Tidarfelagi.com

የአውሮፕላን ታሪክ በኢትዮጵያ 

የመጀመሪያው አውሮፕላን በ1921 ዓ.ም. አዲስ አበባ መድረስ ለኢትዮጵያውን ከውጭው ዓለም ጋር ለመገናኘት አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ቀን መሆኑ አስደስቷቸዋል፡፡ ለፈረንሳዮቹ ደግሞ በኢትዮጵያ አቪዬሽን ታሪክ ከሌሎች አገሮች በተለይ ዝግጅቱን አጠናቆ ከነበረው ጀርመን መቅደማቸው አስፈንድቋቸዋል፡፡ ለአብዛኛው ኢትዮጵያ ግን የአውሮፕላን መምጣት ግርምትና ትዕንግርት ፈጥሮበታል፡፡

‹‹ከቶ ምን አሳየኝ ይሠሩትን ያጡ
ጠንቀቅ በል ጌታዬ ወደ አንተም ጋር መጡ›› ብሎ እስኪዘምር ድረስ፡፡ መንገድ ሳይሠራለት፣ ሐዲድ ሳይነጠፍለት በአየር ላይ ተንሳፎ የመጣው ያን አውሮፕላን የአየር ባቡር የሚል ስም ወጣለት፡፡ በዚህ ሁኔታ ነበር የዛሬ 87 ዓመት በኢትዮጵያ የአቪዬሽን ታሪክ የተጀመረው፡፡

በኢትዮጵያ አቨየሽን የተጀመረው ንጉስ ተፈሪ በገዟቸው 3 ፈረንሳይ ስሪት ፖቴዝ አውሮፕላኖች ነው፡፡ አንደኛዋን ፈረንሳዊው ሙሴ አንድሬ ማዬ ከጅቡቲ በማብረር ነሀሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም “ስጋ ሜዳ” አውሮፕላን ማረፊያ ከቀኑ 7 ሰዓት ከ 10 ደቂቃ ላይ ባሳረፈበት ወቅት ነው፡፡ አውሮፕላኗም “ንስረ ተፈሪ” ተብላ ተሰየመች፡፡ ጅቡቲ ቀርተው የነበሩትን ሁለቱን ፖቴዝ አውሮፕላኖች አንዷን ካፕቴን ማዬ ፣ ሁለተኛዋን ደግሞ ጀርመናዊው ካውንት ሼዝበርግ እያበረሩ መስከረም 12 ቀን 1922 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ አመጧቸው፡፡ እነዚህ አይሮፕላኖች ከመጡ በኋላ “ንስረ አስፋወሰን” እና “ንስረ መኮንን” የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ከዚያም የፈረንሳይ ተፎካካሪ የነበረው የጀርመኑ ጀንከርስ (Junkers) አውሮፕላን በባሮን ሻን ኢግል አብራሪነት በከተማዋ ውስጥ ጃን ሜዳ አረፈ፡፡ በጃንሜዳ ውስጥ በማረፉ ከፈረንሳዩ አውሮፕላን የበለጠ በርካታ ተመልካች እንዲኖር አድርጐታል፡፡

የመጀመሪያ የአገር ውስጥ በረራ ጀንከርስ አውሮፕላን አዲስ አበባ ከደረሰ አንድ ወር በኋላ ነበር የአገር ውስጥ በረራውን የጀመረው፡፡ ያ ጉዞው የመጀመሪያው የአገር ውስጥ በረራ መሆኑ ነው፡፡ ያልተሳካው የመጀመሪያው በረራ ሊባልም ይችላል፡፡ ጀንከርስ የመጀመሪያ የአገር ውስጥ በረራው ወደ ጐን ሲሆን ተልዕኮውም የኢሊባቡር ጠቅላይ ገዥ የነበሩትን ራስ ናደውን ለማምጣት ነበር፡፡ ይህም አውሮፕላን በኢትዮጵያ በሽተኛ ለማጓጓዝ ሲበር የመጀመሪያው መሆኑ ነው፡፡ ራስ ናደው በጽኑ ታመው ነበርና የሚተኙበትን አልጋና ፍራሽ ጨምሮ ወደ ዋና ከተማቸው ጐሬ በረራውን ቀጠለ፡፡ ነገር ግን በአየር ሁኔታው አመቺ አለመሆን ምክንያት ተመልሶ እንድብር አካባቢ ለማረፍ ተገደደ፡፡ በማግስቱም ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡

በኢትዮጵያ በ1922ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ የመጀመሪያው የአውሮፕላን በረራ ት/ቤት በፈረንሳዊው ሙሴ ጋስቶን ቨርዲየር መምህርነት ተቋቋመ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያውን የአውሮፕላን በረራ ስልጠና የወሰዱት ኢትዮጵያውያን፡-

1. አስፋው አሊ
2. ሚሽካ ባቢችፍ /በአባት ሩሲያዊ በእናት ኢትዮጵያዊ/
3. ስዩም ከበደ
4. ባህሩ ካባ
5. ደምሴ ኃይለኢየሱስ
6. ደመቀ ተክለወልድ
7. ወ/ሮ ሙሉመቤት እምሩ ናቸው፡፡

eth_first_pilot_trainee

አስፋው አሊ እና ሚሽካ ባቢችፍ በመጀመሪያ ስልጠናቸውን በማጠናቀቅ ጥቅምት 3 ቀን 1923ዓ.ም ከንጉሰ ነገስቱ እጅ የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡ ት/ቤቱም ስራውን የጀመረው በሁለት አውሮፕላኖች ነበር፡፡ በኢትዮጵያ አቭዬሽን ታሪክ የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን አውሮፕላን አብራሪዎች አስፋው አሊ እና ሚሽካ ባቢችፍ ናቸው፡፡ ሁለቱም የብቻ በረራቸውን ያካሄዱት በ1923ዓ.ም ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ1935 የታተመው የአሜሪካ ጋዜጣ ስናፒ ላንዲንግ ሌዲ በርድ የሚል አድናቆት የሰጣቸው ወ/ሮ ሙሉመቤት እምሩ የመጀመሪያዋ የሴት አውሮፕላን አብራሪ ናቸው፡፡ የመጀመሪያውን የብቻ በረራ ያካሄዱት በ1927ዓ.ም ነበር፡፡ ወ/ሮ ሙሉመቤት እምሩን አውሮፕላን መንዳት በማስተማር ታሪክ የመጀመሪያይቱ አፍሪካዊትም እንዲሆኑ ያስቻሏቸው ኮለኔል ጄ.ሲ.ሮ.ቢንሰን የተባሉ ጥቁር አሜሪካዊ ናቸው፡፡

ምንጭ፡-
ethiopiaanything.com

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...