Tidarfelagi.com

የባል ገበያ – (የመጨረሻ ክፍል)

“ጌትዬ ንረገኝ? ያሰብሽው ልክ አይደለም በለኝ?” ከየት መጣ ያላልኩት እንባዬ ከቃላቱ ጋር ፈሰሰ። አይኖቼን ሽሽት ፊቱን አዙሮ ዝም አለኝ።……

“ኦ…ህ ማ…ይ ዲ…ር ጋ…ድ! አዲሱ(የመውደድ አባት ነው) ያወራልኝ ልጅ እንዳትሆን?” መውደድን ነው የምትጠይቀው ቀጠል አድርጋ “አባቷ ሊሞት ነገር ነው ካልተሳሳትኩ?” እሱን እየጠየቀችው ቆሻሻ እንዳየ ሰው በመፀየፍ ስታየኝ ባንቃት ደስ ባለኝ። …… ክንፏን ያጣች ቢራቢሮ ሆኛለሁ። የኔ መውደድ እንዲህ ስንጓጠጥ ሰምቶ ዝም አይልም። ……

ማንም ቢሆን ዘሎ ይከመርበት ነበር። …… ትቻቸው ስወጣ አልተከተለኝም። የሴትየዋ ዝገት ዝገት የሚል ሳቅ ተከትሎኛል። …… የማውቀው ሁሉ ነገር ጠፋብኝ…… የማምነው ነገር ሁሉ ተንኮታኮተ… የማስበው ነገር አጣሁ…… አላለቀስኩም። ግራ ገብቶኛል። ……

እቤት ስደርስ “እመቤቴ ሁሉንም ነገር በቅርቡ አስረዳሻለሁ። በነፍሴ ልክ አፈቅርሻለሁ።” የሚል መልዕክት ደረሰኝ ምንም ማመዛዘን አልቻልኩም። መናደድም አቃተኝ። …… ጠበቅኩት። …… እራሴን ያለእርሱ ማሰብ በፍፁም አልቻልኩም። …… መጥቶ የሆነ ምክኒያት እንዲነግረኝ ጠበቅኩት። እንዳምነው…… ምንም እንዳልተፈጠረ ረስተን አብሬው ልሆን…… የሴትየዋን ለዛ ያጣ ቅብጠት መርሳት አቃተኝ። …… ልጆቿ ከሚያካክሉ ወንዶች ጋር የመውጣት ልክፍት እንዳለባት ስለርሷ የነገረኝን አስታወስኩ።

ከኔጋር የሚያብደውን የፍቅር እብደት ከሷ ጋር ሲያብደው ማሰብ ጨርቄን ሊያስጥለኝ ይደርሳል። … መውደድ ትልቅ ቂጥ ይወዳል። … ከኔ ጋር ፍቅር ስንሰራ እንደሚያደርገው ትልቅ ቂጧን ማየት በሚችልበት አቅጣጫ እያደረገ ሲሰራት አስባለሁ። …… ግዙፍ ሰውነቱ ላይ ስትፈነጭበት እስላታለሁ። እሪሪሪሪሪሪ ማለት ያምረኛል። …… መስታወቱ ፊት እቆማለሁ። ዞሬ ኋላዬን አያለሁ።

ቀናት አለፉ። …… አልመጣም። የአባዬን ደህንነት ለማረጋገጥ እንኳን እታባጋ ሆነ የሚደውለው። …… ብዙም ባልራቀ ቀን ያቺን ሴትዮ ማግባቱን ስሰማ አዞረኝ። …… ከእርሱ ለማረጋገጥ እቤታቸው ስሄድ ጭራሽ ከሴትየዋ ጋር ከሃገር መውጣቱን ነገሩኝ። …… የማታ የዞረ ድምሩ እንዳለቀቀው ሰካራም ስደነባበር የአባዬ ነፍስ አባት ለአባዬ መታከሚያ የሚሆን ብር መገኘቱን አበሰሩን። ታክሞ ግን መዳን አልቻለም። ገንዘቡ በጊዜው አልደረሰለትም። …… ከወራት በኋላ እቤቱ ተመልሶ አረፈ። …… እታባ ከአባዬ ሞት በኋላ ባሰባት። …… ቤቷን ማስተዳደር ስላለባት አየታመመች ለመስራት ብትሞክርም ከአቅሟ በላይ ነበር።

ይህቺ አለም የሌላውን ውድቀት መጠቀሚያ የሚያደርጉ ብሽቅ ሰወች የሞሉባት ናት። …… እንደውም አንዳንዱ ሌላው ካልወደቀ ከፍታው ደስ አይለውም። …… ስኬቱን የሚለካው በራሱ ስኬት ሳይሆን በሌላው ውድቀት ነው። …… አባዬን ልጅህን ካልዳርክልኝ እያለ የሚነዘንዘው ታደሰ የሚባል ነጋዴ አጋጣሚውን ተጠቅሞ እቤታችንን ይደግፍ ነበር። …… አብሬሽ ካልተጋደምኩ ብሎ ሲታገለኝ በብርጭቆ እስከፈነከትኩት ቀን ድረስ። … …
ትምህርቴን እንደነገሩ እየተማርኩ።እስከረጨርስ ስራ በተጨማሪ መስራት ነበረብኝ። አዲስ ቤት ተከራየን።

የአይኑን ብርሃን በቅርቡ እንዳጣ ሰው በእያንዳንዱ ቀኖቼ ውስጥ አስተካክዬ የማልረግጥ ደንባራ ሆንኩ። …… እየቆየ መውደድን ብቻ ሳይሆን ፍቅርን፣ እምነትን፣ እውነትን አርቄ ቀበርኳቸው። …… የእታባንና የሚያውቁኝን ሰወች ሁሉ “ለአንድ ወንድ ብለሽ ቆመሽ ልትቀሪ ነው” ንዝንዝ በድንዛዜ ባልፈውም ጥሎኝ ለመሄዱ በቂ ምክኒያት ሊሰጠኝ ያላከበረኝን ወንድ በልቤ ዙፋን ላይ እንደሾምኩት ማኖር ከአቅሜ በላይ ከባድ ነበር። ……

በየቀኑ መልስ የሌለው ጥያቄ እጠይቃለሁ። ለምን?
……
……
“የጉድ ሃገር ገንፎ እያደር ይፋጃል!” አሉ… …
ክህደቱ ሳያንሰኝ ‘ላንቺ ስል ነው‘ ይበለኝ? ላንቺ ስል ነው ማለት ምን ማለት ነው? … ለኔ ሲል ነው ፍቅራችንን ገድሎ የቀበረው? ላንቺ ስል ነው የከዳሁሽ፣ ላንቺ ስል ነው የተውኩሽ፣ ላንቺ ስል ነው ልብሽን ያነካከትኩት፣ ላንቺ ስል ነው በሌላ ሴት የቀየርኩሽ… ማለቱ ነው?… …

ጭራሽ ምክንያቱ ለይቅርታ ሚዛን መብቃቱን ለማመዛን እንድሰማው ሲጠይቀኝ ምላሱን እንኳን ድንቅፍ አላለውም። ………
……
…… በሁለቱም ተቃራኒ የስሜት ጠርዝ የሚቸነክረኝ ሰው ነው መውደድ። …… በፍቅርና በጥላቻ፣ በክብርና በውርደት፣ በፈንጠዝያና በመሪሪ ሀዘን፣ በስኬትና በውድቀት፣ በፍሰሃና በህመም…… …… በነዚህ ሁለት ፅንፎች የሚያላጋኝ እሱ ነው። ……

አሁን ላይ ምንምና ስለማንም ባልሰማ፣ ባላይ፣ ባላስብ…… የሆነ ዓለም ጠርዝ ላይ ብቻዬን ብሆን…… ‘እገሌ ምን ይለኛል?‘ ‘እገሌን ምን እለዋለሁ?‘ የማልልበት… … ቦታ ላይ ብገኝ? የሰው ልጅ እንደሰው ሰራሽ ኮምፒውተር ‘undo‘ ጠቋሚ ቢኖረው ምንነበር? …… የምመልሳቸው ብዙ ውድቀቶች ነበሩኝ።…………

ስልኬን አጠፋፍቼ ኡኡታዬን ማዳመጥ ጀመርኩ። ……… ስለ መውደድ ማሰብ በሸሸሁ ልክ ምላሴ ጨው ጨው እስኪለኝ ክህደቱን እንደገና ማሰብ ጀመርኩ።…… አንዳንዴ የምር ግን ምክኒያቱ ምን ነበር? እላለሁ። ……

“ውሻዬ? አባ ይፈልጉሻል።” አለችኝ እታባ ከውጪ እየገባች።

“አባ? አባ? ………ወደውስጥ አይገቡም እንዴ?”
የአባቴ የነፍስ አባት ነበሩ። ወጥቼ እንዲገቡ ብወተውታቸውም አልገባ አሉኝ።

…… እዚህ ቤት ከገባን በኋላ መጥተው አያውቁም። የዛሬ ጉብኝታቸው ገርሞኛል። … ለምን እንደፈለጉኝ ሲነግሩኝ የሆነ ቅዠት እየቃዠሁ መሰለኝ።………

“የዛኔ ለምንድነው ያልነገሩኝ?” ብዬ ጮህኩባቸው

“አትንገራት ብሎኝ ነበር። የሆነውን ሁሉ ያወቅኩት አሁን ነው።” በቆሙበት ትቻቸው ወደውስጥ ገባሁ። ያገኘሁትን ለብሼ ስወጣ ከእታባ ጋር ቆመው እያወሩ ነበር።

“አይደለም። አባዬን ለማዳን ብለህ አይደለም ከዛች ሴትዮ ጋር የሄድከው። እንደዛ ቢሆን ትነግረኝ ነበር።” የሆቴሉን ክፍል በር እንደከፈተልኝ እየደነፋሁ ገባሁ።

“ብነግርሽ እሺ ትዪኝ ነበር? ከአባትሽና ከእኔ ምረጪ ብልሽ ማናችንን ትመርጪ ነበር? አንቺን እዛ አጣብቂኝ ውስጥ መክተት ያመኝ ነበር። አባትሽን ለማዳን እኔን አይሁን እንጂ ምንም ትከፍዪ ነበር።”

“አላምንህም!! ስትዋሸኝ ነው። አራት አመት ሙሉ… …”

“ይሄን የምንነጋገረው አባትሽ መትረፍ ችለው ቢሆን ኖሮ ትርጉሙ ይቀየር ነበር። ፍቅሬን ከፍዬም ላድናቸው አለመቻሌን ስሰማ ሁሉንም ጥዬ መጥቼ ነበር። …… አንቺ የት ነበርሽ? ከታደሰ ጋር…… ረስተሽኝ ነበር።” የሚያወራው ግራ ገባኝ

“እኔ? እኔ ከታደሰ ጋር? በወራት ውስጥ ፍቅሬን እንኳን ብረሳ ክህደትህ የሰጠኝን ቁስል ድኜ ከሌላ ሰው ያውም ከታደሰ… … ከየት ያመጣኸው ወሬ ነው?”

ሸሚዙን ከፍቶ ደረቱ ላይ ያለ ጠባሳውን አሳየኝ። …… ለቅፅበት ደረቱን ሳይ ሙቀት ተሰማኝ።

“አይንሽን ለማየት ጓጉቼ እቤት ስደርስ እታባን አገኘኋት። …… ስታየኝ ፊቷ ላይ የነበረው ጥላቻ እንደዛ ትንሰፈሰፍልኝ የነበረችው እታባ አትመስልም። … አልፈረድኩባትም። … ከታደሰ ጋር ልትጋቢ መሆንሽን እና እንዳልበጠብጥሽ ነገረችኝ። …… ተስፋ ሳልቆርጥ ላገኝሽ ሞከርኩ። … ሁሌም ከታደሰ ጋር ነበርሽ። ከቁርስ እስከ እራት……”

(አየሁሽ ያለኝ ቦታ ሁሉ ነበርኩ። ነገር ግን እሱ እንዳሰበው ከታደሰ ጋር ፍቅር ጀምሬ አልነበረም።)

“ታደሰ መምጣቴን ሰምቶ ነበር ላገኝሽ እንዳልሞክር አስጠነቀቀኝ። … እንደማገኝሽ ነገርኩት። ይሄንን እርሱ ነው የወጋኝ። ከሆስፒታል ስወጣ ቤት ቀይራችኋል። እታባ ማንም የቀየራችሁትን ቤት ለእኔ እንዳያሳይ ሰፈር አስጠንቅቃቸዋለች።እመኚኝ ላገኝሽ ያልሞከርኩበት መንገድ አልነበረም። እኔ አንቺን በመፈለግ ስባዝን ሄለን(ቂጣሟ ሚስቱ) የኔን ልጅ ስትወልድ ህይወቷ አለፈ። … ቢያንስ ለልጄ ስል መመለስ ነበረብኝ። ተመለስኩ።………”

” ምኑም እውነት አይመስልም። …… ሰበብህ ነው። ያገኘሃት ጊዜ ይሄን ሁሉ ለእታባ ልትነግራት ትችል ነበር። ልታገኘኝ የምትችልበት አንድ መንገድ አታጣም ነበር። …” ያለው ሁሉ እውነት ባይሆን ነው ደስ የሚለኝ ……

“ሞክሬ ነበር። …… በሩን ይዛ ቆማ ነው እንድወጣላት የጮኸችብኝ። ……አስጠልቻት ነበር።”

ከዚህ በኋላ ያለውን በትክክል አልሰማሁትም። የሸሚዙን ቁልፍ ከፍቶ ያጋለጠውን ደረቱን ፈዝዤ አየዋለሁ። …… መንካት ያምረኛል። …… አብሮት የሚሰራ ነጭ ሰውዬ ሳይቱ ላይ ያለውን ፎቶ እያሳየው ቆንጆ መሆኔን እንዲያረጋግጥለት የጠየቀው ጊዜ እንዳገኘኝ የነገረኝን ሰምቼዋለሁ። ……እጄን ሲይዘኝ በርግጌ መነጨቅኩት። ትቼው ስከንፍ እቤት ሄድኩኝ።ማሰብ ስላቆምኩኝ እንጂ የምጠይቀው ጥያቄ ነበረኝ። …… እታባ ስነግራት በእንባና በፀፀት ልትፈነዳ ደረሰች። …… ምን እንደተሰማኝ አላውቅም።

ማልቀስም መሳቅም አልቻልኩም። ዝም ብቻ… …… እገባለሁ ፣ እወጣለሁ፣ እተኛለሁ ፣ እነሳለሁ፣ እቀመጣለሁ……… የማስበው ምን እንደሆነ አላውቅም እኮ ግን ወጥሬ እያሰብኩ ነው። ያወራውን ሁሉ መርሳት ፈልጋለሁ። …… የታችኛው ቁልፍ ብቻ ቀርቶ የከፈተውን ሸሚዙን አስባለሁ። ……… ባሰብኩት ቅፅበት የቀረውን ቁልፍ በጥሼ ራቁቱን ማየት ያምረኛል።…… ወደ ውጪ ስወጣ መሽቷል። …… ለሊቱ ቶሎ እንዲነጋ ይናፍቀኛል። ነገ አዲስ ነገር ይዞ መምጣቱን አላውቅም። …… ተኛሁ። ማንቀላፋት አቃተኝ። …… ጀርባዬ እስኪቀላ ተገላበጥኩ።… … አንዱን ስይዝ አንዱን ስለቅ እኩለ ለሊት ሆነ። …… መጨረሻ ላይ ማሰብ የቻልኩት መውደድ እቅፍ ውስጥ መገኘት መፈለጌን ብቻ ሆነ። …… በዛ ለሊት የሆቴሉ በር ላይ መገኘቴን ማመን የቻለ አይመስልም። …… ሸሚዙን ቀይሮታል። የሆቴሉን ጋውን ለብሶ ነው የከፈተልኝ። ……

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...