Tidarfelagi.com

ጃጋማ ኬሎ

በ15 አመቱ ሀገሩን ከወራሪ ፋሽስት ኢጣልያ ጦር ነፃ ያወጣው ባለ አፍሮ ፀጉሩ ወጣት አርበኛ: ጃጋማ ኬሎ
በሚልድሬድ ዩሮፓ ቴይለር

ጃጋማ ኬሎ ሀገሩ ኢትዮጵያን ከ1928ቱ የኢጣሊያ ወረራ ለመከላከል ወደ ጫካ በመግባት መዋጋት ሲጀምር ዕድሜው ገና 15 ብቻ ነበር።

በመስከረም 1928 ኢጣልያዊው ፋሽስት የጦር መሪ ቤኔቶ ሙሶሎኒ በኢትዮጵያ ወረራ ጀመረ። በንጉሰነገስት ኃይለሥላሴ ጦር ዙርያውን ተከቦም ቢሆን የኋላ ኋላ ሙሶሎኒ ሚያዚያ 27/1928 አዲስ አበባ ገብቶ ኢትዮጵያ የኢጣሊያ እና የኢጣልያ የምስራቅ አፍሪካ ግዛት አካል ሆናለች በማለት አወጀ።
ንጉሰነገስቱም የኢጣልያ ወረራ ተከትሎ ወደ ፈረንሳይ ሱማሌላንድ አቀኑ።

የባለፀጋ ባላባት ልጅ የነበረው ጃጋማ የኢጣልያ ጦር በወረራው እየገፋ ሲመጣ ከገበሬ አስከ ታዋቂ ሰዎች በመሰባሰብ እንደ ህዝብ ወራሪውን ጦር ለመመከት ጫካ ገብተው የተደራጁትን አርበኞች የጦር መሳሪያ በመያዝ ከወንድሙ ጋር በመሆን ቤታቸውን ጥለው ተቀላቀሉ።

በወቅቱ የጃጋማ ወንድም ሽጉጥ የነበረው ሲሆን ጃጋማ ግን ምንም መሳሪያ አልነበረውም። ያም ሆኖ ተደብቀው የኢጣልያ ወታደሮች ላይ አደጋ በመጣል በፍጥነት ራሳቸውን ማስታጠቅ ጀመሩ። ሌሎችም በሂደት ትግሉን የተቀላቀሉ ሲሆን በጦርነቱ መጨረሻ ጃጋማና ታላቅ ወንድሙ ከ3,000 በላይ በስራቸው የሚታዘዙ የአርበኞች ጦር ነበራቸው።


በአንድ ወቅት በተደረገ ቃለ መጠይቅ ጃጋማ ካደረጓቸው ጦርነቶች ሁሉ ከአዲስ አበባ 55ኪ.ሜ ርቃ በምትገኘው በስዩመ ማርያም ላይ ያደረጉት እንደነበር ያስታውሳሉ። በጦርነቱ አንዲት ሴት አርበኛ ለጃጋማና ለአርበኞቹ የኢጣልያ ወታደሮች የት እንደሚገኙ በነገረቻቸው መሰረት በኢጣልያ ጦር ላይ የድንገቴ ጥቃት በመሰንዘር 72 የኢጣልያ ወታደሮችን ገድለው 3,000 ጠብመንጃዎችን መማረክ ችለው ነበር።

በንጉሰነገስት ኃይለሥላሴ ከአምስት አመት የብሪታንያ የግዞት ቆይታቸው በኋላ በ27/08/1933 ወደ ሀገራቸው መዲና አዲስ አበባ ተመለሱ። ሀይልን መልሶ በእጅ ለማድረግ ትዕግስት እንደሚጠይቅ የተረዱት በንጉሰነገስቱ ሀገራቸውን ከወራሪው ፋሽስት ኢጣልያ ነፃ ለማድረግ ፖለቲካዊ ግንኙነቶችንና የምዕራባውያን ወዳጆቻቸውን የጦር ድጋፍ አቀናጅተው ተጠቅመዋል።

በርግጥ የኢትዮጵያ ነፃነት በአምስቱ የጦርነት አመታት እንግሊዝ ምንም አይነት ድጋፍ ባለማድረጓ የመከዳት ስሜት ተሰምቷቸው ንጉሰነገስቱ ወደ ሀገራቸው በመዲናዋ በተደረገው የአቀባበል ስነ ስርዐት ለመገኘት አሻፈረኝ እንዳሉት ጃጋማ ኬሎና መሰሎቻቸው ትግል እውን አይሆንም ነበር።
በወቅቱ ከነበሩት የኢትዮጵያ የሚዲያ ዘገባዎች መረዳት እንደሚቻለው ንጉሰነገስቱ ሸዋ ውስጥ ወደምትገኘው የጃጋማ መኖሪያ ጊምጪ ከተማ ጉዞ አድረገው የነበረ ሲሆን ጃጋማም ወደ 3,500 የሚደርሱትን ወታደሮቻቸውን አሰልፈው ተቀብለዋቸዋል።

ከመሞታቸው ጥቂት ግዜያት በፊት ተደርጎላቸው በነበረ ቃለመጠይቅ ጃጋማ ከሰልፉ በኋላ ንጉሰነገስቱ ጃጋማን በራሳቸው መኪና ወደ ቤተ መንግስታቸው የወሰዷቸው ሲሆን በዚያም ገበርዲን ኮት እና የወርቅ የእጅ ሰዐት እንደሸለሟቸው ጠቅሰዋል።

ጅማ ከተማ በኢጣልያ ቁጥጥር ስር የነበረች በመሆኗ የነፃነት ትግሉ ሙሉ ለሙሉ አልተደመደመም ነበር። በመሆኑም እርዳታቸውን በንጉሰነገስቱ የተጠየቁት ጃጋማ ወታደሮቻቸውን ወደ ጦርነቱ በማሳተፍ 500 የኢጣልያ ወታደሮችን ማርከው ለእንግሊዝ ጦር አስረክበዋል።

ያለ ሸጉጥ ትግሉን የጀመረው ወጣቱ አርበኛ ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ በብሔራዊው ጦር ሰራዊት ውስጥ በመቆየት እስከ ሌተናንት ጀነራል የማዕረግ ደረጃ አድጓል። በ1950ዎቹ መግቢያ ላይም በባሌ የተነሳውን አመፅ በመቆጣጠሩ የአውራጃ ጦር አዛዥነትን ማዕረግ ተሸልሞ ከፍተኛ ሹመት ሊያገኝ ቾሏል።

ጃጋማ በነበረው አፍሮ ፀጉር የተነሳ ጠላቶቹ ይፈሩት እንደነበርና ለስኬቱም አንድ አስተዋፅዖ እንደነበረው ያምናል። ለዚህም ነው በአንድ ወቅት በከፋ የወባ በሽታ ተጠቅቶ ሊያክመው በነበረው እንግሊዛዊ ዶክተር አፍሮ ፀጉሩን መቆረጥ እንዳለበት ሲጠየቅ አልቆረጥም በማለት የመለሰው።በወቅቱም በአዲስ አበባ የነበረው ሆስፒታል ጃጋማ ፀጉሩን እስካልተቆረጠ እንደማያክመው ቢገልፅም ጃጋማም ከኢጣልያ ወታደሮች ጋር በዱር በገደሉ በነበረው ውጊያ የጠላት ወታደሮችን በፍርሃት እንዲርዱ ያደረገልኝን ፀጉሬን አልቆረጠውም በማለት በእምቢተኝነቱ ፀንቷል።

በመጨረሻም ንጉሰነገስቱ በጉዳዩ ገብተው ባቀረቡት ተማፅኖ ጃጋማ ተሸንፎ ህይወቱ ሊተርፍ ችሏል።
በአፄ ኃይለሥላሴና በጃጋማ መካከል የነበረው ግንኙነት እንዲህ የጠለቀ ነበርና ንጉሰነገስቱ በታህሳስ 1953 ብራዚል በሄዱበት ወቅት በተቃዋሚዎቻቸው በተደረገው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ካልተሳተፉት የጦር አመራሮች አንዱ ጃጋማ ኬሎ ነበሩ።

የመፈንቅለ መንግሰቱ ሙከራ አፄ ኃይለሥላሴ ከስልጣን ካወረዳቸው የ1966ቱ አብዮት በቀር በዘመናቸው ካጋጠሟቸው አደጋዎች ሁሉ የከፋው ነበር።

ጃጋማ ኬሎ በ96 አመታቸው መጋቢት 29/2009 በአዲሲ አበባ የሚገኝ ሆስፒታል ሞቱ በህይወት የነበሩት የመጨረሻው የአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የጦር ጀነራል ነበሩ።

ከሄሊኮፕተር አደጋ ለተረፈ እና በጦርነቶች ብዙ ጉዳቶችን ላስተናገደ ሰው፤ ጃጋማ ኬሎ የደርግ መንግሥት በ1983 በወደቀ ማግስት የኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲን ከመሰረቱት ሰዎች አንዱ በመሆን በሽምግልና ዕድሜያቸው እንኳን ንቁ እና ለኢትዮጵያ ሀገራቸው ታታሪ ሰው እንደነበሩ አስመስክረዋል።

ጃጋማ ኬሎ የካርታ ቁማር ጨዋታ አጥብቀው ይወዱ እንደነበርና እስከለተሞታቸውም ድረስ ይጫወቱ እንደነበር የተለያዩ የኢትዮጵያ ሚድያ ዘገባዎች ያስረዳሉ።

ምንጭ፡ www.face2faceafrica.com
ብሩክ አያሌው
ቸር ይግጠመን

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...