Tidarfelagi.com

በአልጋው ትክክል (ክፍል ዘጠኝ)

ትላንት 10 ፡00 ሰዓት አካባቢ ከሆስፒታል ወጣሁ …. ልክ በጓደኞቸ በእናቴና በእህቶቸ መሃል ሁኘ …ከሆስፒታል ሳይሆን የሆነ ትልቅ ጀብዱ ሰርቸ ከዘመቻ የምመለስ ነበር የምመስለው … ልክ ሆስፒታሉ ኮሪደር ላይ ስደርስ ሁለት ነርሶች ነጭ ጨርቅ ጣል የተደረገበት አስከሬን በተሸከርካሪ አልጋ እየገፉ በአጠገባችን አለፉ ….የሆነ ነገር ሸከከኝ …. ከኋላ የሟቹ ዘመዶች ሆስፒታሉ እስኪንቀጠቀጥ እየጮሁና በተለይ አንዷ ፊቷን እየነጨች አለፉ …. እህቴ (መቸም ወሬኛ ናት) አስከሬኑን ተከትለው ከሚሄዱት አንዱን ቁመቱ ከመርዘሙ የተነሳ ሱሪው ብቻ ሳይሆን ቆዳው ራሱ ያጠረው የሚመስል ልጅ ክንዱን ያዝ አድርጋ አስቆመችውና ….
‹‹ይቅርታ ወንደሜ ምን ሁኖ ነው ›› አለችው ወደአስከሬኑ በአገጯ እየጠቆመች
‹‹ ሙቶ ነዋ ሌላ ምን ይሆናል ›› ብሏት በዛ ቁመቱ ለሶስት ሰው የሚሆን የእርምጃ በጀት ባንዴ እያፈሰና አየሩን እየቀዘፈ ትቷት ሄደ ….የሰውየውን መጣደፍ ለተመለከተ አስከሬኑን ሳይሆን የሟቹን ነፍስ ርቃ ሳትሄድ ለማስመለስ የሚሮጥ ይመስል ነበር ! እንደው እዛ እየተለቀሰ አንስቅም ብለን እንጅ እኔም ጓደኞቸም በሰውው መልስ …ሳቃችን እስከነገ ባላለቀ ነበር … እናቴ እጀን ያዝ አድርጋ ፈጠን ፈጠን እያለች ወደውጭ መንገዳችንን ቀጠልን ….እህቴ እናቴን እያየች ፈገግ አለችና ወደጆሮየ ጠጋ ብላ
‹‹ ማሚ ፈርታለች ›› አለችኝ !
‹‹አንችስ›› አልኳት …የኛ ጀግና በሚል የማሾፍ ድምፅ
‹‹እኔማ ሞት ጋር አንገት ላንገት በመተናነቅ ይሄው አትርፌ ወደቤትህ እየወሰድኩህ ነው ››ብላ ቀለደች ….ድምፅዋ እንደወትሮው አልነበረም ጎርነን አለብኝ (ህቴን ድምፅ መች አጣሁት) ….ዞር ብየ አየኋት …. አቀርቅራ ነው ምትራመደው …አገጮን በሁለት ጣቶቸ ደግፌ ቀና አደረኳት …አይኖቿ እንባ ሞልተው ነበር …በቃ እንዲህ ናት ….የሞተ ሰው ስትመለከት ከሞት አፋፍ መመለሴ ዛሬ ገና ትዝ ሳይላት አልቀረም …. አቀፍኳት እቅፌ ውስጥ ልጥፍ አለች ! ‹‹አብርሽ ትንሽ ለእኛ እንኳን አትጠነቀቅም ለምን የማይረባ ድፍረት ትዳፈራለህ ምናለበት እኛ ጋር ብትሆን …ለምን ብቻህን ትሆናለህ ….አንድ እዚህ ግባ የማይባል ተራ ዱርየ ዘመድ እንደሌለው ሰው እንዲህ ሲጨማለቅብህ …. ›› ብላ እየየ ……
‹‹አንች …በሰላም አገር የምን ለቅሶ ነው ….›› ብሎ ጓደኛየ ሊያሾፍ ሲሞክር
‹‹ዝም በል እዛ …. አያገባህም ›› ብላ ቀልቡን በጩኸት ገፈፈችው ሰው ሁሉ ዞር ብሎ እስኪያየን (አራስ ነብር)
‹‹እናንተ ጓደኛ ከሆናችሁ አትመክሩትም ….. የናት ያባቱ ቤት እያለ የትም ብቻውን ሲንከራተት እንደጓደኛ አትመክሩትም … በስርአት ምግብ እንኳን አይበላ … ሁልጊዜ ብቻውን ….አትመክሩትም ጓደኞቹ ከሆናችሁ …..›› ብላ ጠንካራ የምላት እህቴ እንባ በእንባ …..እንደህፃን እቅፌን ጠበቅ አድርጌ አባበልኳት …
‹‹ልቀቀኝ እዛ ህፃንህን ፈልግ ….›› ብላ ቆንጠር ቆንጠር እያለች በእናቴ በኩል ዞራ ቆመች ….እናቴ አንድ ነገር አልተናገረችም ይሄ ዝምታ እህቴን መደገፍ መሆኑን አውቃለሁ !ሁልጊዜ የተከራየሁትን ቤት ለቅቄ ቤተሰቦቸ ጋር እንድኖር እንደነዘነዘችኝ ነው እንኳን ይች ሰበብ ተገኝታ ! እንደውም ፈጠን ፈጠን ብለን እንድንሄድ እየመራችን ነበር ….የእናቴን ፍርሃትና ፍጥነት ለተመለከተ ሰው ሃኪሞቹ ከኋላ ጠርተው ‹‹አብርሃም በስህተት ነው ከነህይዎትህ የወጣሃው ና ተመልሰህ ሙት ›› የሚሉኝ ነበር ያስመሰለችው ….
በዚሁ ስሜት በዝምታ ተውጠን ስንወጣ ልክ በር ላይ እማማ ቁንጥሬ ሲገቡ አገኘናቸው ….(ተመስገን በሚዶክክ ስሜት ውስጥ እማማ ቁንጥሬንም ቢሆን ልኮ ከዝምታ ያወጣን አምላክ) በእጃቸው ቬርሙዝ ይዘዋል ….
‹‹ውይ ወጣህ እንዴ…. ምን አስቸኮለህ ልጀ ›› አሉ …እናቴ በስጨት ብላ አየቻቸው ! ቀጠል አድርገው ‹‹እሰይ ከተሸለህማ እንኳን ወጣህ ….ወደቤት ነው የምትመጣው አይደለም ? ›› ሲሉ ጠየቁኝ (ይች ሴትዮ ነገር ያበላሸ ርእስ አንስተው አረፉ…እዚች ሴትዮ ውስጥማ ሰይጣን አለ)
‹‹አይ ትንሽ እኔጋ ይሁን እማማ ›› አለች ማዘር …‹‹አዎ ትንሽ እናትህ ቤት አረፍ በል ….ቤት አከራይህም በጧት መጥተው በርህን ሲወግሩ ነው ያረፈዱት እኔም ማታ እንቅልፍ ወስዶኝ ያላየሁት ድራማ እያየሁ እንዳላቋርጥ ብየ ‹የለም › አላልኳቸውም … ›› አሉና ሳንወድ በግዳችን አሳቁን ….ተንኮለኛ እኮ ናቸው …እስቲ አከራየ እጃቸው እስላይ ቤቴን ሲያንኳኩ ብቅ ብለው የለም ለማለት ምን ጊዜ ይወስዳል ….አይ እማማ ቁንጥሬ !
‹‹ይሄን ያዥ…እናቱ ….. እንግዲህ እንደወጣቶቹ ሾርባ ጣፍጦህ ባትጠጣውም ምንም አይልህ ….ሌላው ቢቀር የቬርሙዙን ቀለም እያየህ ጨክነህ ጠጣው ›› አሉና እማማ ቁንጥሬ ቬርሙዙን ለእህቴ እያቀበሏት (ይች አሽሙር እንግዲህ የልእልትን ሾርባ ለመንካት ነው …ልክ ሲናገሩ ነው የቬርሙዙ ቀለም አረንጓዴ መሆኑን ያስተዋልኩት ልክ እንደልእልት ቬርሙዝ …..አሁንማ እንኳን እኔ እናቴም ባናባቸዋለች ነገረኛ የሆኑ ሴትዩ ) እህቴ ፊቷ በታፈነ ሳቅ ተሞልቶ በአክብሮት ተቀበለቻቸው
እማማ ቁንጥሬ እንደሄዱ እህቴ ‹‹ይች ሴትዮ ግን የመጨረሻ ነው የተመቹኝ ….በደንብ ከቀረብካቸው አሪፍ ዘመድ የሚሆኑ ነገር ናቸው ሂሂሂሂሂ›› አለችኝ የቅድሙ ኩርፊያና ለቅሶዋ ድራሹ ጠፍቷል !
‹‹ አንች ራስሽ ቁንጥሬ ነገር አይደለሽ ሌላ ነገረኛ ዘመድ ምን ያደርግልኛል ››
‹‹እስቲ አትነዝንዥው አንችየ ›› አለች እናቴ …(አይ ቅድም እንደዚህ አትልም ነበር) ሆስፒታሉን ዞር ብየ አየሁት ….ለምን እንደሆነ እንጃ … ከሆስፒታል ሳይሆን ተወልጀ ያደኩበትን አገር ጥየ የምሰደድ መስሎ ተሰማኝ …. እህቴ በነገረኛ አይኗ አይታኝ ወደጆሮየ ጠጋ አለችና …በሹክሹክታ
‹‹ ለልእልት ደውየ ከሆስፒታል መውጣትህን ነግሪያታለሁ ›› አለችኝ
‹‹ ማን አዘዘሽ …ከምር አንች ልጅ ግን አንዳንዴ ታበዥዋለሽ ›› አልኩ ቆጣ ብየ ….እሷ እንኳን ቁጣየ ሊያስደነግጣት ጭራሽ ፈገግ ብላ እንዲህ አለችኝ
‹‹ አቡቹ ከሆስፒታል እንደወጣ እኛ ቤት ነው የሚቆየው … ያንን በምድራችን ላይ ካሉ ምግቦች ሁሉ ወንድሜ የሚወደውን ሾርባሽን ይዘሽ ሆስፒታል ድረስ እንዳትደክሚ ….ብየ የቤታችንን አድራሻም ነግሪያታለሁ ›› በግርምት አየኋት …
‹‹ በተያያዘ ዜና …..ልእልት ‹እንኳን ለዚህ አበቃህ ነገ ጧት እመጣለሁ› ብላለች ›› ብላኝ ….ጠቀሰችኝ ….(እህቴን እንደዛሬ ወድጃት አላውቅም የኔ ምርጥ እህት !!) ቢሆንም ኮስተር ብየ እንዲህ አልኳት ‹‹ማድረግ አልነበረብሽም … ሌላ ነገር አስመሰልሽው !›› (ለታናሽ እህት ፊት አይሰጥም እንጅ አቅፌ ብስማትም ሲያንሳት ነው)
‹‹ሌላ ነገር ሳይመስል እንዲሆን ነበር የምትፈልጉት ሂሂሂሂ ›› እንዲሁ ከጎኔ ተሸጉጣ እየጠዘጠዘችኝ…. በአጀብ ወደእናቴ ቤት ሄድኩ !እህቴ ቅድም አስደንግጣው ዝም ላለው ሚስኪን ጓደኛየም አልተመለሰች ….‹‹ነርሷን ቻው አልካት ?›› አለችው ….ቅድም ለጮኸችው ጩኸት ይቅርታ መጠየቅ በሚመስል ድምፅ ….
የትንሸዋን መኪና መሪ በጥንቃቄ ይዞ
‹‹ልንዳበት ….እንግዲህ አትነጅሽኝ አንች ልጅ ›› አላት …እና ምንም በሌለበት …ጲፕ አደረገው ክላክሱን
‹‹ባዶው መንገድ ላይ መንፈሷ ጋውን ለብሶ ገባብህ እንዴ ›› አለች እህቴ ….
‹‹ይች ልጅ ግን ያንች ልጅ ነች ማዙ …. የእማማ ቁንጥሬ ልጅ እየመሰለችኝ ነው›› አለ ጓደኛየ ታረቁ ማለት ነው በቃ … !!
**** ****** ******
በቀጣዩ ቀን ጧት ወደአራት ሰዓት አካባቢ እህቴ መኝታ ቤቴን በርግዳው ገባችና ‹‹ሚስታችሁ መጣችልህ ›› ብላ በመጣችበት ፍጥነት ተመልሳ ወጣች ስልኳ እጇ ላይ እየጮኸ ነበር ….. ልእልትን ልትቀበል እየሄደች ነው …. ከአልጋየ መነሳት ሸክም ሁኖብኝ ስገላበጥ ያረፈድት ሰውየ ….እንደጥይት ተስፈንጥሬ ተነሳሁና ከላይ የለበስኩትን ፒጃማየን አሽቀንጥሬ ጥየ ቲሸርት ለበስኩ …… ፊቴን ታጠብኩ ….መቸም ልእልትን የምትቀጥራት ሹሉቃ ሻይ ቤት ነው …..ማንም ሰው ቤታችን ሲመጣ እዛ ነው ምልክቱ …..
ጅራታም ኮከብን በሚያስንቅ ፍጥነት ሳሎኑን አቋርጨ ምኝታ ቤቴ ተመለስኩና የተዝረከረከውን ልብስ የት የት እንደሸጎጥኩት እንጃ ምኝታ ቤቴ ፀዳ አለች …. ከዛ የአልጋ ልብሴን ለብሸ ምንም እንዳልተፈጠረ ለጥ አልኩ (አለ አይደል ሁልጊዜም ቢሆን የተዝረከረከ ነገር አይመቸኝም የሚል መልእክት መሆኑ ነው) እህቴና ልእልት እንደአስር አመት ጓደኛሞች እተሳሳቁ መጡ … ልእልት እናቴ ጋር ሰላምታ ስትለዋወጥ ከምኝታ ቤቴ ሁኘ ድምፅዋን እንደሰመመን እየሰማሁ ደስ አለኝ ….
እናቴ ቤት ድረስ ተወልጀ ያደኩበት ቤት ድረስ ስትመጣ እንዲሁ የበለጠ የመቀራረብ ስሜት ተሰማኝ (((አብረን ውሃ እየተራጨን አፈር እየፈጨን ያደግን መሰለኝ ))) …. እህቴ እየመራች መኝታ ቤቴ ድረስ አመጣቻት …..(ይች ልጅ በዚህ አያያዟ አቅፋ አልጋየ ላይ ሳታስቀምጣት አትቀርም) ልእልት ዛሬ ደግሞ ለየት ብላለች …. ስታየኝ ፊቷ በፈገግታ ተጥለቀለቀ …. (እኔ ከልእልት የሚገርመኝ አንድ ነገር ቢኖር ….(እሱማ ብዙ ነገር ነው የሚገርመኝ) ፈገግታዋ የህፃን ልጅ ፊት የለበሰች ያስመስላታል የሆነ አንጀት የሚበላ እናቱን የናፈቀ ድንቡሸ ህፃን አይነት) ) ጉንጭ ለጉንጭ ተሳሳምንና ‹‹ አብርሽ …እንኳን ለቤትህ አበቃህ ›› አለችኝ ….ያ አረንጓዴ ፔርሙዝ አብሯት ነበር…. እህቴ ተቀበለቻትና ወደኔ ዞር ብላ ጠቀሰችኝ ‹‹ ተጫዎቱ ›› ብላን በሩን ዘግታው ሄደች …. ልእልት የምኝታ ቤቴን ከዳር እስከዳር ቃኘቻት…
‹‹ እዚህ ድረስ ደከምሽ ›› አልኳት
‹‹ኧረ ችግር የለውም ›› ብላ ትክ ብላ አየችኝና ትንሽ ፈገግ ብላ ‹‹አሁን ምንም አይሰማህም አይደል ›› አለችኝ
((አሁንማ ምንም አይሰማኝ መስሚያየ ጥጥ ነው አንች እያለሽ ልእልትየ )))) ማለት እያማረኝ ‹‹ አሁንማ ዳንኩ በቃ ….›› አልኩ !
‹‹ ፊትህ ራሱ ተመለሰ እንደድሮህ ሆንክ ›› አለችኝ …( አአአአአአ?? ድሮ መቸ ነው?? ….ከዚህ በፊት ታውቀኝ ነበር ማለት ነው ?…..) ((ይሄማ በገለልተኛ ወገን ሌላ ጊዜ መጣራት ይኖርበታል !))

ልእልት እና እኔ የምናወራው የጠፋብን ይመስል ዝም ብለን ተቀመጥን ….እኔ ግን በሃሳቤ የነገረችኝን ታሪኳን ተመልሸ ማሰብ ጀመርኩ … አንዳንዱ ታሪክ ከባለ ታሪኩ ፊት ጋር አይሄድም ….ለምሳሌ የሂትለርን ፎቶ እያዩ ታሪኩን ቢያነቡ እውነተም ይሄ ግንባሩ የጨካኝ ይመስላል ምናምን ይባላል … የእማሆይ ቴሬሳን ፊት እያዩ ደግ ሰውነታቸውን ቢሰሙ ፊታቸው ከስራቸው ጋር ይሄዳል ….የአንስታይንን ፎቶ ያየ ማንም ‹‹ይሄ ፎቶው የሚታየው ሰውየ ሳይንቲስት ነው በሳይንስ ጢባጢቦ የተጫወተ ሰው ነው ›› ቢባል ያምናል …. ማንም ሰው ግን የልእልትን ፊት እያየ ክፉ ትሁን ደግ ማሰብ አይችልም ….እውነቴን ነው በቃ ዝም ያለ ፊት ነው ….እዛ ፊት ፊት ማሰብ አይቻልም ዋጥ ነው የሚያደርገው … ፔርሙዳ ትሪያንግል ልእልት ፊት ላይ ይዞታ ሳይኖረው አይቀርም ! ሁሉም ሃሳቤ ልእልት ፊት ላይ ሲደርስ የደረሰበት ይጠፋኛል !! በዛ ላይ አእምሮየ ማንንም ይጢረጥራል እያንዳንዷን ቃል ይሰነጥቃል ….ልእልት ላይ ግን ዝም !!
ልእልት ደግ ፊት ናት ….ሰላም ፊት ናት ….ረፍት ፊት ናት ….ወደቅላት የሚወስደው ይይምናዋ … ሰፊ የሰላም መስክ …. አይኖቿ መስኩ ላይ በንፁህ ውሃ ተሞልተው የተቀመጡ ጉድጓዶች ….. ልእልት ውብ ናት !! ሰው ይሄን ገላ አቅፎ ተኝቶ እነዚህን ጡቶች ተንተርሶ ኑሮ ….በእነዚህ ከንፈሮች እንደሚፈቀር ተመስክሮለት ….እንዴት ቢላ ይዞ ጎረቤቱ ላይ ይዘምታል በግዚአብሔር ??
ለነገሩ መልክ አሳሳች ነው ….. ስንቱ የውብ ፊት ባለቤት ነው ደግ ሩህሩህ መስሎን ልባችንን እንደፈሪ ጅብ ዘንጥሎት የሮጠው …. የደበቀውን ክፋት ….. እድሜ ልክ የማናጸዳው ፀፀትና ቁጭት ገልብጦብን የሄደው ….ስንቶችስ ናቸው አረመኔ መሳይ ቆዳቸው አስፈርቶን የሸሸናቸው ሰዎች …. ስንቀርባቸው ግን መለአክ ሁነው ያገኘናቸው ….. ምን እሩቅ አስኬደን ….የዚች የውበት ስንክሳር የተከተበባት ልእልት ባል …‹‹ወንዴ አንበሳው›› ….. አለ አይደል ቆንጆ ሴት ሊመስል ግማሽ መንገድ የጀመረ ቆንጆ ፊቱን አይቸ ገራገር የመሰለኝ ሰው …ቢላውን ይዞ ከተፍ ያለው !
(((በዚች ምድር እንደሰው ፊት የተወሳሰበ ስሜት የተፃፈበት ምን መፅሃፍ አለ ?))) ቢሆንም ጠንክረው ሊቆሙ የሚፍገመገሙት የልቤ እግሮች ….የልእልት አይኖች ባረፉብኝ ቁጥር እያዳለጣቸው ይንገዳገዳሉ …. ምናልባት በፍቅር ይሁን በሌላ መሻት ….. ይች ልእልት መንገዱን እያጨቀየችባቸው ይሆናል ….? መንሸራተቱስ ይሁን እየወደቁም እተነሱም ይወጡታል ….ብቻ ይሄ የልእልት ውበት አሮንቃ ሁኖ እስከአንገታቸው ሰጥመው እንዳያርፉ ….ጎታች እንኳን በሌለበት ….ማንስ ቢሆን ….ማን የሰው ትዳር አሮንቃ ውስጥ ግቡ አላቸው ነው የሚለው እንጅ እንዲች ብሎ እወጣ ዘንድ እጁን የሚልክ የለም ….

ምን ውዳሴው ቢበዛ ምንም ባየኋት እና ባሰብኳት ቁጥር ውስጤ የሚሰማው አድናቆት ለልእልት ቢያንስ …ምንም የልእልት ውበት የምድር ውበትና የምቾት ፍፃሜ ቢመስልም ቅሉ …..(((በዚች ምድር እንደሰው ፊት የተወሳሰበ ስሜት የተፃፈበት ምን መፅሃፍ አለ ?))) ይሄን ገራገርና ሳቂታ ….ውበቱ ልብን ፀሃይ ላይ እንደተቀመጠ ቅቤ የሚያቀልጥ የልእልትን ፊት ስንገልፀውም እንደሚመስለው ሳይሆን ….በተቃራኒው ይህ ሰቆቃና የህይዎት ውጣ ውረድ ተፅፎበት እናገኘዋለን ….

በአልጋው ትክክል (ክፍል አስር)

 

 

One Comment

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...