Tidarfelagi.com

ጉደኛ ምሽት

ከጥናት፤ከጥፈት እና ከዩቲውብ በተረፈኝ ጊዜ አውደለድልበታለሁ በተለይ አርብ ምሽት ፤በቤቴ አቅራቢያ ወደ ምትገኝ ባር ጎራ ማለት ደስ ይለኛል፤ እዛ አሪፍ የአይርሽ ድራፍት አዝዤ ወደ ባንኮኒው አፈጣለሁ፤ባንኮኒው ጀርባ የባሩ ባለቤት ቆማ አስተናጋጆችን ታሰማራለች ፤ባየችኝ ቁጥር ረጅም ፈገግታ ትለግሰኛለች፤ እኔም እንደ ውሃ ፈሳሽ ፤እንደ እንግዳ ደራሽ ፤የሆነ ፈገግታ እመልስላታለሁ፤

እድሜዋ ከሃያሁለት እስከ አርባ ሁለት ይገመታል፤ የሚያብረቀርቅ ወይባ ፀጉር አላት፤ጡትዋ…በዚህ የጦም ቀን ስለጡትዋ ከመናገር እቆጠባለሁ፤ እንደክብሪት የቀጠነች ሲጃራ ትጠጣለች፤ ሰውነቱዋ ላይ ንቅሳት አይታይም ፤ ንቅሳት የሌለው፤ የሰራ አከላቱን ያልበሳ ፈረንጅ ማግኘት ከባድ ነው፤

ቤቱ የነጮች ነው ፤ ጥቁር ድርሽ አይልበትም ፤ በጣም ውድ ስለሆነ ይሆናል ፤ ብቸኛው ጥቁር እኔ ነኝ፤ ያገሬን ገፅታ በሚመጥን መልኩ ሁሌም ዝንጥ ብየ እመጣለሁ፤ ብብቴ ስር ሽቶ እነፋለሁ፤ ነጭ ሼሚዜን እለብሳለሁ፤ የሚሆነው አይታወቅም ብየ ኮንደም(ላርጅ ሳይዝ🙂) በኪሴ ውስጥ መያዝ አልረሳም፤ አብዛኛው ኮንደም ኪሴ ውስጥ እያለ ያገልግሎት ዘመኑ ያልፋል፤

እንደምታተኩርብኝ ስባንን፤ የሞቀኝ አስመስየ ደረቴ ላይ ያለውን የሸሚዜን ቁልፍ እፈታለሁ፤ደረቴ መቸም የሰጠ ነው፤ብሉኬት ያስፈልጣል፤ትንሽ አጋነንሁት መሰል ፤ እሺ፤ብሉኬት ያስነቅሳል፤

ከባንኮኒው ጀርባ ትቆማለች ፤ ሁሌ ወደምቀመጥበት ቦታ አይኑዋን ትሰደዋለች፤ ታገኘኛለች፤ፈገግግግ!!! እየቆየሁ ፈገግታዋ የሆነ ድብቅ አጀንዳ ያዘለ ይመስለኝ ጀመር ፤በምላሹ ገራም፤ ያልተገራ፤ ያልተላገ ያልተጠረበ ፈገግታ እለቅባታለሁ፤የሱዋ ፈገግታ ብዙ አይቆይም፤ባንፃሩ የኔ ፈገግታ እንደ ሪዝ ፤ አፌ አካባቢ ለረጅም ጊዜ ይቆያል፤

አንድ ቅዳሜ ምሽት፤ ወደ እኔ መጣች፤ ሞቅ እንዳላት ያስታውቃል ፤ በሶፍት ወረቀት የተፃፈ ማስታወሻ ጠረጴዛየ ላይ አስቀምጣልኝ በጉዋሮ በር መቀመጫዋን እየወዘወዘች ወጣች

ወረቀቱን ገለጥ አድርጌ ሳየው፤

“I will wait you in the restroom” ሽንትቤት እጠብቅሃለሁ” ይላል፤

ገና አንብቤ ሳልጨርሰው እግሬ መሀል ያለው ሞተር ሲቀሰቀስ ይሰማኛል፤

ዞር ዞር ብየ አየሁ፤መሸተኞች በቲቪና በቢራ ተጠምደዋል፤

መፀዳጃ ቤቱ ውስጥ አግኝቻት ላቅፋት ስንጠራራ፤
“ ስማ፤ ይሄንን መፀዳጃ ቤት የምታፀዳልኝ ከሆነ በሰአት ስምንት ዶላር ልከፍልህ ዝግጁ ነኝ” አለችኝና ሲጃራ ማጨስዋን ቀጠለች፤

ጥቁሮች እዛ ቤት ለምን ድርሽ እንደማይሉ የገባኝ ያኔ ነው፤

ከጥቂት አመታት በፊት ባልንጀራየ፤ ራሱን ለማጥፋት ሙከራ ከማድረጉ በፊት የፃፈው የግጥም ኑዛዜ ትዝ አለኝ፤

የማይሆን የማይሆን፤ ስለተመኘሁኝ
ይበለኝ ! የግሬን አገኘሁኝ
ቅሌቴ፤
አሳይለም ሳላገኝ ፤ነጭ ልንጭ ማለቴ
በምቾት ሳልከርም፤ በምኞት ማጨቴ
ደሞ እንደቀናው ሰው፤ ያንን መላጨቴ
ሳያጣሩ ድርያ ፤ለማንም ላይበጂ
እኔን ብሎ በጂ

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

2 Comments

  • weluteklit2017@gmail.com'
    ሰሜ ምግባሬ ነው። commented on December 7, 2019 Reply

    😁😁😁😁
    አሪፍ ነው! አሪፍ ነው!
    ይገፋበት።

  • ኮዲኒ commented on June 6, 2021 Reply

    አረረረረረ ኡሩሩሩሩ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...