Tidarfelagi.com

ስለ ተድላ

የጥንቲቱ ፋርስ ካፈራቻቸው ባለቅኔዎች መካከል ኣንዱ ኦመር ካያም ነው፡፡ ፈላስፋ ሳይንቲስት እና የተዋጣለት የሂሳብ ሊቅ ነው፡፡ሩባኣያት የሚል የግጥም ዘይቤ ፈልስፏል፡፡ሩባያት ኣራት መሥመር ያለው ሲሆን ከሦስተኛው መሥመር በቀር ሌሎች ቤት ይመታሉ ፡፡

ኦመር ካያም መናፍቅ ነበር፡፡ ትንሳኤ ሙታን መኖሩን ይጠራጠራል፡፡ህይወት ከስንዝሮ የምታጥር ድንክ እንደሆነች ያምናል፡፡እንደሱ ኣስተሳሰብ ለህይወት ኣጭርነት መፍትሄው ቶሎ ቶሎ ማፍቀርና ቶሎ ቶሎ መደሰት ነው፡፡የሚከተሉት ሦስት ሩባያቶች የፍልስፍናውን ናሙና የሚያሳዩ ይመስለኛል፡፡
1
ጎህ እንደቀደደ፤ በሚጣፍጥ ዜማ
መላክ ከሰማይ ላይ፤ እንዲህ ሲል ተሰማ
ቶሎ ቶሎ ውደድ
የድሜህ ጀንበር ሳይጠልቅ፤ ሳይውጥህ ጨለማ
2
በህይወት መስከር ነው፤በፍቅር መመርቀን
የፊት የፊቱን ኑር፤ ምንድነው ሰቀቀን
ህያው ፍጥረት ሁሉ
ያከትማል ኣንድ ቀን
3
ነገን ከነጭንቁ፤ ኣሽቀንጥረህ ጣለው
ይልቅ ዛሬ ቀምቅም፤ ጥዋህን ኣጉድለው
ብትጃጅ ወይ ብትቀጭ
ተፈጥሮ ግድ የለው!
(ትርጉሞች የኔ ናቸው)

ከላይ ከላይ ስታየው የኦመር ካያምን ስብከት ያክል የሚመች ፍልስፍና የለም ፡፡ይሁን እንጂ ፤ የሰው ተፈጥሮ ስሩ ሲማስ ዱሩ ሲጣስ ከዚያ በላይ የተወሳሰበ ነው፡፡ ከቀመቀመህ በኋላ በቅርብ ራስምታት በርቀት ሀንጎቨር ይጠብቅሃል ፡፡

ርቦሽ በልተሽ ከጠገብሽ በኋላ በረጂሙ ታፏሽኪያለሽ፡፡ ላጉርስሽ የሚልሽን ሰው ካልደበደብኩሽ እያለ እንደሚጋበዝ ደመኛሽ ጠምደሽ ትይዥዋለሽ፡፡ ምግብ ያለበት ኣካባቢ መቆየትን እንደ ከባድ ሸክም ትቆጥሪዋለሽ፡፡

ወሲብም እንደዚያው ነው፡፡

እዚህ ሃያሁለት ማዞርያ ሰፈሬ ውስጥ ከሚገኙት ስፍር ቁጥር ከሌላቸው ምኝታ ቤቶች ካንዱ ፊትለፊት የወንዶች የውበት ሳሎን ይገኛል፡፡እዚያ ገብቼ፤ ጢሜን ለመቆረጥ ወረፋ እየጠበቅሁ ወደ ምኝታ ቤቱ የግቢ በር ኣይኔን ኣነጣጥራለሁ፡፡በቀደም ለታ፤ ጥንዶች ወገብ ለወገብ ተቃቅፈው እንደ ብርሃንና እንደ ነበልባል ተዋህደው ወደ ግቢው ዘለቁ፡፡ነገሩን ኣጠናቀው ሲወጡ መተቃቀፉ በቦታው የለም፡፡እሱ እጁን ኣርቆ ኪሱ ውስጥ ደብቆታል፡፡ እሷ እጆቿን ደረቷ ላይ ኣመሳቅላዋለች፡፡ እሱ ለማምለጥ የተዘጋጀ ይመስል ከፊትለፊት ሲጣደፍ እሷ ለማፈግፈግ የተሰናዳች ይመስል ከኋላ ትከተላለች፡፡ወንዱ የልጂቷን ፊት እንኳ የሚያይበት ወኔ ኣልነበረውም ፡፡ ሳየው”ያ ሁሉ ውጣ ውረድ ለዚች ብቻ ነው?“የሚል ግለ-ሂስ ፊቱ ላይ ተጽፏል፡፡ የሷ ፊት ላይም የመሰላቸትና የጸጸት ስሜት ተደባልቆ እንደፓውደር ተለጥፏል፡፡

ምናልባት በዚያን ቀን የተደሰተ ሰው ካለ የምኝታ ቤቱ ኣከራይ መሆን ኣለበት፡፡
በፋርሱ ገጣሚ ስንኞች ውስጥ ያለው የህይወት ርካታ ምድር ላይ ኣለ?ላገኘልኝ ወረታውን እከፍላለሁ፡፡

ከኦመር ካያም በተሻለ ጥልቀት፤ የተፈጥሯችንን ባህርይ የተረዳው ጥንታዊ የኢትዮጵያዊ ባለቅኔ እንዲህ ሲል ተፈላስፏል፡፡
ከማሃ ተድላ ኣለሙ
ዘኢረከባ ይተክዝ ፤ ወዘረከባ ይጻሙ
(እንዲሁ ተደላ የሚሉት ፤የሚገኘው ባለሙ
ባጡት ጊዜ ሲያስተክዝ፤ ሲጨብጡት ማድከሙ፡፡)የሚል ነው ነጻ ትርጉሙ፡፡

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

One Comment

  • Anonymous commented on April 3, 2019 Reply

    በውቄ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...