ተኮላ የተባለ ሰው አፍቅሬ በትዳር መኖር ከጀመርኩ አሁን ሰማንያ ሰባት ነው አይደል? አዎ አንድ አመት ተኩል አለፈኝ፡፡ በዚህ …. ማለት በቃ ከእሱ ጋር አንድ ቤት ውስጥ ሚስቱ ሆኜ በመኖሬ ደስተኛ ነኝ፡፡ አንዳንድ ሰዎች በማያገባቸው መግባት የሚወዱ ወይም የማናቀፍ ጉጉታቸው ወሰን የሌለው ‹ለምን ተኮላን አገባሽው?› ይላሉ፡፡ ብቀርባቸውም ባልቀርባቸውም ነው፡፡ ያጠያይቃል እንዴ? ካገባሁት አገባሁት ነው፡፡ ድርቅና በሉት ወይም ፈጣጣነት በሉት ብቻ ግራ ያጋቡኛል፣ ምን ግራ ያጋቡኛል፣ ደብሩኛል ልበል እንጂ፡፡ ሁልጊዜ የምመልሰው ‹ስለወደድኩት ነው› ብዬ ነው፡፡ ፊታቸውን አዙረው ወይም ለማንሾካሾክ እንዲመቻቸው ከእኔ ፈቀቅ ብለው ከሚመስላቸው ጋር (ከአሽሟጣጭ ጋር፣ ከአናቃፊ ጋር፣ የውሸት ተጠራጣሪ ጋር፣ የሀቁን ቀናኢ ጋር) ‹ነው እንዴ?› እንደሚሉ እገምታለሁ፡፡
የሕልውናን ትርጉም በሚያበላሽ ቋንቋ እንደ እነሱው በልቼና ጠጥቼ ያደግኩ መሆኔን በሚያስቅ ስልት ይረሳሉ፡፡ የሚጠይቁኝ ከእሱ ጋር መኖሬ አከራካሪ እንዲሆን ስለሚሹ ነው፡፡ የጠራ ሰማይ ሲያዩ ለማደፍረስ ስለሚቃጡ (ዓይኖቻቸው ቀልተው)፣ አለ አይደለ ካፈቀርኩት ሰው ጋር በመኖሬም ደደብ ቅናት ጨምድዷቸው፡፡ ሌላ ምን ሊሆን ነው ታዲያ? ደጋግመው ሲጠይቁኝ ዝባዝንኬም ስለማልወድ ‹ተኮላን ያልወደድሽ ማን ነበርሽ?› የሚል እራሳቸውንም የሚጨምር መልሴን እወረውራለሁ፡፡ የከፈቱአቸውን አፎቻቸውን ሳያስጠጡ ይዘጋሉ፡፡
ቤተሰቦቼ በዕድሜ እኔን የሚበልጠኝን ተኮላን በማግባቴ ይበሳጫሉ፡፡ አያስገርመኝም፡፡ ታዲያ ዘመኑ ነጻ አድርጎን ይሄው የወደድነውና የወደደን ወንድ ቤት ዘው ብለን እንገባለንና ከጥንት ባህል ሲቃረንባቸው ምን ያድርጉ? ሌላ ምን ሊሆን ነው ታዲያ? ካልተጠላለፉ፣ ወይም ዘመድ፣ ወዳጅና ቤተሰብ ካልፈቀደላቸው የማያገቡበት ዘመን ስለተወለዱና ስለአደጉ ልፈርድባቸውም፡፡ የምፈርደው በዞረባቸውና ባሁኖቹ ‹ወጣት ነን› በሚሉ የመንፈስ አጁዛዎች ነው፡፡ በአደባባይ ስለነጻነት የሚነሰንሱት ፍልስፍናቸው በልቦናቸው ክፋትና ድንቁርና ሲበረዝ፣ ቃላተ-ዲሞክራሲያቸው በልጋጋቸው ውሃ ሲታጠብና ከቁጩ ብራናቸው ላይ ሲለቅ፣ ይሄው እንዲህ ያጋጥመኛል፡፡ ዕጣዬ በዕድሜ የገፋ ሰው ላይ ቢጥለኝም፣ ምን አለበት ፍቅር ክንድ ላይ ነው፡፡
ግን ደግሞ ‹አልተመቻችሁኝም› ብትሏቸው ማረፍ አባታቸውን ገድሏልና፣ (ወይም ዘር ማንዘራቸውን) የዘጉትን አፋቸውን መልሰው መላልሰው እየከፈቱ (ሃፍረተ ቢስነት የለመደባቸው)፣ የነገር መንገድ ትንሽ ቀያይሰው፣ በፈጣጣ አማርኛ ‹እሱ እኮ ሴት መያዝ ይችልበታል› ይላሉ፡፡ ይሄ አባባል ግልጽ አይደለም፡፡ የበሰልኩ ነጻ ልጅ ስለሆንኩ ‹መያዝ› የተባለው ቃል ሲያልፍ አይነካኝም፡፡ እወደዳለሁ እንጂ አልያዝም፡፡ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ተኮላ ያለውን ችሎታ አልደብቅም፡፡ መያዝ ማፍቀርን ከተካ ጠማማው የዘመኑ አተረጓጎም እንጂ የእኔ እንዳልሆነ ይቆጠርልኝ ዘንድ ያለትህትና እጠይቃለሁ፡፡
መዋሸት ግን ማንን ይጠቅማል? ራሴን ለመከላከል ብዬ ትንሽ ሳላጠቃልል አልቀረሁም፡፡ በራሴ ጉዳይ አክራሪ ብሆን አውደልዳዮች ምን አገባቸው? ትንሽ ግን አለበት፡፡ ከመያዙ ማለቴ ነው፡፡ ማፍቀሩ ግን ዋናው ነው፡፡ መናዘዜ አይደለም፡፡
ሰሙኝ የኔ እንኮዬ?
***
የስንብት ቀለማት
One Comment
ጥበብን ለተጠማች ነፍስ እውነተኛ የርካታ ምንጭ ናችሁ። ምስጋናዬ እጅጉን የበዛ ነው።