንና በእለት ተእለት ውሉዋችን በፖለቲካ አማርኛ የምንግባባ ቢሆን ህይወት እንዴት እጅ እጅ ይል ነበር? ሳስበው ራሱ ዘገነነኝ! ነገሩን በንፅፅር ለማየት የሚከተለውን ከፍቅር እስከመቃብር የተቀነጨበ ውብ ስነፅሁፍ አንብቡልኝ፤
“ ሰብለ ወንጌል የገብሬን አንዲር እንዲህ በሩቁ በሰማች መጠን ያፏ ምሬት እየጣፈጠ፤ ጠቅላላ ስሜቷ ካዘን ወደ ደስታ እየተለወጠ ሄደች፤ የእንባ ጎርፍ ያበላሸው ፊቷ እንደገና ውበትና ደም ግባት ትንሽ በትንሽ መቀባት ጀመረ፤”
( ፍቅር እስከ መቃብር፤ ሀዲስ አለማየሁ ገፅ 96)
ይሄንን አንቀፅ አንድ የዘመናችን ፖለቲከኛ ቢፅፈው እንዲህ ሊያደርገው ይችላል፤
“ በአማራ ክልል ፤ ምስራቅ ጎጃም ዞን ነዋሪ የሆነችው ፤ሰብለ ወንጌል ከአርብቶ አደርነቱ ጎንለጎን ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያ በመጫወት ህብረተሰቡን የሚያገለግለውን የገብሬን ዋሽንት ከፍተኛ ትኩረት መከታተል ጀመረች፤ በከባድ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቆ የቆየው ገፅታዋ ተሻሻለ ፤ ቀደም ብሎ የነበረው እና ዛሬ ድረስ እየተንከባለለ የመጣው ሀዘኗ ባስቸኳይ ተቀረፈ! መስቀልኛ መንገድ ላይ የነበረ ውበቷ ቀስ በቀስ ወደ ትክክለኛ መስመር መመለስ ጀመረ! ለረጅም ጊዜ ተራርቀው የነበሩት ፊቷና ደም ግባቷ ተቀራርበው መነጋገር ጀመሩ! “
( የፀጥታ ችግር እስከ መቃብር፤ አንቀፅ 96)
Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

One Comment

  • ኮዲኒ commented on June 4, 2021 Reply

    ወቸ…ጉድ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...