Tidarfelagi.com

በአልጋው ትክክል (ክፍል 19)

ልእልትን አፍቅሪያታለሁ !! ግልግል!! ይህንን ቃል ለመናገር ይህንን ምርኮኝነቴን አምኘ እጀን ለማንሳት ከራሴ ጋር ስታገል ስንትና ስንት ቀኔ … አውቃለሁ ባለትዳር ነች …ትዳሯ ቅጥአምባሩ ቢወጣም ልእልት ባለትዳር ናት ! ትዳሯ እንዳለቀለት ባውቅም ያው ባለትዳር ናት ! ባለትዳር!!! …በሰውም በፈጣሪም ፊት አንድ ወንዴ ለሚባል ወንድ ሚስት መሆኗን ቃል የገባች ሴት መሆኗን ጣቷ ላይ ያለው ቀለበት እጇ በተንቀሳቀሰ ቁጥር እየጮኸ ቢነግረኝም ….ልእልትን ግን አፍቅሪያታለሁ …!!
(((ፍቅር በሞተበት ትዳር ውስጥ ቀለበት የቃልኪዳን ምልክት ሳይሆን ከወርቅ የታነፀ የሰቆቃ ህይዎት ሃውልት ነው !! የግፍ መታሰቢያ !!))) አሁን እንደባሏ ክፋት ቢሆን የልእልት ውብ ጣት ላይ ያለው የቃልኪዳን ቀለበት …(ልጅቱ ልእልት ሁና እንጅ) ገና ድሮ ተወልቆ የቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ መጣል አልነበረበትም ? ! ግን የቃል ኪዳን ቀለበት የሰው ብቻ ሳይሆን የፈጣሪም እማኝነት ያለበት ህያው ቃል ነውና በልእልት ዙሪያ የሽቦ አጥር ሁኖ መግቢያ ቀዳዳ እንዳጣ ሌባ ዙሪያዋን ያዞረኛል ….!!
የትኛውም የሞራል ህግ በፊቴ አቅመቢስ የሆነብኝ … የልእልትን አይኖች ሙሉ ቀንና ሌሊት ማየት እንደአንዳች ሱስ የሚናፍቀኝ ስላፈቀርኳት ነው !! የልእልት አይኖች ሲያርፉብኝ አንዳች የማልገልፀው ናፍቆት የሚጨመርብኝ ስላፈቀርኳት ነው …. አይኗን ማየት ፈራሁ ….እየፈራሁ አይኗን ማየት ናፈኩ ….እየናፈኳት ደግሞ አልደውልላትም …. ለራሴ የገረመኝ ባለፈው ቢሮየ ቁጭ ብየ ስልኬን አነሳሁ ….ለልእልት ልደውል ….እና እጀ ተንቀጠቀጠ ማመን አልቻልኩም ሳያቋርጥ ነበር የሚንቀጠቀጠው ! መደወሌን ተውኩት ….እጀም መንቀጥቀጡን አቆመ ! አሁን ይሄን ነገር ፊልም ላይ ባየው …ምን ያካብዳሉ አልልም ነበር ?….እላለሁ እንጅ !!! ዘንድሮ ምን ጉድ ነው ከሰላም ኑሮየ እያንቀለቀለ እንዲህ አይነት ችግር ውስጥ ያስገባኝ በ,ግዚአብሔር !
የሆነ ጭንቀቴ ወሰን አጣ ….ፍቅር የነፍስ ጉዳይ ነው አይደል ….. ነፍሴ ዝሆን የሚያክል ፍቅር ካለአቅሟ ውጣ ስትወጣጠርና ስጋየ ሲጠባት ይሰማኛል ….የሆነ በጭንቀት የምፈነዳ መስሎ ይሰማኛል …. ያ የተረገመ ወንዴ ስጋየን በቢላ ቀዶ ፍቅር የሚባል አየር ሞልቶ መልሶ የሰፋኝ እስኪመስለኝ ውስጤ እንደባሉን ውጥርጥር ሲል እና የተንሳፈፍኩ ሲመስለኝ ይሰማኛል ….ደግሞ የማያቋርጥ የራስ ምታት ያጣድፈኛል …ቤተሰቦቸን ማየት አስጠላኝ ….ጓደኞቸን ማየት አስጠላኝ … ስራየ ሁሉ አሰልች እየሆነብኝ መጣ ….(ይሄኔ ነው ፍቅር ጉሮሮየ ላይ ሊቆም ሽቅብ እየተናነቀኝ መሆኑ የገባኝ ) ቢገባኝ ምን ዋጋ አለው ….ምንም መፍትሄ የለኝማ …
የማነው ደፋር ለመሆኑ ፍቅርን ((የሚጣፍጥ ስቃይ)) ብሎ የተፈላሰፈው …በምን ምላሱ ቀምሶት ነው የጣፈጠው ?ወይስ ወሬ አሳመርኩ ብሎ ነው ….ወሬኛ !! እንዴት እንደሚመር እንደሚያንገሸግሽ ….የኔን የራሴን ፍቅር ግለፅ ብባል …የሆነ እጅግ መራር የሆነ ነገር ምላስ ላይ አስቀምጦ መዋጥም መትፋትም አለመቻል አይነት ስሜት መሆኑን በተናገርኩ ነበር ….በቃ ልእልት ልእልት ….ልእልት ብቻ …..ልእልኮ አስተያየቷ አነጋገሯ እያንዳንዷ እንቅስቃሴዋ አሳሳቋ ሃዘኗ ሁሉ ነገሯ ለስላሳ ሚሳኤል ነው …..ትኛውንም ጠንካራ ልብ በርግዶ አፈራርሶ የሚገባ ! አሁን ምናባቴ ነው የማደርገው …..
እንዲህ ስጨነቅ ይች እንደመለአክ ከተፍ የምትል እህቴ ደወለችልኝ ….. የእህቴን ድምፅ ስሰማ የተሰማኝን ሁሉ ዝርግፍ አድርጌ ነግሪያት እንደሴት ስቅስቅ ብየ ባለቅስ ብየ ሁሉ ተመኘሁ ! ግን ወዲያው ምን መንፈስ እንዳረፈብኝ እንጃ ….ኮስተር ብየ ማናገር ጀመርኩ (ምንም እንዳልተፈጠረ …ሃሃ ከተፈጠረልኝ ነገር አንድም አልቀረምኮ ሁሉንም ልእልት ወስደዋለች)
‹‹ጎረምሳው ጠፋህ›› አለችኝ ! አነጋገሯ የሶስት ጊዜ ታላቄ እንጅ በሁለት አመት የምበልጣት ታናሸ እህቴ አትመስልም …..
‹‹አለሁ ባክሽ …. ››
‹‹ባክሽን ምን አመጣው ታዲያ ?››
‹‹ ድካም ነዋ››
‹‹ ፓ! ‹ስታርስ ነው ስትጎለጉል› አለች ማሚ …..ቁጭ ብሎ የሰው ሚስት ማሰብ ምን ያደክማል??››
‹‹እሽ ለምን ደወልሽ …?››
‹‹ባክህ አትኮሳተር እዛ … የምትችለውን ምታ ቢሉት አሉ ወደ……….›› ተረቱ ጠፋት ነገር ለማሳጠር ብየ
‹‹ወደሚስቱ ሮጠ ›› ብየ የጀመረችውን ተረት ጨረስኩላትና ‹‹እ ምን ልታወሪኝ ነው ?›› አልኳት
‹‹ ሂሂሂሂሂሂ ሚስት ነክ ተረቶች ላይ ብቃትክ ጨምሯል ….ወደሰው ሚስት ሮጠ ትላለህ ብየ ነበር ሂሂሂሂ ›› ዝም አልኩ …
‹‹ ነገ ምን ፕሮግራም አለህ ?››
‹‹ያው ስራ ነዋ ››
‹‹ቅዳሜኮ ነው ››
‹‹ኦ ረስቸው …በቃ እቤት ነው የምውለው ››
‹‹ሃሃ ቀኑ እስኪጠፋህ ጢምቢራህ ዙሯል ….ቀጥሎ ስምህ ይጠፈሃል ….ከዛ እየደወልኩ አስታውስሃለሁ ! ሂሂሂ እእእ …..ነገ ሳምሪ ምሳ ጠርታናለች ….እና ያ ጅል ወንድምሽ እንዳይቀር ንገሪው ብላኛለች …››(ሳምሪ ጓደኛዋ ናት እኔም ጋር እንቀራረባለን)
‹‹አይ አይመቸኝም …..›› አልኩ ስልችት ብሎኝ …እንደውም ነገ አርብ መስሎኝ ነበር ….ቅዳሜ ከሆነማ እቤቴ ለጥ ብየ ማሳለፍ ነው እያልኩ በማሰብ ላይ ነበርኩኝ ……ይሄ ሳምንት እንደመርግ ነው ተጭኖኝ የነበረው … ደግሞ ዝም ብሎ ራሴን ያመኛል …
‹‹ አብርሽ ሰው አክብሮ ሲጠራህማ አትባልግ ›› ድምፅዋ ውስጥ ማለማመጥ አለ ….በዚች ምድር ላይ ‹‹አትባልግ›› የሚለውን ቃል በጨዋ ድምፅ ተናግራ ምርቃት የምታስመስል ብቸኛ ሴት እህቴ ትመስለኛለች !
‹‹እግዜር ያክብርልኝ ….ግን አይመቸኝም …›› አልኩ ቆጣ ብየ …..(እስቲ አሁን ምን አስቆጣኝ) እናም ‹‹ቻው ›› ብያት ስልኩን ዘጋሁባት ….<<ምሳ>> ትላለች እንዴ ….ከሳምንት እስከሳምንት ልፋት…. በዛ ላይ የልእልት ነገር አዛ አድርጎኛል …ለምን እንደሆነ ደግሞ እንጃ በእነዚህ ሁለት ቀናት አልደወለችም …ስልኬን አንስቸ ደወልኩላት !(እንዴ ደወልኩላት ለልእልት ) አንዳንዴ እጅ ከአእምሮም ይፈጥናል …. ዛሬ ምን አጀገነው መንቀጥቀጥ የለ ምን የለ …..ደግሞ ቁጥሩን ሲጠቀጥቀው ፍጥነቱ ….(የሚገርመኝኮ ስልክ በቃሌ አልይዝም… የቢሮየን ስልክ እንኳን ‹ኦፊስ› ብየ ሴቭ አድርጌ ነው የያዝኩት ቁጥሩን አላውቀውም ….የልእልትን ስልክ ደግሞ ሴቭ አላደረኩትም ግን ልክ እንደራሴ ስልክ ነው በቃሌ የማውቀው) እንጅማ ለልእልት መደወል ሳስብ አእምሮየ የማያግተለትለው ሃሳብ አልነበረም …. !!
‹‹አ ብ ር ሽ የ ›› አለችኝ ! ድምፅዋ ውስጥ ስርቅርቅ የሚል ደስታ አለ …. የዚችን ልጅ ድምፅ ስሰማ ውስጤ የሚሰርግ ሰላም አለ … የሆነ ልቤ የድምፅዋ ባህር ውስጥ ተነክሮ የወጣ ስፖንጅ ይመስል ሙሉውን ቅላፄዋን ምጥጥ ነው የሚያደርገው ! ብቸኝነት ድሮም ድርቀት አይደል ! የደረቀ ልቤ አንዳች ለብ ያለ ውሃ የተሞላ ገንዳ ውስጥ የገባ ነው የሚመስለኝ …..
‹‹ልእልት ›› አልኳት ስሟ ላይ ‹የ› ልጨምርበት ነበር ….እንደምንም ነው ከከንፈሬ ላይ የመለስኳት ‹የ›ን !
‹‹ አ….ሁን እያሰብኩህ ነበር የደወልከው አይገርምም …›› አለች ከልቧ በሆነ ስሜት ….መታሰብ እንዴት ደስ ይላል ….ከምር ‹‹ሳስብህ ደወልክ›› እንደመባል ለወደደ ሰው የሚያስፈነድቅ የመግቢያ ሰላምታ የለም ! ከሆነስ ሆነና ልእልት ስታስበኝ ምኔን ታስበው ይሆን …እኔ እንኳን ከአስር የእጅ ጣቶቿ (ያውም ስለትንሿ ጣቷ ብቻ ) አንድ ሙሉ ቀን ማሰብ እችላለሁ ….!ከምር እችላለሁ ! ልእልት ማለትኮ ሙሉ አካሏ ቱባ ነው ….ማንም ቁጭ ብሎ ሲመነዝር መዋል ይችላል ….ይችን ልጅ ጎበዝ ገጣሚ በታክሲ ሲያልፍ እንኳን በውልብታ ቢያያት በሳምንቱ መፅሃፍ ይዞ ማተሚያ ቤት የሚገኝ ነው የሚመስለኝ !!

ኧረ ደግሞ ስለልእልት ላስብ ከተባለ ….አእምሮየ ራሱ ደስ ብሎት ሌላ ስራውን ሁሉ እርግፍ አድርጎ ትቶ ነው የሷን ነገር ሲያመነዥክ የሚውለው !! ግን ልእልት ስለኔ ምን ልታስብ ትችላለች ?…በደንብ አስተውላ ያየችኝ እንኳን ሆስፒታል ነው … የግልኮስ ቲዩብ የተሰካበት ክንዴን ይሆን ቀድማ የምታስታውሰው ? …ባሏ እንደጎመን በቢላ የቀረደደው ቆዳየን ይሆን ዝግንን ብሏት የምታስበው ? ….ዝም ብየ እየተቁለጨለጨኩ እሷን ማዳመጤን ይሆን ?…ምኔን ነው የምታስታውሰው ?… ምኔ ነው የሚታወሰው ….ለነገሩ እንኳን ልእልት እኔ ራሴ ስለራሴ ሳስብ ምንም ትዝ አይለኝም …ከመሬት ተነስቶ ባዶነት ይሰማኛል … ምንጊዜም በትንሹ እንኳን የተደሰትኩባቸውንና የረካሁባቸውን አጋጣሚዎች ለማደፍረስ ‹‹ከዛስ›› የሚል ጥያቄ ከአእምሮየ ውስጥ አባርቶ አያውቅም !
ዛሬም ይሄ የተረገመ ጥያቄ አእምሮየ ውስጥ ፈነዳ ‹‹ልእልት ቀለበቷን አውልቃ ወርውራ አብርሽየ በቃ ካንተ አልለይም እንደፈለክ አድርገኝ ይዘኸኝ ከዚህ አገር ጥፋ ወይ አጥፍተኸኝ ጥፋ ወዘተርፈ ….ብትልህ ምንድነው የምታደርጋት ›› ይለኛል አእምሮየ …እውነትኮነው ምንድነው የማደርጋት ….. መቸም ህይወት ተረት ተረት አይደል ‹‹ከዛ በኋላ አብረው በፍቅርና በሰላም ይኖሩ ጀመር ›› ተብሎ አይዘጋ ነገር ….!!
አገሩ አዲስ አበባ …ልጅቱ ልእልት…..ሰውየው እኔ ኑሮየ ወር ደመወዝ ጠባቂ …..ልእልትን ባገባት እንደህንድ ፊልም ጫካ ሂደን ስንዘፍንና ውሃ ስንራጭ ውለን ስንመለስ ቤተመንግስት የመሰለ ቤት ተዘጋጅቶ አይጠብቀን ….የቤት አከራይ ነው የሚጠብቀን ….ሰው ሞኝ ነው …‹‹ብር ንቃ ፍቅር ተርባ ነው የመጣችው›› ይል ይሆናል …..(ማለት ቀላል ነው መኖር ነው ከባድ) ሰው የሌለው ነገር ነው የሚናፍቀው …..ብርም ፍቅርም ነበራትኮ ልእልት …..እንደፀረ ሙስና ኮሚሽን የባሏ የሃብት ምንጭ ይጣራ ….ነጋችን በላባችን ፍሬ ላይ ይቁም ማለቷ ነው ህይወቷን ያተራመሰው ….ምን ለውጥ አለው ባገባት ስራ የላት ምን የላት ያው በእኔ ደመወዝ መኖሯ አይደል እንዴ ….እና የወንዴ የቅንጦት ጥገኛ ከመሆን ወጥታ የእኔ የድህነት ጥገኛ መሆን ለውጡ የቁጥር እንጅ ሌላ ምንድነው ….

በነገራችን ላይ ጭንቀቴ እንዳለ ሁኖ ……ትዳር የሚባለውን ነገር እንደቀትር ጋኔል የምፈራው ሰውየ ‹‹ልእልትን ባገባት›› ብየ ሳስብ ገና አፌ ላይ ቃሉ ጣፈጠኝ ….ያንን መራራ ጎምዛዛ ግራ የገባው ፍቅር ጣፋጭ ነገር ሞላው ….ሰውን ውለድ ክበድ ብሎ ከመመረቅ እና ከመምከር …‹‹ከባድ ፍቅር እንደናዳ ይጫንህ ›› ብሎ መምከር ሳይሻል አይቀርም…ፍቅር ልክ ያስገባው ወንድ ተንቀልቅሎ ነው ትዳር ውስጥ ባናቱ የሚገባው …..እንደው የቀን ህልም አይሁንብኝና ….ስከፍተው ቅዝቃዜው የምድር ዋልታን የሚያስንቅ ቤቴ ውስጥ ከውስጥ የልእልት ፈገግታ ሲጠብቀኝ ማሰብ ምን ያህል ደስ እንደሚል ማን ሊገምተው ይችላል …. በዛ ላይ እሷን የመሳሰሉ ስምንት ልጆች መውለድም አለ ….ትጎዳብኛለች ብየ እንጅ እኔማ አስራአንድ ልጅ ነው የምፈልገው ….ቀልድ አይደለም ….በዚች ምድር ላይ በጣም በብዛት እንዲኖረኝ የምፈልገው ነገር ቢኖር ልጆች ናቸው …እግዚአብሔር ብዙ ብር እንዲሰጠኝ የምመኘው ብዙ ልጅ ወልጀ ማሳደግ እንድችል ነው ….. ለሰው ተናግሬው አላውቅም እንጅ ሰዎች ሁለት ልጅ ወልደን ምናምን ማሳደግ ሲሉ(የደሃ ምኞት እላለሁ) አስራ አንድ ልጅ …ልእልት ጋር ደርዘን !! ይሄ ነው ቤተሰብ ማለት !! ወላ ቤተ ስብሰባ ይባል !! የልእልት ድምፅ ከቁም ህልሜ አባነነኝ !
‹‹እንዴት ነህ ጠፋሁኝ አይደል ››አለችኝ …ድምፅዋ ውስጥ እኔን የመጠየቅ ሃላፊነት ያለባት ይመስል እራሷን መውቀስ ነበረበት
‹‹ ልደውል እያሰብኩ ስራ በዛብኝ ….›› ብየ ወቀሳውን ወደራሴ አዞርኩት
‹‹ አሁንኮ ሲስ ደውላልኝ (ሲስ የምትለው እህቴን ነው) ነገ ጓደኛዋ ቤት ምሳ መጋበዜን ነግራኝ በቃ እዛው እንገናኛለን እያልኩ ሳስብ ነበር ››
‹‹ተይ እንጅ ደወለችልሽ ….ትመጫለሽ ?…..›› አልኳት ሰፍ ብየ ….
‹‹አዎ ….አንተም እንደምትመጣ ነግራኛለችኮ ›› አለችኝ …. (የተረገመችና የተመረቀች እህት …..እንደው ማዘር የኔ አይነቱን እንከፍ ትታ የሷ አይነት የተረገሙ አንድ ሶስት ልጆች ብትጨምር….)
‹‹አ…..ዎ …አዎ እሄዳለሁ በቃ እዛው እንገናኝ …›› የልእልትን ስልክ እንደዘጋሁ በደስታ ሳስብ ቆየሁና ለእህቴ ደወልኩላት ….ስልኳ ተይዟል …ቆይቸ ደወልኩ
‹‹ እ ›› አለችኝ ….ድምፀዋ ውስጥ ማሾፍ አለ
‹‹ ለሳምሪ አይመጣም ብለሽ እንዳታስቀይሚያት እንሄዳለን በቃ …. ››
‹‹ ተ……….ው እንጅ ወንድማለ…….ም !! ሳምሪ እንዳትቀየም ነው እንዲህ በብርሃን ፍጥነት ሃሳብህን የቀየርከው ?….ሂሂሂሂ››
‹‹እና?…ከፈለግሽ እቀራለሁ እሽ ››
‹‹እሽ !! ግን ለልእልት አሁን ደውለህ እንደምትመጣ ነግረሃታልኮ….ወንድ ልጅ ደግሞ ደሙን ላፈሰሰላት አጥንቱን ለከሰከሰላት ልጅ ….ቃሉን አያጥፍም …. ሂሂሂሂሂ›› ብላ ሳቀች …. ጆሮዋ ላይ ዘግቸባት በረዥሙ ተነፈስኩ … ፈገግታ ፊቴ ላይ እንደፅጌሬዳ አበባ ሲፈነዳ ይሰማኛል !! ያንን የአዲስ አመት ርችት እዚህ መስሪያ ቤት አምጥቸ ባፈነዳውም ሲያንስ ነው እንኳን ፈገግታ !
*** **** ****
በስማም !! ይች ልእልት የምትባል ልጅ ችግሯ ምንድነው በግዚአብሔር …..እንዴት ነው ዛሬ ደግሞ ያማረባት …ቆይ ልብስ በቀየረች ቁጥር እኔ ልቤ ተሰነጣጥቆ ማለቅ አለበት እንዴ ….ደግሞ በዚህ ላይ ስታየኝ ፈገግታ ትጨምርበታለች (ግዴለም ሌላም ጠላት የለኝም እኔ ገዳየ እህቴ ነች )
‹‹አብርሽየ …››ብላ ጥምጥም አለችብኝ ልእልት …ልክ የሚሰበር እቃ እንደሚይዝ ሰው በቀስታ እጀን ጀርባዋ ላይ አሳርፌ አቀፍኳት ፀጉሯ አዲስ ስለተሰራ አዲስ የተጠኮሰ አይነት ሽታ አለው ….አፍንጫየ እስከቻለው ጠረኗን ከፀጉሯ ከሽቶዋ ጋር ሳብኩት …..ፍስሃ !! የሆነ የሚያሰክር ጠረን ….!!
በዛ ላይ ጡቶቿ ደረቴ ላይ እንደትራስ በስሱ ተጨፍልቀው ሲመለሱ ልቤን ይዘውት የተመለሱ እስኪመስለኝ ውስጤ ባዶ የሆነ መሰለኝ እቅፍ እንዳደረኳት ብኖር ደስታየ …. የእህቴ ጓደኛ ሳምሪ ጥሩ ልጅ ነች አንድ መስሪያ ቤት ነው የሚሰሩት …. ቆንጆ ቤት አላት የቤተሰቦቿ ነው ….ሰጥተዋት አሜሪካ ይሁን ምናምን ሄዱ(የፈለጉበት ይሂዱ ምናገባኝ ) ታዲ እኔና ልእልትን እህቴና ሳምሪ አስተናገዱን ….አሪፍ ምሳ ጋበዙን (ልእልት ስትበላ አያታለሁ …አቤት ጉርሻወቿ አተናነሻቸው ….ፈርታ መስሎኝ ነበር ግን የሁሉም ጉርሻወቿ መጠን እኩል መሆናቸውን ሳይ እንዲህማ ሳይፎርሹ ማስመሰል አይቻልም ብየ በቃ የልእልት ጉርሻወች እንደዚሁ መሆናቸውን ታዘብኩ ….ድንገት ሳያት ቀና ብላ አየችኝ ተገጣጠምን … ደንገጥ ብላ መልሳ ፈገግ አለች ….አፍሬ ‹‹ብይ›› አልኳት ….በዚያው ፍጥነት እህቴ ቀና ብላ ስታየኝ በአይኔ ግራ በኩል ይታየኛል ….ሳላያት ፊቷ ላይ የሆነ የማሽሟጠጥ ፈገግታዋ ይታየኛል (እንግዲህ አመለጠኝ ምን ይሁን )
ቡና ተፈልቶ እንደጠጣን …እህቴና ጓደኛዋ ሳምሪ ለመሄድ ተነሱ ….(ኧረ ጉድ እንዲህ እሳት ላይ ጥለውኝማ አይሄዱም) ተገርሜ እህቴን አየኋት ….እንደውም ልእልት ይደብራታል ብየ ቀና ብየ አየኋት ፈገግ ብላ ….(ጥርግ በሉ በሚል አይነት ፊት) ታያቸዋለች ….የእህቴ ጓደኛ ‹‹በሉ ተጫዎቱ ጉዳይ አለን…. ስትሄዱ ከደወላችሁልን ወደፒያሳ አንጠፋም ›› ብላን ወጣች …እህቴ ወደኋላ ቀረት ብላ ቦርሳዋን ፈተሸችና …ቁልፍ አውጥታ ….‹‹ ልእልትየ በቃ መሄዴ ነው የኔ ቆንጆ እንደነገርኩሽ ›› ብላ ቁልፉን አቀበለቻት (እንደነገርኩሽ ??…..ምንድነው እዚህ ቤት የሚሰራው ነገር ….??)

እኔና ልእልት ብቻችንን ቀረን …. ቤቱ ከልእልት ላይ በሚነሳው ለስላሳ ሽቶና ….ቡና ሲቀዳ በተጨሰው እጣን ቅሪት ጠረን ….ተሞልቷል …..ህልም በሚመስል ሁኔታ እኔና ልእልት ጉልበታችን ሊነካካ ትንሽ ቀርቶት ፊት ለፊት ተፋጠን ተቀምጠናል ….(ከጉልበቷ እስከጫማዋ ያለው እግሯ እርዝመት ይገርመኛል ) ሶፋ ላይ !እነዛ የተረገሙ እህቴና ጓደኛዋ መሃላችን ለቡና ብለው ሳብ አድርገውት ጠረጴዛው እንኳን የለም ….(ሜዳውንም ፈረሱንም ሳሎን ጥለውት ጠፉ)
‹‹ እሽ አብርሽ እንዴት ነበር ሳምንትህ ›› አለችኝ ልእልት ዝምታውን ለመስበር ሳይሆን ከልቧ እንደሆነ በሚያስታውቅ …..ድምፅ …እኔ ጋር ማውራት ደስ እንደሚላት ከገባኝ ቆይቷል ….ግራ የገባኝ ….ይሄ ፍለጎቷ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ነው …‹‹ፍቅር›› እንዳልል እህቴን የምታወራበትና እኔን የምታወራበት ፊትም ድምፅም አንድ አይነት ነው …..(ልእልት በግዚአብሔር ዘለሽ እቀፊኝና በፍቅሬ ማበድሽን ንገሪኝ እላሁ በውስጤ ….እንደወንድ ፈሪ ፍጥረት በዚች ምድር አለ ግን ….ዝም ብለን እኮ ነው ያዙኝ ልቀቁኝ የምንለው …እስቲ ይችን የመሰለች ውብ ልጅ ፊት ለፊቴ አስቀምጨ በሃሳብ መዛበር ምን ይባላል ….አፈቅርሻለሁ ማለት ምን ቁም ነገር ሁኖ ነው እንዲህ ውስጤ የሚናወጠው)
‹‹ ደባሪ ሳምንት ነበር ›› አልኩ ….( በለው ! ለምን እንዴት ካለችኝ ከንፈሬ ላይ ያለው ምላሽ አንድና አንድ ነው መቸም …..ድምፅሽን ስላልሰማሁ …..ስለናፈቅሽኝ …ልእልት ካላንች ሁሉም ነገር ስቃይ ነው …..ማለት ነው ያማረኝ በቃ !! )
ልእልት ግን ዝም ብላ ምንጣፉን ስታይ ቆየችና ….‹‹እኔም አጉል ለምጃችሁ እቤት ቁጭ ስል እየናፈቃችሁኝ ›› አለች ….እኛ እነማነን ….እኔና እህቴ መሆናችን ነው ….ልእልት እባክሽ ለይተሸ ተናገሪ …..የምን እናተ ነው … አሁንስ እንደጃንሆይ ‹‹እኛ›› ማለት እኔ ብቻ በሆነ ብየ ተመኘሁ ትክ ብየ አየኋት …ልእልት ቆንጆ ናት ….እግዚአብሔርን ምንም ቃል የማይገልፃት ቆምጆ ናት ….ከነቃል ኪዳን ቀለበቷ ቆንጆ ናት …… ቀና አለች …አይኖቻችን ተገጣጠሙ …… ከኋላየ የሆነ ሰው ቁሞ በሁለት እጆቹ ግራና ቀኝ የያዘኝ ይመስል ወደግራም ወደቀኝም መዞር አልቻልኩም ልእልት ላይ እንዳፈጠጥኩ ….ቀረሁ ….ልእልትም ዝም ብላ አየችኝ …… አይኖቿ እናባ የኳተሩ ይመስላሉ ….
ልእልትን አፍቅሪያታለሁ ….. ያፈቀርኳት ልእልት ይቻትና ፊት ለፊቴ ….ግንኮ ከምር ልእልት በትክክል የእኔ ሚስት ለመሆን የተሰራች ሴት ነች !! ….በሆነ ስህተት ነው እዛ ወንዴ ጋር ሂዳ የነበረችው ….. በምን አወክ ላንተ መፈጠሯን ሊባል ይችላል …. የሆነ ጎኔ አካባቢ ….ያሉ አጥንቶች …አፍ አውጥተው …..‹‹ጓደኛችን ተገኘች ›› እያሉ ሲፈነደቁ ይሰማኛል ….. ግነት አይደለም …. ሰው ጎኑ ላይ ብቻ ሳይሆን ልቡም ላይ ትልቅ ክፍተት ይዞ የሚኖር ፍጥረት ነው ….ያ ክፍተት በእይታ ብቻ ልኩን ሲያገኝ የሚሰማው ሙሉነት አለ ….ልእልት ሙሉ ስታደርገኝ ይሰማኛል …..

አይኖቿን ወደምንጣፉ መለሰቻቸውና አቀርቅራ ዝም አለች …. ትንሽ ወደግራ ዘንበል ብላ በግራ ክንዷ የሶፋውን ጠርዝ ደገፍ አለች …ዳሌዋ ወደቀኝ ሰፋ ያለ ቦታ ይዞ ደረቷ ወደውጭ ወጣ አለና እነዛ ውብ ጡቶቿ የፍቅር ቤተመንግስት እንደሚጠብቁ የበር ዘቦች ቀጥ ብለው በተጠንቀቅ ቆሙ ….ከምኔው የተለየ ውብ አቀማመጥ ፈጠረች ?….ትንሽ በተንቀሳቀሰች ቁጥር ትልቅ ውበት የምትጨምር ጉድ!! ….ዝም ብየ አያታለሁ(ጅል ካመረረ አሉ) የግራ እጅ ጣቷ ላይ የቃል ኪዳን ቀለበቷ ያብረቀርቃል ….ቀለበቶቹ የተደራረቡ አንድ ባለፈርጥና አንድ ‹ኖርማል› የጋብቻ ቀለበቶች ናቸው ….እንደበፊቱ አላስፈሩኝም …

አዎ ….ፍቅር በሞተበት ትዳር ውስጥ ቀለበት የቃልኪዳን ምልክት ሳይሆን የሰቆቃ ህይዎት ወርቃማ ሃውልት ነው !! የግፍ መታሰቢያ !! የፍቅር ጡሩር የታጠኩ እኔ ይህን ጥላቻ የተቀረፀበት ሃውልት …. በፍቅር ብራና ላይ የፀፀት ታሪኩን በጥቁር ቀለም ተሸክሞ ‹‹ልእልት›› የተባለች ውብ ከተማ ጣት ላይ የቆመ የጥላቻና የግፍ ሃውልት አፈርስ ዘንድ …..ፍቅር ልኮኛል ….!! ያኔ ፈገግታዋ ነፃ ይወጣል … መጭው ትውልድም ልእልትን በጠቆረ ታሪኳ አያውቃትም … ፍቅር የመከነ ነፍሷ እንደሃና ወደፈጣሪው ጩኋልና ከእኔ የብቸኝነት ጩኸት ተዳምሮ …. የሚፈጠር ተአምር በዚህ አለ ….

በአልጋው ትክክል (ክፍል 20)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...