መንደርደሪያ
ሰኔ 15 በባህርዳር የተከሰተውን ሁኔታ ተከትሎ እያነጋግሩ ካሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ክስተቱ ምን ተብሎ መጠራት አለበት የሚለው ነው። ሁኔታውን ‹‹መፈንቅለ-መንግሥት›› ብለው የጠሩትና ቃሉን ለመጀመሪያ ጊዜ በደምበኛ(ሜይንስተሪም) ሚዲያ የተጠቀሙት በመንግሥት ሚዲያ የመጀመሪውን መግለጫ የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አፈቀላጤ ንጉሡ ጥላሁን ናቸው። ከወደ አፍሪካ መሰል ዜና መስማት ብርቃቸው ያልሆነው የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ይህንን ዜና ከጫፍ ጫፍ ተቀባብሎ ርዕሰ-ዜና ለማድረግ ጥቂት ጊዜ ብቻ ነበር የወሰደባቸው።
ሁኔታው በዚህ መልኩ መገለጹ ያልተዋጠላቸው የኢንድኮት ኮሌጅ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ሰማኸኝ ጋሹ አበበ ‹‹መፈንቀለ መንግሥት ብላችሁ አትጥሩት›› ሲሉ ለኢትዮጵያ ኦብዘርቨር ጻፉ። የክርክራቸው ማዕከላዊ ነጥብ የመፈንቅለ መንግሥቱ ዋና ተዋናይ ሆኖ የተገለጸው ሰው ካለው የውትድርና ልምድና የፖለቲካ ንቃት አንጻር እንዲህ ዓይነት ሊሳካ የማይችልና ቢሳካ እንኳ በምን መልኩ ሊፀና ይችል እንደሆነ ግልጽ ያልሆነ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገባል ብሎ ማሰብ ይከብዳል የሚል ነው።
በተመሳሳይ መልኩ የፈረንሳይ የዜና ወኪል ‹‹አምስት ጥያቄዎች በኢትዮጵያ ቀውስ ላይ›› በሚል ርዕስ ባተመው ጽሑፉ ላይ ያነጋገራቸው ዠራር ፕሩንዬ የተባሉ የአፍሪካ ቀንድ ተማራማሪ ‹‹መፈንቅለ-መንግሥት ትርጉም ያለው የወታደር ንቅናቄ ወይም እንደ አየርማረፊያና ሚዲያን የመሰሉ ወሳኝ ተቋማትን መያዝ የሚያካትት ክስተት በመሆኑ የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ የለም›› ሲሉ ተከራከሩ። ለዚሁ ትንታኔ ሀሳብ ያዋጣው ዊሊያም ዳቪሰንም አገራዊ ሥልጣንን የመቆጣጠር ሙከራ አልታየም ሲል የፕሩንዬ ሀሳብን ደግፏል።
ደፋሩ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በፍትህ ጋዜጣ ላይ ‹‹ድንቄም መፈንቅለ መንግሥት›› በሚል ርዕስ ባስነበበው ረጅም ሀተታው ሁኔታውን ‹‹ግርግር›› ብሎ ለመጥራት አንድ አንቀጽ አልወሰደበትም። ‹‹መፈንቅለ-መንግሥት የሚያስብለው ነገር የለም›› ብሎ የደመደመው በሦስት ጉዳዮች በመንተራስ ነው። የመጀመሪያው በኢትዮጵያ ታሪክ ‹‹መፈንቅለ-መንግሥት›› ተብለው የሚታወቁ አጋጣሚዎችን ከክስቱቱ አኳያ በድጋሜ በመፈተሽ ነው። ሁለተኛውና ሦስተኛው ከሞላ ጎደል ቀደም ሲል ከቀረቡት ሀሳቦች የሚቀራረቡ ሆነው በመንግሥት መግለጫ ውስጥ የተጣረሱ መረጃዎች መኖራቸውና መፈንቅለ መንግሥቱ ‹‹ቁልፍ ተቋማትና ወሳኝ ዒላማዎችን›› የዘነጋ መሆኑ ጋር ተያያዘው የተነሱ ናቸው። እነዚህን ክርክሮች ከመጨረሻው በመጀመር ለማሄስ እንሞክር።
መፈንቀል መንግሥት ምንድነው? ያልሆነውስ?
መፈንቅለ መንግሥት ምቹ ሁኔታዎቹ፣ መንስኤዎቹ፣ ስኬቱና ክሽፈቱን የሚያብራሩ ምክንያቶች በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ውስጥ የሚሸፈኑ ሁለንተናዊ ጽንሰ-ሀሳብ ነው። በተለይም በላቲን አሜሪካና በአፍሪካ ተደጋግሞ በመከሰቱ እስከ ቅርብ ጊዜ ድርስ ትልቅ ትኩረት የሚስብ የጥናት ርዕስ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። እንዲህ ዓይነቱን ሰፊ ጽንሰ-ሀሳብና አድማሰ-ሰፊ ክስተትን በኢትዮጵያ ታሪክ ታጥሮ ለመበየንና ለመፈተሸ መሞከር ጉዳዩን ለኢትዮጵያ ብቻ የተሰጠ ‹‹ዋልያ›› ጽንሰ-ሀሳብ አድርጎ ከማቅረብ አይተናነስም። እንዲህ ዓይነቱ ምልከታ ምናልባትም የተወሰነ ስሜት የሚሰጠው በኢትዮጵያ ሕግ ‹‹መፈንቅለ-መንግሥት››ን በግልጽ የሚበይን ሕግ ካለ እሱን መሠረት አድርጎ ጉዳዩን የመተንተን ሙከራ ቢከተል ነበር። ይህም እጅግ ፖለቲካዊ የሆነውን ጉዳይ ጠባብና ህግ-ተኮር በሆነ አቀራረብ በመቃኘቱ ከትችት አያመልጥም።
የመፈንቅለ መንግሥት ጉዳይን የመፈተሻው ተገቢው መንገድ በንጽጽራዊ የፖለቲካ ጥናት፣ እንዲሁም በታወቁ በጉዳዩ ላዩ የተጻፉ ድርሳናት መፈንቅለ-መንግሥት ተብሎ የሚጠራው ተግባር ዘመድ አዝማድ ከሆኑት ሥልጣንን በእጅ ለማስገባት ከሚያስችሉት ከሕዝባዊ አብዮት፣ ከአርነት ንቅናቄ፣ ከእርስ በርስ ጦርነት፣ ከውጭ ወረራ ባንድ በኩል፤ በሂደታቸው ከሚሳሰሉት ወታደሮች ጥቅምና መብታቸውን ለማስከበር ከሚያደርጉት አመጽና እገታ፣ ሽብርተኝነት፣ ከፖለቲካዊ ግድያና ከውንብድና ግርግር በሌላ በኩል፤ ተለይቶ የሚቀርብበትን ብያኔ በማስቀመጥ ነው።
ይህ አቀራረብ የባህርዳሩን ክስተት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ለመወሰን፤ ካልሆነ ደግሞ ቀደም ሲል ከተጠቀሱት ተመሳሳይ ሁኔታዎች ወደ አንዱ ለመመደብ ይረዳናል። በቀጥታ ጉዳዩን በዚህ መልኩ ከማየት በፊት መፈንቅለ መንግሥትን በተመለከተ መረጃ የሚያደራጁ አንዳንድ ተቋማት ‹‹የመፈንቅለ መንግሥት ሴራ(በውጥን ላይ ሳለ የከሸፈ)(1)፣ ያልተረጋገጠ የመፈንቅለ ሴራ (ሴራ ተብሎ የቀረበ ነገር ግን ሴራው ለመኖሩ አስተማማኝ መረጃ ያልተገኘለት)(2)፣ ያልተሳካ መፈንቅለ መንግሥት(3)ና የተሳካ መፈንቅለ መንግሥት(4) ብለው በመልክ በመልክ እንደሚያስቀጧቸው ማንሳት ጠቃሚ ነው።
የኤድዋርድ ሉትዋክ ‹‹መፈንቅለ መንግሥት፡- ተግባራዊ መመሪያ›› የተሰኘው መጽሐፍ በርዕሰ-ጉዳይ ከተጻፉ ድንቅ መጽሐፍት መካከል አንዱ ተደርጎ በብዙዎች የሚጠቀስ ነው። ደራሲው መፈንቀለ መንግሥት በሰፊው ሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ የማይታገዝና እጅግ ግዙፍ የሆነ የጦር ውጊያን እንደማያካትት ያትታል። በተጨማሪም መፈንቅለ መንግሥት ድርጊቱ ከተሳካ በኋላ ሊወሰድ የሚችለው የፖሊሲ አቅጣጫ በግልጽ የሚታወቅ አለመሆኑን በመጥቀስ መፈንቅለ መንግሥት ‹‹consists of the infiltration of a small but critical segment of the state apparatus, which is then used to displace the government from its control of the remainder.› ሲሉ ይበዩናታል። (የተቀረው(የመፈንቅለ መንግሥቱ ተሳታፊ ያልሆነው) የመንግሥት ክፍል ያለውን የሥልጣን ቁጥጥር ለመግፈፍናና ለመተካት አነስተኛ ግን ወሳኝ የሆነ የመንግሥት መዋቅር ክፋይን የማስረግ ሂደትን የያዘ ተብሎ በግርድፉ ሊተርጎም ይችላል።)
ክላየን ማዕከል ለዴሞክራሲ የተባለ ተቋም በመፈንቅለ መንግሥት ፕሮጀክቱ መፈንቅለ መንግሥትን ድንገተኛና ኢ-መደበኛ (ሕግ በጣሰና በሕግ ባልተደነገገ አግባብ) በራሱ የቆመ መንግሥትን አስፈጻሚ አካል ማስወገድና ፈንቅሎ ሥልጣኑን በቁጥጥር ስር ማዋል ብሎ ይተረጉመዋል። ሴንተር ፎር ሲስተሚክ ፒስ የተሰኘ ተቋም በበኩሉ ከማኅበራዊ አብዮት፣ በእርስበርስ ጦርነት አማጺ ኃይሉ አሸናፊ ከሚሆንበት ሁኔታና ከሕዝባዊ አመጽ የተለየ መሆኑን በማስመር መፈንቅለ መንግሥት በአንድ አገር የገዥ ወይም የፖለቲካ ልሂቃን መካከል አፈንጋጭ ወይም ተቃዋሚ በሆነ አንጃ በማስገደድ የሚደርግ የሥልጣን ንጥቂያ አድርጎ ያቀርበዋል። አንድ መፈንቅለ መንግሥት ተሳካ የሚባለው መፈንቅለ መንግሥቱን ያሴረው ጥቂት ሀይል ሥልጣን ነጥቆ የራሱን ሥልጣን ማንበር ሲችል ነው። በአንጻሩ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ደግሞ እንዲህ ዓይነቱን ዓላማ ለማሳካት የተወሰዱ እርምጃዎች የተነሱበትን ግብ እውን ሳያደርጉ ሲከሽፉ የሚፈጠረውን ሁኔታ የሚገልጽ ነው።
ከላይ ከቀረቡትና ከሌሎች በርካታ ተመሳሳይ ብያኔዎች እንደምንረዳው መፈንቀለ መንግሥት ወይም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ግዴታ ደም አፋሳሽ መሆን ባይጠበቅበትም ከሴራና ዕቅድ ባሻገር ራሱን ትርጉም ባለው ደረጃ በተግባር መግለጽ አለበት። ዓላማውም አመራር ከመግደል፣ መብትና ጥቅምን ከመጠየቅ ባለፈ ሕግን ባልተከተለ አግባብ አስፈጻሚውን ለመገልበጥ ዒላማ ያደረገ መሆን ይገባዋል። እዚህ ላይ አብዛኞቹ ብያኔዎችም ‹‹መንግሥት›› ሲሉ በአመዛኙ በማዕከል ያለ መንግሥትን እያሰቡ መሆኑን ማስታወስ ይገባል። በፌዴራል ሥርዓት ሁለት መንግሥታት መኖራቸው ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት አሁን ትርጉም ያለው የአመጽ ሀይል የሚያዝ በተግባርም የፌዴራል መንግሥቱን በአንዳንድ ሁኔታዎች ለመገዳደር የበቃ የክልል መንግሥት የተፈጠረበት ሁኔታ ላይ እንደምንገኝ ግንዛቤ ውስጥ መክተት ይገባል። በመሆኑም በክልል ደረጃ የሚደረግ መንግሥትን የመገልበጥ ድርጊት ከልማድ አንጻር ሲታይ እንግዳ ነገር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የክልል መንግሥት የሚባል መዋቅር እስካለና በዚሁ ደረጃ የሚደረግ ትርጓሜውን የሚያሟላ እንቅስቃሴ ከተደረገ መፈንቅለ መንግሥት ተብሎ ቢጠራ የተገባ ነው። በዚህ ረገድ ቢያንስ አንድ መፈንቅለ-መንግሥት ተብሎ የሚጠራ ድርጊት በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል። ይህም በ1898 በአሜሪካ Wilmington, North Carolina በአካባቢ መንግሥት ላይ የተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ነው። በመሆኑም በክልል ደረጃ መፈንቅለ መንግሥት ሊደረግ አይችልም ብሎ መደምደም ስህተት ነው የሚሆነው።
ቁልፍ ተቋማትና ሚዲያ መቆጣጠር፡- እንደ መፈንቅለ መንግሥት መለኪያ?
በሰሞኑ በሶሻል ሚዲያ ከሚሰጡ አስተያየቶችና መግቢያው ላይ ከተወሱት አስተያየቶች እንደምንረዳው አንድ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሚዲያና አየር ማረፊያን ካልተቆጣጠረ ሊያጠቃው የሚችለውን ሃይል አስቀድሞ ካላጠቃ በዚህ ስም ሊጠራ አይገባም የሚሉ ዓይነት ክርክሮች ይደመጣሉ። መፈንቅለ መንግሥቶች በጣም የተለያዩ የመሆናቸውን ያክል የሚከተሉት ስልትም የተለያየ ነው። የድርጅትና የቅንጅት አቅማቸው፣ የዕቅዳቸው ጥራት፣ የሚያሰማሩት የሰው ኃይል ብዛትና ጥራትም እንዲሁ። እርግጥ ነው መፈንቅለ መንግሥቶች የሚሳኩት ከሞላ ጎደል ማድረግ የሚገባቸውን ሁሉ ሲያደርጉና በጥንቃቄ በተተለም ዕቅድ በምቹ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ድባብ ላይ ሲካሄዱ ነው። በአንጻሩ የከሸፉ ሙከራዎች ግን የከሸፉት ማድረግ የሚገባቸውን ስላላደረጉና የተካሄዱበት ወቅትና ሁኔታ ድርጊቱን የማይደግፍ ሲሆን ነው።
ስለዚህ ክርክሩ መሆን ያለበት አንድን በግልጽ መንግሥትን በኃይል ለመገልበጥ አስቦ የተንቀሳቀሰ አካል ‹‹ይህን ስላልተቆጣጠረ›› የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሊባል አይችልም ሳይሆን የተሳካ እንዲሆን ይህን መቆጣጠር ነበረበት ተብሎ ነው መቅረብ የሚገባው። በሌላ አነጋገር በተዘረከረከ ሁኔታ የታቀደና የተተገበረ መንግሥትን የመገልበጥ ጥረት ወሳኝ ግቦች ሳይሳካ ባጭሩ ቢቀጭ ዕቅዱና አተገባበሩ ሊተች ይችል ይሆናል እንጅ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተብሎ ከመጠራት ውጭ ሌላ ዕድል የለም። በመሆኑም ሚዲያና መሰል ወሳኝ ተቋማትን መቆጣጠር ከመፈንቅለ መንግሥት መሳካት/መክሸፍ ጋር ካልሆነ በስተቀር ከአንድ ክስተት መፈንቅለ መንግሥት(የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ) መሆን/አለመሆን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የለውም።
በሌላ በኩል የሚዲያው ጉዳይ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የቀረበውን ችክ ያለ ክርክር ስንመረምረው ሀሳቡ በተወሰነ መልኩ ሃያኛው መቶ ክፍለ-ዘመን ላይ ተቸክሎ የቆመ እንደሆነ ይገባናል። እንዲህ ሶሻል ሚዲያ በሌለበት፣ የግል ሚዲያ ባልተስፋፈበትና አንድ ብሔራዊ ሚዲያ የመንግሥት ምልክትና ራሱ መንግሥት ሆኖ በሚታይበት ባለፈው ምዕተ ዓመት(በተለይም በአዳጊ አገራት) በእርግጥም ሚዲያን ሳይቆጣጠሩ የተሳካ መፈንቅለ መንግሥት ማካሄድ የማይታሰብ ነበር ማለት ይቻላል። በዚያ ዘመን ሚዲያን መቆጣጠር ብቸኛውን የመንግሥት ልሣን መዝጋትና በዚያም የራስን መልዕክት ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ትዕምርታዊ(symbolic) ዋጋ ያለው ተግባር ነበር። የመንግሥት ሚዲያ ይህ ዓይነቱ ሚና አሁን ላይ አለው ማለት ያስቸግራል። የመንግሥት ሚዲያ ከሚዲያዎች መካከል አንዱ ወደ መሆን ወርዷል። ሚዲያን መቆጣጠር ለመፈንቅለ መንግሥት ስኬት ያለውን ሚና ማናናቅ ባይገባም የቱርኩ ፕሬዝዳንት በቅርቡ የተቃጣውን መፈንቅለ መንግሥት እንዲከሽፍ ማድረግ የቻሉት በፌስታይም በተላከና በግል ሚዲያ በቀረበ የቪዲዮ መልዕክት መሆኑ ስለዘመኑ መቀየር የሚነግረን ነገር ትልቅ ነው።
‹‹ስሜት አይሰጥም ስለዚህ መፈንቅለ መንግሥት ሊሆን አይችልም!››
ሁኔታውን የ‹‹መፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ›› ብላችሁ አትጠሩት የሚሉት ሰዎች የሚያነሱት ሌላው ሀሳብ፣ የክስተቱ ዋና ተዋናይ ሆነው የቀረቡት ሰው የፌዴራል መንግሥቱ በቀላሉ እንደሚያከሽፈው የታወቀ በክልል ደረጃ እንዲህ ዓይነት ምንም ስሜት የማይሰጥ ተግባር ሊፈጽሙ አይችሉምና ጉዳዩ መፈንቅለ መንግሥት ሊሆን አይችልም የሚል ነው። የዚህ ክርክር አስኳል ‹‹ሊደረግ አይችልም›› እንጅ መደረጉ ቢረጋገጥ ጉዳዩ የ‹‹መፈንቅለ መንግሥት›› ሙከራ ተብሎ አይጠራን የሚያካትት አይመስልም።
እዚህ ላይ ሁለት ነገር ማንሳት ይገባል። የመጀመሪያው የትግራይ ክልል ሕግንና የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣን በመጋፋት የፌዴራል ፖሊስ የሚያግትበት፣ የሀገር መከላከያ እንቅስቃሴን የሚያስተጓጉልበት፣ በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ምሽግ የሚሆንበት ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ባለበት፤ በክልል ደረጃ የተሳካ መፈንቅለ መንግሥት አድርጎ መሰንበት በጭራሽ አይቻልም ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ከባድ ነው። ሁለተኛ ድርጊቱን መሩ የተባሉት ሰው ነገሮችን የሚገመግሙበትን ሚዛን፣ የነበሩበትን አጠቃላይ ሁኔታና ወደዚህ ዓይነት ውሳኔ ሊገፋቸው የሚችለውን ምክንያትና ስሜት በሚገባ የማያውቅ ሰው ባልተሟላ መረጃ ሀሳባቸውን በሩቅ ‹‹ወለፈንዲ›› ነው ብሎ መደምደምም የሚቸግር ነገር አለው። ሌላው ደግሞ እጅግ የተራቀቀ አዕምሮ አለው የምንለው ሰው ሁሉ አንዳንዴ በጎዶሎ ቀን በተስፋ መቁረጥ፣ በተለያዬ ሀይል ግፊትና የስሜት ውጣ ውረድ ‹‹የሕፃን ጨዋታ›› የሚመስል ነገር ለመሥራት ሊሠናዳ የሚችልበትን ዕድል ዝግ አለመሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል።
መውጫ
ቀደም ሲል የቀረቡት አናቅጽ ለመጠቆም እንደሞከሩት፣ የባህርዳሩን ክስተት (ከአዲሳባው ጋር ሳይገናኝ) በመንግስት ከቀረቡት መረጃዎች መካከል በተመረጡ የመንግሥት ተቋማት ላይ የተወሰዱት እርምጃዎች በጸጥታ ቢሮ ኃላፊው የተመሩ መሆናቸውና ይህም እርምጃ የተወሰደው ለጋዜጠኛው በስልክ እንዳብራሩለት ‹‹የአማራን ጥያቄዎች ቀልብሷል›› ያሉትን አመራር ማስወገዳቸውና እንዲሁም ትዕዛዝ ከሳቸው እንዲመነጭ መፈለጋቸው እውነት መሆኑ ብቻ ክስተቱን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ብሎ ለመጥራት በቂ ነው። በኔ ግምገማ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ሊነሳ የሚችል ቢሆንም እነዚህ አጠቃላይ ሁለት መረጃዎች ውሸት ናቸው ብሎ ለመጠራጠር በቂ ምክንያት ስለሌለኝ ክስተቱን በዚህ ስም መጠራቱ ‹‹ድንቄም›› የሚያሰኝ ሆኖ አላገኘሁትም። ይሁንና ሙከራው በክልል ብቻ ታጥሮ የታቀደ መሆኑ የመጨረሻ እውነት ከሆነ ቢያንስ ዒላማው ባደረገው የሥልጣን ማዕከል ጋር በተያያዘ መፈንቅለ መንግሥቱ ‹‹እንግዳ›› ባሕርይ ያለው አድርገን እንድንቆጥረው ያስገድደናል።
አንድን ጉዳይ ‹‹ መፈንቅለ-መንግሥት›› ብሎ መጥራት በሚፈጥረው አጠቃላይ ድባብ፣ መንግሥት ምላሽ አድረጎ በሚያሰማራው ኃይልና የእርምጃ ደረጃ ጋር በተያያዘ የሚያስከትለው መዘዝ ስላለ፣ ስም ማውጣት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ውይይት “what is in the name?’’ ብልን ልናጣጥለው የምንችለው ዓይነት አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ግን ክስተቱ የፈለቀበትን ህመም፣ ፖለቲካዊ አንድምታውን፣ ከሁኔታው አገግመን በሁለት እግራችን የምንቆምበት መንገድ ላይ ከምናደረገው ወሳኝ ውይይት ልናጠፋው ከሚገባው ጊዜ ሰርቆ እንዲወስድብን መፍቀድ የለብንም። ለምን ሆነ? ምን ሆነ? መንግስት ምን ምላሽ ሰጠ? በክልሉና በሀገር ፖለቲካ ምን ዳፋ አስከተለ? ጉዳት ቀንሰን በአጠረ ጊዜ እንዴት እናገገም? ወ.ዘ.ተ ጥያቄዎች ላይ መወያየት የበለጠ ይበጃል።