በእንግሊዝ አገር የአራዊት፣ የአእዋፍና የአሳ መጠበቂያ ማህበር ግንቦት ፲፪ (12) ቀን ፲፰፻፺፫ (1893) ዓ/ ም መቇቇሙንና ኢትዮጵያም በዚህ ማህበር እንድትገባ በማለት ሙሴ ቤርድ ለምኒልክ ኣጫወታቸው። የደምቡንም ግልባጭ አነበበላቸው። ምኒልክ በሰሙት በአራዊት ጥበቃው ደንብ ተደሰቱ። ይህንንም ሁኔታ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ መንግስት ባለሙሉ ስልጣን ሚኒስትር የሆነው ሚስተር ሃሪንግተን የአገሩን መንግስት ጠይቆ የተብራራ መልስና ሙሉውንም የማህበሩን ደንብ እንዲያስመጣላቸው ጠየቁት። ሚስተር ሃሪንግተንም ሁሉን አሟልቶ ካስመጣላቸውና ካስረዳቸው በሇላ ምኒልክ የማህበሩ ሊቀመንበር ለነበሩት ለእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚከተለውን ደብዳቤ ፃፉ።
ይድረስ ከክቡር ሎርድ ላንድሰድወን።
የእንግሊዝ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
በሎንዶን ከተማ በግንቦት ፲፪ ቀን ፲፰፻፺፫ ዓ/ ም የኤሮፓ ነገስታቶች የተዋዋሉትን የአውሬና የአእዋፍ፣ የአሳ መጠበቂያ ውል በኮሎኔል ሃሪንግቶን እጅ ተቀብዬ አየሁት። መረመርሁት። በዚህ ውል ያገኘሁትን ሃሳብና የነገስታቶችን መልካም ፍቃድ እጅግ ወድጃለሁ። ይህንንም ያሰቡትን የአውሬና የወፍ፣ የአሳ መጠበቂያ በመንግስቴ ውስጥ ለመፈፀም እኔ የሚቻለኝንና የሚመቸኝን ሁሉ ለማድረግ ፍቃዴ መሆኑን አመለክታለሁ።
ህዳር ፳፰ (28) ቀን ፲፰፻፺፬ (1894) ዓ/ ም አዲስ አለም ከተማ
ኢትዮጵያ ከአራዊት ጥበቃ ማህበር ከገባች በሇላ ምኒልክ አውሬ እያደኑ የሚኖሩትም ሰዎች ቦሆኑ ባንድነት ባንድ ቦታ ሰፍረው ሊያድኑ የሚችሉት አውሬዎች ተለይቶ ተነገራቸው። ከዚህ በተረፈ ግን ማንም ሰው ያለመንግስት እንዲያውም ያለ ምኒልክ ፍቃድ ታላላቅ አውሬ እንዳያድን በጥብቅ ተከለከለ።
በቅርቡ ታሪኩን በማስታወስ UNDP ባወጣው ዶኩመት ላይም “Ethiopia is still one of the best kept secrets in the world for visitors to catch sight of an astonishing range of wildlife comprising 320 listed mammal species, 36 of which endemic” በማለት የኢትዮዽያን ለዩ የአራዊት ሃብት ጠቅሷል ።
ዋና ምንጭ:
አጤ ምኒልክ
በጳውሎስ ኞኞ