ሙዚቃ የየሰው የኑረት እውነት፣ የመስተጋብራችን ቀና ትርክት፣ የጉድለታችን ሙላት፣ የስህተታችን ጥቁምት… ይልቁንም የስክነታችን አብነት ሲሆን የነፍስን ጆሮ ያነቃል – የሥጋን ትፍስህት ያመጥቃል… አንዳንድ ሙዚቃዎች በጆሮ ከመደመጥም በላይ ለዓይን የውበት ቁንጮ፣ ለምላስ የጣዕም ልኬት፣ ለአፍንጫ መልካም መዓዛ የሚፈጥሩ ሆነው አድማጭን ያስደምማሉ… የሃሳብና የስሜት ሞገዶቻችንን እንዳሻቸው ይቆጣጠራሉ…
__
በተቃራኒው የልዩነት ማስተጋቢያ የሆኑ፣ የፍቅር ድርቅ የመታቸው፣ የእውነትም – የውበትም – የሕይወትም መልክ የማይነበብባቸው፣ በሃሳብ ውሃ የማያነሱ፣ በዜማም ከልብ የማይደርሱ ሲሆኑ… የሰሚውን ልዕልና ያዘቅጣሉ – የኑረትን ቀለም ያደበዝዛሉ…
__
፩ – ግዕዝ
__
እውነቱ ከጥንት ጀምሮ ቢታወቅም ድምጽ በማንኛውም አካል /matter/ ላይ ያለው ቀጥተኛ ተጽዕኖ በብዙ አጥኚዎች ዘንድ ልዩ ግምት እየተሰጠው የመጣው አሁን አሁን ነው ማለት ይቻላል… የ Cymatics ሳይንስ እንደሚገልጸው “…When sound waves move thru a physical medium air, water, sand, metallic particles, etc. the frequency of the waves has a direct effect upon the structures which are created by the sound waves as they pass thru that particular medium…”
__
ከአስር በላይ መጻሕፍትን በውሃ ርዕሰ ነገር ላይ የፃፉት ዶ/ር ማሳሮ ኢሞቶ ‘human consciousness has an effect on the molecular structure of water’ የሚል እምነት አላቸው… እኒህ ጃፓናዊ ምሁርና ሌሎች የሩሲያና አሜሪካ ተመራማሪዎች በሰሩት ጥናት ውሃ ‘memory’ እንዳለው ተደርሶበታል… ይህም ማለት ባለፈበት መንገድም ሆነ በተቀመጠበት ቦታ ‘የሚሰማውን’ ድምጽ መዝግቦ የማኖርና የድምጹን በጎነትና ክፋት ተከትሎ መዋቅሩን የመቀየር ተፈጥሮአዊ ጸባይ አለው… በዚህም ምክንያት ውሃውን የሚጠቀመው ሰው ላይ የሚታይ ጉልህ ለውጥ ይኖራል… የተግባቦታችን ስር የሆነው ቃል በተለያየ ሞገድና ቀለም ላይ እንደመገኘቱ የየራሱን አሻራ ውሃው ላይ ይተዋል ማለት ነው… እኛን ጨምሮ ማናቸውም ተዳሳሽ ነገሮች ላይ…
__
ነገሩን በተራ አማርኛ ለማስቀመጥ… በአንዲት መደበኛ የገጠር መንደር አልያም ጸጥታ በሰፈነበት ገዳም ውስጥ የምትጠጣውን የምንጭ ውሃ መርካቶ መሃል ከሚቀርብልህ ውሃ ጋር አንድ ነው ብለህ ማሰብ አይኖርብህም… የመንደሩ ጸጥታም ሆነ የገዳማውያኑ የምስጋናና የተመስጦ ኑረት በውሃውም ሆነ በአካባቢው ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ አለው… ስለዚህ እዚያ ደርሰህ ስክነትን ብትላበስ፣ መንፈስህ ቢረጋጋ፣ ጥሞና ቢከብህ፣ አልያም ውሃውን ጠጥተህ ደዌ ቢላቀቅህ እንዳይገርምህ… የክርስትናውን ‘ጠበል’ እና የእስልምናውን ‘ዘምዘም ውሃ’ እዚህ ላይ ልብ ይሏል…
__
የድምጽ ምንጭ የሆኑት ድግግሞሽ /Frequency/ እና ንዝረት /Vibration/ ያላቸው ምስጢራዊ ኃይል፣ ጆሮ በዙሪያው በሚሰማው ማንኛውም ድምጽ /ሙዚቃ፣ መዝሙር፣ ጫጫታ፣ ንግግር/ ምክንያት የሰው ልጅ በአስተሳሰቡ፣ በአኗኗሩ፣ በጤንነት፣ በማሕበራዊ መስተጋብርና ተግባቦቱ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ እንዲያርፍበት አድርጓል…
__
“…Frequency and Vibration hold a critically important yet hidden power to affect our lives, our health, our society and our world. The science of Cymatics proves that Frequency and Vibration are the master keys and organizational foundation for the creation of all matter and life on this planet. Music has a hidden power to affect our minds, our bodies, our thoughts, and our society…” The 440 Enigma
__
፪ – ካዕብ
__
የአንድ ሙዚቃ ግጥም /ቃል/ በልቡሰ ጥላ /Sub-conscious mind/ ላይ ያለው ተጽዕኖ እንዲሁም ሙዚቃው የተሰራበት የድግግሞሽ /Frequency/ ልኬት /hertz/ በአጠቃላይ አኗኗራችን ላይ የሚያመጣው ጉዳት ከዚህ በመለስ የሚባል አይደለም…
__
በተደጋጋሚ የምንሰማቸው ቃላት ይዘት በአስተሳሰባችን ላይ አዎንታዊና አሉታዊ ውጤት አላቸው… ልቡሰ ጥላ በእውነታና ቅዠት መሃል ያሉ ልዩነቶች አይገቡትም… ፋክትን ከፊክሽን አይለይም… እስካሳመንከው ድረስ ግለቱን በራድ ብሎ ሊጠራ፣ ጨለማውን ብርሃን ብሎ ሊሞግትህ ይችላል… ወደቅሁ፣ ተጠላሁ፣ ተከዳሁ፣ ኑሮ መረረኝ፣ ሰው አገለለኝ፣ አመመኝ፣ … የሚሉ ቃላት ያሉበትን ሙዚቃ /ድምጽ/ እየሰማ ከቆየ በዚያው መሰረት መተግበር ይጀምራል… በአንፃሩ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ መተሳሰብን፣ ማሸነፍን፣ … የሚሰብኩ ቃላትን ከመገብከውም እንደ ቃላቱ ይቃኛል… It is truly the ‘Genie in the bottle’, which grants your wishes according to the ‘commands’ you give it in the ‘intimate conversations you have with yourself ’. እንዲል የልቡሰ ጥላ አዕምሮ ሕግ…
__
የቡድሃ አባባሎችን የሰበሰበው ‘Dhammapada’ የመጀመሪያ ቨርስ ላይ እንዲህ የሚል ገዥ ቃል ሰፍሯል… “All that we are is the result of what we have thought: it is founded on our thoughts; it is made up of our thoughts. If a man speaks or acts with an evil thought, pain follows him, as the wheel follows the foot of the ox that draws the carriage.” እኛ የምናስበው ነገር ውጤት ነን… የሆነውን ሁሉ የሆነው ከአስተሳሰባችን የተነሳ ነው…
__
እናስ… እየሰማህ ያለኸው ነገር ምን ምን ይላል?… በልቡሰ ጥላህ እየተከማቸ ያለውስ መረጃ ምን ዓይነት ነው?… አሁን በዚህ ቅጽበት በውስጥህ እየተመላለሰ ያለው ሃሳብስ ምንድነው?… አካባቢህ ምን እየነገረህ ነው?… አዕምሮህ ምን እያለህ ነው?… ከያኒው ከማጫወቻህ የደገሰልህ ምንድነው?…
__
፫ – ሣልስ
__
የድምጽ ሳይንስ /Cymatics/ ተመራማሪዎች እንደሚነግሩን አንድ ሙዚቃ በ 432 hertz ሲሰራ ሰሚው ከነገረ ፍጥረቱ /Essence/ ጋር የሚስማማበትን አውድ ይፈጥራል… በዚህም ምክንያት ከዙሪያ ገባው ተፈጥሮ ሕብር የሚሰራበትን ጥሞና ያገኛል… የዛፉን ሽውሽውታ የሚተረጉምበትን – የአዕዋፋቱን ጺውጺውታ የሚረዳበትን – የወንዙን አወራረድ ትካዜ የሚጋራበትን ልዕልና ያገኛል… 432 ነፍስን በቋንቋዋ የሚያናግር ስሌት ነው… ከልባችን የምት ሥርዓት አንስቶ እስከ ከዋክብቱ አደራደር /Constellation/ ቀመር የሚዘረጋ ምስጢርም አለው…
__
ጀርመን ውስጥ በዘመነ ናዚ… እ.አ.አ. በ1939 ዓ.ም. የተከሰተውን ታሪካዊ ክፋት ለሙዚቃው ዓለም የጣዕም መበረዝ እንደ መነሻ የሚጠቅሱ ብዙ ናቸው… ከ 1901 ዓ.ም. አካባቢ ጀምሮ በሙዚቃ የብዙሃንን አዕምሮ የመቆጣጠር ዓላማን ያነገቡ ጥቂቶች አሜሪካ ውስጥ ያልተሳካ ውጥናቸውን በናዚ የማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምሩ በወቅቱ የናዚ የፕሮፓጋንዳ ኃላፊ በነበረው Joseph Goebbels ተቀባይነት በማግኘታቸው የሙዚቃው ቅኝት ከ 432 Hz ወደ 440 Hz ተቀየረ… ይህም ወታደሮቹን ለቀጣይ ጥፋት ለማዘጋጀት ጥሩ መነሻ ሆኗል… ይሁን እንጂ ይህ ባዕድ ቅኝት በ 1940 ዎቹ ወደ አሜሪካ ለመሻገርና በ 1953 ደግሞ ISO Standard ላይ ዓለም አቀፍ “Concert Pitch” ለመሆን ጊዜ አልፈጀበትም… ይኸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዓለም በጦርነትና መሰል የጥፋት መንገድ ውስጥ እንደባዘነች አለች ይሉናል ጸሐፍት… L. C. Vincent ስለዚህ ቅኝት ሲጽፍ እንዲህ ብሏል… “This unnatural standard tuning frequency (440 Hz), removed from the symmetry of sacred vibrations and overtones, has declared war on the subconscious mind of Western Man.”
__
እርግጥ ችግሩ ምዕራባውያኑ ላይ ብቻ አልተወሰነም… በሉላዊነት ሰበብ የኛውንም መንደር ጣዕመ-ዜማ የሚበርዝበት ዕድል አግኝቷል… ባሕላዊ መሳሪያዎቻችን ለብዙ ሺህ ዓመታት የኖረውን 432Hz – Cosmic sound /የነፍስያ ቅኝት/ የያዙ ቢሆንም በዘመናዊ መሳሪያዎች ሰበብ እየተውናቸው ስለመጣንና ዘመነኞቹንም ለትክክለኛው ቅኝት ለማስገዛት ስለማንጥር ውዥንብር ውስጥ ገብተናል… “Obviously, the ancient people did not have tuning forks or digital meters and so it is presumed that this frequency of 432 is intuitive, meaning that it somehow sounded right to the human ear.”
__
፬ – ራብዕ
__
ታላቁ ኮንፊሺየስ… “If one should desire to know whether a kingdom is well governed, if its morals are good or bad, the quality of its music will furnish the answer.” ይላል… ማሕበረሰብ በሚሰማው ሙዚቃ ስምረት ከፍ ይላል… በሚሰማው ሙዚቃ ውድቀት ይነጥፋል… የኑረት ስክነቱም ሆነ የመውጣት መግባት ቅኝቱ በጆሮው ምግብ ምንነት ይቀነበባል… ለዚህ ነበር ጥንታውያኑ የቻይና መሪዎች ወደ ሕዝቡ እየወረዱ የማሕበረሰቡን የሙዚቃ ስምረት ያጣሩ የነበረው… ሙዚቃን እንደመዝናኛ ብቻ መረዳት ስህተት ነው ብሎ ያምን የነበረው ግሪካዊው የሂሳብ ሊቅ ፓይታጎረስ በበኩሉ “…a medicine for diseases of the body, the emotions, & the Soul…” ለሚላት ሙዚቃ ብዙ ደክሟል… ማንኛውም ሩሕያውን ከመለኮታዊ ተፈጥሮዋ /Devine nature/ ጋር በሙዚቃ አማካይነት የሚያስማማ ሰው የነፍስያን ስምረት /Soul Adjustments/ ይጎናጸፋል… እንዲሁም ሙዚቃን በአግባቡ እስከተጠቀምንበት ድረስ “…can bring the faculties of the Soul into harmony, compose and purify the mind, heal the physical body, thus restoring & maintaining perfect health…” ይል ነበር…
__
ይህን ነገር ዝም ብለው ካሰቡት ቀላል ይመስላል… ነገሩ ግን የየአዘቦታችን አካል ነው… መሸተኞች በሚሰሙት ሙዚቃ መዳፍ ስር ወድቀው ልካቸውን ሲስቱ፣ አሽከርካሪዎች በከፈቱት ሙዚቃ ፍጥነትና ርጋታ ተቃኝተው መኪናቸውን ሲዘውሩ፣ የውይይት መሰባሰቦች በዙሪያቸው ባለ ድምጽ ተጽዕኖ የረብሻ ምክንያት ሲሆኑ፣ ረጋ ያለ ድምጽ ለመግባባት – ጫጫታ ለግጭት ሰበብ ሲሆን፣ …. ብዙ ጊዜ አይተናል… ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ ድምጾች ለራስምታትና ጭንቀት ምክንያት ሆነው ገጥሞናል… ጠብና ክርክር ያለው ገበያና መጠጥ ቤት እንጂ አስኳላ አይደለም… ግርግርና ሁከት ያለው ከተማ እንጂ ሃገር ቤት አይደለም… ድምጽ ከትራፊክ አደጋ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው… ከተግባቦት ስምረት ጋር… ከሰው ለሰው ግንኙነት ጋር… ከጤንነት ጋር… ከሰላም ጋር… ከፍቅር ጋር… ከመንፈስ ልዕልና ጋር… ወዘተ… እስኪ ከ 1980 ዎቹ አጋማሽ በፊትና በኋላ ያለችውን ኢትዮጵያን ልብ በሉማ… በማሕበራዊ መስተጋብር ዕድገት፣ በሃገራዊ እሳቤዎች አንድነት፣ የራስ ቀለምን በማክበር እውነት… ወዘተ…
__
፭ – ሐምስ
__
ድምጽ ሌሎች ተዓምራትም አሉት… በሚሰሙት ክላሲካል ሙዚቃ የዕድገት ሁኔታቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ ስለታየባቸው አበቦች በተደጋጋሚ ሰምተናል… ላሞችም የሚሰጡት የወተት መጠን ከሰሙት ሙዚቃ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ኖሮት አጥኚዎችን አስገርሟል…
__
ዳዊት በበገና መዝሙር የንጉስ ሳዖልን የሚያስጨንቅ መንፈስ ያስወግድ እንደነበር መጽሐፍ ነግሮናል… ያሬድ በሚያዜመው ዝማሬ ተመስጦ የንጉስ ገ/መስቀል አንካሴ እግሩን ሲወጋው እንዳልታወቀው አንብበናል… እስራኤላውያን በሕብረ ዝማሬ የኢያሪኮን ቅጥር ስለማፍረሳቸው ተነግሮናል… ወዘተ…
__
ድምጽ በእርግብግቢታዊ ኑረቱ /Vibration state/ ይታወቃል… ለነገሩ እኛን ጨምሮ በዙሪያችን ያለ ማንኛውም ነገር /Matter/ በእንቅስቃሴ ውስጥ /State of motion/ ነው ያለው… ስሪቱ ከአተም ነውና… አተም እረፍት አያውቀውም… እናም ሁሉም ነገር ድምጽ ነው ማለት ልንል እንችላለን… ‘በመጀመሪያ ቃል ነበረ…’ እንዲል… እናም እያንዳንዱ ድምጽ የራሱ የሆነ የእርግብግቢት ድግግሞሽ አለው… ይህንንም ሳይንሱ በኸርዝ ይለካዋል… እኔና አንተ ስናወራ አልያም አንድ ድምጽ ስንሰማ ስምረቱ የሚፈለቀቀው ከሞገዱ ተፈጥሮ ነው… ይህም ማለት ሞገድህ ከሞገዴ ሲሰምር ነው ተግባቦቱ የሚሰምረው… ‘እኔና አንተ በአንድ ዓይነት ሞገድ ላይ አይደለንም’ የሚለው የአሜሪካውያኑ የንግግር ዘዬ ይህንኑ ነው የሚነግረን… ጥቁር አሜሪካውያንና ነጭ ፖሊሶች ሳይግባቡ እየቀሩ ጠብመንጃ የሚማዘዙት በተለያያ ሞገድ ስለሚያወሩ ነው… መንግስትና ሕዝብ የማይግባቡት በተለያየ ቅኝት /Tuning/ ስለሚነጋገሩ ነው…
__
በቀላል ምሳሌ አንድን ቆርቆሮ በወጉ እየጠበጠብክ የሙዚቃ ቅኝት ውስጥ ልታስገባው የመቻልህን ያህል በወለል ላይ እየጎተትከው ‘ሲጢጥ’ በማድረግ ለጆሮ የሚቀፍ ድምጽ እንዲያወጣ ልታደርግ ትችላለህ… በዚህ ሁኔታ ተጽዕኖ ያሳረፍከው በእርግብግቢት ልኬቱ ላይ ነው… ጆሮህ ትርጉም ሊሰጠው ከሚችለው የእርግብግቢት ልክ የሚያልፍ የትኛውም ድምጽ ደግሞ መንፈስህን ይረብሸዋል… አውቶብስ ተራ ሄደህ ከወያላ ጋር አውርተህ የማትግባባው በተለያየ ሞገድ ላይ ስለምትገኝ ነው… የእግርኳስ ደጋፊዎች ድምጽ ከበጠበጠህ፣ የመጠጥ ቤት ጩኸት ካስበረገገህ ሞገድህ ለዚያ አልተቃኘም ማለት ነው… ጮክ ብሎ ከሚያወራ ሰው ጋር የማትግባባው በሃሳብ ስለተለያየህ ብቻ አይደለም… ተመሳሳይ ነገርን በተለያየ ድምጸት ስለምታወሩ እንጂ…
__
፮ – ሳድስ
__
ስለ ስምረት ስናነሳ የአሜሪካው የጠፈር ሳይንስ ኤጀንሲ /ናሳ/ የኛ ሕዋ ላይ የሚገኙት ፕላኔቶች በራሳቸው ዛቢያ ሲሽከረከሩ የሚያሰሙትን ድምጽ ለመቅዳት ሞክሮ ያገኛቸው ድምጾች እጅግ አስገርመዋል… በተለይ የምድራችን ድምጽና የወፍ ድምጽ መመሳሰል አስደማሚ ነው… የአዕዋፋት የማለዳ ዝማሬ ዓይነት… ወፊቱ ለካንስ የምድር ቋንቋ ገብቷት ነው በራሷ ድምጽ አዋርታ ቀለብ በብላሽ የምታሰፍራት?… ለካንስ ኢየሱስ ‘የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ.. አይዘሩም፣ አያጭዱም…’ ማለቱ ወዲህ ነውና?…
__
ይህንን ሁሉ ይዘን አሁን አሁን የምንሰማቸውን ሙዚቃዎች ስንገመግም እንኳንስ ከነፍሳችን ታዛ ዘልቀው ሊደመጡና እዝነ-ልቡናችንን ሊመስጡ… የጆሮዋችንን ቀልብ የመሳብ አቅም ያላቸው እንኳ ከስንት አንድ ሆነው እናገኛቸዋለን… ብዙዎቹ ጩኸት ይበዛቸዋል… ሰው ሰው አይሸቱም… ሕይወትን አይወክሉም… ተፈጥሮን አይተርኩም… ከልብ አይዋሃዱም… ለስክነት አይዋጁም…
__
ይባስ ብሎ ዘመነኞቹ ሙዚቃዎች አንዳች ቅኝት ውስጥ እያስገቡን በመምጣታቸው ምክንያት መለኪያ /Standard/ የማበጀት ተፈጥሮአዊ ዝንባሌያችንን ተጭነውታል፣ የምርጫ /Preference/ ዝማሜያችንን /Instinct/ ነጥቀውናል… በተለይ ሚዲያው እርሱ የመረጠልህን እንጂ አንተ የምትመርጠውን የማትሰማበት የመሆኑ እውነት ነገሩን አባብሶታል… አሁን እኮ ተፈጥሮን በቋንቋዋ እያወራናት አይደለም… ነፍስያችን ልትሰማ የምትወደውና እኛ የምናሰማት ነገር ፈጽሞ አልተገናኘም… እናም በኑሮአችን ደስታ የለንም፣ በቤታችን ሰላም የለንም፣ በቅቶን አያውቅም፣ ስቀን አናውቅም፣ ስክነት ይናፍቀናል፣ ፍቅር ይርበናል፣ ሌማት ያጥጥብናል፣ ማድጋ ይነጥፍብናል፣ አብሮነት ኮስሶብናል…
__
፯ – ሳብዕ
__
የዓለማችን ምርጡ የፈጠራ ሰው Nikola Tesla እንዲህ ብሎ ነበር… “If you want to find the secrets of the universe, think in terms of energy, frequency and vibration.” እዚህ ቃል ውስጥ ብዙዎቹ የምድራችን እንቆቅልሾች ተሸጉጠዋል… የኒህ ሦስት ነገሮች መሰረታዊ ግንዛቤ ያለው ሰው የዩኒቨርሱን ምስጢር ለመረዳት ቅርብ ይሆናል…
__
የዘፈን ደራሲዎቻችን ይህ ገብቷቸው ሙዚቃዎቻቸውን ይሰሩልን ዘንድ እንመኛለን… በተለይ ፓይታጎረስ በሂሳባዊ ቀመር ያስቀመጠውን ነፍስን የሚያነጋግር የተባለለትን ቅኝት ያንቆረቁሩልን ዘንድ እንመኛለን…
____
[የምትሰማውን ሙዚቃ ንገረኝና ማን እንደሆንክ እነግርሃለሁ]
መልካም አሁን ውዶቼ
[Re_po]
2 Comments
ጥሩ እይታ
በጣም ተምሬበታለሁ፤በነገሮች ላይ የነበረኝን ዕይታና ግንዛቤዬን አዳብሮልኛልና ምስጋና ይገባቸዋል።