Tidarfelagi.com

‹‹የኤንሪኮ ኬክ ፍርፋሪዎች…››

አራት ኪሎ ሮሚና ተቀምጬ ኮካዬን ስመጠምጥ የሚያስደነግጥ ነገር አየሁ።

ጌትሽ!

ጌትሽ አምሮበት።

ጌትሸ ከሌላ ሴት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ አየሁት።

የድሮ ፍቀረኛዬ ነው። እየወደድኩ የተለየሁት። ተለይቼ እቅፉን፣ ገላውን፣ ፍቅሩን እየናፈቅኩ የምኖር የድሮ ፍቅረኛዬ።

በፍቅረኛ ደንብ ሶቶ ለሶቶ ተያይዘው ወደ ተቀመጥኩበት ቦታ ሲመጡ እንደ ጨው መሟሟት፣ እንደ ክር መበጠስ የጀመርኩ መሰለኝ።

ባላየኝ። ባላየኝ።

ጋዜጣዬን ከፍ አድርጌ ፌቴን ሸፈንኩ።

‹‹ሄሉ….›› ሲል እንደተያዝኩ ገባኝና ጋዜጣውን ከፊቴ አውርጄ ልክ አሁን እንዳየሁት ሁሉ ተነስቼ ‹‹ጌትሽ…እኔ አላምንም!›› አልኩ።

ያኔ ልክ እኔን ይይዘኝ እንደነበረው ይዟታል።

እጆቹን ከእጆቿ ነጻ አውጥቶ ካቀፈኝ በኋላ በዝምታ የተቆራረጠ ደስ የማይል ሰላምታ ተቀያይረን አዲሲቷን እኔን፣ ቀጫጫዋን ፍቅረኛውን እንደ ነገሩ አስተዋወቀኝ።

‹‹ሰምሃል ትባላለች…ጓ..ጓደኛዬ ናት›› ብሎ።

ጣውላ ቂጥ ነገር ናት።

‹‹ሄለን›› ብዬ ተዋወቅኳት።

ከዚህ በኋላ ብዙ አልቆዩም። እሷ በእግር በፈረስ ያገኙትን ወንበር እንዳያጡ ፈጥና ሄዳ በጣውላ ቂጧ ስትቀመጥ ‹‹በናትሽ ደውይልኝ..ማወራሽ አለኝ…›› ብሎኝ ሄደ።

ጋዜጣዬን የማነብ መስዬ ሰረቅ አድርጌ አያቸዋለሁ።

እጆቿን እንደኔ እጆች ከያዘ እኔን ይስመኝ እንደነበር ይስማት ይሆን? እጆቿን እንደኔ እጆች ከያዘ እኔን ያየኝ እንደነበር ያያት ይሆን?
የሴትነት ቀዳዳዋን በወንድነቱ ከመድፈን…መተኮስ ሲያምረው ከመተኮስ ውጪ ከእሷ የሚያስተሳስረው፣ ከእሷ የሚገምደው የስሜት ገመድ፣ ስውር የስሜት ስፌት ነገር ይኖር ይሆን?
ከእሷ ያለው ነገር ውጋ ነቀል ብቻ ከሆነ…ይግባ ውጣ ብቻ ከሆነ፤ እሱን እሱንማ ማንም ወንድ ከፈሎም ያደርገዋል…ቺቺኒያ ቢሄድ ቀይ ከጥቁር ቀጫጫ -ከዶለዝ ጣውላ ቂጥ ከቋጥኝ ቂጥ አማርጦ እያገለባበጠ ያገኘዋል…

እኔ ማወቅ የምፈልገው እሱን አይደለም።

ለመሆኑ ሯሷን ጭኑ ላይ አድርጋ እንድትኛ ይፈቅድላታል?
ጥርሷን ሳትፍቅ የጠዋት አፏን ይስመዋል?
ጀርባዋን አቅፎ ሲተኛ ሰላም ይሰማዋል?

ሃሳቤን ሽሽት ታክሲ ውስጥ ገብቼ ቤቴ ሄድኩ።

ለምን በናትሸ ደውይ አለኝ…ለምን ፈለገኝ?

ያላመለጥኩትን ሃሳብ ሽሽት በልብስ የተጨነቀ ቁምሳጥኔን ወግ ለማስያዝ ከፈትኩ። ምስቅልቅሉ ወጥቷል። ሁሉንም ልብሶች አውጥቼ አልጋ ላይ በተንኳቸው።

ለምን ደውይ አለኝ?

አልደውልም።

ልብሶቹን እያጣጠፍኩ መመለስ ስጀምር ከአምስት አመት በላይ ያልለበስኩትን አንድ የረሳሁት ቀሚስ አገኘሁ።

አምስት አመት ያልለበስኩት ቀሚስ ቁምሳጥኔ ተቀምጦ ከሁለተ አመት በላይ ልቤን የሰጠሁትን ሰው አሽቀንጥሬ መጣሌ ሞኝነት መሰለኝ።

ቢሆንም አልደውልም።

አምስት ልብሶች አጣጥፌ ከተትኩ።

አልደውልለትም።

አስራ ምናምን ልብሶች አስተካክዬ ሰቀልኩ።

መደወል የለብኝም።

ልብሶቹን ጥዬ ሳሎን ሄድኩ።

ደወልኩለት።

– ሄሎ… የሴት ድምጽ

እመት ጣውላ ቂጥ ናት።

ዞር አለብኝ።

ዘጋሁት።

ለምን ረሳኋት? ለምን አብራው ልትሆን እንደምትችል ዘነጋሁ? ሮሚና ሮሚና ብቻ እንደማያገኛት ማሰብ ለምን ተሳነኝ?

– ቢሆንስ ግን ምን ሆና ነው የሱን ስልክ የምታነሳው..?ቁጥጥር መሆኑ ነው….?ከኔ ጋር ነው ለማለት ነው….?ቢች….!

መደወል አልነበረብኝም።

አምስት አመት ሳልለብስ ያስቀመጥኩት ቀሚስ ቆይቶ ይሆናል።

ግን አሁንም ልኬ ነው። ግን አሁንም የኔ ነው።

ጌትሽ ግን ከእንግዲህ ልኬ አይደለም። ጌትሽ ግን አሁን የኔ አይደለም፡ የእመት ጣውላ ቂጥ ነው።

መደወል አልነበረብኝም። ሺት!

በንዴት የጋለ ፊቴን በቀዝቃዛ ውሃ ለማቀዝቀዝ ወደ መታጠቢያ ቤት ገብቼ ውሃውን እንደከፈትኩ ስልኬ ጮኸ።

ቧንቧውን ሳልዘጋ ተንደርድሬ ሳሎን ተመለስኩና አየሁት።

ሺት ! ሺት !ሺት…!እሱ ነው

አላነሳውም።

ካነሳሁት …
– ምነው ደውለሽ ፍቅረኛዬ ጆሮ ላይ ዘጋሽው…እንዴት እንዲህ ታደርጊያለሽ…ደውለሽ እሷ ስታነሳ በመዝጋትሽ ሌላ ነገር ያለ መስሏት ብትጣላኝስ….ለምን ሕይወቴን ትበጠብጫለሽ…ለምን ደስታዬን ታውኪያለሽ ቢለኝስ…

አይ…ማንሳት አለብኝ…

ካላነሳሁት ሌላ ነገር ይመስልብኛል…አለ አይደል…ያልተዘጋ ፋይል ይዤ እምባዬን እያዘራሁ…ስለ አዲሱ ፍቅረኛው እያሰብኩ ንፍጤን እያዝረበረብኩ የማለቅስ…ለምን ተለየሁት…ለምን የእኔ አይደለም ብዬ ስታመስ የምውል የማድር ይመስለዋል…

አነሳሁት።

– ሄሎ…አልኩ አእምሮዬ በስሌት ሲጨነቅ፣ በስሜት ፈረቃ ሲወናበድ እንዳልቆየ ሁሉ ድምፄን ፍፁም ግድየለሽ…ዝንት…ዝንትንት ያለ አድርጌ። ላላየኝ ወይን ጠጅ እየጠጣሁ ኮሜዲ ፊልም ሳይ ቆይቼ ስልኩን ያነሳሁ ልመስል እችላለሁ

– ሄሎ ሄሉ? አለኝ ጆሮ በሚያሞቅ ድምጹ

(ጌትሽዬ የኔ የማር ስራ…ጌትሽዬ የኔ ዘንካታ…)

– ሄሎ…ጌትሽ…ጌታሁን…ጌትሽ

(ተወናበድኩ። ግድ የለሽ ለመምሰል የጣርኩት ጥረት በድምፁ ድል ተነሳ። በአንዴ ብትንትኔ ወጣ)

– ሃይ ሄሉዬ…

(ለምንድነው ሄሉ የሚለኝ? ሚስቱ አይደብራትም ወይስ ከልቡ ስላልወጣሁ ስለርሷ ስሜት ግድ የለውም…?ኦህ ማይ ጋድ…አሁንም ይወደኝ ይሆን…?ለዚያ ነው ግድ የሌለው…ለዚያ ይሆን እንዳልተለየ ሰው፣ እንዳልተጣላ ሰው…በሄለን ፈንታ ሄሉ የሚለኝ?)

-ጌትሸ… አልኩ ጉልበት አሰባስቤ
– ሄሉዬ ደውለሽ ነበር እንዴ..ሻወር ነበርኩ..
-ኦ..አይ…አልደወልኩም…ማለቴ ደውዬ ነበር

(አብረን እያለን…የሚወደኝ ጊዜ…የምወደው ጊዜ ባንድነት ሻወር የምንገባው…ገብተን በውሃ የምንጫወተው…ጎረቤት ያሉ ሰዎች ቧንቧ ሲከፍቱ ውሃው ቀጥ ሲል ‹‹በረደኝ…አሙቀኝ›› እያልኩ ላዩ ላይ የምለጠፍበት…ከነሳሙናዬ አቅፎ እየሳመ….ስሞ እያቀፈ ጮክ ብለ አረ ውሃ ዝጉ የሚለው…ውሃው ሲመጣ ፀጉሬን እያጠበ አፌን፣ አፍንጫዬን፣ አይኔን፣ ጀርባዬን ደግሞ የማይነገረውን ነገሬን ሁሉ እየሳመ ታጥበን ሳንጠራ፣ ከነሳሙናችን ትእይንቱን ወደሌላ የሚቀይረው ትዝ እያለኝ ስልኩን ክርፍፍ ብዬ ይዤ ቀረሁ…መቼ ነው እንደገና አብሬው የምታጠበው? መቼ ነው አብሬው የማድረው?)

– ሄሎ…ሄሉ…አለሽ…?
– አለሁ ጌትሸ..-
– ሻወር ነበርኩ እያልኩሽ ነበር..
– አዎ…ገባኝ…ደውዬ ነበር…
– እሱንማ አወቅኩ አለ ያን የአንጀት ሳቁን እየሳቀ (ፎጣ አገልድሞ እንደሚያወራኝ እጠረጥራለሁ….ካንጀቱ ሲሰቅ ሁሉ ነገሩ አብሮ ይስቃል…ሰውነቱ ይርገፈገፋል..ፎጣ ካገለደመ ፎጣው ልውደቅ እያለ ይግደረደራል ብዬ አሰብኩ…ብዙ አሰብኩ…ያቺ ሲምቢሮ እያየችው ይሆን? ታድራለች? ያን የመሰለ ሰውነቱ ላይ ስትፈነጭበት ልታደር ነው….እናቷን!)
– ደስ ብሎኛል ስለደወልሽ ሄሉ…ሰምሃል ናት ያነሳችውና ሲዘጋ ትንሽ ግራ ገባት…ለዛ ነው የደወልኩት…

ምን እንደምል ግራ ገባኝ።

በመደወሌ ደስ ስላለህ ደስ ብሎኛል…ለምን ደስ አለህ? የት እንገናኝ? ሰምሃልን ይቅርታ በልልኝ? መቼ ነው እንደገና አብሬህ የምተኛው?

– እህም…ይቅርታ በልልኝ…ኔትወርክ መሰለኝ ተዘጋብኝ…ደሞ….መልሼ ስደውል ካገልግሎት መስጫ ውጪ ምናምን ስትለኝ በኋላ እደውላለሁ ብዬ ተውኩት…ረበሽኳችሁ እንዴ ?አልኩ….(አቤት መወሽከት…አቤት መቅጠፍ…)
– ኖ…አልረበሽንም…አልረበሽኝም…እንዳልኩሽ እኔ ሻወር ነበርኩ…ብቻዬን…ማለቴ እሷ ሳሎን ነበረች…

(ድል አድራጊነት ተሰማኝ። …በጣም ደስ አለኝ። ከእኔ ጋር ያደርግ እንደነበረው አብሯት አይታጠብም ማለት ነው። አብሯት ካልታጠበ ሯሷን ጭኑ ላይ አድርጋ እንድትኛ አይፈቅድላትም።
ጥርሷን ሳትፍቅ የጠዋት አፏን አይስመውም።
ልሳምህ ብትለውም ‹‹ኡፍፍ…በናትሽ እስቲ መጀመሪያ ጥርስሽን ፋቂ…›› ብሎ ፊቱን ያዞርባታል..
ጀርባዋን አቅፎ አይተኛም። እንደውም ከኔ ጋር እያለ የነበረውን አፋቃሪ ጠባብ አልጋ የሜዳ ቴኒስ በሚያጫውት ትልቅ አልጋ ተክቶ እሷ ምእራብ እሱ ምስራቅ ነው የሚተኙት…

ይሄ ሁላ ምን ማለት እንደሆነ ታውቃላችሁ? ታውቃላችሁ ወይ? አይወዳትም። እኔን ይወደኝ እንደነበረው አይወዳትም። )

– ኦ..እሺ….አልኩ መንፈሴ ሲፍታታ እየተሰማኝ…(ታዲያ መቼ ነው እንደገና አብሬህ የምተኛው?)
– የት ሆነሽ ነው? አለኝ (ከድምፁ መዝናናት ሴቲቱ አብራው ያለች አይመስልም። የት አስገብቷት ወይ የት ገብቶ ነው?)
– ቤቴ…አልኩኝ ፈጠን ብዬ
– ብቻሽን?
– አዎ..ብቻዬን (ለምን ማወቅ ፈለገ…?)
– አሪፍ…ሊስን ሄሉዬ…ቅድም ስንገናኝ ደውይልኝ…ቶሎ እንገናኝ ስልሽ የነበረው ለትልቅ ምክንያት ነው…እፈልግሻለሁ…

(አይኔ እንደ ገበቴ ውሃ ወዲህ ወዲያ ዋለለ።፡ ልቤ ከለመደው ድርብ ድርብ መምታት ጀመረ። ‹‹እፈልግሻለሁ›› ሲለኝ ሁለንተናዬ…ከጣፊያ እስከ ሳንባዬ፣ ከኩላሊት እስከ ትንሹ አንጀቴ፣ ከአንጎል እስከ ቁርጭምጭሜቴ ሁሉም የሰውነት ክፍሌ ዋና ስራውን ትቶ ጆሮ ሆኖ የሰማ ይመስል በደስታ ነሆለለ።

– ትፈልገኛለህ? አልኩ ፈንጠዚያዩን መደበቅ እያቃተኝ
– አዎ…ሲሪየስ ነገር ነው…ነገ እንገናኝ?
– ሹር…የት…? አልኩ አሁንም ድምጼ በደስታ ስሜት እንደተሸነፈ..

(ቤርጎ ላግኝህ የኔ ጌታ? ቤትህ ልምጣ የኔ ሁለንተና?)
– በፊት እንገናኝበት የነበረው….ቢሎስ ካፌ…እዛ ሰባት ሰአት ትችያለሽ?

(አንተ ልከህብኝ…እንኳን ቢሎስ ካፌ ቲምበክቱ እቀራለሁ? እንኳን ከቀኑ ከሌሊቱ ሰባት ሰአት አልችልም እላለሁ?)

– አሪፍ። እመጣለሁ። አልኩ በፍጥነት
– ሄሉዬ…. አለ በዚያ ልብ እንደ ሰም በሚያቀልጥ ‹‹ሴክሳም›› ድምጹ
– ወዬ…ጌትሽ…..
– አንድ ነገር ላስቸግርሽ..
– ምን ጌትሽ…
– ያ የሃይስኩል ጓደኛሽ…የሚከየፍብሽ… አሁንም የኤንሪኮ ማኔጀር ነው? ሚሊዮን?
– አዎ…ምነው…በምን ትዝ አለህ? (ከእሱ ከተጣላሁ በኋላ ከሚሊ ጋር አንድ ሰሞን ወጣ ገባ እንዳልኩ አያውቅም)
– አይ…ልክ እንደ ድሮ…ያኔ ስንገናኝ እንደምታረጊልኝ የኤንሪኮ ኬክ ይዘሽልኝ ነይ…ያው በዘመድ.. ያስቀምጥልሽ የለ…?

(ለየለት። ለየለት ልጁ…ፍቅራችን ጡዘት ላይ በደረሰበት ጊዜ እናደርግ የነበረው ነገር ነው። እኔ ሚሊን አስቸግሬ ከወፈ ሰማይ ህዝብ ተደብቆ የተቀመጠልንን 6 የኤንሪኮ ኬኮች ተቀብዬ፣ እሱ ቤቱን ፏ አድርጎ አፅድቶ ጠብቆኝ አልጋ ውስጥ እንገባና ኬክ በፍቅር እንበላለን…ኤንሪኮ ኤንሪኮ በሚል አፉ አፌን ይስማል፣ አፍንጫዬን በአፍንጫው ይነካካል…አይኖቼን እንደመላስ ያደርገዋል…ሁለንተናችን ከኬክ ኬክ.. ይሸታል…ኬኩና የእሱ ሰውነት ይምታታብኛል….አልጋችን በፍቅራችን እና በኬኮቹ ፍርፋሪዎች ይሞላል….ይሄ ዝም ብሎ ግብረስጋ አይደለም…ይሄ ወሲብ አይደለም…ይህ ፍቅርን መስራት ነው…በፍቅር መውደቅ መነሳት ነው….መውደድ ነው….ታዲያ ለዚህ ልጅ እንኳን የኤንሪኮ ኬክ የጨረቃ አፈር ይዤ ብሄድ ይገረማል?)

– ችግር የለውም…ደስ ይለኛል…
– በይ ቻው…ነገ እንገናኝ…
– ቻው…

ስልኩን ዘግቼ ትንሽ እንደተቀመጥኩ መታጠቢያ ቤት ከፍቼ የተውኩት ውሃ ሲፈስ ተሰማኝ።

ሮጬ ሄጄ ዘጋሁት።

የፎጣ ማንጠልጠያዩ ላይ የተሰጡትን ቁሌታም የውስጥ ሱሪዎቼን አየሁ።

ነገ የማደረገው ባለጌውን ቤኪኒዬን ነው።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...