Tidarfelagi.com

‹‹ኑ! አንድ ቤት ግቡ!››

መስሪያ ቤቴ ሁለት የከፍተኛ መደብ ልጆች ብቻ የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች መሃከል የተሰነገ ነው።
ጠዋት ሲገቡ፣ እረፍት ሲወጡ፣ ማታ ሲሄዱ አያቸዋለሁ።

ከወዛቸው፣ ከቀብራራነታቸው፣ አማርኛን ከደቆሰው እንግሊዝኛቸው ጎልቶ የሚታየኝ፤ መጀመሪያ የሚቀበለኝ ዘወትር ዳንኪራ የሚረግጡበት አደንቋሪ፣ ተንጫራሪ ራፕ ሙዚቃቸው ነው።

የነ ድሬክ፣ የነ ክሪስ ብራውን፣ የሊል ዋይን፣ የነ ፊውቸር …ጩኸት በኪራይ ከሚያመጣቸው ሚኒ ባስ፣ ከሚኒ ሚዲያቸው፣ ሲልም ከነሱ የምሰማው የየእለት የቀን አዝማቼ ነው።

…ዛሬ ግን ሌላ ሰማሁ።

ወጣ ብዬ አየኋቸው።

እንደፈለጉ ባበጁት ዘመነኛ ዩኒፎርማቸው ሆነው፣
ግማሾቹ ያንጨባረሩትን ፀጉራቸውን እየፈተሉ፣ ግማሾቹ እጆቻቸውን ወደ ሰማይ እየሰቀሉ
በውድ ጫማዎቻቸው ላይ እየነጠሩ፣
በከባድ ስሜት ተውጠው፣
እጅብ ብለው በቆሙበት፣ ጥርት ባለ አማርኛ፣ በጋለ ስሜት እንዲህ እያሉ ሲዘፍኑ ሰማኋቸው።

‹‹ተዉኝ ይውጣልኝ -ልጥራት ደጋግሜ፣
ኢትዮጵያ ማለት -ለኔ አይደል ወይ ስሜ››

የቴዎድሮስ አዲሱ ሙዚቃ ወጥቶ ሳያልቅ ብዙ አቃቂር ወጥቶለታል። ብዙ ሙገሳ እና ውዳሴም ዘንቦለታል።

ሙያ ያልነካው ተራ የአድማጭ አስተያየት ቢኖረኝም ፣ ‹‹ሙሉው ስራ ካልወጣ በወጀቡ ተወስጄ ቀድሜ አላውራም›› ብዬ ራሴን ገዝቼ ብቀመጥም.. የነዚህ ልጆች ነገር ግን ልቤን ነሳኝ።

ነጥቤ ይሄ ነው፤

ሙዚቃውን ወደድነውም አልወደድነው፣
ጥማችንን አረካውም አላረካው፣
በሙያው ቀመር ሚዛን ደፋም አልደፋ፣

እንደነዚህ ያሉ የራፕ ሰለባ ልጆቻችን፣
እነዚህ የዘር ፖለቲካ ዘመን ፍሬዎቻችን፣
የፀለምተኝነት ስብከት ኢላማዎቻችን፣

ከጊዜ ጊዜ፤ የአንድነት፣ የተስፋ እና የኢትዮጵያዊነት ክትባት ያስፈልጋቸዋል። ከታቢው ማንም ሆነ ክትባቱ ግን በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል።

‹‹በአንድ ካሴት አንድ የሀገር ዘፈን›› ግዴታ በነበረበት ዘመን ልጅ የነበርንም ሰዎች ያነፀን የሃገር ፍቅር ስሜት፣ የሚያንዘረዝረን የኢትዮጵያዊነት ፍቅር ኩባያ ጎድሏልና በየጊዜው፣ እንደ አዲስ የሚሞላው ሰው ያሻናል።

‹‹እየወገናችሁ›› ስንባል የስንት አመት ቆዳዎችም ከብት ተራ ቆመናልና ‹‹ ኑ! ወደ አንድ ቤት ግቡ‹‹ እያለ የሚጠራን ሰው ክፉኛ ያስፈልገናል።

 

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...