Tidarfelagi.com

ነጋድራስ (የነጋዴ ራስ) 

ያቀናነው ገበያ — እዩት ተሽመድምዶ
ሻጩ ሲያረፋፍድ — ገዢ መጣ ማልዶ
በመደብ ስንጠብቅ — በየቋንቋው ለምዶ
* * *

ገበያችን ደራ — ሻጭ ተትረፈረፈ
ገዥ በነቂስ ወጣ ፣
ደጋግመው ሲገዙን —ደጋግመው ሲሸጡን
በተሸጥን ቁጥር ዋጋ ብናወጣ ።
* * *

አድሏቸው እንጂ
የሸማች ግርግር — መደነባበሩ
የዛሬ ገዦችሽ — ትናንት ሻጭ ነበሩ
የሸማቹ ግፊያ — ከገበያ ያወጣው
ትናንት የገዛኝ ነው — ሻጬ ሆኖ የመጣው
ገበያውን አርገነው — እንዳይሆን እንዳይሆን
የዛሬው ገዢ ነው — ነገ ሻጭ የሚሆን
* * *
ሻጭ አንቺን ከጀለሽ — ገዢ እኔን ፈለገኝ
ዋና ማናስነካ — ትርፍ ሆነን ብንገኝ
* * *
ትርፍ ነህ ይሉኛል — ትርፍ ነሽ ይሉሻል
በገዙበት ዋጋ — መቼ ይሸጡሻል

ትንሽ ነው ይሉኛል — አይረባም ይሉኛል
ግብሬን አሳንሰው
ሊገዛህ ሲመጣ — ማጣጣል ወጉ ነው
መቼም የዛሬ ሰው
ጊዜ የሰቀለውን — ሻጩ እስኪቀንሰው
ወትሮም በገዢ ነው — ማጣጣል ሚብሰው
* * *
ገዢ ሲያሳንሰኝ — ሻጭ ሲያቆላምጠኝ
ዋናው ማንነቴ — በትርፍ አመለጠኝ
ገዢ እያራከሰ — ሻጭ እያስወደደሽ
በድርድር መሀል
በክርክር መሀል
ውሸት አስለመደሽ
* * *
አድርባይ ደላላሽ
ዳተኛው ደላላሽ — ለእውነት የለገመ
ሲያስሸጥሽ ይውላል
ሲያስገዛሽ ይውላል — እየደጋገመ
ለገዥ አስረክሶ — ለሻጭ ያስወድዳል
ደላላ ክፉ ነው — ከሁሉም ይለምዳል
ከሁሉም ይወስዳል

ላንተ ግን ልንገርህ
ጊዜ የጣለን እንጂ — ስላይደለን ጀንፈል
ገዢም ሻጭም — ሆነህ የደላላ አትክፈል
ቀኑ ሲጨላልም
ዝምድና — ከልክሎት
ግርግር — ከልሎት
አልታወቅ ብሎ
ስለጠፋባቸው — የግብይት ውሉ
በዘመድ ዋጋ ነው
ሲሸጡን አርፍደው — ሲገዙን የዋሉ

የገዢ ክርክር — ሻጩ ላይ ሳይተጋ
የሻጭ አማችነት — ገዢን ሳይዋጋ
እየገዙን አሉ
እየሸጡን አሉ
ቀን በጣለው ዋጋ

One Comment

  • berekettw60@gmail.com'
    Bereket commented on September 9, 2019 Reply

    Konjo new

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...