Tidarfelagi.com

አለመታደል ነው (ክፍል ስድስት)

ስምሪት ያስደነገጣት የኔ መምጣት ይሆን ወይም የመጣሁበት ሰዓት አላውቅም። …… ደነገጠች።

“እንዴ? ኪሩቤል?” ተንተባተበች። …… ጨበጠችኝ።

ሰውየው ለኔ ማሳወቅ የፈለገው ነገር ያለ መሰለኝ አቅፎ ወደ ራሱ አስጠግቶ ፀጉሯን ሳመ። …… እሷ በድርጊቱ ያፈረች መሰለኝ። አይኔን ሸሸችው።

” ማሬ የስራ ባልደረባዬ ነው።” አለች ለሰውየው። ለኔ ደግሞ “የአርሴማ አባት ነው።” ተጨባበጥን።

“ኦው ፖሊስ ነህ? የሆሊውድ አክተር ነበር የመሰልከኝ። ሃሃሃ” ሰውየው መቀለዱ ነው። ብሽቅ!! በቡጢ ዱልዱም አፍንጫውን ባጠፋለት ደስ እንደሚለኝ ቢያውቅ። በዚህ መሃል አርሴማ አይኗን እያሻሸች በአባቷና በእናቷ እግር መሃል ብቅ አለች። ስታየኝ ፈገግ አለች። ያስታወሰችኝ ስለመሰለኝ ደስ አለኝ። ልስማት ስጠጋት ግን ሸሸችኝ……

“ይቅርታ በማይሆን ሰዓት መጣሁ መሰለኝ። የስራ ጉዳይ እቤት ድረስ ይዤ መምጣት አልነበረብኝም።” መናገር ስለነበረብኝ አልኩኝ እንጂ እግሬ ከመሬቱ ጋር ያዛመደው ነገር ያለ ይመስል አልተንቀሳቀስኩም። ሰውየው እንድገባ ጋበዘኝ። …… ለአፉ እንዳለው ያስታውቅበታል። …… ተሰናብቻቸው እግሬን ከተተከለበት አንቀሳቅሼ በመጣሁበት አቅጣጫ መራሁት… … ‘ቀላውጦ ማስመለስ‘ አልኩኝ ለራሴ…

የምፈልገው ስለርሷ አለማሰብ ነው። የማደርገው ግን ተቃራኒውን ነው። ሙሉ ስሜን የጠራችው ሰውየው የስራ ባልደረባዋ መሆኔን እንዲያምናት ብቻ ነው? ድምፅዋ ውስጥ ለምን ፍርሃት ሰማሁ? ለምን ባለቤቴ ነው አላለችኝም? ለምን የአርሴማ አባት ነው አለችኝ? የዛን እለት አርሴማ አባቷ እያለ በምን ስሌት እኔጋ ደወለች? የት ሄዶስ ነበር?

ደጋግሜ እሷን ማሰቤን ለማቆም እታገላለሁ። የሚገባኝ እሷን ማሰብ ስለማቆም እያሰብኩ እንኳን የማስበው እሷን መሆኑን ነው። ……

አንዳንዴ ራስህን ለማግኘት ራስህን ልትከፍል ትችላለህ። ……

ለመጀመሪያ ጊዜ ስሜቴን በሱስ መበረዝ አላማረኝም። መታመም ፈለግኩ። …… ወደ ቤቴ ሄጄ ተጋደምኩኝ። …… ሁሉም ነገር ፀጥ አለብኝ። በምድሪቷ ያሉ ፍጡሮች ሁሉ በሆነ መዓት አልቀው እኔና ቤቴ ብቻ አንድ የምድር ጠርዝ ላይ ተርፈን ከሆነ እንቅልፍ የነቃሁ መሰለኝ …… አመሻሹ ሲገፋ የመጠጣት ፍላጎቴ ታገለኝ። …… ስልኬ ጠራ …… አላመንኩትም። ስምሪት ናት።

” እንደ ባለጌ ሴት ነው አይደል የምታስበኝ?” አለችኝ ስልኩን አንስቼ ሄሎ ከማለቴ

“በምን ምክኒያት?” መለስኩላት

“ምን እንደምታስብ ይገባኛል።” አለችኝ በቀሰስተኛ ድምፅ

“በፍፁም!! መገመት እንኳን አትችዪም።… ስምሪት አጠገብሽ ሆኜ እንባሽን ከጉንጭሽ ላይ መጥረግ ነው ፍላጎቴ ” ጥቂት ዝም አለች

“ማልቀሴን በምን አወቅክ?”

“ባለቤትሽስ? ወጥቶ ነው?”

“አብሮኝ አይኖርም። አንዳንዴ ነው የሚመጣው።” መለሰችልኝ… … መስማት የፈለግኩት ግን ‘ባለቤቴ አይደለም‘ የሚለውን ነበር።

“ልምጣ? እንዳይሽ ብቻ ነው።”

መሽቷል፣ አርሴማ ተኝታለች…… ብዙ ምክንያት ደርድራ እንዳልሄድ ከለከለችኝ። እውነቷን ነው መሽቷል። … ወደርሷ መሄድ ግን እየተጓዙ ማደር ቢሆን እንኳን ደስ እያለኝ አደርገዋለሁ። …… ብዙ ጊዜ የሰቀልከው ተስፋጋ ለመድረስ መጓዝ ተስፋውን ከመጨበጥ በላይ ደስታ አለው። …… ጉልበት እና የተስፋ ስንቅ ያጅቡታል። ስልኩን ዘግቼው ተጋደምኩ። …… መልሳ ደወለች። ግራ ተጋባሁ።

“ሳልነግርህ ረስቼው የእናትህን አድራሻ ፍንጭ የሚሰጥ መረጃ ተገኝቷል።” በእርግጠኝነት ይሄንን ልትነግረኝ እንዳልደወለች ገብቶኛል።

“እሺ በይኝ ልምጣና ልይሽ? 10 ደቂቃ ብቻ? ስለመረጃውም ትነግሪኛለሽ።”

በጣም ታሽታ

“እሺ ግን እኔ ልምጣ! ተመልሶ ሊመጣብኝ ይችላል።” አለችኝ። …… ቁጭ ብዬ እሷ እስክትደርስ መጠበቅ የምችል አልመስልህ አለኝ።

“መሽቷል። እራሴ መጥቼ ይዤሽ እመለሳለሁ። ተዘጋጅተሽ ጠብቂኝ።” አልኳት

የለበስኩትን ቱታ አልቀየርኩትም። እንዴት እንደደረስኩ አላውቀውም። እሷን የማግኘት ጉጉቴ ሰቅዞኝ ለብቻዬ ፈገግ እያልኩ ነበር። …… ታክሲው ውስጥ ምን ያህል እንደተቀመጥኩም አላውቅም። በሯ ላይ ስደርስ ደወልኩ። ከፈተችልኝ። …… ከመደንገጤ የተነሳ መመለስ ሁሉ ዳድቶኝ ነበር። ፊቷ አብጧል። የጣት አሻራ ፊቷን ወርሶታል። …… የላይኛው ከንፈሯ በአንድ በኩል አብጧል።…… ከሰዓታት በፊት ያየኋት ውብ ሴት መሆኗን ያስጠረጥራል። ……

“እሱ ነው?” አልኳት አገኘው ይመስል እጄን ለጡጫ ጨብጬ። በጭንቅላቷ ንቅናቄ አወን አለችኝ። ምን ማለት ወይ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ገባኝ። አቀፍኳት። ጣቶቿ ላይ ያለውን ብልዝ አይቼ ከጥፊ የዘለለ እንደደበደባት ገባኝ። ……

እንዳለችኝ አርሴማ አልተኛችም። ጭራሽም እቤት የለችም። ይዟት እንደሄደ ነገረችኝ። የደበደባት እኔ በመምጣቴ ምክንያት መሆኑን ስትነግረኝ በቁሜ እግሬ ብርክ ያዘው። …… ምንም ቃል ሳልተነፍስ በሯን ዘግተን ወዳቆምኩት ታክሲ ይዣት ሄድኩ። …… ምንም ሳንነጋገር አንገቴ ስር እንደተሸጎጠች እቤት ደረስን።

ስለሰውየው ልታስረዳኝ መናገር ጀመረች። …… ቁስሏን ማባስ መሰለኝ።……

“አሁን ምንም መስማት አልፈልግም። …… ምንም ለኔ ማስረዳት አይጠበቅብሽም። እረዳሻለሁ።” ብያት ትከሻዋን ነካ ሳደርጋት አመማት።

“እዚህጋም መቶሻል?” ተናደድኩ

“ሰውነቴ እንዳለ ቁስል ነው። የተረፈ ቦታ የለኝም።” እየተናገረች እኩል አብጦ ሊጨፈን ከደረሰ አይኗ እንባዋ ይወርዳል።

” የተለመደ ነው።” አለች ቀጥላ
አንዳንዴ ፊቷ ላይ ብልዝ አይቼ እንደማውቅ አስታወስኩ… … ሁሌም ሰበቧ ወድቃ እንደነበር ነው።

የሞቀ ውሃ በርዤ አሰናዳሁላት። …… ከመተኛቷ በፊት ሰውነቷን ዘና እንዲያደርግላት።

“ውሃ አሙቄልሻለሁ። ገላሽን ልጠብሽና የሚበላ ነገር ትቀምሻለሽ።”

“ምንም አልበላም።” መለሰችልኝ

በቀስታ የለበሰችውን ሹራብ አወለቅኩት። የጡት ማስያዣ አላሰረችም። ሰውነቷ በላልዟል። የቀበቶ ግርፋት መሆኑን ብጠረጥርም ልጠይቃት አልፈለግኩም። ……

” አሁን እኔጋ ነሽ!! ነፃ ሁኚ!” አልኳት ስትሳቀቅ ስላስተዋልኩ። …… ልብሷን በሙሉ ስገፈው ሰውነቷ በሙሉ በሰንበር ተዥጎርጉሯል። …… ተጠንቅቄ ገላዋን አጠብኳት። …… ለማንም አዝኜ በማላውቀው ልክ አዘንኩላት። …… እንደምትሰበር ሸክላ አሳሳችኝ… እርቃኗን የአልጋውን ልብስ ገልጬ እንዳስተኛኋት ክንዴ ላይ እንቅልፍ ወሰዳት…… ባይነጋ… … ከእንቅልፏ ባትነቃ…… እንደህፃን ክንዴ ላይ እንደተኛች ብናረጅ…… የሚያሳሳ ገላዋን እንዳቀፍኩ የዓለም ፍፃሜ ቢሆን……

አለመታደል ነው (ክፍል ሰባት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...