Tidarfelagi.com

ለእኔ ያላት እንጀራ (ክፍል ሁለት)

አንዱን ቅዳሜ መስፍኔ ቤት አድሬ ካልጋ ላለመውጣት እገላበጣለሁ። ጥሎኝ ሲወጣ ተገርሜ፣
– በናትህ ዛሬ እንደ ሮማን እና ፀጋዬ አልጋ ውስጥ እንበስብስ አልኩት።
የበአሉ ግርማ በተለይ የኦሮማይ ፍቅሩ ሌላ ነው። ከአስራ አምስት ጊዜ በላይ እንዳነበበው ከአስራ አምስት ጊዜ በላይ ነግሮኛል። አልጋ ውስጥ አብሮኝ ማርፈድ ከፈለገ ሁሌም የሚለኝ ነገር ነው…እንደ ሮማን እና ፀጋዬ አልጋ ውስጥ እንበስብስ።
– አይ…ባንክ መሄድ አለብኝ….አለ ትላንት አውልቆ የጣለውን ካኪ ሱሪና ሸሚዝ ቶሎ ቶሎ እየለበሰ።
– ባንክ? ብር ለማውጣት ከሆነ ኤቲኤም አለህ አይደል…› አልኩኝ በሌላ ጎኔ ተገልብጬ፣ በአይኖቼ ስቤ አልጋ ውስጥ ልጨምረው እየተስለመለምኩ።
– አይደለም…አርባ ስልሳ ማስገባት አለብኝ…ቀኑ አልፎብኛል….ትላንት ወይንዬ የራሷን ስታስገባ የኔንም አስገቢልኝ ብዬ እሰጣታለሁ ብዬ ረሳሁት። ጫማውን ማድረግ እየጀመረ መለሰ።

አርባ ስልሳ ይቆጥባል!
ልቤ በስስ ካኔተራዬ ላይ ትር ትር ስትል እስኪሰማኝ ደስ አለኝ። አርባ ስልሳ የሚቆጥብ ወንድ ስለ ወደፊት የሚያስብ ነው። ስለወደፊት የሚያስብ ወንድ ደግሞ ስለትዳር የሚያስብ ነው። ስለትዳር ካሰበ ደግሞ….

የልቤን ፈንጠዝያ በቃላት አሽጌ በአፌ ላወጣው ስል ሄዋን ትዝ አለችኝ። ‹‹እንዲያገባሽ ከፈለግሽ ትዳር የሚባል ሃሳብ እንደሌለሽ ማሳየት አለብሽ…ወንድ ልጅ የሚወደው እንደዚያ አይነቷን ነው….ሰናይን አታይም…በሁለት አመቱ ራሱ አገባኝ….››
– አርባ ስልሳ ትቆጥባለህ እንዴ…?ውይ ምስኪን….አልኩት
አልጋው ጫፍ ላይ ተቀምጦ ሁለተኛ ጫማውን እያሰረ ነበር። አንገቱን ዞር አድርጎ አየኝና፣
– ምስኪን? አለኝ
– አዎ….ህልም እኮ ነው እሱ…ዝም ብለህ ነው….እኔን አታይም? ቤተሰቦቼ ጋር በዚህ እድሜዬ የምኖረው ለምን ይመስልሃል? ተስፋ የለውም። መቶ ፐርሰንት ለከፈሉት አከፋፍለው ጨረሱት አይደል….አልኩ ቃላቶቹ እያነቁኝ
– እና ዘልአለም የሰው ኩሽና ውሰጥ ኑር ነው የምትይኝ? መሞከር አይሻልም?አለኝ ተነስቶ እየቆመ።
– መሞከር…እኔ የማላውቀውን ወደፊት ለማሳካት መሞከር ምናምን አይገባኝም…ይልቅ ዛሬን ነው መኖር….

ዝም አለ።

– ስማ መስፍኔ….አልኩት ጃኬቱን ለብሶ ለመውጣት ሲሰናዳ
– ወይ….
– እነ ቤቲ እኮ አስመራና ምጽዋ ሄደው መጡ….ብንሄድ አሪፍ አይደለም?
– አስመራና ምፅዋ?
– አዎ…ትኬት ውድ ነው ግን የሚያውቁት ሰው ስላለ የሆቴል ወጪ ብዙ አይኖርብንም….ለምን ሄደን ሽር ብትን አንልም…የድሮ ባህራችን ላይ?
– ከየት መጣልሽ ይሄ ሃሳብ?
– አንተ ነህ ኦሮማይ አስመራ…ኤርትራ ምናምን የምትለው….በፅሁፍ የምታውቀውን ሃገር ብታይ ደስ አይልህም?

ዝም ብሎ ሲያየኝ ቆየና
– አሁን መሄድ አለብኝ ማዲዬ። ከፈለግሽ እዚሁ ቆይኝ…ከፈለግሽ ደግሞ ቆልፈሽ ሂጂ….ብሎ ከንፈሬን ለአመል ስሞኝ ወጣ።

እንደ ወጣ ለሄዋን ደውዬ ግዴለሽ የመምሰል ገድሌን ነገርኳት። ‹‹አንበሳ›› ብለ አንቆለጳጰሰችኝ። ‹በዚህ ከቀጠልሽ በአመት ውስጥ ቬሎ ትለብሻለሽ›› ብላ አበረታታችኝ።
ትንሽ አብዝቼው ይሆን በሚል ጥርጣሬ ገብቶት የነበረው ልቤ ረጋ።

ከሳምነት በኋላ ልደቱ ስለነበር አዲሳባ ውስጥ ምርጡን ክላርክ ጫማ ያስመጣል የተባልኩት ቤት ሄጄ የደሞዜን አርባ አምሰት ፐርሰንት ሆጭ አድርጌ ጫማ ገዛሁለትና የሚወዳቸውን ምግቦች ከሁለት ምግብ ቤቶች ገዝቼ ቤቱ ሄጄ ድግሱንም ራሴንም አዘጋጅቼ እጠብቀዋለሁ።

ለአንድ ሰአት ሩብ ጉዳይ ላይ መጣ።

እንኳን ተወለድክልኝ ምናምን ብዬ አቅፌ ስሜው ራት እየበላን ነበር።
– ምንድነው ይሄ ሁሉ ? አለ አንዴ እኔን አንዴ ትንሷ ጠረጴዛ ላይ ተፋፍገው የተቀመጡትን የምግብ አይነቶች፣ ከዚያ ደግሞ በትልቅ ብልጭልጨጭ ወረቀት የጠቀለልኩትን ስጦታዬን እያየ። ሻማም አልቀረኝ።
– ልደትህ አይደል….በደንብ ይከበርልህ ብዬ ነዋ….አልኩት ከጥብሱ ጎርሼ ቀይ ወይኔን እየተጎነጨሁ…
– እሱማ ገባኝ ግን በጣም በዛ ማዲዬ….ብዙ ወጪ ሳታወጪ አትቀሪም ለዚህ ሁሉ….
– ታዲያ ምናባቱ! እኔ ለዛሬ ነው የምኖረው ጌታዬ! አልኩ ግራ እጁን ጎትቼ ጭምቅ አድርጌ እየያዝኩ። ሰውነቴ የኔ ነው አፌ ግን የሄዋን ከሆነ ቆየ።
ዝም አለ።

– ደስ አላለህም መስፍኔ? እጁን እንደያዝኩ ጠየቅኩ
– ደስ ብሎኛል….ቅዝዝ ብሎ መለሰ።

ራት ስንጨረስ ስጦታውን ሰጠሁት። ዋጋውን ጠየቀኝ።
– እንዴት የስጦታ ዋጋ ይጠየቃል? ምናምን ብዬ አኮረፍኩት።
– ውድ ይመስላል…አለኝ
– እና?
– አይ ምንም…..

ልደቱን ካከበርን በኋላ ባሉት ሳምንታት መስፍኔ ቀስ በቀስ እየተሸራረፈ ሌላ ሰው መሆን ጀመረ።

ስደውል አያነሳም። ሲያነሳ ሰበብ ይደረድራል። እንደ ‹ስራ በዝቶ ነው። ስብሰባ ነበርን። ስልኬ ጠፍቶ ነበር። ካርድ አልነበረኝም›› አይነት።

ቴክስት ስልክ አይመልስም። ለአስር ቴክስት አንድ ሲመልስም ሰበብ ይደረድራል ወይ ስሜት የሌለው ነገር ይፅፋል። ለምሳሌ ‹ ትንሹ መስፍኔ ናፈቀኝ….ዛሬ አብረን አናድርም?›› አይነት ነገር ፅፌለት ‹ኢን ኤ ሚቲንግ› ምናምን የሚል ከስልኩ ጋር የመጣ መጠባበቂያ መልእክት ይልክልኛል። ካልመለሰለኝ ደግሞ አግኝቼው ምነው ስለው ‹‹ካርድ የለውም ነበር። ስብሰባ አለቃዬ ፊት ተቀምጬ ስለነበር ነው›› ይለኛል።

እንደ በፊቱ ቀን በቀን ቀርቶ በሳምንት አንዴ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘን ባለቀ ሰአት ይሰርዝብኛል። ሲዘርዝ ሰበብ ይደረድራል። እንደ ‹‹ፊልድ ሂድ ተባልኩ። እማዬን ትንሽ አመማት። ሃይለኛ ጉንፋን ይዞኛል። የወንይንዬ እናት አረፉ› አይነት።
ምን አጠፋሁ ስለው ‹‹ውይ አረ ምንም›› ብሎ ይምላል ይገዘታል። ከሰበቦቹ ተርፈው በማገኘው ቀን ግን ከወትሮው ተለይቶ ዝም ይለኛል። ፊቴ ይደበታል። አጠገቡ በመቀመጤ አየሩን የተሻማሁ እስኪመስለኝ ድረስ አስሬ ቁና ቁና ይተነፍሳል።

ጨነቀኝ።

ጠማማ እድሌ አድብቶ እና ዘግይቶ፣ ቀስ ብሎ ሮጦ የቀደመኝ መሰለኝ። ብሮጥ የማላምጠው የአርባ ቀን እድል አለኝ ልበል? ፀደቀ ያልኩት የሚደርቅብኝ፣ ሞቀ ያልኩት የሚበርድብኝ፣ የሳሳሁለት የሚሸሸኝ ለምንድነው?

ሳምንታት በእንዲህ ሁኔተ ሲያልፉ የማደርገው ጠፋኝና ተውኩት። ሄዋን ‹‹ወንድ እንዲህ ነው። መወትወትሽን ብታቆሚ ራሱ ይፈልግሻል ››ስትለኝ ተውኩት።

ግን እኔ መደወል ሳቆም በስልክም መነጋገር አቆምን።
እኔ እንገናኝ ብዬ መጠየቅ ስተው መገናኘት ተውን።

ጥፋቴ ሳይገባኝ እንደዛ የወደድኩት ሰው እንደ ጠዋት ጤዛ ባንዴ ታይቶ ባንዴ ጠፋ።

ጠፋ- ጠፋ!

ከሰባት ወራት በኋላ…

ከመስፍኔ ህመም እንደምንም ማገግም በጀመርኩበት ሰሞን ከቤቲና ሄዋን ጋር ቁጭ ብለን ቡና እየጠጣን ነበር። ከማይረባ ብዙ ወሬ በኋላ ቤቲ በተለመደ ችኮላዋ
– ሰምተን መደበቅ ሙድ የለውም…በቃ እወቂው አለች እያየችኝ።
ሄዋን ክው አለችና
– በናትሽ ቤቲ…! ራሷ ሌላ ጊዜ ትስማው በናትሽ አለች
– ምንድነው? አልኩኝ ቆጣ ብዬ…

ተያዩ።

– ምንድነው ለምን አትነግሩኝም? አልኩ እንደገና ተቆጥቼ
ቤቲ ያለወትሮዋ ትንሽ አቅማማችና-
– ማዲዬ፣ …መስፍን አግብቷል። ማወቅ አለብሽ ብዬ ነው…. አለች።

እሳት የተፋችብኝ ይመስል ፊቴ ተቃጠለ። በቀሰም ተነፍታ በነበልባል የምትቃጠል ዶሮ የሆንኩ መሰለኝ።
አጥንቶቼ ሁሉ የቀለጡና ከስጋ ብቻ የተሰራሁ መሰለኝ። ምራቄ ከአፌ ያለቀ መሰለኝ።
እንደምንም ሶፋውን ደገፍ ብዬ ሁለቱንም አየኋቸው።

– ሶሪ ማዲዬ…በቃ…ተይው…..አለች ሄዋን ፀጉሬን እየዳበሰች።

– ራይድ ጥሩልኝ ቤቴ መሄድ እፈልጋለሁ….ስል ብቻ ትዝ ይለኛል።

ቤቴ ገብቼ አንዴ እያለቀስኩ፣ አንዴ በንዴት ጦፌ መኝታ ቤቴ ውስጥ እየተንጎራደድኩ የሆነውን ሁሉ አንድ በአንድ ሳብሰለስል ብውልም፣ ባወጣም ባወርድም ይህ ለምን እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም። የእኔና የመስፍኔ መጨረሻ ይሄ መሆኑ በምንም ስሌት ባስበው ሊገባኝ አልቻለም።

ሞባይሌን አንስቼ ሰአቴን አየሁ። ሁለት ሰአት ከሃምሳ አምስት ደቂቃ። በጣም አልመሸም።

ደወልኩት። ለመስፍኔ ደወልኩለት። ያነሳ ይሆን?
ሁለቴ እንኳን ሳይጠራ አነሳው።
ይባስ ብሎ ልክ ስልኬን ይጠብቅ እንደነበር ሰው ሳይገረም ሰላም አለኝ።

– ሃይ….ማህደር እንዴት ነሽ?
ማህደር? ማህደር?
– ደህና ነኝ…እንኳን ደስ ያለህ ልልህ ነው…
– አመሰግናለሁ….አንቺ ደህና ነሽ?
– ደህና ነኝ….ማውራት ትችል ይሆን? አንድ ነገር ልጠይቅህ ነበር?
– እችላለሁ….
ስሜቴን ተቆጣጠርኩ። ጉሮሮዬን ጠረግኩ። ቃላቶቼን መረጥኩ።
– በዚህ ፍጥነት እንዴት አገባህ…?ማለቴ…ማለቴ ለምን እኔን ለማግባት….
ሳልጨርስ አቋረጠኝ።
– ትዳር የምትፈልጊ አልመሰለኝም…ማህደር እኔ ሃያ ምናምን አመት ሙሉ ገርል ፍሬንድ ነበረኝ። በዚህ እድሜዬ ሚስት ነበር የምፈልገው….ሳይሽ ስለወደፊት አታስቢም….እና…ጊዜ ማጥፋት አልፈለግኩም….እ?
ዝም አልኩ።

– ማህደር?
– አ–ለ—ሁ— አልኩ። ግን አልነበርኩም።
– እህ…ማንን ነው ያገባኸው? አልኩ የሚያውቃቸውን ሴቶች በሙሉ በአእምሮዬ ሳመላለስ መዋሌ በማያስታውቅ ሁኔታ።
– እ…ወይንሸትን…ወይንዬን ነው….

ባለ አርባ ስልሳዋ ወይንሸት!

ምን ብዬ እንደጨርስኩ ሳላውቅ ስልኩን ዘጋሁ።

ፊቴ እንደገና ሲነድ፣ አጥንቴ በንዴት ሲቀልጥ ይሰማኛል።

አልጋዬ ላይ ተዘረጋሁ።
ለኔ ያላትን እንጀራ እኔ ብገፋትም አልሻገተችም። ወይንሸት በልታታለች።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

4 Comments

  • mitikkuke@gmail.com'
    Mitiku Kebede commented on September 21, 2018 Reply

    Appreciate!!

  • Abrahammitku@gmail.com'
    Abraham mitku commented on September 21, 2018 Reply

    Eyalekeskum eyesakum anebebkut

  • እስታይህ አንማው commented on September 26, 2018 Reply

    ሲገርም!
    ብዙ ጊዜ ሰወች በሄዱበት መንገድ እየሄድን ነው ኪሳራችንን የምናበዛው፡፡

  • weluteklit2017@gmail.com'
    ኢዞና ናዛኢ commented on January 30, 2019 Reply

    ራሷን ሁና የሚቀረው ቢቀርባት:ቁጭቱ ብዙም የከፋ አሆንም ነበር….

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...