ሞከርኩ። እስኪታክተኝ ሞከርኩ። የገነባሁትን ላለማፍረስ፣ የለኮስኩትን ላለማዳፈን፣ ያቦካሁትን ላለመድፋት ብዙ ሞከርኩ።
እሱ ግን…
በራሱ አባባል ‹‹አብላጫ መቀመጫ›› ሲያይ የሚንከራተት አይኑ አላረፈም።
ከፊት ቀድመው የሚመጡ ውድር ጡቶችን ሲያይ መቅበዝበዙን አልተወም።
ሌላ ያያል።
ሌላ ይመኛል።
ሽቶ የተቀባች ባለፈች ቁጥር እንደውሻ ያለከልካል።
ቅልብልብ አይኑ የየሴቱ ዳሌ ላይ ፈጥኖ ይለጠፋል።
ፍቅሬ ከእኔ ጋር እያለ፤ ገና ድሮ ጥሎኝ ሄዷል።
መቼ እለት ነው የወሰንኩት። ልክ አመታት እንዳልታገሰ ሰው፣ ልክ ለዘመናት አይቶ ያላየ እንዳልሆነ ሰው፣ አውቆ እንደማይታረም ገባኝ እና የአምስት ብር ሻይ እየጠጣሁ አምስት አመታት የገነባሁትን ቤቴን ለማፍረስ ተስማማሁ።
‹‹ሄደሃልና ሂድ›› ልለው ወሰንኩ።
የተቃጠርንበት ቤና ቤት ቀድሞኝ ተቀምጦ ስፕሪሱን በአላፊ አግዳሚ ሴት ያወራርዳል።
የቴኒስ ጨዋታ እንደሚመለከት ሰው ጭንቅላቱ ከቀኝ ወደ ግራ ከግራ ወደ ቀኝ ሲወራጭ ከሩቅ እየመጣሁ ይታየኛል።
ልቤ ሲረግብ ተሰማኝ። ከጀርባው ነው አመጣጤ። አጠገቡ ስደርስ ስልክ እንደያዘ አየሁ።
ቆም አልኩ።
‹‹ተይ ባክሸ….!ምን የመሰለች ጅራታም ኮከብ አየሁ መሰለሽ አሁን….ግን ካንቺ አይበልጥም…ካንቺ ቂጥ የሚበልጥ ቂጥ የለም!›› ሲል ሰማሁት።
ውሃ ልኬ የተዛባ መሰለኝ።
አውላላ አስፋልት ላይ፣ በገራራ ፀሃይ፤ በቂጤ ዝርፍጥ ልል ምንም አልቀረኝ።
ተንገዳገድኩ።
ድንጋጤ አይደለም።
ለአመታት ፍቅሩን የሚጫረቱኝ ሴቶች እንዳሉ አውቃለሁ።
ሻሞ ውስጥ እንደምሳተፍም ይገባኛል።
አንዳንዴም ትራፊው እንደሚደርሰኝ። እንጥፍጣፊው፣ ያለቀበቱ እንደሚመጣልኝ።
ይሄኛው ስሜት ተስፋ መቁረጥ መሰለኝ።
ላለመወሰን መፍራትን ማቆም መሰለኝ። የተደበቀው በአደባባይ ሲታይ፣ ሰው እየሰማው እንዲህ ሲል፣ ለመያዝ የፈለገ፣ የኔን ‹‹ሂድ በቃ›› ሽኝት የጠየቀ መሰለኝ።
ላለመሰማት፣ ላለመያዝ መሞከሩን ያቆመ መሰለኝ። ሰምቼ ሂድ እንድለው። ቆርጦልኝ እንዳሰናብተው።
እንጥፍጣፊውንም ሊነፍገኝ፣ ያለቀበትንም ሊከለክለኝ የወሰነ መሰለኝ።
ያ መሰለኝ ያሸበረኝ። ያ መሰለኝ ያናወጠኝ።
ስሜቴን በቅጡ ሳላስተናብር አጠገቡ ደርሼ ተቀመጥኩ።
‹‹እሺ…እደውላለሁ በኋላ…›› ወይም ይሄን የሚመስል ነገር ብሎ ስልኩን ዘጋው።
ይወዳቸው በነበሩት አይኖቼ አየሁት።
ሌላ በሚያዬ አይኖቹ አየኝ።
እንደሰማሁ አውቋል። ግን አልደነገጠም።
ግምቴ ልክ ነበር።
በደም ስሬ ደም ሳይሆን የበረዶ ውሃ የሚሄድ ይመስል ያንሰፈስፈኝ ጀመር።
ዘፋኙ ‹‹እትት በረደኝ በረሃ ላይ ቆሜ›› ያለው እንዲህ ያለው ነገር ደርሶበት መሆን አለበት።
‹‹ኤፊ…›› አልኩ ያለኝን ጉልበት አስተባብሬ።
‹‹እ…››
ልብ አድርጉልኝ። ‹‹ወዬ›› ዎቹ፣ ‹‹ወይ ማርዬ››ዎቹ፣ ‹‹ምን አልሽኝ የኔ ቆንጆ››ዎቹ በ ‹‹እ›› ከተተኩ ወራት አልፈዋል።
‹‹እ›› ይለኛል ዝም እንዳይለኝ። አለሁምም የለሁምም ነገር ነው ‹‹እ›› አባባሉ።
እሰማለሁም አልሰማምም ነገር።
‹‹ከሌላ ሴት ፍቅር ይዞሃል?››
‹‹ እ?››
‹‹ሌላ ሴት ወደሃል ወይ?››
ዝም።
መልሱን አውቀዋለሁ።
ኤፊ አይበለኝ እንጂ በነጋ በጠባ ሂድ ሂድ የምታሰኘው ፣ <<ጥለሃት እኔ ጋር ና>> የምትለው፣ እኔ የማላውቃት፣ እኔ ያልሰማኋት ቼ ባይ እና ጋላቢ አለችው።
በፊት የሚፈልገው እኔን ብቻ ነበር።
አልፋና ኦሜጋው እኔው ነበርኩ። ፍቅር ቢያንሰው ባናቱ ጠብ የማደርግለት፣ ቢበርደው የማሞቀው፣ ቢከፋው የማስደስተው፣ ቢያለቅስ የማፅናናው እኔ ብቻ ነበርኩ።
አሁን ግን ሌላ አለው።
ዋናውን በልታ ትራፊውን የምትልክልኝ ሴትማ አለች።
አስኳሉን አጣጥማ ቅርፊቱን፣ ውስጡን ስልቅጥ አድርጋ ልጣጩን የምትሰድልኝማ አለች።
‹‹ ኤፊ››
‹‹አቤት››
አቤት አለኝ!
ሊሰማኝ ፈልጓል። አቆብቁቧል።
ቅድም ያልኳችሁ ነገር ትክክል ነበር። ‹‹ሂድ በይኝ›› ሊለኝ ነው። ሊያፍረጠርጠው ነው።
ዘልአለም የማይከስም እሳት ላይ እንደ በቆሎ እሸት ከሚያገላብጠኝ አፍረጥርጦ ይገላግለኝ ብዬ አሰብኩ።
ነገሩ የቁስል ፕላስተር ከቁስል ላይ እንደመላጥ ነው። ቀ…ስ…ብለው፣ በዝግታ መላጡ ይሻላል ደፈር ብሎ ላጥ ማድረግ….? የዝግታው ይበልጥ ያማል።
ላጥ ማድረግ ፈለግኩ።
‹‹ንገረኛ…››
‹‹ታውቂያለሽ…የምትታውቂውን ባትጠይቂኝ….›› አይኖቹ አይኔን ሳይሸሹ፣ ያልበላውን ፀገሩን በማፈር ሳያክ መለሰልኝ።
አላልኳችሁም?
‹‹ህም…ነው እያልከኝ ነው?›› አልኩት ፈራ ተባ እያልኩ።
የንፍገት ፍቅር ቢቀርብኝ እንደሚሻል ባስብብም፣
የሽሚያ ፍቅር ወንዝ እንደማያሻግረኝ‹ ዳገት እንዳማያስወጣኝ፣ ሌቱን እንደማያነጋልኝ ባስብምም እውነቱን መስማት ግን ፈራሁ።
ግን ደገምኩት።
‹‹ነው እያልከኝ ነው ኤፊ?››
መበርታት አለብኝ። መጠንከር አለብኝ።
ውራጅ ፍቅር አልፈልግም።
መሄድን የሚወድ ሰው ቁጭ በል ቢሉት ትርፍ የለሽ ነው።
ይሉኝታ እንጂ ፍቅር የማያቆየውን ሰው መያዝ እንቅፋትነት እንጂ ሌላ ምንድነው?
‹‹አዎ…ነው…›› ጠንከር አድርጎ መለሰልኝ።
ውይ ሲያም።
ንግግሩ ከጥይት አቆሰለኝ።
ከቢላ ከተፈኝ።
ከመርፌ በላይ ወጋኝ።
ግን መበርታት አለብኝ።
ፍቅር ያላሰረውን እግረ ሙቅ ሆኜ ማሰር አልፈልግም።
የተነሳሳ ልቡን ‹‹በግፍ ነው›› ላስቀምጠው አልሻም።
የሸፈተ መንፈሱን ‹‹በትንሽ ታገስ›› ልደልለው አላቅድም።
ግን ሲያም።
ቃላቱ ከጥይት ያቆስላል።
ከቢላ ይከትፋል።
ከመርፌ ይዋጋል።
‹‹እና ልተውህ…?ልትተወኝ ትፈልጋለህ ኤፌ….?››
መልሱን የማውቀውን ጥያቄ ጠየቅኩት።
ይህችኛዋ የፍቅራችን ሬሳ ሳጥን ላይ የምትመታዋን የመጨረሻዋን ምስማር አቀብለኝ እንደማለት ነበረች።
‹‹እንደሱ አይደለም…ማለት…በውለታ መታሰር አልፈልግም…ጥሩ ነገር አሳልፈናል ግን…›› አለ አሁንም በድፍረት እያየኝ።
‹‹ግን ምን ኤፊ…››
‹‹ የምወድሽ አይመስለኝም…ማለቴ አሁን…ዛሬ…››
ንግግሩ ስጋዬን ቦጫጨቀው።
…. ደም እየፈሰሰኝ ይመስለኛል።
በጆሮዬ፣ በአይኖቼ፣ ….በሁለመናዬ ደም እየፈሰሰኝ ይመስለኛል። ሰውነቴ እንደጎማ ሲተነፍስ…ደግሞ ሲግል ይሰማኛል።
አመመኝ።
ፍፁም ታመምኩ።
አየሁት። አይኖቹ በፍፁም ልበሙሉነት ያዩኛል። የሚጠጣውን ስፕሪስ አየሁት። ፍቅራችን ጀምሮ እንደተወው ቀዝቃዛ ስፕሪስ ለዛ ቢስ ሆኗል። እሱ ደግሞ ሊተወው…ሊደፋው እንጂ..ሊያሞቀው አይልግም
አየሁት።
ፍቅራችን እንደ ተበሳሳ ጣራ ነው።
በጠብ ጠብ ጀምሮ ቀስ በቀስ እንደሚያበሰብስ…ሙሉ በሙሉ ካልተቀየረ ሁሌም እንደሚያፈስ…እንደሚያለፋ የተበሳሳ ጣራ።
እሱን በማጣቴ ሕይወቴ ውሉ የጠፋ ልቃቂት እንደሚሆን አውቃለሁ።
ፀሃዬን ሰርቆ ጭለማ ውስጥ እንደወረወረኝ እረዳለሁ።
ቀስተ ደመናዬን ባለ ጥቁር እና ነጭ እንዳደረገው እገነዘባለሁ።
ግን ልሂድ የሚልን ሰው አትሂድ ማለት በመንገዱ ላይ እንደተቸመቸመ ጋሬጣ መሆን ነው።
እንቅፋት መሆን ነው።
እንቅፋት ልሆን አልፈልግም።
ሳላውቀው ተነሳሁ።
‹‹ኤፊ…››
‹‹ወዬ››
አያችሁልኝ! ሂድ ልለው እንደሆነ ሲያውቅ ‹‹ወዬ!›› አለኝ…. ለደረሰብኝ ሁሉ ከዚህ በላይ ምን ምስክር ምን ያስፈልጋል?
ኤፊ…ሂድ ስለው ወዶኛል።
‹‹ሂ….ድ…›› አልኩት በ ሂ እና ድ መሃከል የኪሎሜትር ያህል ርቀት እያስቀመጥኩ።
ዝም አለ።
‹ኤፌ››
‹‹ወዬ…››
‹‹መሄድ ስለፈለግክ ሂድ…ቀድሜ ማለት ነበረብኝ…ቢሆንም ዛሬም ቢሆን ሂድ…ጊዜህን መጫረት ሰልችቶኛል…የፍቅር ትራፊ መሮኛል ስለዚህ…ሂ….ድ ››
ዝም አለ።
ዝም እንጂ አልሄድም አላለም።
የመዋደዳችን ግብአተ መሬት ለመፈፀሙ ከዚህ በላይ ምን እማኝስ ያሻል?
‹‹ኤፌ››
‹‹ወዬ መአዝዬ…››
‹‹ሂድ ግን … እግርህ ጆሮህ እስኪደረስ ብትሄድ የኔን ያህል የሚወድህ ሰው አታገኝም…›› አልኩት መሄድ ጀምሬ።
ዝም አለ።
እና….
እንዲህ አድርጌ የምወደውን ሰው ሂድ አልኩት።
ለሚጓዝ እንደሚደረገው ዳቦ ቆሎ ሳይሆን ያልቆረጠ ልቤን ቆርጬ ሰጥቼ ላኩት።
መቀመጫዋ ያበጠ፣ ጡትዋ የተወደረ፣ ሰበር ሰካ ባይ ሁላ እንዳሻት ከቀለበችው፣
መዳፍዋ የሰፋ ሁሉ እንዳሻት ከዘገነችው.
የኔ መሆኑ ካቆመ ዘመንም የለውምና ይሂድ።
…ግን እግሩ ጆሮው ጋር እስኪደርስ ቢሄድ…እንደኔ የሚወድው ሰው ማግኘቱ ዘበት ነው።
በመንገዴ ላይ ፤ ሰማዩን ቀና ብዬ አየሁት።
ፀሃይቱ የት ገባች…?
ቀስተ ደመናውንስ ማን በእርሳስ ሳለው…?
….መበርታት አለብኝ።