Tidarfelagi.com

የባል ገበያ (ክፍል ሁለት)

ምኑ እንደዘገነነኝ አላውቅም። ፍሬ— አልባ መሆኑ? አሁንም አሁንም አፍንጫውን እየሞዠቀ ቆለጡን እየነካካ ማለቃቀሱ? ብቻ የሰውነቴ ቆዳ ሽፍ እስኪል ሸከከኝ…… ጥዬው ብሄድ ደስ ባለኝ። …… እንደምንም ለሁለት ሰዓታት ታግሼ አየር ማረፊያ ድረስ ሸኘሁት። …… እቅዳችን የነበረው ከወር በኋላ ተመልሶ መጥቶ ልንጋባ ነበር።…… ፊቴን ሳዞር የመጀመሪያ ስራዬ ሊያገኘኝ የሚችልበትን መንገዶች በሙሉ መዝጋት ነበር። ………

“አዚቲ እኮ ቪዛዋ ተሰጣት።” አለች አፀደ እንደ ልምዷ እየተቅለበለበች። ክላስ ውስጥ ያለው ሴት በሙሉ በቄንጥ ተንጫጫ

“ምን ያደርጋል ግን……” ቀጠለች ሴቱ ለ ‘ኦ ማይ ጋድ‘ ቄንጥ የሰቀለውን እጁን ከአየር ላይ ሳያወርድ

በአንድ የአውሮፓ ቋንቋ ትምህርት ቤት ውስጥ ቋንቋ ለመማር ነው የተሰበሰብነው። …… በሚገርም ሁኔታ ከአንድ ወንድ በቀር ሁላችንም ሴቶች መሆናችን ሲገርመኝ። ሁላችንም ለቪዛ ከትምህርት ቤቱ የቋንቋ ብቃት ሰርተፊኬት ስለሚያስፈልግ የምንማር ነን። ከዚህ በላይ የደነቀኝ ግን ከሁለት ሴቶች በቀር ሁላችንም በተመሳሳይ የሳይበር ጠበሳ ትዳር መስርተን በጋብቻ አመሃኝተን ከሀገር ለመውጣት የሚጠበቅብንን እያሟላን መሆናችን ነው።

አዚቲ (ቪዛዋ የተፈቀደላት) ከወራት በፊት ነበር ያገባችው። ጓደኞቿ ሲያላግጡባት

‘ባሏ ከመምጣቱ ሳምንት በፊት አስቀድሞ ከዘራውን ነው የላከው። ከዘራውን ይዛ ሄዳ ነው ቦሌ የተቀበለችው‘ ይሏታል። እሷ በራሷ የምትፎግር ፍሪክ ናት። ትስቃለች።

ያገባችው ሰው ከተጋቡ ጀምሮ ቪዛው እስኪፈቀድ ሀገሩን ትቶ ገስትሀውስ ተከራይተው አብሯት እየኖረ ነበረ። አዚቲ እንኳን በደሞዝ በእቁብ የማትቻል ወመኔ ሱሰኛ ናት። …… ሰውየውን በስተርጅና ቃሚና ቀምቃሚ አደረገችው። …… እንደአፀደ ገለፃ ቪዛው መፈቀዱን በሰማ እለት በከፍተኛ ምርቃና ውስጥ ሆኖ አንድ ነገር ተከሰተለት። …… ኢትዮጲያን ወዷታል። …… አዚቲን የመሄዱን ሀሳብ ትተው እዚሁ እንዲኖሩ ቢያማክራት ‘ነብር አየኝ በል‘ አለች።(በእርግጥ በእንግሊዘኛ እንዴት እንዳለችው እንጃ!) በመጨረሻ ሰውየው ውሳኔውን አስተላለፈ።

“ከፈለግሽ አንቺ መሄድ ትችያለሽ! እኔ ከዝች ሀገር እግሬ ንቅንቅ አይልም!”

አፀደ ወሬውን ከአፏ ቀምቶ ሌላ ሰው የሚያወራባት ይመስል እየተሽቀዳደመች አውርታ ስትጨርስ ፍርፍር ብዬ መሳቅ አምሮኝ ነበር። ከሀብቴ(የክፍላችን ብቸኛ ወንድ) በቀር ሁሉም የለቅሶ ቤት ፍራሽ ላይ የተቀመጡ ያህል ተክዘው ሳይ ሳቄን ዋጥኩት። ……

ባለአንድ ፍሬውን ተጣማሪዬን ከተለየሁ በኋላ ለቪዛ እየተማርኩ የመገኘቴ ኋሊት እንዲህ ነው። ……

ሸኝቼው ስመለስ የምቀጥለው ኑሮ እንዳልነበረኝ ገባኝ። የሆነ መንገድ ላይ መኖሬን ቀጥ አድርጌዋለሁ…… የሆነ ሩቅ መንገድ ላይ…… መኖር ወደውጪሃገር መሄድ ሆኗል። …… እዛች ቦታ ላይ ኢትዮጲያ ውስጥ መኖር አቁሚያለሁ። …… መኖር ከሃገር ለመውጣት መሰናዳት ሆኗል። …… …… ይሄን አቁሜ እዛጋ የሰበርኩትን ድልድይ ገጥሜ መኖር እንደማልችል የገባኝ…… ፈረንጅ መጥበሴን እናቴ በሰማች ማግስት ስልክ ደውላ

“እልልልል ልጄ ከሰው እኩል ልታደርጊኝ ነው?” ስትለኝ

“ፈረንጅ ካገባሽ ሳይክል ትገዢልኛለሽኣ?” ታናሽ ወንድሜ በለሊት ቀስቅሶኝ ሲጠይቀኝ

“አሰይ ልጄ የአባትሽን መቃብር አሳድሽለት!” ስትለኝ አክስቴ

“መድሃኒያለም ሳልሞት ያንቺን ዓለም ሊያሳየኝ ነው።… …እንደው ልጄ የምትታለብ ላሜ ሞታብኛለች ደህና ላም አይተሽ ግዢልኝ። እመርቅሻለሁ።” ስትል አያቴ

ይሄኔ ለራሴ ወሰንኩ። በየትም መንገድ ከሀገር እወጣለሁ። …… ከውሳኔዬ እኩል መፃፃፍ አቁሜ ከነበረው አንደኛው ሰውጋ መፃፃፌን ቀጠልኩ። ……

መልኩ ምን እንደሚመስል አላውቅም።የውጪ ዜጋ ከመሆኑ ውጪ ስለራሱ የነገረኝ ነገር የለም። ሲያወራኝ (በፅሁፍ) ግን የማውቀው… … የሚያውቀኝ…… ረዥም ጊዜ አብረን የሆንን አይነት ነው የሚሰማኝ። …… ሰው የማያውቀውን ሰው ይለምዳል? ለመድኩት። …… የእውነት ያለ ሰው መሆኑን እንኳን ማረጋገጥ የማልችለውን ሰው አመንኩት። …… ጣቶቼ ከስልኬ ላይ ሳይነሱ ይመሻል። ……… ስለብዙ ነገር በማውራታችን የተዋወቅን መሰለ። …… ሰው ይሁን ማሽን፣ ሴት ይሁን ወንድ፣ እብድ ይሁን ጤነኛ… … የማላውቀው ሰው ትንፋሽ ይሞቀኛል። በህልሜ ሁሉ አየዋለሁ። …… ጠዋት ያየሁትን ፊት ለማስታወስ ብሞክር አይመጣልኝም። …… እበሳጫለሁ። …… ራሴ ያበድኩ ያበድኩ ይመስለኛል። ……

መጥቶ እንደሚያገባኝ ቃል ገባልኝ። …… ላላምነው ብፈልግም አመንኩት። …… ቋንቋውን እንድማር በአካውንቴ ብር አስገባልኝ። …… የማደርገው ሁሉ መጃጃል እንደሆነ እየገባኝ ተመዝግቤ መማር ጀመርኩ።……

እመጣለሁ ያለበት ቀን ስምንት ቀን ብቻ ቀርቶታል። …… መጃጃሌን አላቆምኩም። …… ስቀበለው ምን እንደምለብስ፣ የምሰጠውን አበባ፣ የቀኑን እርዝመት…… አስባለሁ። …… ባይመጣስ? እላለሁ መልሼ። ምን ስለመምሰሉ ቦታ ያለመስጠቴ ይገርመኛል። ላስብም ብሞክር ወዲያው ተወዋለሁ።

አራት ቀን……
ሶስት ቀን……
ሁለት ቀን……
አንድ ቀን……
አንድ ሰዓት ሲቀረው ቦሌ ተገኘሁ።…… ትምህርት ቤት ስለሰማኋቸው የሴቶች ገጠመኝ እያሰብኩ ‘እንዲህ ቢሆንስ?‘ ‘እንዲያ ቢሆንስ?‘ ሀሳብ እገምዳለሁ።

የባል ገበያ – (ክፍል ሶስት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...