፩ – Solid vs Stranded
___
ስለ ኤሌክትሪክ ስናወራ በጭራሽ የማንዘለው አንድ ነገር Wire (Conductor) ነው.. ኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ (ሽቦ) እንለዋለን… ዋየር በሚሰራበት ቁስ በርካታ በአዘገጃጀት ደግሞ ሁለት መልክ አለው… Solid (አንድ ‘ነጠላ’ ሽቦ) እና Stranded (የቀጫጭን ብዙ ሽቦ እጅብ)… እንደምንሰራው የስራ ዓይነት ባለ ነጠላውም ሆነ ባለ አጀቡ ኬብል በእኩል ሚ.ሜ. ሊዘጋጅ ይችላል… ሁለቱም ‘በጣም’ የሚፈለጉበት ቦታ ቢኖርም ‘ብዙ ቦታዎች’ ላይ የሚመረጠው ግን Stranded የሆነው ነው…
___
ሁለቱም ሽቦዎች (ኬብል) በእኩል ውፍረት ተዘጋጅተው እንኳ ከባለ ነጠላው ይልቅ ደቃቃዎቹ ሽቦዎች የሚፈጥሩት ጥምረት የበለጠ ጠንካራ ነው… ይህም ብቻ አይደለም… እንደልብ የመተጣጠፍ (flexible) ተፈጥሮ ያለው ስትራንድዱ ስለሆነ በቀላሉ አይሰበርም… [የጭነት መኪና ላይ ግልጋሎት የሚሰጠውን ካቦ ልብ ይሏል… ሲቋጠር ሲፈታ ቢኖርም በቀላሉ አይበጠስም… መኪና ሲጎትትም እንዲሁ ብርቱ ነው] ስትራንድድ ኬብል ከፍተኛ እንቅስቃሴዎችና ተደጋጋሚ ለውጦች ባሉበት ቦታም ጽኑ ነው… በቀላሉ አይቆረጥም… ሶሊዱ ግን ቅንጥስ ባይ ነው…
___
ምን ይነግረኛል…
___
ሀ) ብርታት ከህብር ክንድ እንጂ ከጉልበታም አሃድ እንዳይወለድ… የብዙ ድምር ብልሃት እንጂ የተናጥሎ ስኬት ዘላቂ እንደማይሆን…
~
“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር”
“ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ”
~
ለ) ችግር ሁሌም አለ… ከእንከን የጸዳ ኑረት የትም የለም… ግን ደግሞ መፍትሔም አለ… ሁሉም መፍትሔ ሁሉ ዘንድ ግን በፍጹም አይኖርም… ለዚህ ነው ለቤትህ ክፍተት የጎረቤትህ አለኝታነት የሚያሻህ… ግትር ሆነህ መከራውን ሁሉ በሌጣ ልጋፈጥ ብትል ግን ትሰባበራለህ…
~
“… ስንቱን ትልቅ ችግር ሲፈታ የኖረ
ከእርሱ አልፎ ለሌሎች ዘዴን የቀመረ
ቀላል ነገር ገጥሞት ሲከዳው ብልሃቱ
በታናሹ ምክር ‘ካሳብ ከጭንቀቱ – ሲወጣ ማየቱ
… ኦ… ይገርማል …” ~ ኢዮብ መኮንን
~
፪ – Whole vs Each part
___
Gestalt Psychology የስነልቡና አንድ ቅርንጫፍ ነው… በዚህ የስነልቡና አስተምህሮ እሳቤ የአንድን ነገር ገጽታ የምንገነዘበው በጥቅል ውቅሩ እንጂ በነጠላ ይዘቱ አይደለም… ‘images are perceived as a pattern or a whole rather than merely as a sum of distinct component parts’
~
የተዳምሮ ውጤት የሆነችው ኢትዮጵያን በቅንስናሽ ክልላዊ አጥር እየቆራረጥን አይደለም የምንረዳት… ሕብር ያቆማት ግዙፍ ጎጆ አድርገን እንጂ… ጎጆው እኮ በብዙ ውህዳን ቁሶች እንደተወለደ እናውቃለን… ቁምነገሩ ግን በተናጥል ልዩልዩ ስም የነበራቸው ቁሶች የፈጠሩትን ግዙፍ ምስል ነው አብልጠን የምናየው…
~
Gestalt እንዲህ ባማረ መንገድ አስተምህሮውን ይቋጫል… “The whole is greater than the sum of each parts.” የድምሩ ትልቀት ከተደማሪዎቹ የድምር ልኬት ይበልጣል እንደማለት… በአጭር ቃል አዲስ አበባ እና 10 ክ/ከተማዎች እኩል አይደሉም… አዲስ አበባ ትበልጣለች… የአዲስ አበባን ግዙፍ ምስል ’10 ክ/ከተሞች’ የሚለው ቃል አያክለውም… ኢትዮጵያም እንዲሁ ናት – ‘ክልሎች’ አይስተካከሏትም!!!
___
፫ – መቋጠር vs መጋመድ
___
ታገል ሠይፉ በመጀመሪያ መድብሉ ላይ ለጊዜው አወራረዱ ትዝ የማይለኝና ሃሳቡን ብቻ የማስታውሰው አንድ ግጥም አኑሯል… ‘በጥላቻ የቆሰለን ልብ በፍቅር፣ በጠብ የተፈጠረን ልዩነት በመነጋገር፣ በክፋት የተራራቁ ልቦችን በይቅርታ መቋጠር ይቻል ይሆናል፤ ግና ቋጠሮውን ባዩ ቁጥር ተጣልተው እንደነበር ማሰብ አይቀርም’ የሚል ሃሳብ አለው…
~
“The dead past should not lead the living present.”
~
የትናንቱ ህመም በመደመር ሲታከም ከርሞ ግርሻ የማይጎበኘው ስንቋጠር አይደለም – ስንጋመድ ነው… መቋጠር መበጠስን ያስታውሳል… መጋመድ መታደስን ያሰርፃል፤ መቋጠር የመፈታት ዋዜማ ነው… መጋመድ ደግሞ የዝልቀት ምልክት፤ መቋጠር ግንቡን አፍርሶ ፍርስራሹን መተው ነው… መጋመድ ግን ግንብ እንዳልነበር ማድረግ፤ መቋጠር መጨባበጥ ነው… መጋመድ ግን መዋሃድ፤ ቋጠሮ ድንበር ይለያል… ተጋምዶ ድንበር ያጠፋል፤ ቋጠሮ ትርፍ ያበጃል… ተጋምዶ ሁሉን ያቅፋል…
___
እነሆ የመጨረሻው ቃል…
__________
“Nothing ever exists entirely alone. Everything is in relation to everything else.” ~ Buddha
_____
ፍቅርን ከመስጠት በላይ ዕዳ አይኑርባችሁ!!