Tidarfelagi.com

መስኮት

የቀሰቀሰኝ የሙልጭታ ድምጽ ነው –የማዳለጥ። ማታ ራት በልተን፥ እዚያው የተውነውን ሳህን በዕንቅፍ ልቧ ሳትረግጠው አልቀረችም። አስታውሳለሁ በዕንቅልፍ ልቧ የመሔድ ችግር እንዳለባት የነገረችኝ እንደቀልድ ነበር።

–ደግሞ እንዳትደነግጥ በዘረመላችን ያለ ነው። እናቴም ስሊፕ ዋከር ነበረች ሂሂሂ… ብላ ስትነግረኝ የምሯን አልመሰለኝም ነበር።
(ዐምደኛ ለሆንኩበት መጽሔት ‘ የዘረመል ሂያጆች ‘ የሚል ርዕስ ያለው ጽሑፍ አዘጋጅቼ የነገረችኝ ሰሞን አስነበብኩ።)

እንዲህ ስትለኝ አፏ አከባቢ የከሸፈ ፈገግታ ነበር። ወዲያው ገጿ የተዘቀዘቀ ነጠላ የለበሰ መሰለ –ጨዋታ ቀየረች። አንድ ፊት ላይ ይሄን ሁሉ አይነት ኪነት መመድረክ ትንሽ አይከብድም? እያዘነች ለምን ትስቃለች? እየሳቀችስ ለምን ታዝናለች? ከእሷ በቀርስ ሂሂሂታንና ምፅታን ኩታ ገጠም ማድረግ የቻለ ማነው?

በሰማሁት ድምጽ እንደባነንኩ እጆቼን አንሶላው ውስጥ ሰደድኩ — አልነበረችም። መብራቱን አብርቼ ስመለከት ግርግዳውን እየዳሰሰች ነበር። ተነስቼ ወደ አልጋው ጫፍ አቅፌያት ተመለስኩ። ደረቴን ተንተርሳም ለደቂቃዎች በተቀመጥንበት በዝምታ ቆየች። የፖስታ ስጎ የረገጡ የእግር ጣቶቿን አያለሁ። ጣቶቿ የሚበሉ የፓስታ ክርታስ መስለዋል። የራስ ጸጉሯን በቀስታ እፈትላለሁ። ኅሊናዬ ውስጥ የቢትልስ ‘ ዌን ማይ ጊታር ጀንትሊ ዊፕስ ‘ ይፈስሳል። (ይሰማት ይሆን? ማለት ወደ ኅሊናዬ እንደማዘንበል ብላለች) የጸጉሯ ዛሎች እንደ በገና አውታር ናቸው። ጣቶቼ ጸጉሯ ውስጥ ሲርመሰመሱ ያላቸው ዜማ ምንድነው?? ኖታውስ እንደምንድነው??

— ታውቃለህ… መስኮት እየፈለግኩ ነበር – መስኮት።

— መስኮት??

–አዎ መስኮት። አልገርምም??

በእንቅልፍ ልቧ ለምን መስኮት ትፈልጋለች?? . . .ግራ ቢገባኝ ክፍሌን አየሁ። ተራ የወንደላጤ ቤት ነው። ተራ ያስባለው የመስኮት አለመኖር አይደለም። በር እንጂ መስኮት ምን ያደርግልኛል? እንዲህ ስል የመስኮት አስፈላጊነት ምንድነውም ማለቴ ነው[?] ከበር የማይገኝ፥ ከመስኮት ብቻ የሚገኝ ልዩ ጥቅምስ ምንድነው?? ማናፈሻ ነው?? ወይስ የአደጋ ጊዜ መውጫ ነው?? ለጽዳት ከሆነ ክፍሌን እንደ ሴት አጸዳለሁ። ” እንደ ሴት ” አባባሌ አይጥምም። ጽዳትን ሴት ላይ ታግ ማድረግ ይመስላል። ጽዳት ግን ግርድና አይደለም። ፌሚኒስቶች የሚታገሉት? ይህቺ ሐገር የሴት ልጅን ታሪክ ከማዕድ ቤት ድስት ጋር ሰቅላ ስላኖረች ነው። የሉሲያውያን ታሪክ ቢፈለግ? ተደብቆ የሚገኘው የጠለሸ የድስት ቂጥ ላይ እንደ ነቁጥ ሰፍሮ ነው። አብዮቱ ሞር ኩሽናዊ ነው –ከዚያ አልወጣም።

” እንደ ሴት አጸዳለሁ” ስል የሚገባቸው አሉ። እንደ ሴት የሚለው ቃል ግራ ዘመምና ቀኝ ዘመም አለው –በዚህም ተከፍለናል። ” እንደ ሴት ” ስትል ለብዙ ይተነተናል። ” እንደ ሴት ” የሚለው ቃል የሕብረተሰቡ መስፈሪያ ነው። አንዱን ከአንዱ የሚያነሱበት፥ የሚያነጽሩበት፥ የሚመዝኑበት –ማስተዛዘያቸው ነው። እንደ ሴት ያደርገዋል ካሉህ –ጄንትልሜን አይደለህም። ” እንደ ሴት ” ለወሬ አመላላሾች ነው። እንደ ሴት ከተባለ ለአድሃሪያን ነው። እንደ ሴት ለልክስክስ ነው። እንደ ሴት –ጓዳ ጓዳውን ለሚል ነው። እንደ ሴት ለሚልፈሰፈስ ነው –ቆፍጠን ላላለ። የሴት ልጅ ዲሲፕሊንድ ላልሆነ የሚለጠፍ ታርጋ ነው።

ግለሰብ፥ ግሩፕ፥ ሶሳዪቲ፥ ካንትሪ –የሴት ልጆች ናቸው። እዚህ ጋር የትርጉም መጠፋፋት አለ። ተቃርኗዊነትን በሁለት ጽንፍ ይዘናል። እምዬ የሚባል ንጉስ የነበራት ” እናት ሐገር ኢትዮጵያ ” ልጆቿን ” የሴት ልጆች ” እያለች ስትሳደብ ማየት ምን አይነት ሽሙጥ ነው?? በራስ ላይ ኩሸት አይሆንም??

ወንደ ላጤነት ሲባል በቆሸሸ ካልሲ ውስጥ የጠለቀ እግር በዓይኑ ውልብ የሚልበት መዓት ሰው አለ። ቢያንስ የእኔ የወንደላጤነት ዌይ እንደዚያ አይደለም። ይሄን ቤት ያገኘልኝ ደላላ ሲደውልልኝ፤ ክፍሉን ለመጀመሪያ ጊዜ መጥቼ አየሁት። ደስ የሚል ቤት ነው። ለሥራ ቦታዬም ቀረብ ይላል። ተስማምቼ ይሆነኛል ስለው? …ቤቱ መስኮት እንደሌለው አውቅ ነበር። ዕውር አይደለሁም። የመስኮት አለመኖር ግን የአንድን ቤት ሙሉነት አያጎድለውም። በአዲስ አበባ የሚከራይ ቤት ማግኘት ብቻውን ሥራ ነው። በዚያ ላይ ‘ መስኮት ያለው ‘ ምናምን እያልኩ ብቀናጣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደመመኘት ነው። ሆሆ ! አስቀድሜ….

–ስፔሻሊ መስኮት ያለው ቤት ፈልግልኝ ብዬው ቢሆን ትንሽ ዊርድ አይሆንም?

ደላላው….

–ምናልባት ካልሲውንና የበላበትን ማጠብ የማይወድ ቁናሳም ተከራይ ቢሆን ነው… ብሎ ቢያስብ በማን ሊፈረድ ነው?

መልሶ ዕንቅልፍ እንደወሰዳት ባይም ማረፍ አልቻልኩም። ዓይኔን ለመጨፈን ስሞክር ቤቴ ውስጥ ያጣሁትን መስኮት ኅሊናዬ ውስጥ እያገኘሁት ተቸገርኩ። መልሼ ገለጥኩት፥ መልሼ ከደንኩት። ትርጉም ለመስጠት ሞከርኩ።

መስኮት . . .መውጪያ መፈለጓን ያሳያል? ከምን ማምለጥ ፈልጋ ይሆን?? . . .መስኮት. . . ከውጪ ወደ ውስጥ ማሾለኪያ ሊሆን አይችልም? ሌላኛው ሰው ማነው? . . .መስኮት ስትፈልግ ወደ ቀጣዩ የሕይወት ክፍል የሚያሸጋግረንን ሌላ ቤት እንፈልግ ማለቷስ ይሆን?? ትዳር፥ ልጅ፥ ቤተሰብ???

ያን መመስረት እንደማልፈልግ ነግሬያታለሁ። እነዚህ ነገሮች ላይ እየተሽከረከርኩ –የድካም ዕንቅልፍ ወሰደኝ።

ነግቶ አይኔን ስገልጥ ለባብሳ ጨርሳ ጆሮ ጌጧን እያደረገች ነበር። የተኛሁበት መጥታ ጉንጬን ስማኝ ቦርሳዋን ይዛ ወጣች። ቃል እንዳልተናገረች፥ እኔም ” ማዕዜ ትመጺ ኃቤየ? ” (ወደ እኔ መቼ ትመጪያለሽ?) እንኳን እንዳላልኳት ያወቅኩት በሩ ከተዘጋና ከረፈደ በኋላ ነው። በሩን ስትዘጋው እንደመጨለም አለ።

One Comment

  • asniwitnes@gmail.com'
    wizme12 commented on December 3, 2019 Reply

    nice

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...