Tidarfelagi.com

የእንባ አውራ ጎዳኖች

ይሄውልሽ እምዬ፡-
በሆዴ የያዝኩት የብሶቴ ክምር
ብዙ ሲናገሩት-አብዙት ሲፅፉት፣ መስሎሽ ባዶ `ሚቀር-
እንዳትታለዪ
ይብሱን ነው `ሚያድግ፣ እጅጉን ነው `ሚንር
ይቀለኛል ብዬ በነገርኩሽ ቁጥር፡፡
ከወደቁ ኋላ መፈረጋገጡ፣ ውጤቱ መላላጥ እንደሆን አውቃለሁ
ግን ከዝም በላይ አይጎዳኝምና ስሚኝ ነግርሻለሁ!

እዚህ ካንቺ ግቢ፣ እዚሁ ካንቺ ማጀት
ሙሉ ቀን ጨለማ ልማድ ከሆነበት
ሰርክ የሚሰራውን የቤትሽን ውሎ
ስሚኝ ነግርሻለሁ፣ ብዕሬ አልችል ብሎ፡፡

አድምጭኝ ልንገርሽ….
አባወራ አድርጎ እራን የሾመው ከእልፍኝሽ ቅጥር
የገዛ ወንድሙን ያንችን ልጆች ደም ነው ዛሬም የሚገብር፡፡
ጀግና መግደላቸው ጀግና ያስባላቸው
የህግ ያለህ ብንል መግደል ነው ዳኛቸው፡፡
የህጋችን ህጉ መጣሱን በማየት ለአምላክ ብናሰማ
አንሳልን ብንለው አንችለውን ፃማ
ይሄዋ ምላሹ እስካሁን አልመጣም
የጥበቃ ትርፉ፣ ተስፋ መቁረጥ እንጂ እምነት አላመጣም፡፡

አድምጪኝ ከሰማሽ፣ እይን ከተያየን፤
ይሄ ያንቺ ኑሮ አምሳለ ሲሲፈስ
የገፉትን ድንጋይ እየገፉ መኖር ዳግም መሬት ሲደርስ!
ትህትና ባጡ፣ እንደጫካ አውሬ ማዘን በማያውቁ
የገዛ ልጆችሽ በልጅሽ አለቁ፡፡
ጊዜ ያደለው ሁሉ ፋንታዬን እያለ ፋንታውን ሲያነሳ
ለጥረት አይደለም፣ አደጉ ላልሻቸው ሃብታም ሀገሮች ነው እጅሽ የተነሳ!
አንም አሸናፊ በሌለበት ሜዳ፣ ተሸናፊ ሆኖ ልጅሽ የሚጠፋ
አሸነፍኩ የሚለው ተሸናፊነቱን ባለማወቁ ነው- የነገሽ ክፋቱ ከዛሬ `ሚከፋ፡፡
“የተማረ ይግደለኝ” የሚለው ያንቺ ቃል፤ የተማረ ይገደል በሚል ተቀይሮ
ለወንበሩ ጤና ፣እልፍ ምሁር ያልቃል ጉድጓድ ተጨምሮ፡፡
ስንት ተስፋዎችሽ፣ ተስፋ ባጡ ጊዜ ቢልልን እያሉ
በበረሃ መሃል በሞት ይቆላሉ
ላላቀች ተስፋቸው፣ ከማያውቁት ሀገር ተስፋን እየጣሉ
ከጣሉት ሳይደርሱ ቀድመው ይወድቃሉ፡፡
ታያለሽ እናቴ?!…
ዋስ ይሆነን ተፍቶ ለነገ ኑሯችን
“እያወቁ ማለቅ” ሆኗል ተረታችን
ቢያወሩት የማያልቅ ሆኖ መከራችን
ዝም፣ ዝም ብቻ ሆኗል ፈሊጣችን፣
የውስጥ ውስጥ ለቅሶ ብሶት ማቅለያችን!!

ዝም አይነቅዝም ብለን አጉል ተሰቅዘን
ኑሮ አይሉትን ኑሮ፣ አለን ኑሮ ብለን
አለን!….. አለን ብለን!


 

************************************************

የእንባ አውራ ጎዳኖች- ሁለት

ሰቆቃ ሀገር አንቲ፤
ካንቺ ተቀምጬ ተሸሽጌ ከጥግ
ስንት አየሁ መሰለሽ ወኔ የሚያጠወልግ-
ፍርሀት የሚያሳድግ
ነብስና ህሊናን ደርሶ `ሚያጨፈግግ፡፡
ጨለማሽ አይደክመም ፀሀይሽ አይበረታ
ያንቺ ፅልመት ብቻ ምነው አይረታ?
ተመልከቺ ይሄው፤
ነጋ ጠባ ለቅሶ ሆኗል ሙዚቃችን
እልልታ ጨርሷል ሀዘን ነው ልባችን
……………………….መቃተት አጥራችን
………………………ዋይታ ነው ቤታችን!

እነሱ እንዳረጉት “ታላላቆቻችን”
እውነትን ረግጠን ሀሰን ቀለማምደን እንኑር ብንል እንኳ
ሀገር ምድር የሞላው ያዘነብሽው እንባ፣ መች ያሻግረናል ካላበጀን ታንኳ
ይታይሽ እንግዲህ፣
ዳቦ ስንለምን ጥይት ከዘነበ
አንደበት ምንድን ነው፣ ከርሃባችን በላይ ሲገድል የተራበ?
እይን ከተያየን፤
ወርቅ ቀርቁ ተዘርፎ ወጥቶ ከሃገራችን
የአማድ አፋሽነት ግብር እና ኑሯችን፡፡
ፈረንጆች በወንጌል አፍሪካን አሞኙ፤
እኚህ ዶሞክራሲን ሲዘፍኑብን ዋሉ
ሸንጦን ብንጨፍር ተኩሰው ሊጥሉ፡፡
እስቲ ልጠይቅሽ፤
በምን ነው የሚለይ፣ ጠላት ወዳጃችን
አፈወርቁ በዝቶ በዙሪያ ገባችን፡፡
ተስፋዬ የምትይው፣ ጀርባውን ከሰጠ ዓይንሽን እንዳያይ
ዕጣን ከምን ለምን ላይ ነው፣ ማነው ያንች ገላጋይ?

የየዕለት ጩኸትሽ በአምላክ መች ተሰማ
ዜናው ሰላም ነው ነው፣ ነብስሽ ያለአቅቦ በልጅሽ ሲደማ፡፡
ዛቻ ፉከራችን ሽለላችን ሁሉ፣
የናቁ የደፈሩሽ ከእግርሽ ጫማ በሃፍረት ይወድቃሉ
ለምን ነው የሆነው?

መዋቲ ልጆችሽ፡-
አስታጥቄ አላቸው መግደል ከፈለጉ
በደማችን ግብር፣ ለውሻነታቸው ቅንጥብጣቢ ስጋ ካለው ሊያሳጉ
አንቺ ሀገር ብዙ አየሁ፣ ካንቺው ተቀምጬ ካንቺው ተጠግጌ
አምባ ገነኖችሽ መድፍ ሲተኩሱ ግጥም ተሸሽጌ፡፡

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...