(ካልፎሂያጁ ማስታወሻ የተቀነጨበ)
ዲሲ ውስጥ ፈረንጆችና አበሾች የሚያዘወትሩት ሬስቶራንት አለ። ካጠገቡ የሶማልያ ሬስቶራንት ተከፍቷል። ኢትዮጵያ ሲፈርድባት አሜሪካ ውስጥ እንኳ ከሶማሌ ጋር ተጎራብታለች።
ክፍሉ ውስጥ የተለያዩ ፊቶች ይታዩኛል ። ጭው ያለ ፊት – ከእንቅልፍ ጋር የተቆራረጠ ፊት – እናቱን የናፈቀ ፊት-ዶላር ወደ አገር ቤት በመላኩ የተከዘ ፊት – ዶላር ወደ አገሩ በመላኩ የኮራ ፊት-ወሲብ የጠማው ፊት -መከራ የተተየበበት ፊት -ለማበድ ያቆበቆበ ፊት – “ስንቱ አሳለፍኩት ስንቱን አሰብኩት ፊት” ..ወዘተረፈ ፊት- ክፍሉን ሞልቶታል። በዚህ መካከል የወይንሸት በደስታና በፈገግታ የተለኮሰ ፊቷን ይዛ ብቅ ባትል ምን ይውጠን ነበር?
“አንተ ወደ አገርህ አትመለስም?”አለች ይዛው የምታልፈውን ትሪ ጠረጴዛችን ላይ አኑራ እየሳመችኝ ። ወድያው ካጠገቤ ወደ ተቀመጠው ሰውየ ዞራ “ ቢል ቮድካ ልጋብዝህ ?” አለችው ። ቢል ያለችው በላቸውን ነው። በላቸው አልኮል በደረሰበት እንዳይደርስ ሀኪም ከልክሎታል። ግን ወይኒ ጋብዛው ማን እምቢ ይላል?? እንኳን ቮድካ የግራዋና የጡት አስጥል ቅጠል ደባልቃ ብትጋብዘው እምቢ ማለቱን እንጃ ።የወይኒ ፈገግታ የሀኪም ትዛዝ ያስረሳል። የወይኒ ፈገግታ በቮድካው ውስጥ ያለውን አልኮል ያረክሳል።
“ደስታውን አልችለውም”አለ የቀድሞ ሻለቃ በላቸው።
“ደስታውን ካልቻልከው፤እኔ በሸክም አግዝሀለሁ” አለው ካጠገቡ ቁጭ ብሎ ቢራ የሚጠጣ ድምጻዊ ፋኑኤል ። ወይኒ ሳቀችለት ፡ ሻለቃው ፋኑኤልን ገላመጠው ። ሁለቱ ወንዶች የወይኒን ትኩረት ለማጥመድ ሲሻሙ እያየሁ እዝናናለሁ።
ሻለቃ በላቸው የቀድሞ ሠራዊት መኮንን ነው።ሶማልያ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ ዘምቶ ጀብድ መፈጸሙ በታጠቅ መጽሄት ሳይቀር ተተርኮለታል ይባላል ።እሱ ሲተርከው ግን በጣም ያጋንነዋል።
“ሲያቀብጣቸው ቀን ሲጎድልባቸው ሊወሩን ቃጡ። በመጀመርያ ለማስጠንቀቅ ያክል ኦጋዴን ላይ ሰባት መቶ ሺህ ጦር ፈጀሁባቸው።እምቢ ሲሉ እስከ ሞቃዲሾ ድረስ በታንክ አባረርኳቸው። መንግስቱ ሀይለማርያም ደውሎ፤ “ በቃ ! በቃ! አንተና ታንክህ እረፉ፤ ሱማሎችም ለዘር ይትረፉ ብሎ ተማጸነኝ ። የለም ዚያድባሬንና ግልገሎቹን ባህር ውስጥ ሳልደፍቃቸው አልመለስም ብየ እስከ አፍሪካ ውቅያኖስ ድረስ አሳደድኳቸው”
“ህንድ ውቅያኖስ ማለትህ ነው?”
“ለህንድ ማን ሰጣት ? አፍሪቃ ውቅያኖስ አልኩህ “
“በጀ”
ከዛ መንጌ ባድራጎቴ መናደዱን ሰማሁ ።ይሄ ጠሞዝ ባርያ ትዛዙን ባለመፈጸሜ ዋጋየን ሊሰጠኝ ነው ብየ በታንኬ ያሳ አጥማጅ ጀልባ ለውጨ፤እልም አልኩ። አመጣጤ ወደ ኩባ ነበር። አውሎ ንፋስ ወደ ኢምፔሪያሊስቷ አሜሪካ ገፋኝ”
ወይኒ ቮድካውን በሻለቃ በላቸው ፊት እያስቀመጠች ፤ ከዛም አይና አፋሩን ፋኑኤልን እያየች፤
” ሰላሜ የሚለውን ዘፈንክን ትንሽ አንጎራጉርልኝ“ አለችው
” አይ ጉንፋን ይዞኛል ባክሽ ሌላ ጊዜ ” አለ ፋኑኤል ለመግደርደር ያክል።
”በናትህ “
”ወይኒ“ ሻለቃ በላቸው ተጣራ።
“ በናትህ ካልሽ እሺ….. እንግዲህ እህህም እህህም“ ፋኑኤል ጉሮሮውን መሳል ጀመረ።
“ወይ….ኒ !”
“ወየ ሻለቃ ቢል”
በደረቴ ውስጥ፣ ሥጋ ለሥጋ የገባች የቺቺ ጥይት ተሸክሜ እንደምዞር ታቂያለሽ?
“አትዋሽ ቢል ”
“እንደ ቶማስ ካልዳሰሽ አታምኝም መቸም ” አለና እጇን ስቦ ሸሚዙ ውስጥ ከተተው።
“ይሄ ነው?”
“እሱ ጎድን አጥንቴ ነው። ትንሽ ዝቅ በይ!፤ ትንሽ ዝቅ ፤ እሱ ጋ!“
”ነካሁት! ጀግና እኮ ነህ“ አለች እጇን ነጻ ለማውጣት እየተጣደፈች።
“በዚህ ትደነቂያለሽ? ታፋየ ላይ ተሸክሜው የምዞረውን የመትረይስ ጥይት ብትነኪ ምን ልትይ ነው”
በለው! መጥፋት ላይ ያለው የጦር ሰራዊት ጅንጀና ጥበብ !በሻለቃ በላቸው ደረት ላይ የቺቺ ጥይት የለቀቀበት ሶማሌ የተባረከ ነው። ከንቅሳትና የክትባት ምልክት በቀር በደረታችን ላይ ይዘነው የምንዞረው የክብር ምልክት የሌለን ተራ ተስተናጋጆች ሻለቃ በላቸውን በቅናት እንገላምጠው ጀመር።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ የዲጄ ሙዚቃ ክፍሉን ሞላው። የዳንሱ ወለል መአት አይነት እግር ሲርመሰመስ አያለሁ። ሦስት ዙር የሥጋ መመቀነት ወገባቸው ዙርያ የጠመጠሙ ወፈፍራም ፈረንጅ ሴቶች ከፊት ለፊት ይታዩኛል።
ብድግ አልኩ።
“የት ልቴድ ነው?” አለ ሻለቃ።
“ልደንስ”
“ባለትዳር አይደለህም እንዴ”
“እና ባለትዳር አይደንስም?”
“ወንድሜ እዚህ አገር ዳንስ እንዳገርህ እስክስታ በአንገትና በወገብ የተወሰነ እንዳይመስልህ። አንዷ ወፈፌ ትንደርድራ ትመጣና ትለጠፍብሃለች።ከዚያ መርፌ ለመወጋት የተዘጋጀች ይመስል መቀመጫዋን አዙራ ማንጠልጠያህ ላይ ለጥፋ ትታከክሃለች። አምስት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አጭር ምንሽርህን አቀባብላብህ ትሄዳለች። ጨዋ ሴት አገር ቤት ቀረ!!”
ትንሽ ቆይቶ ሻለቃ በላቸው በጉርምስና ዘመኑ ስለነበረው የፍቅር ፈተና ረጅም ዲስኩር አቀረበ።ዲስኩሩን አሳጥሬ በራሴ ቋንቋ ሳቀርበው ይህን ይመስላል።
”ያሁኑን ባላውቅም በኛ ጊዜ ከሴት ጋር ከመውጣት ካገር መውጣት ይቀል ነበር። ጎረምሳ እያለሁ የመጀመርያ ፍቅሬን ለመሳም የከፈልኩትን መስዋእትነት በሰሜን ድንበር አካባቢ ብከፍለው ኤርትራ አትገነጠልም ነበር። ትዝ ይለኛል ለምወዳት ልጅ አምባር ለመግዛት ፈልጌ ከአባቴ አስር ብር ሰረቅሁ። አባቴ ፤ “እንዴት ከኔ ከድሃው ላይ አስር ብር ጨክነህ ሰረቅህ ብሎ ምርር ካለቀሰ በኋላ የሃያ ብር በርበሬ ገዝቶ አጠነኝ ። በጊዜው ጎረቤት ለወጥ መሥርያ የሚሆን እፍኝ በርበሬ አበድረኝ ስትለው የለኝም የሚልህ ልጄን ላጥንበት ነው ስትለው አንድ ቁና ማረቆ በነጻ ያበረክትልሃል። ከወላጆህ ጭካኔ ተርፈህ እንሶስላ የሞቀ ፊት ይዘህ ጅንጀናህን ትቀጥላለህ። ሲፈርድብህ ፤ ልጂቷ ወንድም ይኖራታል። እግዜር አንዲት ቆንጆ ሴት በፈጠረ ቁጥር አብሮ ቀናተኛ ወንድም ለምን እንደሚፈጥር አይገባኝም። ወንድምየው በጉልበት የሚበልጥህ ከሆነ መስቀልኛ መንገድ ላይ ጠብቆ በጠረባ ይጥልሃል ። በጉልበት የሚያንስህ ከሆነ ደግሞ ውሻ ገዝቶ ፤ያንተን ታፋ ከእህቱ ታፋ ለይቶ እንዲ ነክስ አሰልጥኖ ይለቅብሃል። በርበሬ የታጠነ ፊት፤ የተሰበረ አፍንጫ የተነከሰ ታፋ ይዘህ ተስፋ ይዘህ፤አይሲስ ያፈረሰው ሀውልት መስለህ ጅንጀናህን ትቀጥላለህ። በመጨረሻ ይሳካልህና ልጂቷን ይዘህ ወደ ጫካ ትወርዳለህ።ጫካው ውስጥ ሣር አንጥፈህ ውዲቱን ጋደም አድርገህ ልትንበለበልባት ስትሰናዳ ፤ ባካባቢው የተመደበ ደንጠባቂ ሽማግሌ ደርሶ በወይራ ሽመል ያበራይሃል ። ለምን ?እንጃባቱ! ደን ጠባቂው በመንግሥት የተመደበው ደን እንዲጠብቅ ነበር፤በራሱ ጊዜ ያካባቢው ኮረዶች ድንግልና ጠባቂ ሆኖ ይሠማራል”
One Comment
abo beweketu endante ayent merte sehafi yetme ayegegnm