Tidarfelagi.com

ከመኖሪያ ቤቱ ስር…(ክፍል፦15)

እኔም አሁን አንድ ነገር ታፌ ቢወጣ እትዬ ተነስተው ተነጨርቄ ተመዋጥ አይመለሱም።

“ተእብድ አጠገብ ፥ ድንጋይ አይወረወርም” አለች ያቺ ያገር ቤቷ ሚስኪን ጎረቤቴ። እዚህ እማ ምን ኮረቤት አለ። ሰው ሁሉ ደም የተቃባ ይመስል ተሸሽጎ ነው የሚኖረው። ተቸገርኩ ቢባል ለጋሽ፣ ኡኡ ቢሉ ደራሽ፣ ሞቱ ቢባል አልቃሽ የለለበት መንደር ያመጣኝ እድሌ ነው። ይለፍልፉ እትዬ እኔ እንደሁ በውስጤ ልቃጠል እንጂ ቃል አይወጣኝ።  እኔ የውስጤን ፍም ለማብረድ በውስጤ ትልጎመጎም እትዬ ድምጣቸውን እየጨመሩ  አዲስ ርእስ ጀመሩ። ቲጀምሩ ሳቃቸውን ተጠራ በላይ ለቀቁትና …”አይ የኔ ባል..የኔ ባል እኮ ጀግና ነበር እሄን ታውቂያለሽ?” ዝም ብዬ ታቁለጨልጭ “አታውቂም? ታውቂያለሽ?!” አሉና አፈጠጥቡኝ። ጭንቅላቴን ግራና ቀኝ በማወዛወዝ አላውቅም አልኻቸው።

“እሺ ኢትዬጲያ ውስጥ ስንት ቡድን እንዳለ ታውቂያለሽ?ቡድን ስልሽ የግር ካስ ቡድን እንዳይመስልሽ ክክክ።”

አላውቅም።  ” ድሮስ ምን ታውቂያለሽ አንቺ ሙትቻ ድሮም በቁምሽ ሞተሻል እኮ ወስዶ ሬሳሽን እሚያቃጥል ጠፍቶ እንጂ ክክክ…።”

ሴትዮዋ እንዴት እንዴት ነው የሚያደርጋቸው ጃል..የገሀነም እሳት ይብላቸው እቴ ደሜን አፈሉትኮ! ቆይ ብቻ በልሁን አንዴ ላግኘው እንጂ ተዛ ሻንቆ ተሚሉት ሾተላይ ማምለጫ አናጣም በያቸው ታለኝ በተኙበት አንገታቸውን ታልበጠስኩት እኔ ሰናይት የናቷ ልጅ አይደለሁማ!። እንደ ዶሮ እያስካኩ ወሬውን ቀጠሉ…

“በሂወት ውስጥ ብዙ አርቴፊሻል ቡድኖች አሉ  የኔ ባልና አጋሮቹ ለራሳቸው እንዲመቻቸው ከፋፍለው የቦደኗቸው ታድያ የኔ ባል ትልቁ የስራ ድርሻው ተሱ ቡድን ውጪ ያሉትን አንዳንድ ነፈዝ ተጫዋቾች ከቡድንቸው ሳይለቁ እዛው እንዳሉ በብር ይገዛቸውና እራሳቸው ቡድን ላይ ጎል እንዲያገቡ ያደርጋቸዋል ክክክ..አሁንም ማግባታቸውን አላቆሙም ክክክክ.. ወይ የኔ ባል አንበሳ እኮ ነህ ስንቱ ገልቱ ላይ ተጫወትክበት ክክክክክክ!” ወይ እኝህ ሴትዬ ዛሬ እንጥላቸውም ታይበጠስ አይቀር በድምጥ ማጉያ ጆሮዬ ላይ የሳቁ እስቲመስለኝ ድረስ አደነቆሩኝ እኮ።

“አንቱ ትተረጉሙ ፥ አንቱ ትደረግሙ” ያለው ማን ነበር እቴ ምን እንደሚያወሩ ተመነሻውም ታይገባኝ የሚያወሩ እሳቸው የሚስቁ እሳቸው። ጠርሙሱን ብድግ አድርገው ቀድና በረዶውን ቀይሪው አሉኝ። ለሊቱን ሙሉ በልሁን ቲያሰቃዩ እንቅልፍ ያጡት እትዬ በሮዶውን ይዤ ትመለስ እዛው እሶፋው ላይ ማንኮራፋት ጀምረዋል።  በልሁ ጋር ለመግባት ታስብ የጠፋው ፍርሄቴ ተመቅፅበት መላ እካላቴን ወረረኝ። ማድ ቤት ገባሁና ለበልሁ ተቁርስ የቀረውን ምግብ እጎድጓዳ ሰሀን ውስጥ ከትቼ ያዝኩለትና ወደ ጠሎት ቤት ገባሁ ፈራሁ ወደ እትዬ ታማትር ተወገብ በታች እንጂ ተወገብ በላይ አይታዩም ታልተነሱ በቀር እተኙበት ሆነው አይናቸውን ቢገልጡም ጠሎት ቤቱ አይታያቸውም። ምንጣፉን ገልጬ የወለሉን በር በጥንቃ ከፍቼ ቁልቁል እየወረድሁ በልሁን ተማየቴ በፍት እንቅፉን የተኛውን ዘንዶ ታይ ብርክ ያዘኝ እግሬን ማዘዝ ተሳነኝ።ጥርሴን ነክሼ በልሁጋ ትደርስ የበልሁ ሁኔታ ፍርሀቴን ሁሉ አጥፍቶ ያንሰቀስቀኝ ገባ።እግርና እጁ ተወጥሮ የተደፋውን አንገቱን ቀና አድርጌ ፊቱን በቀሚሴ እየጠራረኩ  …በልሁ አንተ በልሁ እባክህ ሰናይት ነኝ  አናግረኝ የኔ ጌታ ….በልሁ ምንም ድምጥ አላወጣ ብሎ ተስፋ ቆርጬ ቆሜ ታለቅስ “ውሃ  አምጭልኝ ሰንዬ ውሃ….ውሃ” ቲለኝ ሽቅብ በመሮጥ ማድ ቤት ገብቼ ተፍሪጅ ውስጥ የታሸገ ሁለት ሊትር ውሃ ይዤ ትወጣ..ሳሎን መሀል ላይ ተገትረው ሁለት እጃቸውን አፋቸው ላይ እንደጫኑ አይናቸውን ቲያጉረጠርጡብኝ  እቆምኩበት ሰማይና  ምድሩ ድብልቅልቅ አለብኝ….

ይቀጥላል

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...