ክፍል አስር፡ በ“ጨለማው መስከረም” ዋዜማ
ዮርዳኖስ የፍልስጥኤም ታጋዮች በ1968 እና በ1969 ያካሄዷቸውን ጠለፋዎች “አስደናቂ ጀግንነት ነው” በማለት ካወደሱት ሀገራት አንዷ ነበረች። ከዓመት በኋላ የPFLP አባላትና ደጋፊዎች ሶስት አውሮፕላኖችን ጠልፈው ወደ ግዛቷ ሲያመጡ ግን በጣም ነበር የተቆጣችው። የግንባሩ መሪዎች በግዛቷ የነበሩትን ተዋጊዎችና ንብረቶቻቸውን በአስቸኳይ እንዲያስወጡላትም ትእዛዝ አስተላለፈች። ዮርዳኖስ በዚህ ሳታቆም በያሲር አረፋት የሚመራው “ፋታሕ”ም በተመሳሳይ ሁኔታ ግዛቷን ለቆ እንዲወጣ አዘዘች። ከመስከረም 20/ 1970 ጀምሮ የታጠቀ ፍልስጥኤማዊ ግለሰብና ቡድን በግዛቷ መንቀሳቀስ እንደማይችልም አወጀች።
የዮርዳኖስ አዋጅ ለPFLP እና ለሌሎች የፍልስጥኤም ተዋጊ ቡድኖች ዱብ እዳ ነው የሆነው። “በ1967ቱ ጦርነት ያሸነፈችንን እስራኤልን በእጅ አዙር እንበቀላታለን” በማለት ጆርጅ ሐበሽ እና ያሲር አረፋት ባሹት ስፍራ የጦር ሰፈራቸውን መሥርተው እንዲንቀሳቀሱ የጠሯቸው ንጉሥ ሑሴን ራሳቸው ነበሩ። ከ1967-1970 በነበሩት ዓመታትም ሀገሪቱ ለድርጅቶቹ ከፍተኛ የሆነ የሎጂስቲክስ ድጋፍ ታደርግ ነበር። ከሁለቱ ታላላቅ ድርጅቶች በተጨማሪ ለፍልስጥኤም ነፃነት እታገላለሁ የሚሉ ሌሎች ቡድኖችን በሙሉ ትደግፍ ነበር። የአራቱ አውሮፕላኖች እገታ ድራማ እንዳበቃ በድንገት ተነስታ “ከግዛቴ ውጡልኝ” ማለቷ ግን ግራ ነው የሆነባቸው። በጠለፋው ተሳትፎ ያልነበራቸው ፋታሕን የመሳሰሉ ድርጅቶችም ውጡ መባላቸው በጣም ነበር የደነቃቸው።
በወቅቱ የነበሩት የፍልስጥኤም ድርጅቶች ሁሉ በጋራ ምክር ቤታቸው ተሰባስበው በጉዳዩ ላይ ከመከሩ በኋላ የPFLP መሪዎች ለወደፊቱ ታጋዮቻቸውን አሰማርተው የአውሮፕላን ጠለፋዎችን እንዳያካሄዱ አስጠነቀቋቸው። የምክክሩ ውጤትም ለዮርዳኖሱ ንጉሥ ሑሴን ተገለጸ። ይሁን እንጂ ዮርዳኖሱ ንጉስ ሑሴን ፍልስጥኤማያዊያኑ ድርጅቶች ከግዛቴ ይውጡልኝ የሚለውን ትእዛዝ ሊያጥፉት አልቻሉም። በሳምንት ጊዜ ውስጥ ከዮርዳኖስ እንዲወጡም አሳሰቡ። ሌሎች የዐረብ ሀገራት በጉዳዩ ውስጥ ገብተው ለመሸምገል ያደረጉት ጥረትም ከሸፈ።
——
የንጉሥ ሑሴን ትእዛዝ ከምን የመነጨ ነው? የታሪክ ምሁራን የንጉሡ ውሳኔ ብዙ መነሾዎች እንደነበረው ጽፈዋል። ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።
ዮርዳኖስ ነፃነቷን የተጎናጸፈችው በእንግሊዞች እርዳታ ነው። ከነፃነቷ ማግስት ጀምሮም ከእንግሊዞችና ከሌሎች ምዕራባዊያን ጋር ሞቅ ያለ ግንኙነት ነበራት። ሀገሪቷ ለግብይትም ሆነ ለጦር መሳሪያ ሸመታ የምትመካው በምዕራባዊያን ላይ ነው። በመሆኑም ምዕራባዊያኑን ላለማስከፋት ትጠነቀቅ ነበር። በዚህም መሠረት አውሮፕላኖቹ ተጠልፈው ወደ ግዛቷ በመጡበት ወቅት እንግሊዝና አሜሪካ ፍልስጥኤማዊያን ድርጅቶችን እንድታባርር በድብቅ ሲጠይቋት ፍላጎታቸውን ለማሟላት ወስናለች።
በሁለተኛ ደረጃ ዮርዳኖስ በፍልስጥኤም ላይ የምታራምደው ድብቅ አጀንዳ ነበራት። ፍልስጥኤም በ1948 ከተወረረች በኋላ በእስራኤል ያልተያዘው ምዕራባዊ ዳርቻ (West Bank) በጊዜያዊነት በዮርዳኖስ ስር ነበር የቆየው። ይህም የተደረገው ፍልስጥኤማዊያን ተደራጅተው የራሳቸውን መንግሥት እስኪመሠርቱ ድረስ ነበር። ይሁንና ዮርዳኖስ ግዛቱን ለምንጊዜውም በራሷ ስር የማቆየት ፍላጎት ነበራት። በ1967 በተደረገው የስድስቱ ቀን ጦርነት ምዕራባዊውን ዳርቻ ከተቀማች በኋላም ይህንን ፍላጎት አልቀየረችውም። በዚህ የተነሳ የዐረብ ሊግ በ1968 ባደረገው አስቸኳይ ጉባኤ “PLO የፍልስጥኤም ህዝብ ብቸኛ ወኪል ነው” በማለት በድጋሚ ውሳኔ ያስተላለፈውንም ውሳኔ ተቃውማለች። ታዲያ ፍልስጥኤማዊያን ድርጅቶች ጠንክረው ለነፃነታቸው መዋጋታቸው ልትፈጽመው ያቀደችውን ድብቅ አጀንዳ የሚያከሽፍባት ሆኖ ነበር የታያት። ስለዚህም ድርጅቶቹን ከግዛቷ ለማስወጣት ወስናለች።
ንጉሥ ሑሴን የፍልስጥኤም ድርጅቶችን ቀስ በቀስ ለማስወጣት ነበር የፈለጉት። ንጉሡ ድርጅቶቹን የሚያባርሩበትን ጊዜ በማማረጥ ላይ ሳሉ እርሳቸው ያልጠበቁት ግፊት ከራሳቸው ባለስልጣኖችና የጦር መሪዎች ተፈጠረባቸው። የሲቪል ባለስልጣኖችና ወታደራዊ መኮንኖች ንጉሡ ፍልስጥኤማዊያን ድርጅቶችን በቶሎ እንዲያባርሩ የገፋፏቸው ድርጅቶቹ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የውጊያ አቅም መፍጠራቸው ስላሳሰባቸው ነበር።
በታሪክ እንደሚታወቀው የዐረብ ሀገራት ከእስራኤል ጋር ባደረጓቸው ሶስት ጦርነቶች (በ1948፣ በ1956 እና በ1967) ተሸንፈው ነበር። በዚህም የተነሳ እስራኤልን ፊት ለፊት ከመግጠም ተቆጥበዋል። ይሁንና በያሲር አራፋት የሚመራው “ፋታሕ” በ1968 ሊያጠፋው የዘመተበትን የእስራኤል ጦር ኃይል በከራማ ሸለቆ መክቶ ሲመልስ በዐረቡ ዓለም ከፍተኛ አድናቆት አግኝቶ ነበር። የPLO ተዋጊዎች በዚያ ድል ተነቃቅተው ለቀጣይ ጥቃቶች በመዘጋጀት ላይ እያሉ PFLP በርካታ አውሮፕላኖችን እየጠለፈ በመውሰድ የምዕራብ ሀገራት ፍላጎቱን እንዲፈጽሙለት ለማድረግ መቻሉ ፍልስጥኤማዊያን በዝና ላይ ዝና እንዲቀዳጁ ነው ያደረገው (በነገራችን ላይ የግብፅ ጦር በ1973 የእስራኤልን ጦር ወግቶ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስበት የቻለው የፍልስጥኤማዊያኑ ጀግንነት የሞራል ስንቅ ስለሆነው ነው)።
ይሁን እንጂ ፍልስጥኤማዊያን የተቀዳጁት ዝና በወቅቱ በስልጣን ላይ የነበሩትን የዮርዳኖስ ጠቅላይ ሚኒስትርን እና የጦሩን መሪዎች ክፉኛ ነበር ያስደነገጣቸው። “የአመራር ብቃት የላቸውም” ተብለው ከስልጣን በተባረሩት አሕመድ ሹቀሪ ምትክ የፍልስጥኤም ነፃ አውጪ ድርጅት ሊቀመንበር ሆኖ የተመረጠው ትንታጉ ታጋይ ያሲር አረፋት እንደ ቀድሞው ሊቀመንበር ለየትኛውም የውጪ አካል የማይታዘዝ ሆኖ መገኘቱም የዮርዳኖስ መሪዎችን ከፍተኛ ስጋት ላይ ጥሎአቸዋል። በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የጦር መሪዎቹ ወደ ንጉሥ ሑሴን ዘንድ በመሄድ “ፍልስጥኤማዊያን ድርጅቶችን ከሀገራችን ካላስወጣናቸው ከአጭር ጊዜ በኋላ መንግሥታችንን መገልበጣቸው አይቀርም” በማለት ወተወቷቸው። ንጉሡም የባለስልጣናቱ ስጋት ስለተጋባባቸው በረጅም ጊዜ ሊፈጽሙት ያቀዱትን ተግባር በዚያው ሳምንት ውስጥ ሊከውኑት ተነሱ።
—-
አፈንዲ ሙተቂ
ታሕሳስ 13/2010
በሸገር ተጻፈ።
One Comment