በዳግማይ ምኒልክ ዘመን ባንዱ ገጠር ውስጥ አንዱ ባላገር የሌላውን ሚስት ወሸመ፤ባልየው ሲባንን ውሽምየውን በጥይት ልቡን አለውና ካገር ተሰደደ፡፤ ይህንን የሰማ ፤ ምህረቴ የተባለ ፤እንደ ሆመር አይነስውር የሆነ፤አውቆ አበድ ባለቅኔ እንዲህ ብሎ ገጠመ፤
“አገሩ ባዶ ነው፤ ያም ሄዶ ያም ሞቶ
የፈለጉት ነገር በቤታቸው ሞልቶ”
ውሽምየው እሚፈልገው ምን ነበር? ፍቅር ፤ ምናልባትም በሴት ገላ መታቀፍ፤ ባል እሚፈልገው ነገር ምንድን ነበር? ትዳሩን አስጠብቆ ባገሩ መኖር ፤ጀብደኝነት ሁለቱም ሁሉንም አሳጣቸው ፤ ውሽማ ውድ ህይወቱን አጣ ፤ ባልየው ደግሞ አገሩን አጣ ፤መከበር ባገር ነው፤ ባንድ ጊዜ ትዳሩን፤ አገሩን ክብሩን በገዛ እጁ ተነጠቀ!
ሁለቱ ቆም ብለው ቢያስቡ ኖ አማራጭ አያጡም ነበር፤ ውሽማው ትንሽ እልፍ ቢል ሌላ ያልተያዘች ቆንጆ ሊያገኝ ይችላል፤ ግን የቆመበት ሰው ቆም ብሎ አያስብም! ባልየው ቢታገስ ውሽማውን በፍርድ ከሶ የማስቀጣት አማራጭ ነበረው፤ ባገራችን በትዳር ላይ የማገጠ ሰው የሚቀጣበት” ይናፋ “ እሚባል ህግ ነበር፤
ባለቅኔው “የፈለጉት ነገር እቤታቸው ሞልቶ “ያለው ይሄንን ነው፤ ሁለቱ ወደረኞች ባገሩ ውስጥ የሚገኙትን የኑሮ አማራጮችና የ ፀጋዎች ማየት ተስኑዋቸው መና ቀሩ!
የፖለቲካ ታሪካችንም ከዚህ አይለይም! የሚያስሞት ምክንያት ሳይኖር በከንቱ መሞት፤የሚያስገድል ምክንያት ሳይኖር በከንቱ መግደል፤ መነጋገር መወያየት እና መሸመጋገል የሚባሉ ብዙ ፀጋዎች በቤታቸው ሞልተው እንደሚገኙ በመርሳት መጋደልን ብቻ ማሰብ! በባላንጣነት መተያየት! ጨዋታው ከዚህ አያልፍም!
“ አገሩ ባዶ ነው” አለ ምህረቴ! ሁለት ሰዎች ስለተጠፋፉ “አገሩ ባዶ ነው” እንዴት ይላል? አገሩ ሁለት ሀይለኞች ስለጎደሉበት እንዴት ነው ባዶ እሚሆነው? የዚህ መልስ ግልፅ ነው፤ሃይለኞች ሲወድቁ ብቻቸውን አይወድቁም ፤ጦሱ ለጭፍራቸው እና ጉዳዩ ለማያገባው ሰላማዊ ሰው ይተርፋል!
ጀብደኝነት ወንዝ አያሻግርም!!
የህግ የበላይነት ይቅደም!
የህዝብ ሰላም ይቅደም!
የሽማግሌ ያለህ!