‹‹ባጥፈው ደነዘዘኝ ምላሴን እንደ,ግር ጤናና ገንዘብ ነው የልብ የሚያናግር ››
የሚል ግጥም ሰምቸ አውቃለሁ ….እንግዲህ ሆድ የባሳት ልእልት ግን ‹‹ሲያጥፉት ከሚደነዝዝ ምላስ በላይ ሲያቅፉት የሚደነዝዘው ያጣ ሳይሆን ድንዙዝ ሃብታም የወለደው ባል ነው ትለኛለች …. እሰማለሁ ‹‹እንዴት ማለት ልእል((ቴ)) እያልኩ ….
‹‹…ወንዴ ጋር የተዋወቅነው የአስራአንደኛ ክፍል ተማሪ እንደነበርኩ ነው …. ያኔ ትምህርት ቤታችን ጎን የአባቱ ጣውላና ሲሚንቶ መሸጫ ትልቅ መጋዘን ስለነበር(አሁንም አለ) ‹እዛ ስመላለስ አየሁሽ › ነው የሚለው እሱ …. አንድ ቀን መኪናውን አቁሞ(ጥቁር ቢኤም ደብሊው) አራት እንሁን አምስት ሁነን ከቆምን ጓደኞቸ መሃል በመስኮቱ አጎንብሶ … ወደመኪናው እንድሄድ በምልክት ይጣራል ….ሁሉም ጓደኞቸ ኮስተር ቆጣ ብለው (ልክ መጠራታቸውን እንዳልፈለጉት ሁሉ) ‹‹እኔን ነው ? ›› አይነት ጥያቄ በምልክት ሲጠይቁ እራሱን እየነቀነቀ ሁሉንም እንዳልሆነ ሲያሳይ ….. እንግዲህ ሁሉም ተዳርሰው ተራው እኔ ላይ ደረሰ እኔን እንደሆነ ቢገባኝም እንዳለየ ፊቴን አዞርኩ (ወጉ ነዋ ኩራት….. በውስጤ ግን ትንሽ እንዲለማመጠኝ ፈልጌ ነበር ….ድንገት አስነስቶ ፈትለክ እንዳይል እየፀለይኩ ›› ፈገግ አለች ልእልት ….
ፈገግታዋ ያሳዝናል ….ልክ አንድ ትልቅ ህንፃ እያየ ‹‹ይሄ ህንፃኮ የኔ ነበር ባንክ በሃራጅ ሸጠብኝ እንጅ ››እንደሚል ጊዜ የጣለው ባለሃብት ፊቷ ላይ የሚያንገበግብ ቁጭት ነበር ! ፍዝዝ ባለ ቀለም ግድግዳው ላይ ትዝታዋ የተፃፈ ይመስል ውብ አይኖቿን ግድግዳው ላይ ተክላ ነበር የምታወራኝ ….በዚህ አመለካከቷ ለቀጣይ አስር ደይቃ ከቀጠለች የምታይበት ቦታ ላይ ግድግዳው የሚሸነቆር እስኪመስለኝ …እንኳን እኔን እያየች ያላወራች …ምንበወጣኝ ሌላ ቢላ ያውም ሁለት ….ያውም ልቤ ላይ(ትንሽ ከፍ ቢል ልቡን ነበር አሉ እማማ ቁንጥሬ…ትንሽ ዘወር ብትል ልቤን ነበር …..) የታችኛው ከንፈሯን ወደአፏ ውስጥ ሳብ አደረገችና ምጥጥ አደረጋ ለቀቀችው ርጥብ አለ ….ከንፈሯ ሊጠበስ የተዘጋጀ ቀይ ጥሬ ስጋ መሰለ ! ግሎ የሚጠብቀው መጥበሻ ላይ ጣል ሲደረግ ቸሰስስስስ የሚል ዓይነት ! (ጥሬ ስጋ ስለማልወድ በልቸ አላውቅም …ምን ምን ይል ይሆን ብየ አሰብኩ …ይሄ ሁሉ ወፈ ሰማይ የአበሻ ህዝብ በየስጋ ቤቱ ጥሬ ስጋውን እየቆረጠ ያለነገር አልተኮለኮለ )
…በእነዚህ እርጥብ ከናፍርት ምናለ የሆነ ስርቅርቅ የሚል ዘፈን ነገር ቢዘፈንባቸው…ምናለ የሆነ የፍቅር ነገር ቢወራባቸው …. ብየ ሳስብ ልእልት ቀጠለች
‹‹ እና እኔን ነው ? እኔን ነው ? ሲሉ ቆይተው …ጓደኞቸ የራሳቸውን ጨርሰው እጃቸውን እኔ ላይ ቀስረው አመለከቱትና ‹‹እሷን ነው ›› ሲሉት …. ‹‹አዎ›› አለ ….
‹‹ይጠራሻል›› አሉኝ በጉጉት ……ሁሉም በአንድ ላይ (እስቲ አንድኛቸው ቢነግሩኝ አይበቃም?) ልክ ለሽልማት ወደመድረክ የተጠራሁ ይመስል ግማሽ ቅናት ግማሽ ቅሬታ (ጥሪው ለእነሱ ስላልሆነ) ፊታቸው ላይ ተኮፍሶባቸው ….ከእነዚያ ሁሉ ቆንጆዎች ተመርጨ ያውም መኪና ….ከመኪናም ቢኤም ደብሊው በያዘ ወንድ መጠራቴ ፊታቸውን በቅፅበት ለዋውጦታል ‹‹ከማን በልጣ ነው ›› አይነት ….
(ያኔ የመኪና ስም ማጥናት የጀማመርንባት እድሜ ነበረቻ …አለኮ ባይስክል ባይኖረንም የሚናቅና የሚከበር መኪና ብለን የምንፈርጀው ነገር ….ከማየት ብዛት የእራሳችንን ህያው ቁንጅና አባይ ሚዛን ላይ አስቀምጠን ‹ልኬ ይሄ ወንድ ነው ›› ሳይሆን ‹‹ልኬ ይሄን መኪና የያዘ ወንድ ነው› የምንልበት›› ….. እና በጊዜው ያንን አማላይ መኪና በሚነዳ ወንድ በመጠራቴ ኩራት ተሰማኝ …..ግን ኮስተር ብየ እንዳላየ ዘጋሁት …ጓደኞቸን ‹‹እረፉ ›› ከሚል ግሳፄ ጋር ! ሁሉም ተቁነጠነጡ ….ልጆች ነበርን ያኔ መኪና የያዘ ወንድ አለምን የገዛ ነበር የሚመስለን ….በእኔ ትእቢት የእነሱን አለመመረጥ የተበቀልኩት ይመስል ‹‹ደግ አደረግሽው ይሄ ፈጣጣ ልክስክስ›› እያሉ አሞካሹኝ ! አይ ልክስክስ እቴ መጀመሪያኮ ጲጵ ሲል አዟዟራችን … ሹፌሩ ሳይሆን መኪናው የጠራን ነበር የሚመስለን ›› ዝም ብላ አፍታ ቆየች …..
‹‹ መኪናውን አስነስቶ ሄደ … ወዲያው ጓደኞቸ ጋር ሌላ ወሬ ጀመርን …አለ አይደል ‹‹ሄደ መጣ ግድ አይሰጠንም›› ለማለት ያህል …ግን የሁላችንንም ልብ ጭኖት ነበር የሄደው …. በተለይ እኔ ውስጥ ትንሽ መቆላጨት ነበረች … ፍቅረኛ እንዲኖረኝ አይኔ ግራ ቀኝ የሚቃብዝበት እድሜ ነበር …ከጓደኞቸ የተሻለ ፍቅረኛ እንዲኖረኝ የምመኝበት ጊዜ ነበር … ፍቅረኛ የተለየ ፍጥረት እንጅ ከፒያሳ ከቦሌ ከአቃቂ ከሜክስኮ ወይ ከሆነ ክፍለ ሃገር የሚመጣ ሰው አይመስለኝም ነበር ….ፍቅረኛ የሆነ ህልም ነገር ነበር ለኔ ! አንዳንዴ ገና በማላውቀው ፍቅረኛየ ሁሉ ሌላ ሴት ጋር ቢሆንስ ብየ የምቀናበት አስገራሚ እድሜ ……
ሁሉም ሰው ቆንጆ ነሽ ይለኛል … በየቀኑ የፍቅር ደብዳቤ ከተማሪ እስከአስተማሪ ይጎርፋል …. ያ አድናቆት እራሴን እንደተራ ልጃገረድ ትምህርት ቤት ሳር ላይ ተቀምጨ ተማሪ ጋር የምሟዘዝበት እንዳልሆነ እንዳስብ አድርጎኝ ነበር …በዚች ሁሉ ነገር በገንዘብ በሚሸቀጥባት ርካሽ አለም ….ቁንጅናየን ራቅ ባለ መደርደሪያ ላይ ወስደው ሰቅለውት ….ለማውረድ ዘለግ ያለ የሃብት ወይ የእውቅና ቁመት ያለው ሰው ፍለጋ አፍላ ነፍሴ ስትቃትት ነበር …. እንደልጅ እዛና እዚህ ቦርቄ ከማለፍ ይልቅ አግብታ እንደፈታች ሴት ስቆነንና ሁሉን ነገር አይቸዋለሁ አይነት ባዶ ኩፈሳ እድሜየን በላው …..የሆነ ለየት ያለ ሰው ሳፈላልግ ነበር ….ከመለአክ ዝቅ ያለ ምስሉ ሁሉ አእምሮየ ውስጥ ነበር …..ምናልባት ከአንዱ ፊልም ላይ አንጎሌ ውስጥ የተሻጠ የቅዠት ስእል ይሆናል….ግን ‹ኮራሽ… አንች ገንዘብ ያለው ወንድ ነው የምትፈልጊው › ለሚሉኝ ጎረምሳ ተሜዎች ሁሉ ሁሉ ‹ዋናው ፍቅር ነው› ነበር መልሴ(ወግ አይቀር ንቄቱን ከነማስተባባያው ታጥቀነው ነበር ……የሴትነት ግርዶሸ እንግዲህ መመፃደቅም በለው )
ይሄውልህ እንግዲህ ሳልጀምረው ነበር የአድናቆት ዛፍ ላይ በተቋጠረ የውበት ገመድ ፍቅርን ያንጠለጠልኩት ! የሚቆጨኝ …..አንድ ልጅ (እስከአድማስ የሚባል … እውነትም እስካድማስ ) የለመነኝ ልመና ….አለባበሱ አሁንም አይኔ ላይ አለ …. ቅጥነቱ … የአፍንጫው ስልክክ ማለት አይኖቹ ((((ልክ እንዳንተ ))) (በለው አሁኑኑ ከሆስፒታል ብወጣ አንድ ቁስል አይገኝብኝም በስማም እንዳንተ ብላ አፈረጠችውኮ እንዲህ ሲያመልጥ ደስ ይላል ) ….. ሰው አራት አመት ሙሉ ይለምናል አብርሽ ? … ግን ልመናው በየቀኑ የሚያወራልኝ ወሬና አድናቆት ሁሉ እንደተበጠበጠ ስሚንቶ በጆሮየ እየገባ ልቤን በትእቢት ኮንክሪት አሳበጣት እንጅ ምንም …ርህራሄ የሚባል እንዲች ብሎ አልፈጠረብኝም … አውርቶኝ አውርቶኝ … ቀና ብየ ስመለከተው ያወራኝ ሁሉ ብን ብሎ ይጠፋል ከውስጤ ….አራት አመት ለመነኝ …. ውሸት ነው ሴት ልጅ በጆሮዋ ታምናለች ምናምን የሚባለው …ቢታመን ያ ሚስኪን ልጅ ጆሮየ ተቆርጦ እስኪበር ያወራልኝ ያህል በህይዎት ዘመኔ ሁሉ ማንም እንደማይደግመው ያኔውኑ አውቄ ነበር … ሚስኪን እስከአድማስ …እኔን ውሃ ይብላኝ ወደሊቢያ ነው ወደየት አገር በባህር ሲያቋርጡ ጀልባ ተሰብሮ ሞተ ብለው ባለፈው ሲነግሩኝ ተደብቄ አለቀስኩ … በቃ ያኔ
እኔን ለፍቅር ማሰብ ደመና መጨበጥ ነበር … እንኳን ለሌላው ልገኝ ከራሴም ጠፍቸ ነበራ ! ወንዴ ጋር እንደተጋባን አካባቢ ‹‹ያ ትእቢቴ የማንም መጨዋቻ ከመሆን አድኖ በክብር እንድዳር እንድኳል አደረገኝ ›› እያልኩ ሃሴት አድርጌ ነበር ….ግን መጣልሃ የኋላ ኋላ …በሚሊየን ተባዝቶ !! ትእቢቴ እንደረመጥየጊዜ አመድ ውስጥ ተቀብሮ ኑሮ ባዶ እግሬን በቆምኩበት ሰዓት ተገልጦ አንገበገበኝ !!
ሌላ ቀን ከትምህርት ቤት ወጥተን ከጓደኞቸ ጋር በኤሊ እርምጃ ወደቤታችን እናዘግማለን ….ከትምህርት ቤት እቤቴ ድረስ ፈጠን ባለ እርምጃ እንኳን ብሄድ አስር ደይቃ አይሞላም ነበር ….ግን ጓደኞቸ ጋር ወሬው መንገድ ላይ በአይን መጎነታተሉ እንዲሁ የእለቱን አድናቆት ከማናውቀውም ከምናውቀውም ጎረምሳ መስማቱ (የደፈረ ቃል አውጥቶ ያልደፈረም በእይታው የሚለን ነገር ነበር …የልባችንን መዝገብ በርግደን በደማቅ ቀለም ድምፁንም ድምፅ አልባውንም አድናቆት የምንመዘግብባት መድረክ ነበርች ያች ሰዓትና ያች መንገድ … ድንገት ወንዴ ሌላ መኪና ይዞ (ምናይነትም እንደሆነች እንጃ ነጭ መሆኗ ብቻ ነው ትዝ የሚለኝ) ከኋላችን ክላክስ አደረገ….ሁላችንም ዞርን ….ጓደኞቸ ያ የባለፈው ጥቁር መኪና የያዘው ልጅ ምናምን እያሉ አንሾካሾኩ ….ጭራሽ ከጎናችን መኪናዋን ከእኛም እርምጃ ባነሰ ፍጥነት እየነዳ (የውሃ ቱቦ ውስጥ እንዳይገባ ይሄ ሰው እያልን እየተሳሳቅን)
‹‹ልእልት ሌላው ቢቀር ሰላም በይኝ ›› አይለኝ መሰለህ ….ልቤ ስንጥቅ ነው ያለው ….ዞር ብየ አየሁት ያው እንዳየኸው መልኩ ቆንጆ ነው ….በዛ ላይ የለበሰው ጨለማ የመሰለ ድፍን ሹራብ ቅላቱን እድምቆታል …..መቸስ ሰው ነኝ ….በዛ ላይ መኪናው አለ …ከሁሉም በላይ ጓደኞቸ ፊት ያውም ከነመኪናው ተንበርክኮ ከፍ ያደረገኝ ወንድ ባወጣ ባወርድ የምገፋበት ምክንያት አጣሁ …ደግሞ ስሜን ማወቁ እኔንም ጓደኞቸንም አስደነቀን (ከባድ ነገር ይመስል) አንዳንዴኮ ልባችን እንዴት ትንሽ ንፋስ የሚያርገበግባት ፌስታል ነገር እንደሆነች …ስሜን አወቀው የሚለው ሳይሆን እኔም በሌለሁበት ስሜን ለማወቅ መጣሩ ‹‹ ቁም ነገረኛ …እኔ ህልሙ የሆንኩ ከርታታ ›› መስሎ እንዲታየኝ አደረገ …አራት አመት ስሜን ከነምንጅላቴ ሲደግም የኖረው እስካድማስ ምን ይባል …..ውሃ ይብላኝ የኔ ጌታ ውሃ በላው ! እንባዋ ተዘረገፈ …ወዲያው ጠራረገችው !
ያው እንደነገርኩህ ነው …. ብዙ ጊዜ ንግግሩ ሳይሆን ተናጋሪው ያለበት ሁኔታ ነው የሚሰማን !!((( ሃብት፣ እውቅና ፣ስልጣንና ቁንጅና እንደድምፅ ማጉሊያ ነገር ናቸው ….. ከእነዚህ አንዱ ካለህ የተናገርከው ነገር ምን ተልካሻ ቢሆንም እንኳን ….አንተ ስትናገረው ግን ጮክ ብሎ ሁሉም ጆሮ ላይ ሁሉም ልብ ላይ ይደርሳል ! ሰዎች ቢጥማቸውም ባይጥማቸውም በመስማማት ራሳቸውን ሲነቀንቁ ታያለህ …..‹‹አይ ተሳስተሃል›› የማለት ድፍረቱ ያላቸው በጣም ትንሽ ናቸው))እንዳለመታደል ሁኖ ያኔ እነዚሁም ጥቂቶች አጠገቤ አልነበሩም …ቢኖሩም እሰማቸው ነበር? ….እንጃ ! …..እና ….ያን ቀን ላለመግፋትም ላለመሳብም ዞር ብየ ወንዴን አየሁት …በተለሳለሰች አዟዟር ብዙም በማትቆረቁር አይን ….እንደውም ድምሩ ወደፈገግታ በሚያደላ ፊት ! እንጃ ከአይኔ ምን እንዳደመጠ ፍጥነቱን ጨምሮ ተፈተለከ ….. ‹‹ውይ አንች ልጅ ግፍሽ ›› አሉኝ ጓደኞቸ … አራት አመት ለለመነኝ ሚስኪን ያላሉትን …
ልእልት … ስታወራኝ በወሬዋ መሃል ሁለት ሶስት ጊዜ ጣቶቿን ቀጥ አድርጋ ዘርግታ የጋብቻ ቀለበቷን በቁጭት ትመለከታለች … የወርቅ ቀለበቷ ….ጣቷ ከጊዜ በኋላ የመጣ ውፍረት ተጨምሮበት ሳይሆን አይቀርም በስጋዋ ተውጧል …. ጣቶቿ ቀለበት ከሚያርፍበት ቦታ ጀምሮ እስከአንጓው ወፈር ብለው ይወርዱና ከአንጓው በኋላ እየቀጠኑ ሂደው እንደጦር የሾለ ጫፋቸው ላይ ይፈፀማሉ …. ቆንጆ ጣቶች ቆንጆ መዳፍ …..የመዳፏና የመዳፏ ጀርባ ወደቅላት የሚወስደው ጥይምና አንድ አይነት ነው …. ፊቷና እጆቿም አንድ አይነት ናቸው ….ምናልባትኮ ሙሉ ሰውነቷ አንድ አይነት ይሆናል እያልኩ አስባለሁ (ያው ሃሳብ ነው)
የልእልትን ታሪክ አጠር ላድርገው ….እንግዲህ ከብዙ ምልልሶችና ብዙ ፊት ምንሳቶች በኋላ አንድ ቀን ብቻዋን ወደቤቷ ስትጣደፍ (ጓደኞቿ የት እንደሄዱ እሷም ራሷ ትዝ አይላት) ወንዴ ከኋላ ከች አለ ! ክላክስ አላደረገም …ጠጋ ብሎ ጠራት ‹‹ልእልት›› ዞራ አየችው ከዛ ዙራ ጓደኞቿ አለመኖራቸውን ተመለከተች ….እናም ወደመኪናው ሄደች …. እጁን ለሰላምታ ዘረጋላት ጨበጠችው …. መኪና ውስጥ ‹‹ግቢ›› …‹‹ አልገባም ›› ለደይቃዎች ከተነታረኩ በኋላ ከመኪናው ውስጥ የሚወጣው መልካም የሽቶ ጠረን …የወንዴ ጨዋ ልመና እንዲሁም የውስጥ መሻቷ እንደበሽተኛ ደጋግፈው ወንዴ መኪና ውስጥ አስገቧት …. ከዛን ቀን ጀምሮ …እዳው ገብስ ሆነ … ምን ችግር ወንዴ ሁሉ በጁ ሁሉ በደጁ …. የትምህርት ቤት ሰርቪሷ እስኪመስል ከትምህርት ቤት ስትወጣ በር ላይ ወንዴ አለ ….ቤቷ ቅርብ ስለሆነ የዙሪያ ጥምጥም እያወራት ….ይወስዳታል አንዳንዴም ሻይ ቡና ይላሉ ….ወንዴን ‹‹ልክስክስ›› ያሉት ጓደኞⶩ በመደዳው ግብዣውን አዥጎድጉዶ ቀናቸውን ፋሲካ ሲያደርገው ‹‹ፅድት ያለ ልጅ ›› አሉና ማእቀባቸውን አነሱ ….‹‹በፋሲካ የተገዛች ባሪያ ሁልጊዜ ፋሲካ ይመስላታል››
‹‹ ወደድኩት›› አለች ልእልት ስትነግረኝ ‹‹ ወሬው አይደለም …. እንደውም ወንዴ ከተዋወቅን ጀምሮ እስካሁን ምን ፍሬ ያለው ነገር አወራሽ ብትለኝ ይሄ ነው ብየ የማነሳው ነገር የለም ….እውቀቱ አይደለም ወንዴ ትምህርት ከንቱ ድካም ነው ይላል ….የሆነ ጊዜ አምኘው ነበር …..ቁንጅናውም አይደለም ….ውይ እንደውም ከቀረብኩት በኋላ ቆንጆ መሆኑ ትዝ የሚለኝ ሌሎች ሲነግሩኝ ነው ….መልከ ጥፉ ሰውም ቢሆን ከቀረብነው መልከጥፉነቱ ለሌሎች እንደሚታየው ለእኛ እንደማይታየን የገባኝ ያኔ ነበር ….ግን በቃ ምቾቱ አሰነፈኝ ….ስሄድ ስመጣ በመኪና …አይደክመኝም ….ትምህርት ከደበረኝ እደውልለታለሁ ወንዴ አፍታ ሳይቆይ ከች ይላል.. በቃ ምቹ መኪናው ውስጥ ወንበሬን ወደኋላ ለጥጨ በምቾት እንፈላሰስና ወደፈለገበት እንዲወስደኝ መንገር ነው …. አይኖቸን ስገልጥ የሆነ መናፈሻ ውስጥ ወይም ምርጥ ሬስቶራንት በር ላይ ነን ….ምቾቱ አሰነፈኝ …ስንፍና የወለደው ፍቅር ወንዴ ጋር አጣበቀኝ ….›› ልእልት አይኖቿ ከበፊቱ የበለጠ ቦዘዙ …እንደውም እንባ የኳተሩ መሰለኝ …ፊት ለፊት ማየት ስለምፈራ እንዲሁ በጨለፍታ የማየው ነገር ላይ እርግጠኛ ስለማልሆን ነው መሰለኝ የምለው …..
….ለስላሳ እጆቹ ምን ጊዜም ፀጉሬን እየነካኩ ናቸው ደስ ይለኛል …. መላ ሰውነቴ ላይ እጆቹ አሉ ….ወንዴ ብዙ እጅ ያለው እስኪመስለኝ ….እጆቸ ከእጆቹ ውስጥ አይወጡም ….ደስ ይለኛል ….በቃ ለእኔ ይሄ ህይዎት የምቾት ምናኔ ነበር …. ወንዴም ከዛ አቧራ ፀሃይና የሰው አይን …የሚጠብቅ ቅጥር … አዲስ አበባ ዝቅ አለችብኝ ….ጓደኞቸ ከትምህርት ቤት ወጥተው በእግራቸው ሲኳትኑ ሳይ ለትምህርት ሳይሆን ለሆነ ግዞት ስንቃቸውን በቦርሳቸው ቋጥረው የሚያዘግሙ ይመስሉኛል ….ቀስ በቀስ ከጓደኞቸ ጋር ተራራቅን ወንዴ ብቻ አለሜ ሆነ ….በሆነ የምቾት ባሉን ተንሳፈፍኩ ያ ምቾትም ዘላለማዊ መሰለኝ …በህግ የተደነገገ የማይሰረዝ የማይበረዝ ሰማያዊ ትዛዝ ….እናም ወንዴ ወደአልጋ ሲጎትተኝ አንዳች ፍርሃትም ስጋትም አልተሰማኝም ….የመጀመሪያየ ነበር … ግን ደስ አለኝ ! በዚህ ምቾት ላይ ወሲብ ሲጨመርበት እንኳን ሌላውን ጉዳይ ራሴን ረሳሁ !! መሳሳም ነፍሴ ነው ..(ቀና ብየ አየኋት …ይሄን ከንፈር ይዛ መሳሳም ነፍሷ ባይሆን ነበር የሚገርመው የልእልት)
ቀጠለች ልእልት …(ኧረ ትቀጥል እንዲህ አይነት ጣፋጭ ገመና እንደመስማት የሚጥም ምን ነገር አለ ….) ወንዴ በሁሉም ነገር የእኔ የራሴ ግልባጭ እስከሚመስለኝ ….በቃ ራሴ ጋር የምኖር እስከሚመስለኝ ሁሉ ነገሩ ይመቸኝ ነበር …. ሁሉ ነገሩ ….አይኖቹ ይናፍቁኛል ከንፈሩ በቁሜም ህልሜ ነበር …አንገቱ ስር በቅበጥ እንዴት እወድ እንደነበር ….ደረቱ …ወይኔ ደረቱ ሁልጊዜ ደረቱ ላይ እንደተለጠፍኩ …..እንደዛሬው እንዳይመስልህ ሆዱ ዛሬ ትንሽ ቦርጭ አውጥቷል ያኔ ምንም አልነበረውም …….(አሃ አይን ከንፈር አንገት ደረት ሆድ…… ተው ይች ልጅ አ ሽ ቆ ለ ቆ ለ ች ) …..ለምን እደብቀሃለሁ …..ወንዴ ጋር ‹ሴክስ› ስናደርግም ልብሴን ጥየ ነበር የማብደው !!!!!! (መጀመሪያ ልብሳቸውን ሳይጥሉ ነው እንዴ ወደገደለው የሚገቡት የሚል ‹ነገር ስንጠቃ› አእምሮየ ሲያምረው ‹‹ዝም በል›› ብየ እገስፀውና ወደልእልት ወሬ ጆሮየን አቆማለሁ አሁን እየተወራ ያለው ጉዳይ እጅጅጅጅጅጅጅጅግ መሳጭ ጉዳይ ነው ….ውጋቴ ወላ የቁስሉ ጥዝጠዛ ሁሉ ድራሹ ጠፋኮ እናተ ግን ልእልት ያመጣችልኝና የጠጣሁት ሾርባ እንደመዓበል ሆዴ ውስጥ እየተነሳ ሲፈርጥ ተሰማኝ )
ልእልት ድንገት ወደኔ ዙራ ‹‹አብርሽ›› አለችኝ
‹‹አቤት!! ›› አልኩ ከወሬዋ ምሳጤ ነቃ ብየ!! ‹‹አቤት›› አባባሌን ለተመለከተው ጦር ሜዳ መሪው የጠራው ወታደር እንጅ ከጠያቂው ጋር የሚያወራ በሽተኛ አልመስልም ነበር ! ….የራሷን ጡቶች በሁለት እጆቿ ጭንቅ እስኪላቸው ….እቅፍ አድርጋ
‹‹ወንዴንኮ ስወደው ….›› ብላኝ እርፍ !!
(ብስጭት ብስጭትጭት ! እግዜር በቸርነቱ አፋታልኝ ….የዛን ወፈፌ ባሏን ጉዳይ እንደሰንኮፍ ከልቧ ነቀለልኝ ብየ ከስንት ጠያቂ መሃል ሷን ኮቴ ጆሮየን አቁሜ ስጠብቅ ….ከስንት ጉድ ቬርሙዝ ለይቸ እስቲ ከዛ አረንጓዴ ቬርሙዝ ሾርባ ቅዱልኝ እያልኩ ….ከስንት ጉድ ፍራፍሬ ከስንት ነገር ……ኤዲያ …ደግሞ አለች ወንዴን እወደዋለሁ …..
አንዱ እንደኔ አንጀቱ የበገነ ሰውየ ነው አሉ ድሮ …. እንዲህ እንደኔ አንዷን አይናይኗን በአጉል ክጃሎት ሲመከለከት ያመሽና ወደማታ ባሏ ከች ብሎ ተያይዘው ወደምኝታቸው ይሄዳሉ ….ሰውየው ታዲያ እንደኔ አልጋ ላይ ተጋድሞ ሲብከነከን አላመሸም ቢያንስ ተናግሮ ወጣለት
‹‹ተቀብል ›› አለው አዝማሪውን
‹‹ያማሪካን ስንዴ የሚያልቀው በንኩቶ
ይዛው ጋደም አለች ባል ተገኝቶ ሙቶ !! ሃቅ !
አሁን እኔ እዛ ቦታ ብኖር ድፍን መቶ ብር እዚህ ሰውየ ግንባር ላይ ብለጥፍ ይፈረድብኛል ??
እንዲህ ስርቅርቅ ብላ ‹‹ወንዴንኮ ስወደው›› ትላለች እንዴ …በሽተኛ ነኝ ….በሷ ጠንክ የደረሰብኝን ((መካከለኛ የመቁሰል አደጋ)) እያስታመምኩ ያለሁ ሰው ነኝ …. እንደውም ብርቱ ልጅ ሁኘ እንጅ በዚህ ንግግሯ የተሰፋው ቁስል ትርትር ባለና እማማ ቁንጥሬ እንዳሉት ቁስሉ አመርቅዞ ከነገወዲያ ሳልስቴ በወጣ ነበር !! መዘዘኛ !!….ያንን የሚያክል ሻንጣ እያንዘፋዘፍሽ ለኔም ጦስ ከመሆን አርፈሽ አትቀመጭም ….አዋ ያኔ ደረጃው ላይ ባላገኛት አርፌ እንቁላል ፍርፍሬን በበላሁና ‹በቀኝ አውለኝ› ብየ ወደጉዳየ በሄድኩ ነበር … አሁን ግን እንኳን የፈሰሰው ደሜ ያኔ እሷን ለማገዝ ብየ እንቁላል የያዝኩበትን ፌስታል ግንቡ ላይ ሳስቀምጠው የተሰበረችው አንዲት እንቁላል ቆጨችኝ !! ….ድሮ ሰፈራችን ትልቅ ሰው ሲወድቅ የወደቀበት ቦታ ላይ እንቁላል የሰበርለት ነበር (ሴጣን እንዳይጣላው መሆኑ ነው) ዛሬ ነበር ለእኔ እንቁላል መስበር ከምር ….ከተስፋየ ላይ እኮ ነው አውርዳ ዘጭ ያደረገችኝ !
ለራሴም እስኪገርመኝ ወንዴ ስለሚባለው ‹አጋሰስ › በጎ በጎውን ስታወራ ቅናት እንደቢላ ቆዳየን ሲሰነጥቀው ተሰማኝ … ደግሞ እንጅ አወራሯ ምናለ ለስለስ አድርጋ ብታወራ ! ከምር ማንም ወንድ አንዲት ውብ ሴት ስለሌላ ወንድ እንዲህ በፍቅር ስታወራ ቢሰማና ቢያይ መቅናቱ አይቀርም !! ተበሳጨሁ … እራሴ የገነባሁት ቀቢፀ ተስፋ እንደባቢሎን ግንብ ተንዶ ሲጫነኝ የቁስሌም ጥዝጠዛ አብሮ ሲነሳ ተሰማኝ ….
‹‹ እኔ የምልሽ ልእልት እንዲህ አካብደሽ ምታወሪለት ወንዴ የትኛው ነው ? ይሄ ሰካራሙ …ይሄ ባላደረግሽው ነገር በእኔ ጠርጥሮሽ በቢላ የወጋኝ ….ይሄ በደረቅ ሌሊት እንደጥራጊ ከነልብስሽ ገፍትሮ አስወጥቶ በር የዘጋብሽ ›› ብየ ከጣፋጭ ትዝታዋ ቀስቅሸ የወንዴን መጥፎ መጥፎ ነገር እንድትነግረኝ ወደዛሬ ላመጣት ከጅየ ነበር ! እንዴዴዴ አወራሯኮ አሁኑ ብር ብላ ወንዴ ጋር መሄድ የናፈቃት አይነት ሴት ነው የምትመስለው !!(ይሄማ ያፈሰስኩላትን ደም የከሰከስኩላትን አጥንት በአጠቃላይ የከፈልኩላትን መስዋእት መዘንጋት ነው )
<<ወንዴንኮ እወደዋለሁሁሁሁሁ??>>
አሁን በዚች ምድር ‹‹እንደወንድየ አንበሳው›› የታደለ ሰው አለ? ምንም ሳይሰራ ገድሉን በፍቅር የምትተርክ ውብ ሚስት አለችው…. ያውም በትዝታውና በፍቅሩ ስርቅርቅ እያለች …በዛ ላይ ከተራ ፖሊስ እሰከባለስልጣናት በትውውቅም በእጅ መንሻም ልጃቸውን ነፃ ለማውጣት የሚራወጡ አባት አሉት ….. ከሃብታም አባቱ እና ዘመዶቹ የሚላክለትን ምግብና ያሰኘውን አይነት ልብስ እየቀያየረ …..ጥርስ ከማያስከድኑ እስረኞች ጋር ዘና ብሎ እየተጫወተ ይሆናል ….ምናልባትም ልክ እንደሬንቦ ፊልም እኔን እንዴት እንደዘረረኝ እየተረከ እያስደመማቸው ይሆናል ….
‹‹ ሚስቱን ስለነካሁበት ብቻ ከአራተኛው ፎቅ ላይ በገመድ ተንጠላጥሎ ከወረደ በኋላ እኔ ቤት ሲደርስ እንደኮማንዶ በእግሩ የመስኮቴን መስተዋት ሰባብሮ ተንከረባብቶ ምኝታ ቤቴ ገባ …እኔ ተኝቸ እያንኮራፋሁ ነበር ….ድንገት የመስተዋቱ መሰባበር ከእንቅልፌ አንቅቶኝ ፊቴ በግርማ መጎስ ተገተረውን ወንዴ አንበሳውን ሳይ ከመደንገጤ ብዛት ከእንቅልፌ ነቅቸም ማንኮራፋቴን ቀጥየ ነበር ….ሊምረኝ አስቦ ነበር ግን ቆንጆ ሚስቱን እንዲህ አይነት አንኮራፊ ወንድ መድፈሩ ትዝ ሲለው ‹ሰይጣኑ› ተነሳ …..እናም በግራና ቀኝ ታፋው ላይ የያዛቸውን ጩቤዎች አልሞ በመወርወር እንዴት በአንዴ አንገቴ ላይ እና ደረቴ አካባቢ እንደሰካቸው ›› ለእስረኞቹ እየተረከላቸው ይሆናል … እስረኞቹም እየሰሙት ይሆናል …ልእልት እንዳለችው ሃብታም ቆንጆ እና ባለስልጣን ምንም ቢል ይሰማል !!
ልእልትን ቀና ብየ አየኋት አሁንም ትልልቅ ጡቶቿን እንዳቀፈች ግድግዳው ላይ አይኖቿን ተክላ በራሷ ትዝታ ጠፍታለች …..( የሚያቅፍ ይቀፍሽ እቴ) እንግዲህ ምን እላለሁ …ቀሪውን ገድል እየሰማሁ ልቃጠል እንጅ …..ልእልት ቀጠለች …..
9 Comments
በጣም አሪፍ ነው
ለምንድን ነው ፎቶ የሌለው?
ፍቅርወሳኝነው።
ሀሚኑ
ዋው ያበደ ታሪክ ነው
ወሬ በጣም በዛ ግን ጥሩ ነው።
ዋዉ.ይመቻል
በጣምየሚገርምታርክነዉ