Tidarfelagi.com

በአልጋው ትክክል (ክፍል 17)

አንዳንዴ ‹‹የሁሉ ነገር ፈራጅ›› እየተባለ የሚንቆለጳጰሰው ((ጊዜ )) የሚሉት ጉድ ራሱ ….እልም ያለ ውሸት አሳባቂ ይሆናል ›› !! ….አዎ ቀን አቃጣሪ ይሆናል … ቀን አሳብቆ እና አሳቅሎ እዚህ ግባ የሚባል ስራ ያልሰሩ ሰዎችን በህዝብ ፊት እንደተራራ ሲያገዝፋቸው አይቻለሁና ይሄን አልኩ ….ሃቀኛ ፈራጅ ነው የሚባልለት ((ጊዜ)) የሚሉት የማያልቅ ሰንሰለት ….ከተከበሩበት ታላቅነት ካለስራቸው ካለበደላቸው አምዘግዝጎ ካመድ በመደባለቅ መሳቂያ መሳለቂያ ያደረጋቸው ንፁሃን ሰዎችን አይቻለሁና ይሄን አልኩ …..እኔኮ ‹‹ጊዜ ጣለው ›› ሲባል እንዲሁ ተረት ይመስለኝ ነበር ….ልክ ነው ጊዜ ሲፈልግ ሰርቆ ከህንፃ ላይ የዘለለን ሰው …ልክ አጋጣሚ አስመስሎ ፍራሽ የጫነ መኪና ከስር እንዲጠብቀው ያደርጋል ….(እሰይ እንኳን ሰረክ ና እዚህ ላይ እረፍ እንደማለት) ይሄንን የጊዜ ‹አሽቃብጦት› ‹‹አጋጣሚ›› እንለዋለን ….!!

እኔ ግን የልእልትን ክፉ ግጥጥሞሽ ስሰማ ‹‹እንደጊዜ የወደቀ ግንድ ላይ ምሳሩን ይዞ የሚዘምት …እንደጊዜ ለበዳዮች ጅራቱን የሚቆላ ምን ነገር አለ ›› ብየ በጊዜ ክፋት ተደነኩ …(መቸስ የዚች ልጅ ጦስ ደግሞ ብሎ ብሎ ጊዜ ጋር ሊያጋጨኝ ጀምሮ የለ) ደግሞ ‹‹የጊዜ እንጅ የሰው ጀግና የለውም ›› ይባልልኛላ …እንደጊዜ ፈሪ ከሳቁት ጋር ስምንት ሽ ጥርሱን እያገጠጠ የሚያላግጥ አስቀያሚ ነገር ምን አለ ! ይሄው ይችን ሚስኪን …ይችን ልእልት ….እራሱ ጊዜ ከትምህርት ቤት ጎትቶ አውጥቶ …እራሱ ኩሎ ድሮ ሲያበቃ የኳለው አይኗን በጨካኝ የግጥጥሞሽ ጥፊው አጥፍቶ በምንም ማስረጃ በምንም ቃል ማስተባበል የማይቻል አስመሳይ እውነት ላይ ጣላት !
ማንም ሰው የሰማኒያ ሚስቱ ያውም በራሱ ቤት …ያውም በስስ የቤት ቀሚስ … ያውም የጡት ማስያዣ እንኳን ሳታደርግ … የራሱ ጓደኛ ደረት ላይ ልጥፍ ብላ የጓደኛውም እጅ ሰፊ የቀሚሱ የአንገት ቅድ ያጋለጠው ራቁት ጀርባዋ ላይ አረፍ ብሎ ቢያገኛት ‹‹ ሚስቴ ንፁህ ናት›› ሊል አይችልም !! በጣም ሩህሩህና ደግ የሃይማኖት አባት እንኳን በዚህ ሁኔታ ቢያገኟት …‹‹ከእናተ ሃፂያት የሌለበት ይውገራት›› የሚል ቃሉን ይጠቅሱ እንደሆነ እንጅ ‹‹የለም ይች ልጅ የመከፋት መአበል እየገፋ እዚህ ኢያሱ የሚባል ጨካኝ አለት ላይ የጣላት ሚስኪን ናት›› ሊሉ አይችሉም …ምናልባት የተለየ መገለጥ ከሰማየ ሰማይ ካልተላከላቸው በስተቀር ! ውስጤ በብስጭት ጨሰ ….በዛች ቅፅበት በልእልትና ፊት ለፊቷ ባፈጠጠበት ‹ባሏ› መካከል ቁሜ ‹‹በል እንግዲህ እኔን ግደልና በእኔ ሬሳ ላይ ተረማምደህ ትነካታለህ›› ማለት አማረኝ ….ያች ቅፅበት እኮ (አያድርስ እንጅ) አይናችን ራሱ የሚዋሽበት ቅፅበት ናት !!
በቃ ማንም ምንም ቢለን ‹‹ከአይኔ ወዲያ›› ብለን ግግም የምንልበት ቅፅበት አለኮ (አይንም ምስክር ሁኖ ሞቶ ስንት ጉድ ሰቆቃ አልፎ የፈጠረው አጋጣሚ ላይ መጉረጥረጥ ጀግንነት ይመስል የሞተ ! ዓይን ራሱ አበሳጨኝ) ደግሞ አንድ ነገር ተመኘሁ …አንዲት ነገር ብቻ ….ከምር ተመኘሁ …..ምን ተመኘሁ ?? እግዜር ከሰማየ ሰማያት ወላ በመብረቅ ወላ በብርሃን ሰይፉ ጣራውን ሰነጣጥቆ ….ግድግዳውን ደረማምሶ በልእልትና በወንዴ አንበሳው መሃል ከች እንዲልና ‹‹ልጀን ለቀቅ አድርጋት ንፁህ ናት ›› እንዲለው ! ወይም እግዜር የጊዜን ሰዓት ዞር አድርጎ ….አልያም በሆነ ተአምር ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ የሆነው ሁሉ የተቀረፀበትን ካሴት ነገር ከእግዜር ቤተመዛግብት አውጥቶ ወንዴ ፊት ‹‹ተመልከት›› ብሎ እንዲከፍተው …
‹‹እ………..ሽ ›› አልኩ ቀጥሎ የተፈጠረውን ጉድ ለመስማት ልቤ በጉጉት ዘላ ጉሮሮየ ውስጥ መወተፍ እየቃጣት… የልእልት ውብ ፊት ላይ አይኔን ተክየ ….እንደዛሬ በሙሉ አይኔ ፍጥጥ ብየ አይቻት አላውቅም … ደግሞ እንዲህ አልኩ ‹‹አሁን ይች ልጅ እንኳን ጓደኛየ ደረት ላይ ተለጥፋ እንዲሁ የትም ሳትሄድ ምንም ሳታደርግ አታስቀናም ? በሰው መፍረድ ከባድ ነው … አንዳንዱ ሰው ከመሬት ተነስቶ በቅናት የሚትከነከነው በአፍቃሪው የሆነ ነገር ስለተፈጠረ ብቻ አይደለም ….ቁንጅናው በማንኛውም ሰዓት የሆነ ነገር የመፍጠር አቅም እንዳለው እየገባው ነው …ለብዙሃኑ ወንድ የተጋነነ የሴት ልጅ ቁንጅና ፈንጅ ነው …. አንዴ የፍቅር መንገድ ላይ ከተጠመደ በኋላ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ማንም ሊረግጠውና ሊፈነዳ ይችላል ! ያኔ ራሱን ጨምሮ በአካባቢው ያለውን ነገር ሁሉ እንዳልነበር ከማድረግ ምንም አያግደው ! የልእልት ቁንጅና ደግሞ . . . ኒውክሌር!!
‹‹አልፈራሁም ….አልደነገጥኩም ….አልተጨነኩም ….›› አለች ልእልት ቀጠል አድርጋ የዛን ቀኑን አጋጣሚ ስትነግረኝ ‹‹ግን በሁሉም ነገር ተስፋ ቆረጥኩ!! በፍቅር ….በንፅህና …በእምነት ….በህይዎት በሁሉም ነገር ተስፋ ቆረጥኩ … በእግዚአብሔር ደግሞ አዘንኩ …እሽ እኔ ጥንቃቄ ይጉደለኝ …. እኔ ዝርክርክ ልሁን እኔ በቃ የማረባ ከንቱ ሴት ልሁን … እምነት የሌለኝ ሴትም ልሁን ….ግን ሰይጣን እንዲህ አይነት ቆሻሻ ድራማውን በፍጡሩ ላይ ሲሰራ እግዚአብሔር ዝም ይላል ?? ደግሞ የሰዓቱ መገጣጠም …. ሰይጣን ግን ከምርም ሰይጣን ነው ›› አለች ….አባባሏ በሌላ የሰላም ቀን ቢሰሙት ሳያስቅ አይቀርም ….በዚህ ሰዓት ግን እንኳን ሊያስቅ ፊቷ የሚረጨውን ህመም እንኳን አብሮ አለመታመም አይቻልም ነበር …. እውነቷን ነው ሰይጣን ከምርም ሰይጣን ነው !!
‹‹….ወንዴ በዛች ቅፅበት እኔና ኢያሱ ፊት በቆመበት ሰዓት ምን ሆነ መሰለህ …..ታምነኛለህ ምንም አልሆነም አብርሽ ….. !! ስትለኝ እንደባሉን በጭንቀት የተወጣጠረ ስሜቴ ሙሽሽ ሲል ተሰማኝ …ግን እንዴት ነው ምንም አለመሆን …. ባል ሚስቱን ጓደኛው ደረት ላይ ተለጥፋ አግኝቷት እንዴት ነው ምንም አለመሆን …..ልእልት ጥያቄ የወረረው ፊቴን አየት አድርጋ ቀጠለች …..
‹‹….ኢያሱ እነደዛን ቀን ገርሞኝ አያውቅም … ሊደነግጥ መሰለህ …ሊደነብር መሰለህ ….ዘና ብሎ ወንዴን እንዲህ አለው ‹ታሳዝናለህ ሴትን እንደዚህ ማስለቀስ ትልቅ ነገር መሰለህ ?….ደግሞ ታፈጣለህ ….ከምር አዝኘብሃለሁ› የኢያሱ ድምፅ ጉልበት የሆነኝ ይመስል ከደረቱ ላይ ቀጥ ብየ እንባየን ዘረገፍኩት …(ተዘረገፈኝ እንጅ) እመነኝ አብርሽ ….የዛን ጊዜ አላለቀስኩም … ምንም የሃዘንም የመከፋትም ስሜት አልተሰማኝም ….ዝም ብሎ እንባየ ሲከነበል ፀጉሬን ታጥቤ ከፀጉሬ ላይ ረግፎ ፊቴን እንደሚሸፍን ውሃ ….እንባየ ከአይኔ ሳይሆን ከላይ ጉንጨ ላይ ተፈሰሰ ነው የመሰለኝ …
ወንዴ በዛ ሰዓት የፈለገውን ቢል የፈለገውን ቢያደርግ ውስጤ ባለቤቱ በድካም ሳይዘጋው እንደተኛ በር ተከፍቶ ክፍቱን ቀርቶ ነበር … ምንም አላደረኩም ብሎ ለመከራከርም አንዳንዴ ይሰለችሃል ! ስንት አመት ታመንኩ ለወንዴ …ስንት አመት በሬን ዘጋሁ ….አመቱን ተወው… ከተጣላን ጀምሮ ራሴ ላይ በሬንም አእምሮየንም ዘግቸ ከወንዴ ውጭ ሌላ ወንድ እንደብልጭታ እድሜ እንኳን በአእምሮየ አልተከሰተም ….በዚህ ሁሉ ብቸኝነትና ሰቆቃየ ወንዴ ቀን ላይ ተስቶት እንኳን እቤት ብቅ ብሎም ደውሎም አያውቅም …ዛሬ ይሄው ! ….ይሄው ወንዴ ሌላ ወንድ ደረት ላይ ተኝቸ እያየኝ …በቃ ከዚህ በኋላ ያ ሁሉ የፍቅር ምስሌን ሰርዞ በዚህ ስእሌ ብቻ ሊያስታውሰኝ ወንዴ ፊቴ ቁሞ በጥሞና ያየኛል !!
ኢያሱ ‹‹ተቀመጣ›› አለው ዘና ብሎ ….ልክ ምንም እንዳልተፈጠረ (ለነገሩ ምን ተፈጠረ የፈጠረኝ አምላክ እኔን እንዲህ አይነቱ ምድጃ ላይ ስጣድ እያየ ዝም አለ እንጅ…ማን እንደሚያወጣሽ ጉድሽን አያለሁ ብሎ ) ወንዴ የግንባሩን ቆዳ ወደላይ ለቅፅበት ሰብሰብ አድርጎ መለሰና ግንባሩን በመዳፉ እየፈተገ ዝም ብሎ አንዴ እኔን አንዴ ኢያሱን ተመልክቶ
‹‹ ጭራሽ በኔ ሆነ የሚታዘነው ›› ብሎ ዙሮ ወጣና ሄደ ….
ምን ከተቀመጥኩበት እንዳስፈነጠረኝ አላውቅም ….ከፍራሹ ላይ ተነስቸ ሮጥኩ….. ወንዴን ገና ደረጃውን ሳይወርድ ደረስኩበት ! ፊቱ ቁሜ በቃ የምለው ነገር ሁሉ ጠፍቶብኝ ከንፈሬ ሰውነቴም እየተንቀጠቀጠብኝ ዝም ብየ አየሁት …ወንዴ ካለወትሮው አላኮረፈ አልተቆጣ ዝም ያሉ አይኖቹን አይኖቸ ላይ ተክሎ የምለውን ለመስማት ይጠብቀኛል …. ምነው በሆነ ስድብ ንግግር በጀመረ ….ምነው ከፊቱ ገፍትሮ ከዛ ፎቅ ላይ አምዘግዝጎ በገላገለኝ ….ዝም ! በቃ የደረጃውን ብረት ደገፍ ብሎ (መቆም የደከመው ነበር የሚመስለው) አየኝ ….
‹‹ወንዴ ….›› አልኩ በቃ ሌላ ምን ልበል ….ከየት ነው ይሄ ሁሉ ስንክሳር የሚጀመረው …. ወንዴ በረዥሙ ተነፈሰና ‹‹ልእልት አሳልፊኝ ›› አለኝ ….አልነካኝም ….አልገፋኝም አልጮኸብኝም በቃ ይችን ቃል ሲናገር ፊቱ ላይ የነበረው ቅዝቃዜ ከመንገዱ ዞር አደረገኝ …..‹‹ልእልት አሳልፊኝ›› ድምፁ እስከዛሬ ጆሮየ ላይ ያቃጭላል …. ዝም ብየ አየዋለሁ …. ከደረጃው ወርዶ ወደመኪናው ሄደ ….
ወንዴ ካለወትሮው አካሄዱ ድክም አለብኝ እግሩን እያነሳ እንዳገኘ ነበር የሚጥለው …ደግሞ ትንሽ ጎበጥ ያለ መሰለኝ ….(ከላይ ሁኘ ስላየሁትም እንደሆነ እንጃ ) ….መኪናው የቆመችው ከኢያሱ ውድ መኪና ጎን ነው …. የመኪናውን በር ሊከፍት ሞከረና መቆለፉ ትዝ ሲለው ቁልፉን የትኛው ኪሱ ውስጥ እንዳስቀመተው ጠፍቶበት ኪሶቹን በርብሮ አንዱ ኪሱ ውስጥ አገኘው …መኪናው ውስጥ ገብቶ ረዥም ደይቃ ሳያስነሳ ቁጭ አለ ….ልክ መኪናውን ሲያስነሳ እንደሆነ ፍንዳታ ደንብሬ ከፈዘዝኩበት ነቃሁ …ወንዴ እየሄደ ነው ….አይበልበትና አሁን መንገድ ላይ የሆነ አደጋ ደርሶበት አንድ ነገር ቢሆን እስከዘላለሙ ‹‹እንደካድኩት›› አስቦ ሊቀር ነው አይደል …..ቁልቁል ወደታች ተንደረደርኩ … ታች ስደርስ መኪናዋ ከግቢ ወጥታለች …ወንዴ ሂዷል !!
ወደቤት ስመለስ ተራራ መውጣት በለው ደረጃው ራቀኝ አይኔ ጭልምልም አለብኝ … የመጨረሻውን ደረጃ ስወጣ እማማ ቁንጥሬ ‹‹ምነው ወንዴ ሰላም አይደለም እንዴ›› አሉኝ ….ይታይህ አናግረውኝ አያውቁምኮ ….ዘግቻቸው አለፍኩ …. ከኋላየ ‹‹ተቃጥለህ ሙት ያለው ልጅ›› ሲሉ ጆሮየ ውስጥ ጥልቅ አለ ….ተንደርድሬ ወደሳቸው ተመለስኩ …ከዛ በፊትም ከዛ በኋላም እስከአሁን ሰው እንደዛ ተናግሬ አላውቅም አብርሽ
‹‹ አንቱ ሴትዮ ምንድነው ችግርሁ ….በሰው ትዳር በሰው ጉዳይ ምን ያገባዎታል …የራስዎትን ኑሮ አይኖሩም ….ስራ የለዎትም ›› ብየ ብሎኩን በሚያንቀጠቅጥ ድምፅ አንባረኩባቸው …. እነዛ ነገረኛ ጎረቤቶች ልክ ስማቸው ከነአያታቸው የተጠራ ይመስል በራቸውን እየከፈቱ አሰፈሰፉ ….ወደቤቴ ገብቸ … ባለ በሌለ ሃይሌ በሩን ፊታቸው ላይ ጠረቀምኩት …..በሩን ወርውሬ ስዘጋው …. የሆነ መስተዋት ነገር ከኋላየ ሲሰባበር ድምፁ አሰቅቆኝ ደንግጨ ዞርኩ …. ግድግዳ ላይ ስንት አመት ተሰቅሎ የኖረ የእኔና የወንዴ ባለመስተዋት ፍሬም የሰርግ ፎቶ ነበር … የቲቪ ማስቀመጫው ጠርዝ ላይ ወድቆ የተንኮታኮተው !! ….…የወንዴ አባት ከዱባይ አሰርተው ያመጡልን እጅግ ውድ ስጦታችን ነበር ….ወንዴ ይሄን ፎቶ ይወደዋል አይገልፀውም …ከተጣላን በኋላ እንኳን በቅርቡ ድንገት ከመኝታ ቤት ብቅ ስል …. በጥንቃቄ በሶፍት ሲወለውለው አይቸዋለሁ !! (ወንዴ ፍቅሩ ጨርሶ አልሞተም ብየ …ልቤ ውስጥ ቁራጭ ተስፋ ያኖርኩበት ቀንም ነበር)
ኢያሱ ተረጋግቶ ከተቀመጠበት ፍራሽ ላይ ድንገት ተስፈንጥሮ …..ተነስቶ ‹‹ ልእልትየ እዛው ሁኝ የኔ ቆንጆ …እንዳይቆርጥሽ ! …እንዳንች አይነት ውብ እጆች ከሚቆረጡ የእኛ አይነቱ ከነትከሻው ተቆርጦ ይውደቅ ›› እያለ የመስተዋት ስብርባሪ ይለቅማል … በሩን በጀርባየ ተደግፌ ዝም ብየ ሳየው ቅንጥብጣቢ የሚለቅም ውሻ መሰለኝ …..በዛች ቅፅበት ምን እንዳማረኝ ታውቃለህ አብርሽ?? ተለቅ ያለውን የመስተዋት ስባሪ አንስቸ እዚህ ምቾት ያደነደነው ማጅራቱ ላይ መሰካት !! እሱም ላይ ብቻ ሳይሆን እራሴም ላይ !!
‹‹ኢያሱ ›› አልኩት
‹‹ወይየ ልእልትየ ›› (አሁን ይሄን ሁሉ ‹የ› ምን አመጣው )
‹‹ ውጣ!! ››
‹‹እ??????›› አለ በግርምት በርከክ ብሎ የመስተዋት ስብርባሪውን እንዳንከረፈፈ …..
‹‹ከዚህ ቤት ውጣ ….ሁለተኛ እዚህ ቤት እንዳትመጣ ….!!››
‹‹ል…እ…ል…ት..የ …እኔኮ ››
‹‹ውጣልኝ በቃ !!›› ብየ አምባረኩና በር ላይ የተቀመጠ ጫማውን አንስቸ አፍንጫው ስር ደነቀርኩለት …. ቀስ ብሎ ተነሳና
‹‹እሽ ስብርባሪው እንዳይቆርጥሽ ላንሳው ….??›› አለ
‹‹ ው…..ጣ !›› ጫማውን በቀስታ አጥልቆ …. የመኪና ቁልፉንና አውልቆ ያስቀመጠውን ጃኬት ከፍራሹ ላይ አንስቶ
‹‹ ስሜትሽን ረደዋለሁ ልእልትየ ..ወንዴ እያደረገ ያለው ስራ እንደሚከብድ አውቃለሁ ….››
‹‹ስሙን አትጥራ ….›› ብየ አፈጠጥኩበት…. ወጥቶ ሄደለኝ …. !!
በሩን ቆልፌ ቁጭ አልኩና ስቅስቅ ብየ አለቀስኩ ….ሳሎኑ ውስጥ እንደተበታተኑት ስለታቸው የሚያስፈራ የመስተዋት ስብርባሪዎች ….ስለቱ የሚያስፈራ ቀን …..ከፊቴ እየመጣ መሆኑ በእንባየ ግርዶሽ ታየኝ … ተስፋ የሚባል ነገር የለም ….. ምንም !! መስተዋት ምንድነው ….ጊዜኮነው …. ኑሮኮ ነው ….ትላንት ያማረ መልክህን እያሳየ ጉድለትህን እንድታስተካክል እየመከረ አደባባይ ከመውጣትህ በፊት ሲያስውብህ ነበር ….ዛሬ ሰበብ ፈልጎ ከአብራኩ በወጡ ስለታም ስብርባሪዎቹ ደምህን ሊያፈሰው መንገድህ ላይ ስቃይ ሁኖ ተዘርቷል …. ትላንት ከፊቴ ቁመው ከእኔው ውስጥ የሚወጣውን ተስፋ ሲያሳዩኝ የነበሩት ውብ የቀን መስተዋቶች ሁሉ ተሰባብረው ፊቴ ወድቀዋል …..ምን አማራጭ አለኝ እንባ ማጭዴን ይዠ ጥቁር እርሻየ ላይ መጭውን ሰቆቃ ከማጨድ ውጭ ….ጊዜ ግን . . .

በአልጋው ትክክል (ክፍል 18)

One Comment

  • false commented on November 17, 2019 Reply

    በናትህ ልብ አታንጠልጥል

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...