Tidarfelagi.com

Butterfly Effect

ተተንባይ ኑረት የሌላቸውን ሁነቶች የሚተነትነው ሒሳባዊ ንድፈ-ሃሳብ Chaos Theory ይባላል… ትወራው በዚህ ስም ከመጠራቱ በፊት መገለጫ ባሕሪያቱን ለመተንተን የመጀመሪያ ነው የሚባልለት የሒሳብ ሊቅ Henri Poincaré ይባላል… ፈረንሳዊ ነው… “It may happen that small differences in the initial conditions produce very great ones in the final phenomena. A small error in the former will produce an enormous error in the latter. Prediction becomes impossible.” ብሎ ነበር… ‘ከጅማሬ ላይ የሚታዩ ጥቃቅን ለውጦች በፍፃሜው ሁነት ላይ ትላልቅ ክስተቶችን ሊፈጥሩ ይችላሉ… የጅማሬ ድቃቂ እንከን ከወደ ፍፃሜዋ ከመርግ የገዘፈ ችግር ልትወልድ ትችላለች… መዳረሻውን ፈጽሞ መገመት አይቻልም’… ይህ ንግግር የትወራው መሰረታዊ ማጠንጠኛ ነው…
~~
ቲዎሪው አሁን አሁን ከንድፈ ሃሳብነት ዘሎ ተተግባሪ ሳይንስ እየሆነ መጥቷል… በተለይም በትላልቅ የ Stock ገበያዎች፣ የኢኮኖሚ መግለጫዎች፣ የፔንዱለም እንቅስቃሴ፣ የአየር ሁኔታ ትንበያና ሶላር ሲስተም ውስጥ ሳይቀር የትንታኔ ማሳለጫ ሆኖ ያገለግላል… Edward Lorenz የተባለ ሜትሮሎጂስት በ1960ዎቹ በሰራው ሒሳባዊ ቀመር አማካይነት ውስብስብ መዋቅሮች /chaotic systems/ ለመነሻ ሁነት ስሱ መሆናቸውን ማሳየት ችሏል… በዚህ ሞዴሉ መነሻነት የጠየቃት አንዲት ጥያቄ ታዲያ የትወራው ገናን ምሳሌ ሆና ዛሬም ድረስ ትነሳለች… “Does the flap of a butterfly’s wings in Brazil set off a tornado in Texas?”… ‘ብራዚል ውስጥ ሽር ትር በምትል ቢራቢሮ ሰበብ ቴክሳስ ውስጥ ቶርኔዶ ይፈጠር ይሆን?’ እንደማለት… ሌላ ጸሐፊ ደግሞ እንዲህ ብሏል… “A butterfly flaps its wings in the Amazonian jungle, and subsequently a storm ravages half of Europe.” ― Neil Gaiman
~~
ኑረታችን በመሰል ትርክት ውስጥ የሚያልፉ በርካታ መልኮች አሉት… በድቃቂ ስሁት መነሾ ከቋጥኝ የገዘፈ ውድመት ሲፈጠር አይተናል… ብናኝ ቅንነት እልፍ ቀዳዳ ደፍኖም አስተውለናል… የግለሰቦች መዓዛ ሃገር አውዶ አይተናል… የክፋታቸው ጭቅቅት ድሪቶ አልብሶ ገጥሞናል… የውስጣችን የሃሳብ ተብሰልስሎትም ሆነ የቃል ንግግራችን ይዘት፣ የሰርክ መስተጋብራችንም ሆነ የክት ተግባራችን ቅኝት… የየራሱን ውጤት አዝሎ ይመጣል…
“Small shifts in your thinking, and small changes in your energy, can lead to massive alterations of your end result.” ― Kevin Michel
~
የሃሳብ ተብሰልስሎት የተግባር ፊት እስካላየው ድረስ የበጎነት ማሩም ሆነ የክፋት ምሬቱ የማይገለጽ የሚመስለን ብዙ ነን… ነገሩ ግን ወዲህ ነው… ሃሳብ በውስጣችን በሚመላለስበት ቅጽበት የራሱን ኑባሬ ይፈጥራል… ኑባሬው ሞገዳዊ ነው… ከየልቦቻችን ጣቢያ የሚሰራጨው የ thought, emotion, feeling እና intention ሞገድ እንደየቀለሙ በዙሪያችን ያለውን የ Energy field ይቀላቀላል… ከፍቶ የኑረትን መልክ የማጠልሸቱም ሆነ ቆንጅቶ ፊቱን የማፍካቱ እውነት ከቀለሙ ተፈጥሮ ይመነጫል… በጎ ሃሳብ በውስጣችን በሚመላለስበት ቅጽበት የበጎነት ሞገድ የኢነርጂ ውቅያኖሱን ይቀላቀላል… ክፉ ስናስብም እንዲሁ ነው… እንደ እውነቱ ከሆነ እያንዳንዳችን በእያንዳንዷ ቅጽበት ወደ ሕዋው ቀለማችንን የምንሰድ broadcaster ነን… እንዳሰራጨነው ስሜት ዝማሜ ግብረ መልሳችን ይቃኛል…
“The only simple truth is that there is nothing simple in this complex universe. Everything relates. Everything connects” ― Johnny Rich
~
የምድር ግዙፍ ክስተቶች የደቂቅ ጅምር ጦስ ናቸው… የዛሬ እኩይ ሁነቶች የትናንት ዱካ ውልዶች ናቸው… የክብሪት ብልጭታ ውድመት ስንጥርነቷን ያስረሳል… የጠብታዎች አመሻሽ ቋጥኝ ከስሩ ይነቅላል… አንኳር ጨው ሟሙቶ ሲያበቃ የሰታቴ ወጥ ይሞላል…
~
የዓለም አንድ ጥግ የካርቦን ልቀት በምድር ሌላ ጎን የሙቀት ልኬት ያጠፋል… ያላግባብ የቆረጡት ዛፍ የሃሩር ንዳድ ይጠራል… የግግር በረዶ መቅለጥ የጎርፍ አበላ ያወርዳል…
ውዳቂ የትምህርት ስርዓት ድንዙዝ ትውልድ ያፈራል… አርአያነት ያለው መምህር ዓላማ ያለው ተማሪ ይቀርፃል… ራዕይ የሌለው መሪ ሃገር መቅኖ ያሳጣል… ወንበሩ የተቀመጠበት አለቃ አድሮ እንደ ጠላ ይሻግታል… ለትውልድ የሚያስብ ስብዕና ከርሞ እንደ ወይን ይጣፍጣል… Albert Einstein “A new type of thinking is essential if mankind is to survive and move toward higher levels” ማለቱም ለዚሁ ነው…
~
አሜሪካ ሔሮሺማና ናጋሳኪ ላይ ከ 70 ዓመት በፊት የጣለችው አቶሚክ ቦንብ በጊዜው ለእልፎች ህልፈት ምክንያት ሲሆን ዛሬ ለመቶዎች የአካል ጉድለት ሰበብነቱ ቀጥሏል… እንግሊዝ ሕንድና ፓኪስታንን ለመነጠል የዘራችው ክፉ መርዝ ትናንት ለመለያየት ዛሬ ለጠላትነት ምክንያት መሆኑ ቀጥሏል… እስራኤልና ፍልስጤም፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ፣ ሰሜንና ደቡብ ሱዳን፣ ደቡብ አፍሪካ ነጭና ጥቁሮች፣ ሩዋንዳ ሁቱና ቱትሲ፣ ደቡብ ኮሪያና ሰሜን ኮሪያ፣ ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ የመን… ወዘተ የትናንት አባዜ የሚያናውዛቸው ሕዝቦች ናቸው…
~
“For the want of a nail the shoe was lost,
For the want of a shoe the horse was lost,
For the want of a horse the rider was lost,
For the want of a rider the battle was lost,
For the want of a battle the kingdom was lost,
And all for the want of a horseshoe-nail.”
― Benjamin Franklin

~
የአያቶቻችን የአስተዳደግ ዘዬ ነው አባቶቻችንን የወለደው… የአባቶች የወላጅነት ቅኝት ነው እኔና አንተን ያዋጣው… የየትውልዱ መልክ እያንዳንዱን ቤት ይመስላል… ጥብቅ መሰረት የሕንፃ ደጀን ይሆናል… የአሸዋ ላይ ቤት ንፋስ ባይኖርም ይወድቃል… ትውልድ ሲሰምር ቅን መሪ ውስጡ ይበቅላል… ትውልድ ሲከሽፍ በቅንቅን እብሪት ይታሻል…
~
“Now, there is one thing you might have noticed I don’t complain about: politicians. Everybody complains about politicians. Everybody says they suck. Well, where do people think these politicians come from? They don’t fall out of the sky. They don’t pass through a membrane from another reality… it’s what our system produces: Garbage in Garbage out. If you have selfish, ignorant citizens you’re going to get selfish & ignorant leaders…” ~ George Carlin
~
በሬ ሰርቆ ሲታሰር የደረሰበት እንግልት ሆድ ሆዷን የበላት እናት ስቅስቅ ብላ ማልቀሷን ልጅ ተመለከተና እንዲህ አላት… “በእንቁላሉ ጊዜ ገርፈሽኝ ቢሆን ኖሮ…” ዛሬም ቢሆን በእንቁላል ደረጃ እያለ በአግባቡ ልናርቀው የሚገባን ማሕበረሰባዊ እንከናችን ብዙ ነው… ‘እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል’ በሚሉት ‘አህያዊ’ ዘዬ የዛሬ ጉዳያችንን ስላሳካ ብቻ የምንናገረው ቃል፣ የምንወስነው ውሳኔ፣ የምንዘራው ጥላቻ፣ የምናቆመው ሐውልት፣ የምናፈርሰው ምልክት፣ የምንጽፈው ክታብ፣ የምናበጀው ገደብ፣ የምንቆፍረው ጉድጓድ… ዛሬ ላይ ድቃቂ ቢመስልም ነገ ቀን ቆጥሮ ጥንቡሳሱ ይከሰታል… “The Wrong we have Done, Thought, or Intended Will wreak its Vengeance on Our SOULS.” ― C.G. Jung
~
“የጨው ገደል ሲናድ ብልህ ያለቅሳል – ሞኝ ይስቃል”…
~
በአንዳንድ ቀውጢ ጊዜያት ቢራቢሮዋ የተርገበገበችበትን የመነሻ ዱካ አስሳለሁ… የእንቁላሉን ጊዜ… እቶኑን ልንቆጣጠር እንችል የነበረበትን ጊዜ… አርቆ ማሰብ ያጣንበትን ጊዜ… ወደኋላ የምንደረደረው ግን ወደፊት ለመስፈንጠር እንጂ ተሰፍቼ ለመቅረት አይደለም… የመፍትሔውን ቁልፍ ለማንበር እንጂ የቁርሾ መርዝ ለመቀመም አይደለም… የትኛውም የዛሬ ችግር ከውይይት እንዳይልቅ አውቃለሁ… የአንዳንድ ጊዜ ‘መላችን’ ግን “ዓላማችን እውነት ችግሩን ማጥፋት ነው ወይስ ማስፋት?” ያሰኘኛል…
~
እሳት ለማቀጣጠል ቤንዚን መድፋት ይቻላል… ፈጥኖ እንዳይጠፋ ፍልጥ መከመርም ቀላል ነው… ዳር እስከ ዳር እንዲግለብለብ ትንፋሽ ማዋጣትም አይቸግርም… ለወቅት ሕመም ከርሞ ቁስል የማይሆን ስራይ መፈለግ ግን አዋቂነትን ይጠይቃል… የዛሬ ጥንስስ ቁርሾ የነግ ጥላቻ እርሾ እንዳይሆን መስራት ግን ብልህነትን ይሻል… ከኢጎ ነጽቶ መፍትሔ መሻት ከአፍንጫ ደፍ አርቆ ማሰብን ይፈልጋል… “Problems cannot be solved at the same level of awareness that created them.” – Albert Einstein
~
“…ግፍ፣ ቀን ቆጥሮ ይፈርዳል፣
አጉል ጀብድ፣ ሲያድር ያቅራል
የዛሬ ቢራቢሮ ሕሊና – ነገ አባጨጓሬ ይወልዳል፣
ከሳማ ይልቅ ለብልቦ – ከአጋም ደድሮ ይወጋል፣
ቅስም በሃፍረት ሸብቦ – ናላ በፀፀት ያደማል፡፡
እንጂ ቢሸሹት መች ይሸሻል?
ቢተውት መች ይተዋል?
ቢገሉት መች ይሞታል?…”
(ጌትነት እንየው)
~
እነሆ ውብ መስመር…
~
“To put the world in order, we must first put the nation in order; to put the nation in order, we must put the family in order; to put the family in order, we must cultivate our personal life; and to cultivate our personal life, we must first set our hearts right.” –Confucius
~
ፍቅርን ከመስጠት በላይ ዕዳ አይኑርባችሁ!!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...