ከሌሊቱ ሰባት ሰአት ገደማ።
ተኝቼ ነበር። ህመም አልነበረኝም። ያው ከተለመደው ማቅለሽለሽ ያለፈ ያስጠነቀቀኝ፣ ለዚህ ልብ ስብራት ያዘጋጀኝ ህመም አልነበረኝም።
ብቻ ስደማ ተሰማኝ።…ቀስም ቶሎ ቶሎም የሌሊት ልብሴ ላይ፣ አንሶላው ላይ ስደማ ተሰማኝ። ተደናብሬ የራስጌ መብራቱነ አበራሁት።
ልብሴም፣ አንሶላውም ደም በደም ሆኗል።
‹‹ሶልዬ…ሶልዬ ተነሳ!›› ብዬ ጮህኩ። አጠገቤ የተኛው ባሌ አልሰማኝም።
‹‹ሶል…ሶል…..በማርያም ተነሳ›› የፈሰሰ ደሜን እያየሁ መነሳት ፈርቼ ደግሜ በጩኸት ጠራሁት።
‹‹ምነው…?ምን ሆንሽ…?›› አለኝ ተፈናጥሮ እየተነሳ።
‹‹…እየደማሁ ነው…ምን ሆኜ ነው…? ደም በደም ሆኛለሁ..ሶልዬ…ወይኔ ጉዴ ሶልዬ…ወይኔ ጉዴ እየደማሁ ነው…..››
ከሰአታት በኃላ… ‹‹ተጠርጎ ወጥቷል። አሁን ለጤናሽ የሚያሳስብ ነገር የለም›› አለኝ ሃኪም ቤት ውስጥ ወዲህ ወዲያ ሲያደርጉኝ ከነበሩት ሀኪሞች አንዱ።
የሆንኩት ሰምቼ፣ የተደረግኩትን ተደርጌ ስጨርስ እንደ ቁራጭ ስጋ ስሜት አልባ ሆኜ አልጋ ላይ ተኝቼ ነበር።
የአይኖቼ ክዳኖች የአክንባሎ ያህል ከብደውኛል።
ድምፄ ከጩኸት እና ለቅሶ ብዛት አልቋል።
እንዳልሞት ያህል በግርብቡ በተከፈቱት ደረቅ ከንፈሮቼ እና በአፍንጫዬ እተነፍሳለሁ።
እጆቼ የአልጋውን ብረት ጥፍንግ አድርገው ይዘዋል።
ሆዴ ላይ ዘነዘና ያስቀመጡ ይመስለኛል። ክብድ ይለኛል።
ይሄው ነው የሚሰማኝ።
ስለ እግሮቼ አላውቅም። ስለ ጆሮዬ አላውቀም። ስለ ጣቶቼ አላውቅም። ስለ ሌላ ነገሬ አላውቀም።
ሶል አጠገቤ ቆሟል። በድብቅ ከባድ ለቅሶ ያስተናገደ ፊቱን በወንድ ደንብ ኮስተር አድርጎ ሊያታልለኝ ይሞክር እንጂ እሱም እንደተሰበረ ይታየኛል።
ያልተወለደ ልጃችን ሞቷል።
ያልተወለደ የመጀመሪያ ልጃችን ሞቷል።
‹‹ምንድነው ያለው ዶክተሩ…?›› አልኩት ብቻችንን ስንሆን ጠብቄ.
‹‹ የኔ ቆንጆ…እ…ጠርገውታል…ምንም አትሆኚም ከዚህ በኋላ…›› አለኝ አንደኛው እጄን ከአልጋው ብረት አላቅቆ ጥብቅ አድርጎ እየያዘኝ።
‹‹ልጄን ጠረጉት….ልጄን ጠረጉብኝ…..?ሶልዬ…ልጃችንን…ጠርገው አወጡት? ››
እምባዬ በተኛሁበት በግራና በቀኝ ወደጆሮዎቼ መፍሰስ ጀመረ…
‹‹ማሬ…እንደዚህ አትሁኚ…ያው…ማድረግ ነበረባቸው….ማለት…ላንቺ ጤና…ወደ ፊት ሌላ ልጅ….ሌላ ልጅ እንድንወልድ….››
እጄን የያዘው እጁ ይንቀጠቀጣል።
ወደአይኖቹ መሄድ የሚፈልገውን እምባ በአፉ አስገድዶ እየዋጠ፣ በአፍንጫው ሰንጎ እያስቀረ ሊያፅናናኝ ይሞክራል።
‹‹ልጄን እንደ ቆሻሻ ጠረጉት…ሶልዬ ልጄ እኮ ነው…ስም አለው እኮ…ስም አውጥቼ ነበር እኮ….ልጄ እኮ ነው››
‹‹አንቺ ልጅ…በቃ ዝም በይ…መአት አትጥሪ…ዋናው ያንቺ መትረፍ ነው›› አለች እናቴ በሩን ከፍታ እየገባች።
ተርፌያለሁ እንዴ…?
‹‹አንተም ከሷ አትሻልም…ሂድ አሁን ክፈሉ ምናምን እያሉ ነው…ዛሬውኑ ትወጣለች ብሎኛል ዶክተሩ››
የለመደችውን የሴቶች የማርያም ማህበር ድግስ የምታሰናዳ ነው የምትመስለው፡ ምስር የምትለቅም። ጎመን የምትከትፍ። ሽንኩርት የምትልጥ።
እንደተለመደው ስራ እየሰራች ነው። መሆን ያለበትን እያደረገች ነው።
እናቴ የስሜት ሳይሆን የሚና ሰው ናት። ጎረቤት ሲሞት ከማልቀስ በፊት ገናዥ የምትጠራ፣ ሰው አዳልጦት ሲወድቅ ‹‹እኔን›› ሳትል የምታነሳ፣ ህፃን ሲያለቅስ ‹እሹሩሩ›› ሳትል ዝም የምታሰኝ አይነት ሰው ናት።
ስሜት ሩቋ ነው። የርሷ ስራ ነገሮችን ቦታ ቦታ ማስያዝ ነው። እናቴ ነገር በማስተካከል ተሰተካካይ የላትም። ስሜት ግን እንደ ሰማይ ሩቋ ነው።
ይሄን እያወቅኩ፤
‹እማ….›› አልኳት።
የለበስኩትን ብርድ ልብስ ታሰናዳለች።
‹‹እመት…››
‹‹አሁን…ሀዘን አልቀመጥም…አንቀመጥም?›› ለምን እንደዚህ እንዳልኳት አላውቅም። ምናልባት ሳያብብ ለረገፈው ልጄ ተገቢ ለቅሶ እንድታሰናዳልኝ ፈልጌ ይሆናል። ፍራሽ፣ ዳስ፣ ቀብር ቢጤ።
ሀዘኔ ላይ የ‹‹መስክረናል…ሆኗል›› ማህተም እንድታረግልኝ ፈልጌ ይሆናል።
‹‹አንቺ ልጅ ያምሻል አይደል…ለማን ነው ሀዘን የምንቀመጠው?…›› ትራሴን እያስተካከለች ስሜት ዝር ባላለበት አይኖቿ እያየችኝ መለሰች።
‹‹ልጄ እኮ ነው እማ…ልጄ እኮ ነው የሞተው››
‹‹ወረደ ነው የሚባለው…ሞተ አይባልም…ልጅ ካልተወለደ ሞተ አይባልም›› ዝንጅብል እየላጠች የምታወራኝ ነው የምትመስለው። ከምንድነው የተሰራችው?
‹‹ወረደ…?.›› አልኳት
‹‹አዎ…ይሄ እኮ ብዙ ሴት ያጋጥመዋል…እግዜር ያላለው አይሆንም..ሌላ ትወልጃለሽ ቶሎ..አይዞሽ››
አይዞሽ ስትል እንኳን አይዞሽ ያለች አትመስልም።
‹‹ወረደ ነው የሚባለው…ሞተ አይባልም›› ማለት ምን ማለት ነው። ሰው አልሆነም ማለት ነው…? የሰው ክብር የለውም ማለት ነው…? ልጄ ልጅ አልነበረም ማለት ነው…ስላልተወለደ እውቅና የለውም ማለት ነው….ሀዘን አይደለም…?.የልጄ መሞት አሳዛኝ አይደለም…?የልጄ ሞቱ ጉዳት የለውም?
ከልብ ብቻ የተሰራሁ ይመሰል ልቤ ሲመታ ብቻ ይሰማኛል።
‹‹ እኔ የምልሽ…›› አለችኝ ትንሽ ቆይታ
‹‹እ…›› አይኔን መክፈት የካ ተራራን ከመውጣት እየከበደኝ ነው።
‹‹ለሰው አውርተሻል እንዴ…?››
‹‹ምኑን…?››
‹‹እርጉዝ እንደሆንሽ…››
ለሰው አውርቻለሁ እንዴ?
ለሰው አላውራሁም ግን ሰዎች አውቀዋል። ያቅለሸልሸኝ ነበር። ፊቴ መለወጥ ጀምሮ ነበር። ደስ ብሎኝ ስለነበር ለልብ ወዳጆቼ ነገሬ ነበር።
ሰዎች አውቀዋል።
‹‹ለተወሰነ ሰው…››
‹‹አየሽ…!እኔን አትሰሚም….ሶሰት ወር ሳያልፍ አይወራም..አፍ ጥሩ አይደለም ስልሽ ብትሰሚ ኖሮ…››
ማልቀስ ጀመርኩ።
እውነት ልጄን በአፌ ነው የገደልኩት?
ለሰው በማውራቴ ነው አቅፌ በመሳም ፈንታ ደም አድርጌ ጨርቅ ላይ ያፈሰስኩት…?
እኔ ነኝ ያጠፋሁት?
እኔ ነኝ የገደልኩት?
ለቅሶዬ በበረታበት ባሌ ሲመለስ ከእናቴ ጋር ተጣሉ።
በለቅሶ ደክሜ አይኖቼን ጨፍኜ ነበር ግን ከተዘጋው የክፍሌ በር ባሻገር ኮሪደሩ ላይ
‹‹እንዴት እንዲህ ይሏታል?››
‹‹አንተ ታቀብጣታለህ..ወንድ ሁን እንጂ›› ሲባባሉ ይሰማኛል።
ደከመኝ።
እጅግ ደከመኝ።
ብዙም ሳልቆይ እርጉዝ ሆኜ ገብቼ ባዶ ሆኜ ወጣሁ።
ሁለት ሆኜ ገብቼ፣ አንድ ሆኜ ወጣሁ።
ከአራት ቀን በኋላ ቤቴ ሶፋዬ ላይ ቁጭ ብዬ ‹‹አሁን የእኔ ስም ማነው?›› ብዬ ማሰብ ጀመርኩ።
ለሁሉም አይነት ሰው ስም አለን።
እናቱ እና አባቱ የሞቱበት ልጅ ‹‹የሙት ልጅ›› ይባላል።
ባሏን ፈትታ ብቻዋን ያለች ሴት ጋለሞታ ትባላለች።
ወልዳ የሞተባት ሴት ‹‹ልጇ የሞተባት እናት›› ትባላለች
እኔ ምንድነው የምባለው?
የኔ ስም ማነው?
የኔ ሃዘን ስሙ ምንድነው? ሰው ስለኔ ሲያወራ ምን ሆነች ብሎ ነው?
ከዚያ ደግሞ ስለልጄ አስባለሁ።
አገሩን ሁሉ ያዳረሰ ስም ለእኔ ልጅ ስለማይሆን፣ ልጄን ስለማይመጥን ፤ ብዙ ጥናት ሰርቼ፣ ወጥቼ እና ወርጄ ስም አውጥቼለት ነበር።
ቄሶች አመክሬ፣ አቧራ የለበሱ መጽሃፍት ከፍቼ፣ ከጥንት ኢትዮጵያውያን ንጉሰ ነገስታት የስም ዝርዘር የምመኝለትን አስቤ ስም አውጥቼለት ነበር።
ትንሽ አድጎ በየፀጉር ቤቱ፣ በየኬክ ቤቱ ስንሄድ ቁንጅናውን አይተው፣ በአበባነቱ ተስበው እንደንብ የሚከቡት ሰዎች በሙሉ ከሳሙት በኋላ ስሙን ሲጠይቁት እና ሲነግራቸው ሲደነቁ ይታየኝ ነበር።
‹‹እንዴት የተለየ ስም ነው? በስማም!›. ሲሉ እና እኔም እሱም ስንኮራ ይታየኝ ነበር።
አሁን ስሙን ምን አደርገዋለሁ?
ሌላ ልጅ ስወልድ የርሱን ስም አወጣለታለሁ…?ስሙን እቀማዋለሁ…?
…አላደርገውም። አይወለድ እንጂ…አድጎ አትዩት እንጂ እኔ እኮ ልጄን አውቀዋለሁ…ልጄን እወደዋለሁ።
እቅዴ ውስጥ ነበር። ወደፊቴ ውስጥ ነበረ።
ስሙንምማ አልቀማውም…
‹‹ማሬ እንዴት ዋልሽ ዛሬ…?›› ሶል ከስራ መግባቱ ነው።
‹‹ደህና…..››
‹‹ህመም አለሽ እንዴ…?››
‹‹እ..እ…የለኝም…የለኝም…››
‹‹ ጎሽ…ደህና ሆንሽልኝ›› አለና ግንባሬን ሳም አድርጎኝ ወደ ሽንት ቤት ገባ።
ብዙ ሳይቆይ አለበት ሆኖ፤ ‹‹ልጅቷን ቡና አፍይ በያት…እነ ቅድስት ይመጣሉ›› ሲለኝ ተሰማኝ።
ሰውነቴ እንደ ጎማ ተነፈሰ።
‹‹ለምንድነው የሚመጡት? ››
በዚህ ሰሞን ከሰው በላይ የሚያበሳጨኝ ነገር የለም ።
‹‹ሊጠይቁሽ ነዋ ሆዴ….›› አለኝ ወደ ሳሎን እየተመለሰ።
‹‹ለምን ይጠይቁኛል…ምን ብለው ይጠይቁኛል… በቃ…ደህና አይደለሁ….?››
‹‹ነሽ እሱማ…ያው…ጓደኞቻችን አይደሉ….አትምጡ አይባል ነበር….እንደዚህ አትሁኚ››
እንደዚህ አትሁኚ ሲለኝ በቡጢ በይው በይው ይለኛል።
እንዴት መሆን እንዳለብኝ የማውቅ ይመስለዋል…?
ሳይንስ ያላወቀው፣ ማህበረሰብ እውቅና ያልሰጠውን ሃዘን ላይ ሆኜ፣
ብጥስጥስ ብዬ፣
የሰው ቅርፊት ሆኜ አንዴት መሆን እንዳለብኝ የማውቅ ይመስለዋል›?
ብሽቅ።
እነዚህ ሰዎች ልጄን ወልጄው ቢሆን ‹‹እንኳን ማርያም ማረችሽ›› ብለው ገንፎ ሊበሉ የሚመጡ ሰዎች መሆናቸውን እያሰብኩ ሳያቸው ምን ያህል እንደሚያመኝ ያውቃል?
እነዚህ ልጆች ተወልደው ስላደጉ ልጆቻቸው ገድል እኔ ፊት ሲያወሩ መስማት ምን ያህል እንደሚያደማኝ ያውቃል?
‹‹ሲፓራ እንዲህ አደረገች›› ‹‹ባሮን እንዲህ አለ›› እያሉ ሲለፋደዱ ስሰማ ምን ያህል እንደምቦጫጨቅ ይገባዋል›?
‹‹እንዲህ ስትሆኑ እንዲህ ነው የምትሆኑት›› ተብሎ ህግ ያልተፃፈለትን ነገር ሆኜ፣ ምን መሆን እንዳለብኝ እንዴት ላውቅ ይቻለኛል…?
እንደ ሃዘን ተቀባይነት የሌለው ከባድ ሃዘን ደርሶብኝ እንዴት ነው መሆን ያለብኝ?
ቁምሳጥን በከፈተች ቁጥር የገዛቻቸውን የእርጉዝ ልብሶች እያየች የምታነባ ሴት አንዴት መምሰል ነው ያለባት?
የእርግዝና መፅኃፍ ቤቷን የሞላው እርጉዝ ያልሆነች ሴት ምን ባህሪ ነው መያዝ ያለባት.?.
ልጇን እንደ ቆሻሻ አስጠርጋ የመጣች ሴት አንዴት እንዴት ነው መሆን ያለባት?
ስልክ አስጠላኝ።‹‹ አይዞሽ›› አስጠላኝ። ሶል አስጠላኝ። ሶፋው አስጠላኝ። አልጋው አስጠላኝ። ሳቅ አስጠላኝ።
እናቴ አስጠላችን። ምስር ወጥ አስጠላኝ። ጓደኞቼ አስጠሉኝ። ቤታችን አስጠላኝ።
ሁሉ ነገር አስጠላኝ።
የሚመጣ መስሎ የቀረውን፣ በቤቴ ወለል ላይ ሳይሆን በማህፀኔ ግድግዳ ላይ የተራመደውን፣ እኔ ብቻ የማውቀውን ልጄን ሞት አንዳልተፈጠረ የሚጥሩ፣ እንዳልሆነ የሚያስመስሉ፣ ያልተወለደ ልጄን ታሪክ በእርሳስ ፅፈው በላጲስ የሚያጠፉ ሰዎች እጅግ አስጠሉኝ።
ልጄን- እቅዴን- ወደፊቴን- አለሜን- ቤት ተጎዝጉዞ አንደነበር የደረቀ ሳር ‹‹ተጠርጓል›› ያሉኝ ሃኪሞች አስጠሉኝ።
የራሴ ጥያቄዎች አስጠሉኝ…
የመጀመሪያ ልጄ ይሄ ነው ወይስ ቀጥሎ የምወልደው?
ወደፊት ሁለት ልጅ ከኖረኝ እና ሰዎች ስንት ልጅ አለሽ ካሉኝ ሁለት ነው የምለው ወይስ ሶስት …አይነት ጥያቄዎቼ ክፉኛ አስጠሉኝ።
ከሁሉ በላይ ግን ለተቀማሁት ነገር እና ለሃዘኔ ስምም እውቅናም መስጠት የማይፈልገው ማህበረሰብ አስጠላኝ…