Tidarfelagi.com

የቀበሌ 01 የመጨረሻዋ ድንግል እንደምን አረገዘች!?

(በመጀመሪያ ከላይ የተጠቀሰውን ርእስ ከሁለት ታላላቅ ደራሲዎች የተዋስኩት እንደሆነ ለመግለጽ እፈልጋለሁ።”የቀበሌ 01 የመጨረሻዋ ድንግል” የሚለውን ሀረግ ከአዳም ረታ መጽሃፍ የተዋስኩት ሲሆን “እንደምን” የሚለውን ቃል ደግሞ “ጃፓን እንደምን ሰለጠነች?” ከሚለው የከበደ ሚካኤል መጽሃፍ የወሰድኩት ነው።”አረገዘች” የሚለው ቃል እና የጥያቄ ምልክቱ(?) ግን ሙሉ በሙሉ የራሴ ፈጠራዎች ናቸው።)
እሺ ሰላም ናችሁ ጋይስ?….ምን ሰላም አለና?!……መቼም ይሄ ጽሁፍ ሰሞኑን በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ስላለው የፖለቲካ ውጥረት እንደሚሆን የሚጠበቅ ቢሆንም ጸሃፊው ግን ስለ አንዲት የቀበሌ 01 ልጅ የእርግዝና መንስኤ መወያየትን መርጧል።

ማክዳ የቀበሌ 01 ልጅ ነች። በ16 አመቷ የሰፈሩ ወንድ ሁሉ የአይን ማረፊያ ሆነች።….ቆይ አንዴ ይህ ታሪክ ከመቀጠሉ በፊት አንድ ነገር ልበል…..በነገራችን ላይ በኦሮሚያ ክልል እና በ”ዲሞክራቲከ ሪፐብሊክ ኦፍ ሶማሊያ” መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት በጊዜ እልባት ካላገኘ ወደ አስከፊ ሁኔታ ሊያመራ እንደሚችል ለመናገር የፖለቲካ ምሁር መሆን አያሻም።የመከላከያ ሰራዊታችን ምንግዜም በአፍሪካ ውስጥ የሰላም ማስከበር ሚናውን ለመወጣት እንደሚያደርገው በሩዋንዳ፡ ላይቤሪያ፡ ብሩንዲ ወዘተ እንዳደረገው ሁሉ ማለት ነው በእነዚህ ሁለት “ሀገራት” መካከል በመግባት ሰላማዊ ህዝብ እንዳይጎዳ የበኩሉን ጥረት ሊያደርግ ይገባል ባይ ነኝ።

እና ማክዳ የደሃ ልጅ ነች። ደካማ አያቷ የሚያሳድጓት ክፉ እና ደጉን ጠጋ ብሎ የሚመክራት የሌላት ለመቀጠፍ ደረሰች ውብ የሰፈራችን ኮረዳ……
ሌላ በነገራችን ላይ ……የሶማሊያን(ሶማሌ ክልል ለማለት ስለሚከብደኝ ነው) ነገር ልብ ብሎ ላስተዋለ እንደው አየር ሃይል የላትም እንጂ ሀገር ለመሆን ትንሽ የቀራት ነው የሚመስለው ። ወይ መካሪ ማጣት!..የሶማሊያ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ነኝ ያለው ግለሰብ የጻፈውን (“የለደፈውን” ማለት ይቀላል) መግለጫ ስታነቡ በመግለጫው ሰውዬው የተጠቀማቸው ቃላት እጅግ የወረዱ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ…..የሰውየው የድፍረት ቃላትና ድምዳሜዎች እንኳንስ በአንድ ማእከላዊ መንግስት ስር ያለ የክልል ሃላፊ በአጎራባች ክልል ሀላፊ ላይ ሊጠቀማቸው ይቅርና በፍንዳታው ዶጮ የምትመራው የሰሜን ኮሪያ ቃል አቀባይ እንኳን ደፍሮ በጠላት ሀገር(ያው አሜሪካ ላይ) ላይ ይጠቀማቸዋል ብላችሁ አታስቡም።አቶ አዲሱ አረጋ ለዚህ የወረደ መግለጫ የሰጡት መልስ ” እውነትም የተማረ ይግደለኝ የሚያስብል” ነው….ጀለሴ ለነገሩ ድሮም አመለ ሸጋ ነበረች(ከአስራ ምናምን አመት በፊት ክላስሜትና ጓደኞች ነበርን)……
ምናልባትም ኦቨር ምርቃና ፡ወይ ደግሞ ወገኖቹ በድንገት ሲሞቱ የተፈጠረ ስሜታዊነት… ምናምን የሚሉ መላምቶችን ወደ ጎን አድርገን የዚህ ሰውዬ ድፍረት ማለትም በቅርቡ ሚኒስትር ዲኤታ የነበሩትንና አሁን ደግሞ የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ሃላፊ የሆኑን ሰው በቀጥታ “አሸባሪ” ናቸው የማለት ድፍረት ከየት የመጣ ነው የሚለውን እንመልከት….በዛውም የግጭቱን መንስኤ እና መፍትሄ አብረን እንመርምር……

ወደ ዋናው ታሪካችን ስንመለስ….ማክዳ በተደጋጋሚ የሰፋራችን ጉልቤ ከሆነው አርከበ ጋር መታየት ጀመረች።አርከበ ሰፈር ውስጥ የቪዲዮ ማከራያ ሱቅ አለው….ሱቋ በተለምዶ “አርከበ ሱቅ” የምትባለዋ አይነት ስትሆን በእኛ ሰፈር ደግሞ ሊትራሊ የአርከበ ሱቅ ነች።በነገራችን ላይ እኛ ሰፈር የአብዛኛው ነገር ስም በቀጥታ የሚገናኝ ነው …በሰፈራችን ያለችው አንድ ዲዔክስ መኪና የአርከበ አባት መኪና ስትሆን እኛ የምንላት “ወያኔ ዲኤክስ” ነው ……እሳቸውም “ወያኔ” ናቸው መኪናቸውም “ወያኔ ዲኤክስ” ናት።

አርከበ ይሄ ነው የሚባል ገንዘብ ባይኖረውም ለችስታዋ ማክዳ ግን “ኤፈርት” እንደማለት ነው።አንዳንዶች ዋናው ገቢው ዶላር ከመዘርዘር የመነጨ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ በመንግስት ጆሮነት ይጠረጥሩታል….…ለነገሩ የእነ በርክ ላንካስተርና የአርኖልድ ሸዋዚንገርን ፖስተር ለጥፎ የማርሊን ሞንሮን ፊልም በቻ ለሚያከራይ ሰው ገቢው በእርግጥም ከፊልም ማከራየት መሆኑ ያጠራጥራል……ኤኒዌይስ ማክዳ አርከበን ያማራትን ነገር ባሻት ጊዜ ስትጠይቀው ሳያወላውል ያደርግላታል….በእርግጥ ማክዳም ከጆሮ ጌጥ የዘለለ ከቀይ ወጥ ያለፈ አእምሮት የላትም….(ወይም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የላትም ነበረ)
በነገራችን ላይ ይሄ ሁሉ ሰው እስከሚሞት ድረስ ማእከላዊ መንግስት ምን ይሰራ ነበር?! አውቶክራቱ አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት ቢኖሩ ኖሮ ነገሮች ተካረው እዚህ ደረጃ ይደርሱ ነበር ወይ?! እሳቸው በህይወት በነበሩ ጊዜ ስርአቱስ ግን በእርግጥ የፌደራል ስርአት ነበረ ወይ? በሞታቸው የፌደራል ስረአቱ ወደ እውነተኛ የፌደራል ስርአትነት አላበበም ወይ?! ክልሎች አሁን አሁን እያሳዩ የመጡት ባህሪ የፌዴራል ስርአቱ እየጠነከረ እንደመጣ የሚያሳይ ነው ወይስ የማእከላዊ መንግስትን መዳከም?ይሄ ሁሉ ነገርስ የህወሃት ኢሃዴግ የፖለቲካ ጌም ቢሆንስ?! እነ አብዲ እነ ለማ እና ገዱና አባይ በሙሉ ከጸገዴ እስከ ጪናቅሰን በእነ አባይ እና በረከት የተጻፈላቸውን ስክሪፕት እየተጫወቱ ቢሆንስ?! አቶ አዲሱን “ጀዋር” ብሎ መሳደብ ኢዝ ኢት አ ኮምፕልመንት ኦር አን ኢንሰልት?! አርከበ ማክዳን ለመጀመሪያ ጊዜ በተኛት ቀን ማግስት ያኮረፈው ማክዳ ድንግል አልነበረች ሆና ቢሆንስ?! ማክዳ ቦሌ ሚከኤል ስትመላለስ መንገድ ላይ የሚያስቸግራት እና የሚጥም መአዛ ያለው የሞቃዲሾ ሽቶ የሰጣት አህመድ ከአርከበ ቀድሞ ድንግልናዋን ወስዶት ቢሆንስ!?….
ማክዳ ከማን አረገዘች?! ድሮ ለቀረ የድንግልና ጥያቄ ብሎ አርከበ ሲያኮርፍ አህመድ በዚያው ቢጠቀልላትስ?! ማክዳ ግን በቀቢጸ ተስፋ ያልተፈለገ ልጅ ወደዚህ ምድር ከምታመጣ ብታስወርደውስ!?የማክዳ አያትስ ህልውናቸው አደጋ ላይ ወድቆ ይሆን?!
ማክዳ ከማን ይሆን ያረገዘችው ?!..ከማን እንዳረገዘች እና ያለምንም ሃፍረት እና ሰው ምን ይለኛል ባይነት ሆዷን አንገፍጥጣ መሄዷ የሰፈራችን መወያያ ሆኗል……!…የጽንሱን አባት ግን እሷና ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቁት! ብቻ ለሷም ለአርከበም ለአያቷም ፈጣሪ ማስተዋሉን ይስጣቸው!
አንባቢ ሆይ የማክዳ ጽንስ ከየት የመጣ ይመስልሃል!?
በተረፈ
ይመቻችሁ

2 Comments

  • ሰሎዳ ነኝ ከአድዋ commented on September 16, 2017 Reply

    ይመቻል

  • birhantewolde@gmail.com'
    tewolde commented on September 21, 2017 Reply

    በጨዋ ደንብ እያዋዛህ ነገርከን

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...