Tidarfelagi.com

ከመኖሪያ ቤቱ ስር…(ክፍል፦22)

ም…ን…አልክ..በልሁ? “ምን ላርግ ሰንዬ …” በል ዝም በል አልሁና አፉን ያዝሁት።የሰይጣን ጆሮ አይስማው በልሁ እንዳትደግመው። አልሁት።

እንኳን እቤቱ ተቀምጠን በየሄድንበትም እየተከተለ አላስቀምጥ ያለን ሰይጣን በልሁ ያለውን ተኔ ቀድሞ እንደሰማው እያሰብሁ።እሄን ተማረግ ሞቴን እመርጣለሁ!። ጭራሽ በጄ እንዳጠፋህ ጠየከኝ በልሁ! ደግመህ እንዳታስበው።ደሞ ለኔ ብለሽ ለኔ ብለሽ አትበለይ የቀን ጉዳይ ሆኖ እይ እኔስ ለትዬ ታንተ ምን ልዩነት ኖሮይ ነው። አንተስ ብትሆን በኔ ጦስም አይደል እይህ ጉድ ውስጥ የገባኋው ያን ቀን ስርህ እየመጣሁ ልጥፋ አልጥፋ እያልሁ ስወተውትህ እትዬ ባያዩን እዚህ ጉድ ውስጥ ትገባ ነበር ታሁን ወዲ ለሁለታችን እንጂ ለኔ ወይም ላንተ የሚባል ነገር የለም እሺ?።

ይልቅ የኔ ዥግና አሁን ያልሁህን እስትሞክር ብቻ ታገሰይ ያንተ ስቃይ ታያሰቃየይ ህመምህ ታይሰማይ ቀርቶ እንዳይመስልህ። እንደሚሳካልይ  ውስጤ ትለታወቀይ እና ደሞ እጅን አጣጥፎ ሞትን ተመጠበቅ መታገሉ ይሻላል ብዬ እንዢ።

ምናልባት እንኳን ታይሆንልን ቀርቶ መውጫ ቀዳዳ ሁሉ ተተደፈነብን ምንም እንኳ ያሰብሁትን ነገር እራሱን መልሼ ታስበው ፍርሀት ፍርሀት ቢለኝም።ላንዴ እና ለመጨረሻ ግዜ ላደርገው ያቀድሁት የመጨረሻ ሙከራ ትላለኝ ለኔ ትትል እስተዛ ሁሉን ችለህ ታገሰኝ የኔ ዥግና!። አደራ! አልሁትና ልሄድ ትሰናዳ መልስ ታይሰጠኝ ዝም ብሎ አይን አይኔን ቲመለከተኝ እንባውን ታይኑ ላይ አብሼለት በአይኔ ተሰናብቸው ሰሀኑን ይዤ ደረጃውን መውጣት ጀመሩሁ። ጠሎት ቤቱን እንደነበረው አስተካክዬ ወደ ሳሎን ገባሁ። እታች በወረድሁ ሰአት እትዬ ባለመምጣታቸው ፈጣሪዬን አመሰገንሁ። የትዬን መሂና ድምጥእየተጠባበቅሁ ሳሎን ቁጭ ብዬ ትንሽ እንደቆየሁ ቤቱ እሚበላይ እሚበላይ ትለመሰለኝ ወደ ክፍሌ ገባሁ።በልሁ እንዳለው እታች ቤት ካሜራ ደብቀው አኑረው ተሆነ ቲመለሱ የተቀረፀውን አይተው ምን እንዳደረግሁ ታወቁ ተበልሁ በፊት እኔን ተማረድ ወይ ተመስቀል እንደማይመለሱ ታስብ ብርድ ብርድ አለይ። ጉልበቴን ወደ ሆዴ አስጠግቼ በሁለት እጄ ጠረነፍሁና እየተወዘወዝሁ የውስጤን ሀዘን በንጉርጉሮ ተነፍሰው ዥመር….

እህህ ድማሙ እህህ ድማሙ

እህህ ድማሙ እህህ ድማሙ

የትብቴ መኖሪያ ምነው አንቺ አገሬ

ያካሌ መቅበሪያ ምነው አንቺ አፈሬ

መከራው በዛብይ ታንቺ መፈጠሬ

እህህ ድማሙ እህህ ድማሙ

ስሚኝ አንቺ  አገሬ

የትውልድ ቀየዬ የትውልድ መንደሬ

የሆዴን ልተንፍስ ልናገረው ዛሬ

ክፉዋች በዙና

ለቅሶሽን ያወጁ ለክፋት የቆሙ

በዛብሽ ሀዘኑ ፥ በዛብሽ ህመሙ

ልጆችሽ አለቁ እየተመረጡ እየተለቀሙ።

ንፋስ ቢያይልበት ጎንበስ አለ ዛፉ

እሱ በቃ እስቲለን ፥ ቀን እስቲወጥልን

እስቲ እናንተ ሂዱ እስቲ እናንተ እለፉ።

ሰው ሰው የማይሸቱ ተክፉም የከፉ

ተገርፈው ሳያድጉ ሰው እየገረፉ

እነሱ ሊኖሩ ስንት ሚስኪን ደፉ

መች ይሆን ሚሞላው የሚያበቃው ግፉ

በቃ በለን እምላህ የቀሩት ይትረፉ።

እያልሁ ትቆዝምና ታንጎራጉር በርም ቲከፍቱ ያልሰማሁዋቸው እትዬ፥እኝህ ተንኮልን እዩንቨርስቲ ገብተው በጥሩ ውጤት በድግሪ የተመረቁት መሰሪዋ እትዬ፥አረ ተድግሪም በላይ!

ድምጡ እንዳይሰማ መሂናቸውን አርቀው አቁመው በእግራቸው መጥተው ነው መሰል ኮቴያቸው ታይሰማ እንዴት አድብተው ወደ ክፍሌ እንደዘለቁ እንዣ እክፍሌ በር ላይ እንደዥብራ ተገትረው የክፋት መርዝ ልብ ላይ እየረጨ ልብ የሚያቀልጠውን ትልልቅ አይናቸውን እያጉረጠረጡ “ምን ምን ምን …ምን አልሽ አንቺ” ብለው ቲያንባርቁብኝ :ተመክዳትም ተመከዳትም ይሰውራችሁ ሁለመናዬ ከዳይ!…

 

ይቀጥላል

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...