Tidarfelagi.com

ሞደ ጠባብነት፣ ከጎሳ እስከ ሀገር

«ሞደ ጠባብነት፣ ከጎሳ እስከ ሀገር…
ሀንገር በጠለፋት መንደር » 😉

ፌቡም የጎጠኞች መዲና ሆናለች። ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንፃር ሲነፃፀር የትየለሌ ጨምሯል። ብዙ የቡድናቸው አሳቢዎች አልፎ አልፎ በመግባባት፣ ብዙ ጊዜ በመፈነካከት በዚህች መዲና ይኖራሉ።

ጎሳህ ማንነት ነው የሚሉ ድምፆች ይጮሃሉ። ሎል እያልክ ማለፍ ነው እኚህን። በቡድን ውስጥ ማንነትህ ይጠፋል፣ እንጂ ማንነትህ አይሆንም። ማንነትህ ቡድን ከሆነ፣ አንተ ምንም ነህ። ብትረግጥ አሻራ አታሳርፍም። አርፈህ ቁጭ በል! የቀብርህ ቀን፣ ግለታሪክ ተብሎ የጎሳህ ታሪክ ይነበብልሃል።

ጎሳዊ ህሊና ያለውን ሰው፣ ጎሳውን አክብረህለት እሱን ብትንቀው አትጎዳውም። የሌለ ነገር አይጎዳም። እዛ ቦታ ግለሰቡ የለም።

ጎሰኝነት ከፌደራሊዝም የተምታታበት፣ “ጎሳ በኢትዮጵያ መሬት ረግጧል። ወደድክም ጠላህም አታመልጠውም” እያለ ያፏጫል፤ፉጨታም። እንዲህ አይነቱ ሰው፣ በንጥቂያ ዘመን ሌባ አይሆንም ብለህ አጠብቅ። ሀገሩ በሳር ቢሸፈን፣ “ይሄ ሁላ ሳር እያለ ለምን በግ አንሆንም” ብሎ ዝቅ ብሎ ከመጋጥ አይመለስም።

ከዘር መርጦ ዘራችን፣ ከሀገር መርጦ ሀገራችን ልዩ ነው ቅዱስ ነው የሚሉ ሰልፎችን ማየት ይገርማል (ነው ያሳዝናል?)
አራት እግር ተሰጦት፣ በአንድ እግሩ እንኳን መቆም ያልቻለ ሀገር ይዘህ፣ ልዩ ነን… ቅዱስ ነን ብትል ማን ይሰማሃል?

አንዳንድ ሰው አሻራ የለውም። የራሱ ቀለም የለውም። ህልውና የሚያገኘው የሆነ የቡድን ቋት ውስጥ ሲገባ ነው (ቢያንስ ይመስለዋል) ይመስለውና ገብቶ ይጠፋል። እሱን ፍለጋ፣ የአፋልጉኝ ማስታወቂያ እየለጠፈ የሚለፋ የለም። ለመጥፋት የተፈጠሩ ሰዎች አሉ!

ጎሰኝነት አዕምሮ እንደማይጠይቅ አዕምሮ ያለው ሁሉ ያውቃል። ጉንዳኖችም ይኖሩታል። ንቦችም ይተገብሩታል። ወደ ጉንዳን አነስክ እንጂ ወደ ሰብዓዊ አቅም ከፍ አላልክም።

ጎሳዬ የምትለውም፣ ሀገሬ የምትላትም ኢትዮጵያ ሁለቱም የጎሰኝነት ገላ የለበሱ የአስተሳሰብ መልኮች ናቸው። በፊት በርም፣ በኋላ በርም ከሌሎች ልዩ ነኝ ብለህ ካሰብክ ዘረኛ ነህ።

እኔም አንተም በጋራ የምናውቀው አንድ ሀቅ አለ። ብትሸሸውም አይሸሽህም። «ጎሳኤ ተናቀ፣ ተተፋበት» ብትልም፣ «የጀግና ዘር ነኝ» ብትልም፣ ራስህ እንዳልተከበርክ እናውቃለን። አንተ ተስመህ፣ ጎሳህ እንዳልተተፋበት አይጠፋንም። የጀግና ዘር ነኝ ስትል፣ የምራቅ ጥቅታ የምታክል ጀግነት ልብህ እንደሌለ እናውቃለን። በሌለህበት የምትበደል፣ ባልዋልክበት የምትጀግን ልዩ ፍጡር!

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...