Tidarfelagi.com

የዐቢይ ንግግር ሰባት አዕማድ

የሀገሬ ሰው ‹ካልተናገረ አይታይ ብልሃቱ፣ ካልታረደ ዓይታይ ስባቱ› ይላል። ንግግር የሰው ልጅ ከተሰጡት የላቁ ጸጋዎች አንዱ ነው። ንግግር ሰዎችን ሊያግባባቸው፣ ወደ አንድነትና ኅብረት ሊያመጣቸው፣ ሊያከራክራቸውና ሊያወያያቸው ኃይል አለው። ከመሪዎች ከሚጠበቁ ነገሮች አንዱ ኃይል ያለው ንግግር ነው። ኃይል ያለው ንግግር በሚመርጣቸው ቃላት፣ በሚጠቀምበት ድምፀት፣ በሚያቀርባቸው አገላለጦች፣ በሚሰጣቸው ምሳሌዎች፣ በሚቀርብበት ተፋሰስ፣ በሚዋቀርበት አሰካክና በምጣኔው ይታወቃል። ሊደመጥ፣ ሊነበብ የሚችል፣ በሐሳቡ ባንስማማም በአቀራረቡ የሚማርከን፣ በዝርዝሩ ባንግባባም ሐሳቡ ግን የሚገባን፤ ባንወደውም የምናደንቀው ንግግር ከመሪዎች ይጠበቃል። ዐፄ ምኒልክ ለዐድዋ ጦርነት ሕዝቡን ለመጥራት ያወጁት ዐዋጅ ከዐዋጅነቱ ይልቅ የመሪ ጥሪ የሆነ ቃል አለው። በውስጡ ንጉሡንና ሕዝቡን የሚያቀራርብ፣ የሀገሪቱን ችግር የሚገልጥ፣ ከሕዝቡ የሚፈልጉትን የሚያሳይ፣ ሀገር ስትጠራው እምቢ ብሎ የቀረ የሚገጥመውን ዕጣ ፈንታ የሚያመላክት ቃል ነው። መላዋን ኢትዮጵያ ለአንድ ዓላማ ያሰለፈና ውጤቱን በዐድዋ ተራሮች ላይ ያሳየ ቃል ነው።

በተለይ ደግሞ ሀገር ምጥ ላይ በምትሆንበት ጊዜ የመሪዎች ንግግር ወይ ፈዋሽ ወይ አባባሽ ይሆናል። ከአያያዝ ይቀደዳል ከአነጋገር ይፈረዳል እንዲሉ። አነጋገሩ የሚያግባባ፣ የሚጠራና የሚያቀራርብ ከሆነ ሕዝብን ለመፍትሔ የማሰለፍ ኃይል ይኖረዋል። ንግግሩ ብቻ ሳይሆን ንግግሩ የተዋቀረበት መዓዝን የመሪውን ጉዞ ካርታውን እንድናይ ያደርገናል።

የዶክተር ዐቢይ አሕመድ ንግግር በንግግሩ ይዘት፣ ንግግሩ በተቀናበረባቸው ቃላት፣ ቃላቱ በተሰናሠሉበት አወቃቀር፣ ሐሳቡ በተገለጠባቸው ምሳሌዎች፣ ማሳያዎች፣ ጥቅሶች፤ ትኩረትና አጽንዖት በተሰጣቸው የሐሳብ ዘውጎች፣ ብርታቱና ድክመቱ ሊተነተንና የመሪዎች ንግግር ምን መሆን እንዳለበት መማማሪያ ሊሆን ይገባዋል የሚል ሐሳብ አለኝ። በዚህ ረገድ ንግግሩ የተዋቀረባቸውን ሰባት አዕማድ ለዛሬ ላንሳ።
የዶክተር ዐቢይ የበዓለ ሲመት ንግግር በሰባት አዕማድ የተዋቀረ ነው። እነርሱም ክብር፣ ፍቅር፣ ተስፋ፣ አንድነት፣ ይቅርታ፣ ሰውነትና ኢትዮጵያ/ኢትዮጵያዊነት ናቸው።

1. ክብር፡- ዶክተር ዐቢይ ንግግራቸውን የጀመሩት ከእርሳቸው በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትንና በፈቃዳቸው ሥልጣን ‹ያሸጋገሩትን› አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በማመስገን ነው። በዚህ ንግግራቸው ግን ክብርና ምስጋና የሰጡት ለእርሳቸው ብቻ አይደለም። ሌሎች ሰባት አካላትም ክብርና ምስጋና ተሰጥቷቸዋል።
ሀ. ሽግግሩን እዚህ ደረጃ ለማድረስ ሚና ለተጫወቱ፣
ለ. ኢትዮጵያን ለሚያኮራት ታሪካችን፣
ሐ. ለኢትዮጵያውያን የማይበጠስ አንድነት፣
መ. ለኢትዮጵያ ታላቅነት በየዘመናቱ መሥዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን፣
ሠ. በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣
ረ. ለተፎካካሪ ፓርቲዎች፣
ሰ. አሁን ለመጣው ለውጥ ዋጋ ለከፈሉ ኢትዮጵያውያን ተገቢውን ክብር በንግግራቸው ውስጥ ሰጥተዋቸዋል። ሌላው ቀርቶ ከታሪክ መዝገብ የተፋቀ ይመስል ከመንግሥታዊ ዲስኩሮች ስሙ ጠፍቶ ለኖረው የካራማራ ድል ተገቢውን ክብር ሰጥተውታል።
ኢትዮጵያውያንን የገለጡበት መንገድም ለዜጎች ያላቸውን ክብር የሚያሳይ ነበር ‹ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም ናት። ከፍ ባለ የአገር ፍቅር መንፈስ ሰርክ የሚተጉ ልጆችን አፍርታለች። ልጆቿም ወደቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ፣ የሕዝቧ ሰላምና ፍትህ እንዲጠበቅ፣ ብልጽግና ያለ አድልኦ ለመላው ዜጎች ይደርስ ዘንድ አጥብቀው ይመኛሉ… ይደክማሉ። በሀገር ውስጥና በውጪ ሆነው ስለ ሀገር አንድነትና ሰላም… ስለፍትህና እኩልነት…እንዲሁም ስለብልጽግና ይጮሃሉ…ይሞግታሉ… ይሟገታሉ።› ነው ያሏቸው። የዜጎቻቸውን ትግልና ጥረት ክብር ሰጥተውታል። አሸባሪዎች፣ ነውጠኞች፣ አደገኛ ቦዘኔዎች፣ አላሏቸውም።

ዶክተር ዐቢይ ኢትዮጵያውያን ላደረጉት የዴሞክራሲ፤ የፍትሕ፤ የእኩል ተጠቃሚነት፤ በነጻ ተዘዋውሮ የመኖርና የመሥራት፤ የሕግ አስከባሪ ተቋማት ገለልተኝነት፤ ሕዝብ አገልጋዩን የመተቸት፤ የመምረጥ፣ የመጠየቅ ሙሉ መብት፣ ጥያቄና ትግል ክብርና ዕውቅና ሰጥተውታል።

2. ፍቅር፡- አንድነታችን ፈተና ገጥሞታል፤ ፍቅራችንን የሚያቀዘቅዙ ነገሮች እየተከሠቱ ነው፣ መጠላላቱና መከፋፋቱ በየአቅጣጫው ዕየታየ ነው በምንልበት ወቅት ፍቅርን የሚሰብክ የመሪ መልእክት ኃይል አለው። የዶክትር ዐቢይ ንግግር ይህንን የተረዳና ማሻሪያ ለመስጠት የተዘጋጀ ነበር። በሕዝቡ መካከል ከፍቅር ይልቅ ቅሬታ፣ ከወዳጅነት ይልቅ ጠላትነት፣ የሚያጭሩ ቃላትን ላለመጠቀም ጥንቃቄ አድርጓል። በኢትዮጵያ ታሪክ ከደርግ ዘመን ፓርላማ ወዲህ ‹ፀር› ከፓርላማ የተባረረበት የመሪ ንግግር ነበር። ፀረ አብዮት፣ ፀረ ሕዝብ፣ ጸረ ልማት፣ ፀረ ዴሞክራሲ፣ ፀረ … የሚለውን እንደ ሃሌሉያ አዘውትሮ ሲሰማ ዐርባ ዓመት ላለፈው ፓርላማ እንግዳ ነገር ነው። ጠባብነት፣ ነፍጠኝነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሽብርተኝነት፣ የመሳሰሉት የሰለቹ ቃላት ባመሳተፋቸው አዝነው የዋሉበት ንግግር ነበረ።

የዶክተር ዐቢይ ንግግር በ8 ገጽ፣ በ2776 ቃላት፣ በ12533 ምዕራፍ አልባ ቅንጣቶች(Characters without space)፣ በ15230 ባለ ምዕራፍ ቅንጣቶች(Characters with space)፣ በ79 ዐንቀጾችና በ259 መሥመሮች የተዋቀረ ነው። በዚህ ንግግር ውስጥ በዋናነት የተንጸባረቀው መግለጫ ‹እኛ› የሚለው ራስን ከሕዝብ ጋር የሚያስተሣሥርና ፍቅርን ሊገልጥ የሚችለው አንጓ ነው። ይህን ለመግለጥ በቃላት ላይ – ችን የሚል ድኅረ ቅጥያ ተጠቅመዋል። ኢትዮጵያችን፣ ሕዝባችን፣ ሀገራችን፣ ወገናችን፣ ችግሮቻችን፣ ስኬቶቻችን የሚሉ መግለጫዎች አሉ። በጽሑፉ ውስጥ ይህንን መንገድ ከ86 ጊዜ በላይ ተጠቅመውበታል። ከዚህ መካከል ከ18 ጊዜ በላይ ‹ሀገራችን› የሚለው መግለጫ ይገኝበታል።

3. አንድነት፡- የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር፣ ከማራራቅ ይልቅ የሚያቀራርብ፣ ከመገፋፋት ይልቅ የሚያስተሣሥር፣ ከማግለል ይልቅ የሚያካትት፣ ከመነጣጠል ይልቅ የሚያስተባብር ነበር። ራሳቸውን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው ነው ያቀረቡት። ከመነሻቸው ይልቅ መድረሻቸው ላይ ነው ያተኮሩት። ራስ ካሣ እንዳሉት ‹ፀሐይን ለብቻዬ ልሙቅ አይባልም›። ጠቅላይ ሚኒስትሩም የአንድ ወገን አይደሉም። የጥንቶቹም የዛሬዎቹም፣ የደጋፊዎቹም የተፎካካሪዎቹም፣ የክርስቲያኖቹም፣ የሙስሊሞቹም፣ የሌሎቹም፤ የመረጧቸውም ያልመረጧቸውም፣ የሀገር ቤት ነዋሪዎቹም የዳያስጶራዎቹም ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውን አሳይተውበታል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የትናንቱም የዛሬውም፣ የነገውም ጠቅላይ ሚኒስትር ነውና የቀደሙትን ከዛሬዎቹ ጋር አስተሣሥረው ጠርተዋቸዋል። በታሪካችን ውስጥ ማሳያ የሚሆኑትን ኩነቶች አንሥተው የእገሌ ጎሳ መሬት ነው ሳይሉ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው በየዘመናቱ የከፈሉትን መሥዋዕትነትና በመሥዋዕትነት ቦታቸው የዚያው ቦታ አፈር ሆነው መቅረታቸውን ገልጠዋል።

‹በአንድ ሀገር ውስጥ የሀሳብ ልዩነቶች ይኖራሉ። የሀሳብ ልዩነት እርግማን አይደለም። ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ መደማመጥና በመርሕ ላይ ተመስርተን መግባባት ስንችል የሀሳብ ልዩነት በረከት ይዞልን ይመጣል። በሀሳብ ፍጭት ውስጥ መፍትሄ ይገኛል። በመተባበር ውስጥ ኃይል አለ። ስንደመር እንጠነክራለን። አንድነት የማይፈታው ችግር አይኖርም… አገር ይገነባል። የኔ ሀሳብ ካላሸነፈ ሞቼ እገኛለሁ ማለት ግን እንኳን አገርን ሊያቆም ቤተሰብን ያፈርሳል። ያለችን ኢትዮጵያ ነች ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ ሀገራዊ አንድነት ይበልጣል። አንድነት ማለት ግን አንድ ዓይነትነት ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል። አንድነታችን ልዩነቶቻችንን ያቀፈ ብዝኃነታችንን በኅብረ ብሔራዊነት ያደመቀ መሆን አለበት።› የሚለው መዓዝናዊ የአንድነት መግለጫቸው ነው።

ይህ ለውጥ እንዲመጣ በየመሥመራቸው የታገሉትን የጠሩበት መንገድ፣ ተቃዋሚ ፓርቲ እየተባሉ ሲጠሩ የኖሩትን ኃይሎች ‹ተፎካካሪ ፓርቲዎች› ብለው የገለጡበት አካሄድ። ዳያስጶራውን ማኅበረሰብ ያቀረቡበት መንገድ የንግግሩ አንኳር ነው። ከዚህ በፊት ከተለመደው ወጣ ባለ መልኩ ‹በተለያየ ጊዜ፣ መስዋእትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎችና ፖለቲከኞች፤ በቅጡ ሳይቦርቁ ሕይወታቸውን ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች፤ ለሥነ ልቦናዊና አካላዊ ቀውስ የተዳረጉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች› እና ‹ሰላም ለማስከበርና ሕገ መንግሥታዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ሲንቀሳቀሱ ሕይወታቸውን ያጡ የፀጥታ ኃይሎች› ጎን ለጎን የተመሰገኑበት መንገድ አስደናቂ ነው። መንግሥት ለአንጋቹ እንጂ ለሟቹ የማይወግንበትን አካሄድ ያረመም ነው።

4. ይቅርታ፡- የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ከተዋቀረባቸው አዕማድ አንዱ ይቅርታ ነው። በተለያዩ መንገዶች ገልጠውታል። በተለይም ስድስቱ ዋና ዋና ዘውጎች ይጠቀሳሉ፡-

፩. ‹ያሳካናቸው በርካታ ድሎች እንዳሉ ሁሉ በፍጥነት መቀረፍ የሚገባቸው በርካታ ጉድለቶች እንዳሉም እናምናለን። ከስህተቶቻችን ተምረን ወደፊት በመራመድ ማተኮር ያለብን ጉዳይ የተሻለች ሀገር ለሁላችንም በመገንባቱ ላይ ነው።›፣‹የሁሉም ዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ ማኅበራዊ ፍትሕ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ከማሳደግ አንጻር ክፍተቶች ነበሩ።› የሚለው ስሕተትን የሚያምነው፤
፪. ‹ወቅቱ ከስህተታችን ተምረን አገራችንን የምንክስበት ወቅት ነው!› የሚለው ወቅቱን ከስሕተት አንጻር የገመገመው።
፫. ‹በተለያየ ጊዜ፣ መስዋእትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎችና ፖለቲከኛች፤ በቅጡ ሳይቦርቁ ሕይወታቸውን ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች፤ ለሥነ ልቦናዊና አካላዊ ቀውስ ለተዳረጉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች ከልብ የመነጨ ይቅርታ እጠይቃለሁ› የሚለው ለተፈጠረው ችግር ይፋዊ ይቅርታ የሚጠይቀው፣
፬. ‹በአገር ውስጥም ሆነ በስደት ከአገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከልባችን ይቅር ተባብለን፣ የትናንትናውን ምእራፍ ዘግተን፣ በብሔራዊ መግባባት ወደ ቀጣይ ብሩህ ሀገራዊ ምእራፍ እንሻገር ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ› የሚለውና ከሌላውም ወገን ይቅርታን የሚጠይቀው ንግግር ይቅርታውን በየደረጃው የጠየቀ ነው።
፭. ‹መጪው ጊዜ በኢትዮጵያችን የፍቅርና የይቅርታ ጊዜ ነው!› ሲሉም ይሄንኑ አጽንተውታል። ይህም እንዲሳካ
፮. ‹በአገር ውስጥም ሆነ በስደት ከአገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከልባችን ይቅር ተባብለን፣ የትናንትናውን ምእራፍ ዘግተን፣ በብሔራዊ መግባባት ወደ ቀጣይ ብሩህ ሀገራዊ ምእራፍ እንሻገር ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ።› ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

5. ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት፡– ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ናት? እነዚህን 12 መግለጫዎቻቸውን እንመልከት፡-

ሀ. ኢትዮጵያ ማኅጸነ ለምለም ናት
ለ. ትላንት፣ አባቶቻችን በመተማ፣ በማይጨውና በካራ ማራ አጥንታቸውን ከስክሰው የከበረ ደማቸውን አፍስሰው በክብርና በአንድነት ያቆይዋት አገር አለችን።
ሐ. እኛ ዕድለኞች ነን። ውብ አገር አኩሪ ታሪክ አለን። እኛ መነሻችንን እናውቃለን። በርካታ ዘመናትን የሚሻገር ታሪክ ያለው ታላቅ ሕዝብ ነን።
መ. ኅብረታችን ለዓለም ምሳሌ መሆን ይችላል። ጠላቶቻችንን አንበርክኳል። ሉዓላዊነታችንን ጠብቆ ዛሬ ላይ ከማድረሱም በላይ ለሌሎች ሕዝቦችም የነጻነት ትግል አርአያ ሆኗል።
ሠ. ማንነታችንን እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ፣ እንዳይነጣጠል ሆኖ የተገመደ፣የተዋደደ እና የተዋሐደ ነው!
ረ. የየትኛውንም ኢትዮጵያዊ ክቡር ሥጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ። ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን።
ሰ. ኢትዮጵያ የሁላችን ሀገር፤ የሁላችን ቤት ናት!
ሸ. ያለችን ኢትዮጵያ ነች ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ ሀገራዊ አንድነት ይበልጣል።
ቀ. እኛ ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲና ነጻነት ያስፈልገናል፣ይገባናልም
በ. ኢትዮጵያ የጋራችን፣ የኛ የሁላችን መሆኗን ተገንዝበን የሁሉም ድምጽ የሚሰማበት፣ ሁላችንንም የሚያሳትፍ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የመገንባቱን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን።
ተ. ኢትዮጵያችን፣ አንዱ ሠርቶ ሌላው ቀምቶ የሚኖርባት አገር እንዳትሆን ….
ቸ. እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሥራም ሆነ ለትምህርት በሄደበት ሁሉ ኢትዮጵያን ተሸክሟት ይዞራል። ኢትዮጵያዊውን ከኢትዮጵያ ታወጡት እንደሆነ ነው እንጂ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊው ልብ ውስጥ አታወጧትም የሚባልም ለዚህ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ኢትዮጵያዊነትን ከዜግነት በላይ ሐሳብ፣ ፍልስፍናና ሀገራዊ መርሕ አድርጎ ያቀረበ ነው። ይህንንም በአንድ አንኳር ‹ኢትዮጵያዊነት ያስተማረን እውነታ በጊዜያዊ ችግሮች ተሸንፎ መውደቅን ሳይሆን ፈተናዎችን ወደ ዕድልና መልካም አጋጣሚ ቀይሮ ድል መቀዳጀትን ነው።› ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ‹ኢትዮጵያዊነት› የሚለውን ሉዓላዊ ሐሳብ በክብር ገልጠውታል።

6. ሰውነት፡- ማንኛውም መሪ፣ መሪ ከመሆኑ በፊት ሰው ነው። አብዮታዊ ነን የሚሉ መሪዎች ሰውነትን ይተውትና ተቋማዊነትን ቦታ ይሰጡታል፡፤ ከሰው የተወለዱ፣ ሰው ያሳደጋቸውና የሰው ፍሬዎች መሆናቸው ይረሱታል። መነሻቸውን ከሰው ሳይሆን ከድርጅት ያደርጉታል። የዶክተር ዐቢይ ንግግር አንዱ ዓምድ ለሰውነት የሰጠው ቦታ ነው። ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ዳያስጶራዎች፣ መሥዋዕትነት የከፈሉ ዜጎች የተነሡበት መንገድ ለሰውነታቸው ቅርብ በሆኑ ቃላት ነው። እንደ ቡድን የሚያይ ሳይሆን ለግለሰብነታቸው ዋጋ የሚሰጥ ነው።

ዳያስጶራዎች በምንም ዓይነት የፖለቲካ መሥመር ውስጥ ቢሆኑም ‹ሁላችሁም በታታሪነታችሁ፣ በልቀታችሁ እና የትም በሚከተላችሁ የሀገራችሁ የጨዋነት ባሕሪ የኢትዮጵያና የዕሴቶቿ እንደ ራሴዎች ናችሁ።› የሚለው ገለጻ ግን የማይመለከተው የለም። ‹አንዳንድ ጊዜ ከኢትዮጵያ ያነሰ የተፈጥሮም ሆነ የታሪክ ሀብት ባላቸው ነገር ግን እጅግ በበለጸጉ ሀገራት ውስጥ ራሳችሁን ስታገኙት ስለሀገራችሁ ቁጭት ሳይሰማችሁ አይቀርም።› ሲል ቁጭታቸውን ይቆጫል። ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ‹እንደጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሀሳብ አለኝ ብሎ እንደመጣ አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ› ለማየት ጥረዋል። ከድርጅቶቹ ይልቅ ሰዎቹን ‹ወንድም፣ ዜጋ› እያሉ በሰውነት ጠርተዋቸዋል። ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩም እናታቸውን፣ ባለቤታቸውንና የትግል አጋሮቻቸውን ያመሰገኑበት መንገድ ሰውዬው ሰው ናቸው እንድንል የሚያደርግ ነው።

እናታቸውን ከኢትዮጵያውያን እናቶች አንዷ አድርገው፣ ባለቤታቸውን ሚና ከኢትዮጵያውያን ሚስቶች ጋር አስተሣሥረው የገለጡበት መንገድ ‹ሰውነት› የታየበት ነው። ሰው ከሆኑ ደግሞ እንደሰው ይሠራሉ፣ እንደሰውም ይሳሳታሉ።

7. ተስፋ፡- ሰባተኛው የንግግሩ ዓምድ ተስፋ ነው። ምን ሊሠሩ አስበዋል? ምን እንጠብቅ? ሊሠሩ ያሰቡትን ብቻ ሳይሆን ከሌሎች አካላት የሚፈልጉትንም ገልጠውበታል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ውስጥ ቃል መግባትንና ጥሪን የተመለከቱ 19 ጉዳዮች አሉ። እነዚህም፡-
i. ይህ የሥልጣን ሽግግር አዲስ ምዕራፍ የምንጀምርበት ሌላ ታሪካዊ እድል ነው፤ በመሆኑም በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ልንጠቀምበት ይገባል።
ii. በሀገራችን ዲሞክራሲ እንዲያብብ፣ ነጻነትና ፍትሕ እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ማሻሻያ በማድረግ በዘርፉ ያለውን ክፍተት እንሞላለን።
iii. ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃም ከልብ እንፈልጋለን። የበኩላችንንም እንወጣለን።
iv. ኢትዮጵያችን፣ አንዱ ሠርቶ ሌላው ቀምቶ የሚኖርባት አገር እንዳትሆን ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ በትህትና እጠይቃችኋለሁ
v. አሁን በጀመርነው አዲስ ምዕራፍ፣ ዘረፋን፣ የሀብት ብክነትን እና የተደራጀ ሙስናን፣ መላው ሕዝባችንን በሚያሳትፍ እርምጃ ለመመከት ሌት ተቀን እንተጋለን።
vi. በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን እና ከቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች የሚወጡት ተማሪዎቻችን ከሚገበዩት ዕውቀት የሚነጻጸር ከሂሎት እንዲኖራቸው ከፍተኛ ጥራት ይደረጋል።
vii. የሁለተኛውን የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የሁሉት ዓመት ተኩል አፈጻጸም በመገምገም አስፈላጊ የሆኑ የፖሊሲ እርምጃዎችን በመውሰድ፣ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትን ለማስቀጠል እንታገለን
viii. ኢትዮጵያ ለወጣቶቿ ተስፋ የምትሰጥ እንጂ፣ ተስፋ የምታስቆርጥ አገር እንዳትሆን የምንችለውን ሁሉ እንደምናደርግ ቃል እገባለሁ። በሚቀጥሉት ጊዜያት ለወጣቱ የሥራ ዕድል መፍጠር ብቻ ሳይሆን ወጣት ባለሀብቶች በብዛት እንዲፈጠሩ እንሠራለን። ለዚህ እንቅፋትና መሰናክል ለሚሆኑ አመላካከቶችና የተንዛዙ አድሏዊ የሆኑ አሠራሮች ተወግደው ፍትኃዊ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት እንዲኖረን መንግሥት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
ix. መንግሥታችን ከዚህ ቀደም ከነበረው ፍጥነት እና የትግበራ ስኬት በላቀ መልኩ ለሴቶች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት በቁርጠኝነት ይሠራል።
x. ዜጎች በሀገራቸው ውስጥ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር እና ሀብት የማፍራት መብታቸው መከበር አለበት። በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት ተገቢ ያልሆነ ድርጊት እንዲያበቃና ዳግም እንዳይፈጠር መሥራት ይኖርብናል።
xi. በቀሪው የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዓመታት ቀሪ የልማት መርሐ ግብሮቻችንን በፈጠነ ጊዜ ለማሳካት ጥረት ይደረጋል።
xii. ከመደበኛው የሥራ ሰዓታችን በሚሻገር ጊዜ፣ ከፍ ባለ ፍጥነትና ተነሳሽነት በመሥራት በቅርብ ዓመታት ውስጥ በተከሰተው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የደረሰብንን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳት ለማካካስ አገራዊ ንቅናቄ እንድናደርግ ከአደራ ጭምር መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።
xiii. ዕውቀታችሁንና ልምዳችሁን ይዛችሁ ወደ ሀገራችሁ መመለስና ሀገራችሁን አልምታችሁ መልማት ለምትሹ ሁሉ እጃችንን ዘርግተን እንቀበላችኋለን።
xiv. በውጭ ሀገራት ኑሯችሁን ላደረጋችሁትም ቢሆን በማንኛውም መልኩ በሀገራችሁ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንድትሆኑና ሀገራችንን በሙሉም መልክ ለመቀየር ለምታደርጉት አስተዋጽኦ መንግሥት ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል።
xv. ከጎናችን የቆማችሁ የልማት አጋሮቻችን የሀገራችን ጥብቅ ወዳጆች እንደሆናችሁ እንገነዘባለን። የሀገራችንን ልማት እና ሰላም ለማረጋገጥ በምናደርገው ጥረት እንደ ወትሮ ሁሉ ከጎናችን እንደምትቆሙ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ።
xvi. ለተፈጠሩ ችግሮች እልባት በማበጀት ሕዝባችንን እንደምንክስም ጭምር በዚሁ አጋጣሚ ቃል እገባለሁ።
xvii. በልዩ ልዩ መንገድ የምትታገለግሉ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች፣ አብሮነታችንንና ሰላማችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ፤ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንንም አሳልፈው የሚሰጡ የአስተሳሰብ መስመሮችን በአርቆ አስተዋይነትና ሀገራዊ ፍቅር፤ በሰጥቶ መቀበል መርሕ የተሻለ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር የምናደርገው ጥረት እንድታግዙ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
xviii. ሁላችንም የዳበረ ዴሞክራሲ ለመገንባት እንረባረብ! ሀገራችንን ከድህነት አዘቅት ውስጥ ለማውጣት እንትጋ! ዘረኝነትና መከፋፈልን ከሀገራችን እናጥፋ! የተማረና በምክንያት የሚከራከር ዜጋ እንፍጠር!
xix. ከግድቡ መጠናቀቅ ባሻገር የሀገራችንን ብልጽግና እስከምናረጋግጥበት ከፍታ ድረስ እንድንዘልቅ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
ከእነዚህ መካከል 11ዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወይም መንግሥትን የሚመለከቱ ሲሆኑ 8ቱ ደግሞ ጥሪ የተደረገላቸውን አካላት የሚመለከቱ ናቸው። ይህም የችግሩ ዋና መነሻ የመንግሥት አካሄድ ነውና የመፍትሔው ዋና ቁልፍም በመንግሥት እጅ መሆኑን ያሳያል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃልና ጥሪ 19 ርእሰ ጉዳዮችን የተመለከተ ነው።
፩. የሥልጣን ሽግግሩን አጠቃቀም
፪. የዴሞክራሲ ጥያቄ
፫. የፍትሕ ጥያቄ
፬. የኤርትራን መንግሥት የተመለከተ
፭. ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት
፮. ሙስና
፯. የትምህርት ጥራት
፰. የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ
፱. የኢኮኖሚ ፖሊሲው ማሻሻያ
፲. ለወጣቱ ምቹ የምትሆን ሀገር
፲፩. የሴቶች ተጠቃሚነት
፲፪. ከቦታ ቦታ የመዘዋወርና የመሥራት መብት
፲፫. በተፈጠረው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኪሣራ የተቸገረውን ሕዝብ መካስ
፲፬. የተፈጠረውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኪሣራ የሚያካክስ ሥራ መሥራት
፲፭. ዳያስጶራ
፲፮. የልማት አጋሮች
፲፯. ተፎካካሪ ፓርቲዎች
፲፰. ዘረኝነትና መከፋፈል
፲፱. የሕዳሴው ግድብ ናቸው።

እነዚህን ነገሮች ተግባራዊ አድርጎ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ቁርጠኝነት፣ ቁርጥ ያለ ዕቅድ፣ አካታች የሆነ አካሄድ፣ ሳይዘናጉ መፍጠንና ከአንኳር የሕዝብ አካላት ጋር መወያየትን ይጠይቃል። በተመሳሳይ መንገድ ተጉዞ የተለየ ውጤት ማምጣት አይቻልም። ‹ቃል ይቀድሞ ለነገር› ነውና ይህ ቃል የነገው ተግባር መግቢያ ነው ብለን እናምናለን። በኢትዮጵያ የቅርብ ዘመን ታሪክ እንደታየው ሕዝብ ዕድል ይሰጣል። ሕዝቡ የሰጠውን ዕድል የማይጠቀሙ መሪዎች ሲገጥሙት ግን በአሳቻ ሰዓት እንደተመካከረ ሰው ‹ሆ› ብሎ ይነሣል። ዝምታውን እንደ መሸነፍና ፍርሃት የሚቆጥሩ መሪዎች ዋጋ ከፍለውበታል። የሀገራችን ሊቃውንት ሁለት ዓይነት መብራት አለ ይላሉ። አንዱ ፏ ብሎ የሚበራና መንገዱን ወገግ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ሌላኛው ደግሞ ከሩቁ ሆኖ መድረሻን የሚጠቁም መብራት ነው። የመጀመሪያው ከተገኘ መንገዱን ያለ ዕንቅፋት ለመሄድ፣ በቶሎም ለመድረስ ይመቻል። እርሱ ካልተገኘ ደግሞ ማዶ ተሰቅሎ መድረሻውን የሚጠቁመው መብራት መኖር አለበት። መንገዱን ወገግ አድርጎ ባያሳይም መድረሻውን ያመለክታል። የሚጓዘው ሰው እየወደቀም እየተነሣም ይሄዳል፤ መድረሻውን ያውቀዋልና። በሩቁ ስለሚያየው አይስተውም። ተስፋ አይቆርጥም፣ እንደሚደርስ ርግጠኛ ነውና። ድቅድቅ ጨለማ ግን እንኳን ለሀገር ለግለሰብም አስቸጋሪ ነው።
የዶክተር ዐቢይ መንግሥት ይህ የሕዝብ ድጋፍና ፍቅር እንደ በረዶ ከመቀዝቀዙ በፊት ቢችል መንገዱን ያብራ፣ ባይችል መድረሻውን ያሳይ። ካልሆነ ግን ምናልባት ሌሎቹ ቀደምቶቹ ያገኙትን ዕድል ላያገኘው ይችል ይሆናል። ሰው የሚጠየቀው በተሰጠው መጠን ነውና። አሁን ተግባሩን እንጠብቃለን። ችግሮቹን ሁሉ እንዲፈቱ ሳይሆን መፍታት እንዲጀምሩ፤ ስሕተቶቹን ሁሉ እንዲያርሙ ሳይሆን ማረም እንዲጀምሩ፤ መንገዱን በሙሉ እንዲሠሩ ሳይሆን መሥራት እንዲጀምሩ።

ወቅቱ የትንሣኤ ዋዜማ ነውና እባክዎን ሥራዎትን መፈታት የሚገባቸውን የፖለቲካ እሥረኞች (በተለይም ደግሞ ይህንን የእርስዎን ንግግር ከእሥር ቤት ውጭ እንዲሰሙ ከተፈቱ በኋላ፣ እሥር ቤት ተመልሰው የሰሙትን እነ እስክንድር ነጋን) ና መነኮሳቱን በመፍታት ይጀምሩ። የእርስዎም የሕዝቡም ፋሲካ ድርብ ፋሲካ እንዲሆን።

ይቅናዎት።

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...