Tidarfelagi.com

ኦባማ ኢትዮጲያ ሲመጡ የእራት ላይ ወጋቸው ምናባዊ ቅኝት

ኦባማ ኢትዮጲያ ሲመጡ . . . 40 ታዋቂ ሰዎችን ያናግራሉ
(የእራት ላይ ወጋቸው ምናባዊ ቅኝት…እነሆ )

‹‹እኛ ባቀናነው በሰራነው መንገድ
የማንም ቀዠላ ተወላገደበት››
ቻይና …ትላለች ብለን ያሰብነው፡)
አለም እንደሸንኮራ ተሰንጥቆ ወላ በካርቱን ወላ በአሽሙር የኦባማን ጉብኝት መተቸቱን ተያይዞታል ! ግማሹ ‹‹እሰይ እነዚህን ሚስኪን ህዝቦች ደግ ጎበኟቸው … ቢያንስ ህዝቡ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት አዲስ የመሪ ፊት ይመልከት ›› ብለው ሲያሾፉ …ሌላኛው ቡድን ‹‹ይሄ ሰውየ ምድረ አምባገነንን እየጎበኙ አበጀህ ይበሉና ህዝቡን ያስጨርሱት ››ሲል በቁጣ እና በቁጭት እየቆዘመ ነው ዝም ያሉም አሉ… በተለይ እነቻይና … ምናልባትም በሆዳቸው … ‹‹እኛ ባቀናነው መንገድ የማንም ጥቁር ቀዠላ ተወላገደበት ›› እያሉም ሊሆን ይችላል ….
‪በነገራችን‬ ላይ …. ኦባማ አዲስ አበባችን ላይ ጎራ ሲሉ የሚያናግሯቸው ተብለው የተለዩ ‹ታዋቂ› 40 ኢትዮጲያዊያን ግለሰቦች ተመርጠዋል ማን እና እንዴት መረጣቸው ? የሚለውን ባናውቅም ምርጫው 100 ፐርሰንት ፍትሃዊ እንደሚሆን ግን እናምናለን ! እንግዲህ የተመረጡት ብርቅየ ዘራቸው በኢትዮጲያ ብቻ የሚገኝ ታዋቂዎቻችንን ኦባማ ጋር ተሰብስበው ምን ሊባባሉ እንደሚችሉ በምናብ እንቃኛዋ ሃሃሃ . . . በሉ ይህን ለማንበብ እራሳችሁን እየፈተሸችሁ ወደዚህ ፔጅ ግቡ !(ለደህንነት ሲባል፡))
‹‹ ዌል እንግዲክ ›› ታላቁ አትሌታችን ሃይሌ ገብረስላሴ ከፊት ወንበር አካባቢ መቀመጡ ሳይታለም የተፈታ ነው …እንደውም ኦባማ ማስታወሻ ደብተራቸውን መዝረጥ አድርገው ‹‹ፈርምልኝ ›› ባይሉት ነው ….ከምር ሃይሌኮ ከኦባማ በላይ ሽር ጉድ ሊባልለት የሚገባ ምርጣችን ነው ….እግሩ ይባረክ!! …….እና ኦባማን ፈገግ ብሎ ምን ይላቸዋል ‹‹ ዌል እንግዲክ ማንም ሰው ከሰራ ያልፍለታል …ለምሳሌ እኔን ቢመለከቱ ድህነትን በሩጫ ነው ያመለጥኩት ›› አቶ ውብሸት በባለወርቃማ ጥለት ካባቸው …ሽክ ብለው … ሃይሌን በመደገፍ ከፍ ባለ ስሜት ይናገራሉ (በነገራችን ላይ በር ላይ ሲገቡ ካባቸውን አስወልቀው አራግፈው ስለፈተሹት ትንሽ ቅር ብላቸው ነበር …ገና አሁን ነው ፈገግ ያሉት) እና ምን አሉ …
‹‹ልክ ነው …ሃይሌ አንበሳ ነው …ነብር ነው ሚዳቆ ነው …ግስላ ነው …ኒያላ ነው …ሮዝማን …..እንደርሰዎ ደከመኝ ሰለቸኝ የማይል የጥቁር ትንታግ ነው …. ብርቅ ሃብታችን ነው ! ድህነትን ብቻ ሳይሆን ምቀኝነታችንን ክፋታችንን …ሁሉ ነው በሩጫ ያመለጠው … ምን ይሄ ብቻ በወጣትነቱ እመብርሃንን የመሰለች …መልአክ የመሰለች …ሚሸል ኦባማንም የመሰለች ሚስት አግብቶ በቆንጆ ሴቶች መፈተንንም በሩጫ ነው ያመለጠው ….የዚህ አገር ቆንጆዎች እንዴት ‹እሸት› መሰሎዎት …በቴሌቪዥን ባይታዩ እንጅ እንደርሰዎ ልጅ አምሳ በሬ ጥሎሽ ሆጭ በተደረገላቸው ነበር ….. እንኳን ሰው ክንፉን ረስቶ የመጣ መለዓክ ያስታሉ ….›› በማለት ካባቸውን ወደትካሻቸው ሳብ አድርገው አስተካከሉና አፋቸውን ጠርገው ቀጠሉ ….‹‹ እኔ የምልዎት ሚስተር ፕሬዝደንት ለምን ሃይሌ ጀርመን ላይ ለብሶ የሮጠበትን የግራ እግር ጫማ ገዝተው አይሄዱም ትልቅ ታሪክ ነው ለመላው ጥቁር ህዝብም ኩራት ነው ….፣ ››
ሚስተር ኦባማ ፈገግ ብለው …
‹‹አለባበሰዎት ያምራል ….ለመሆኑ ሙያዎት ምንድነው ›› ይሏቸው የሏቸዋል
‹‹የ መ ጀ መ ሪ ያ ውን ዘመናዊ የማስታወቂያ ድርጅት በመመስረት ስለማስታወቂያ ጥበብ ለኢትዮጲያ ያስተዋወኩ ሰው ነኝ …ገበያ ላይ ቢላዋ እየፋጨሁ ስጋ በማስተዋወቅ ነው የጀመርኩት …›› ካባቸውን ከፍ ወደትከሻቸው
‹‹ሃሃሃሃሃ …ዌል እንዳሉት ጫማውን እገዛለሁ ›› የተሰበሰበው ሰው ጭብጨባ! …በቀጣዩ ሳምንት …‹‹ኦባማን ያስጨበጨበ የማስታወቂያ አሰራር ብቃት ›› በሚል ርእስ ‹ዘራፍ › መፅሄት የቅዳሜ ህትመት ላይ ጋሽ ውብሸት ከነወርቀዘቦ ካባቸው ገጭ !! እኛም የፈረደበት ብሔራዊ በቡና ጨጓራችንን እየላጥን ንብብ !! ከምናውቃትና ከማናውቃት ሃሜት ጋር !!
ድንገት የአንድ ሰው ድምፅ ይሰማል ‹‹ክቡር ፕሬዝደንት የሰዎችን ሃሳብ እንደፓርቲ እናከብራለን …አሁን ሃይሌ ያለውንም ሆነ አቶ ውብሸት የተናገሩትን በመርህ ደረጃ ተቀብለነዋል ግን …በየትኛው ሜዳ ነው የሚሮጠው ነው ጥያቂያችን …. የመሮጫ ሜዳውን ኢሃዴግ አጥብቦብናል …ጥቂት የገዥው ፓርቲ ደጋፊዎችና ለሱ ያደሩ ግለሰቦች ካልሆኑ እዚች አገር ላይ እንኳን መሮጥ መቧደድ ችግር ነው…ድህነትን በሩጫ ማምለጥ ይቻል ይሆናል …ይሁንና ህዝቡ ከጧት እስከማታ ቢሮጥም ድህነትን ማምለጥ አልቻለም … ድህነትእና ሃይሌ ፍጥነታቸው አይቀመስም….በነገራችን ላይ ህዝቡ ነፃ መድረክ ተመቻችቶለት እንዲሮጥ ቢፈቀድለት ከድህነት በፊት የሚያመልጠው ከኢሃዴግ ነው …. አሁንም በየሽንቁሩ እየሮጠ አገርዎትን ያጣበበውን ስደተኛ ያውቁታል ብየ እገምታለሁ ….›› ጭጭ ሁሉም !ኦባም ጭጭ ! ቄሱም ጭጭ መፅሃፉም ጭጭ ! የሰማያዊ ፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ነበሩ ተናጋሪው!
ፕሮፌስ በየነ ጴጥሮስ ጉሮራቸውን አፀዳዱና … ‹‹መሮጡን …እያነከስንም እየቧደድንም እየሮጥን ነው …ግን ከመሮጫ ሜዳው አለመመቻቸት ጎን ለጎን ….እ…..የሩጫ ትጥቅ ችግር አለ …በቂ የመሮጫ ጫማ …በቂ ማሊያና ቲሸርት …እንዲሁም …ደከም ሲለን የምንጎነጨው ውሃ ችግር አለ ….እንደሚያውቁት ሰውነታችን በቂ ሃይድሬሽን ከሌለው እኛም ደርቀን አገር ማድረቅ ይሆናል እጣ ፋንታችን …እና ህግ ጠብቆ ያለመሮጥ ችግርም በገዥው ፓርቲ ሰዎችና በአንዳንድ ተቃዋሚዎችም ዘንድ ይታያል ….ለምሳሌ ፊሽካ ሳይነፋ መሮጥ … ›› እያሉ ዘለግ ያለ ንግግር ማድረግ ! በሳምንቱ ይህን ንግግራቸውን የሰማ የግንቦት ሰባት ቃል አቀባይ በኢሳት ….ፕሮፌሰሩ ትጥቅም ሆነ ፊሽካ ከፈለጉ እኛ ጋር ይቀላቀሉ …ይሄው ፊሽካውን ነፋን ትጥቁንም ይዘን ትግል ጀመርን ካልንኮ ወራቶች ተቆጠሩ (ሊል ይችላል ሂሂ)
የፊልም ባለሙያው ቴውድሮስ ተሾመም ዝርዝሩ ውስጥ አለ …ስብሰባው ላይ ብዙም ባይናገርም ኦባማ እንደተመለሱ ‹‹ከሆሊውድ በመጡ ባለሙያዎች የተቀረፀ ›› ፊልም በሴፓስቶፖል ሲኒማና በሁሉም የመንግስትና የግል ሲኒማቤቶች ለማሳየት ደፋ ቀና ሲል ሊታይ ይችላል … ! ‹‹ጥቁሩ ወላፈን ›› ወይም ‹‹ ጋሽ ለማ ….ወይስ ኦባማ›› የሚል ርእስ ሊኖረው ይችላል ፊልሙ …በኢትዮጲካሊንክና በሰይፉ ፋንታሁን ፕሮግራም ላይ ‹‹ አምስት ሚሊየን ብር የወጣበት በአይነቱ ልዩ ፊልም›› ከሚል ማስታወቂያ ጋር ! (ሞት ይርሳኝ ታዋቂ ሰዎቹ ዝርዝር ውስጥ እንዴት ሰይፉ ፋንታሁን አልተካተተም …የምርጫው ፍትሃዊነት 99 ፐርሰንት ሲሆን ተመልከቱ)
እንግዲህ ኦባማ ተናጋሪዎቹን በጥሞና ካደመጡ በኋላ አጭር ንግግር ያደርጋሉ …‹‹ እንግዲህ ኪነጥበብ ታላቅ መሳሪያ ነው …አሜሪካ በፊልም ኢንዳስትሪወቿ የምትሰራውን ስራ በጦር ሰራዊቷ ከምትሰራው በላይ መሆኑን ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ …እናተም ለአገራችሁ ብሎም ለቀጠናው ሰላም ፍቅርን አብሮነትን በተለይ አርቲስቶች መስበክ አለባችሁ …ኢትዮጲያ የሽብር ስጋት ያለባት አገር ናት …በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ አሸባሪዎች ኢትዮጲያን በክፉ አይን ነው የሚመለከቷት ይሄን ለእናተ መንገር …ለቀባሪው ….ምን አደረገ …እንደምትሉት ነው ›› ይላሉ ፈገግ ብለው ተረታችን ጠፍቶባቸው …
አቶ ውብሸት ከኦባማ አፍ ለቀም አድርገው ተረቱን ከማስታወቂያ ጋር ያሟሉታል …‹‹ለቀባሪው አረዳው…. ልክነወት ሚስተር ፕሬዝደንት …በነገርዎት ላይ ‹የአማርኛ ምሳሊያዊ አነጋገሮች በእንግሊዝኛ በሚል ርእስ በቅርቡ የማሳትመው መፅሃፍ አለ ይተቅመዎታል ቢገዙት›› በሳቅ!
‹‹ …እና በዚህ አልሸባብ …በዚህ ከኤርትራ የሚነሱ የኢትዮጲያ መንግስት አሻሪ ብሎ የሰየማቸው ቡድኖች በዛ ….መፅሔት ጋዜጣ እንዲሁም የፍቅር ደብዳቤ ሳይቀር የሚፅፉ ፀሃፍት …መንግስታችሁ አሸባሪ ብሎ የፈረጃቸው ማለቴ ነው(በፈገግታ) ይሄ ሁሉ አሸባሪ የከበባት አገር በመሆኗ ፖለቲከኛው ነጋዴው የኪነጥበብ ባለሙያው በየፊናው አገሩን የመጠበቅ ግዴታ አለበት አመሰግናሉ›› አሉ ኦባማ …ሞቅ ያለ ጭብጨባ …. በመሃል ጋሽ አበራ ሞላ ከነክራሩ ብዲግ ብሎ (ክራሩ ፍተሸ ላይ አንድ ክሯ ቢበጠስም…ፕሬዝዳንቱ ጊዜ የላቸውም አራት ክር ይበቀሃል ብሎታል ይባላል ፈታሹ ሃሃ ) እንዲህ ሲል ዘፈነ …
ከለታት አንድ ቀን …አንድ ሰው ከቤቱ አረፍ ብሎ ሳለ ….
ጎረቤት መጣና ‹‹ዘጠኝ ሞት መጥቶ ደጅህ ቁሟል ቢለው››
ዘጠኝ ሞት መጥቶ ደጀ ምን አቆመው ስምንቱን ተውና
አንዱን ግባ በለው !
በቀጣዩ ሳምንት ከኳስ ተንታኝነት በሰሞኑ የኦባማ ጉብኝት ሞቅታ የፖለቲካ ተንታኝ የሆነው ‹‹የተመራጩ የተደማጩ …ቢራ በጥባጩ …ከተማም በጥባጩ ሬዲዮ ጣቢያ ባለቤት… ጋዜጠኛ … እንግዳ ….ቴክኒሻን …ስፖርተኛ ….የማስታወቂያ ባለሙየና ስራ አስኪያጅ ›› የሆነው ታዋቂ ሰው እንዲህ የሚል ትንታኔ ይሰጣል ‹‹ጋሽ አበራ ሞላ ኦባማ ፊት… ‹‹ስምንቱን ተውና አንዱን ግባ በለው›› ሲል ጂ ኤይት ….ስምንቱ ሃያላን አገራት … አገራት ቢደመሩ እርሰዎን አያክሉም ማለቱ ነው ?…ኦ ያያያ አዎ ነው አለኝ ረዳቴ …አዎ ነው አለኝ…!! አድማጮቸችን …ይሄን ፕሮግራም ስፖንሰር የሆነን የኦባማን መምጣት አስመልክቶ ቢራወቹ ላይ ታላቅ ቅናሽ ያደረገው ጉስሜ ቢራ ነው …..
እንግዳ ሲመጣ ሞቅ ሲለው ደሜ
እቀዘቅዛለሁ ፉት እያልኩ ጉስሜ ….ይላችኋል !!›› ሃሃሃ..እኛም ሳንወድ በግድ ስምት !!
እንግዲህ ለራት ኦባማ ጋር ከታደሙት እንግዶች … መሃል የመጨረሻው ተናጋሪ ሰርፀፍሬ ስብሃት ነበር ….
‹‹ክቡር ፕሬዝዳንት በዚህ ሁኔታ ህዝብና መንግስት አክብረው መገኘትዎት አስደስቶኛል ደስታየን …በቃላት …በኢትዮጲያ አራቱ ቅኝቶች በዜማ …ብቻ በምንም መግለፅ አልችልም ….በነገራችን ላይ(በፈገግታ) ድምፅዎትን ዝም ብየ ስሰማ ነበር …ይሄ ከሆድዎት የሚያወጡት ድምፅ በጣም ነው ኢምፕረስድ…የሚያደርገኝ …. በንግግር ወቅት ድምፅዎት ከፍና ዝቅ ማለት እንዲሁም ቅላፄው ከእጅዎትና ሰውነተዎ እንቅስቃሴ ጋር ተዳምሮ በእኛ አገር ሽለላና ቀረርቶ የምንላቸው ድምፅቶች ጋር ይመሳሰልብኛል …ይህ ድምፅዎ ለሶስተኛ ጊዜ ቢወዳደሩበትም ለፕሬዝደንትነት የሚያስመርጥዎት ይመስላኛል … በቴሌቪዥን ስመለከትዎትም …በቃ ድምፅዎት አሜሪካ ኢራቅና አፍጋኒስታን ላይ በምታፈነዳቸው ቦምብ ታጅቦ የህፃናትና እናቶች ለቅሶ ጋር ተዳምሮ ሳደምጠው የእኛን አገር ሙሾ ይመስለኛል ! ›› ብሎ ቁጭ …እንግዶች ጭብጨባ …..
ምናባችን ቴዲ አፍሮ ላይ ያቆማል (ከተጋበዙት አንዱ ነውና) ….ያው ቴዲ ከበድ ያለ ጉዳይ ስለገጠመው በእራት ፕሮግራሙ ላይ አልተገኘም ….(አንዳንድ ሰዎች ግርግሩ ደብሮት ነው ….. ሌሎች አሁንስ አበዛው ቁምጣ ለብሰውም ሱፍ ለብሰውም ሲጠሩት የማይገኘው እሱ ማን ስለሆነ ነው …ብለው እንደማኩረፍ ) ቢሆንም ከስድስት ወራት በኋላ ቴዲ አንድ ሲንግል ለቆ አቧራውን ያጨሰዋል …እንዲህ የሚል ግጥም ይኖረዋል
‹‹ ቅድስት ….እ….ማ……ማ …
የገነት ብርሃን የጊዮን ማማ
ወደሩቅ ምስራቅ ስንደናበር
ወደምእራብ ፈጥነን ስንዞር
ቅዱስ አንገትሽ እንዳይሰበር
ቀስ ….ቀስ….. ሄይይይይ …..
ኤይይይይይ ፡)
አብርሃም ወልዴ (ባላገሩ) ጥጉን ይዞ በውስጡ ተናጋሪዎቹን በንግግራቸው ይመዝናል …አንዳንዶቹን ‹‹አላለፉም ›› እያለ፡)
ይህን ሁሉ የዘገበችልን ራት ፕሮግራሙ ላይ በክብር የተሰየመችው ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ብትሆንስ ?፤)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...