Tidarfelagi.com

አድዋ ለኤርትራውያን ምናቸው ነው?

አድዋ ለኤርትራውያን በደል ነው። ከቀሪው ኢትዮጵያ መቀያየሚያቸው ነው። የሀዘን ትዝታቸው ነው። ብዙዎቻችን ግን ይህን አምኖ ከመቀበል ይልቅ የምክንያት ጋጋታዎች ስናበጅ እንታያለን። ታሪክን በአርትኦት ልናርም? በምክንያት ልናቀና?…. ይቻለናልስ?
እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የአድዋ ድል የሚያስደስተኝ፣ መንፈሴን የሚያግለኝ ቢሆንም፣ እንደ ግለሰብ የምኒሊክ የአመራር ጥበብ አድናቂ ቢሆንም የወቅቱን እና የምኒሊክን ስህተት እያዩ ለማካድ አልደፍርም። ያልሰሩትን እያነሱ ከመንቀፍ፣ ከሰሩት አጉል ከፍታ ሰጥቶ ርቀን በታሪክ እውነታዎች ላይ መተማመን እና የጋራ መግባባት መፍተር ብንችል ህልሜ ነው!! ይህን በማሰብ እንዳልሰሯቸው ተትተው ጥግ የያዙ በምክንያት ሊሸፋፈኑ የሚሞከሩ ድርጊቶችን ማየት ወደድኩ።

ጣሊያን ከአድዋ ጦርነትም በፊት ለስድስት ዓመታት በመረብ ምላሽ አካባቢ (በኤርትራ) ቆይታለች። ስድስት ዓመት! ከአድዋ ጦርነትም በኋላ ዳግም ተላልፈው የተሰጡበት ነው።ቀድሞም ቢሆን የአድዋ ጦርነት ስለኤርትራውያን አልነበረም። ከጦርነቱ በፊት የውጫሌው ስምምነት አንቀፅ ሶስት የአካባቢውን በኢጣሊያ ስር መሆን የሚፈቅድ ነበር።
አድዋ ለአፍሪካዊያን ሁሉ የነፃነት ምሳሌ ሲሆን፣ ለኤርትራውያን የቅኝ ግዛትነት እጣ ነበር። ከዓመታት ለኢትዮጵያንዝም እና ለፓን አፍሪካኒስም መሰረት ሲሆን፣ ለኤርትራውያን የቁዘማ መሰረት ነበር።

እውን ጣሊያንን ከኢጣልያ ጠራርጎ ማስወጣት አይቻልም ነበር ወይ ነው ጥያቄው። ይቻል ነበር የሚለው መልስ ይሆናል። ከጥቂት ኤርትራውያን ሙስሊሞች በቀር፣ የኢጣልያንን ከአካባቢው መውጣት ሚፈልጉ ኤርትራውያን ብዙ ነበሩ። ከአድዋ ጦርነት ሲሸሹ፣ በየሜዳው በኤርትራውያን ገበሬዎች ጣሊያናውያን የዚህ ማሳያ ናቸው። ብላታ ሀጎስም አይረሳም። ከአድዋ በኋላ የነበው የብላታ ገብረእግዚሐብሔር ለሚኒሊክ የተፃፋ “የአሳልፈህ ሰጠኸን” ወቀሳ ወዴት ይገፋል?

አሉላ ጣሊያኖችን ከመረብ ምላሽ ወዲያ ለማባረር የኦሮሞ ፈረሰኞችን እንዲፈቅዱለት ምኒሊክን ሲጠይቅ ለምን ሳይፈቅዱለት ቀሩ? ከጣሊያን ጋር የነበረ የቀደመ ስምምነታቸውን ለመጠበቅ?? ፀባቸው ከአንቀፅ 17 እንጂ፣ ከውጫሌ ስምምነት አልነበረም?…

በምኒሊክ እምቢታ የተበሳጨው አሉላ፣ ጦርነቱ ባበቃ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ወደ ኢጥዮጵዯ መጥቶ ከነበረው ዋይልድ ጋር ቃለምልልስ አድርጎ ነበር። ስለጉዳዩ የአሉላ ቃል ዋይልድ እንዲህ አስፍሮታል፤
“ I asked the king to give me his cavalry, and if he had I would have driven the Italians into the see”

የአድዋ ጥቁር መልክ ሆኖ የሚቀረው ይህ ብቻ አይደለም። በባንዳ ኤርትራውያን ላይ የተወሰደውም እርምጃ ጭምር እንጂ!

“… እጅ እና እግር ቆረጣው!”

በአድዋ የኢጣሊያንውያን ወታደሮች ከ17ሺ በላይ ሲሆኑ(ኮንቲ ሮሲኒ 20,170 ነው ይላል) ሲሆን፣ ለኢጣልያ የተሰለፉት ኤርትራውያን ከ 6000 እስከ 6700 ነበሩ። የኤርትራውያኑን ወታደሮች ቁጥር 7200 መሆኑን እና 1600 ያህሉም ተጠባባቂ ወታደሮች እንደነበሩ የሚገልፁ ምንጮች አሉ። ከነዚህ ወታደሮች ውስጥ ከሞቱት ውጪ፣ 4000 ያህል ያህል ወታደሮች ተማርከው ነበር። ከተማራኪዎቹም 1500ዎቹ ኤርትራውያን ወታደሮች ነበሩ። ቁጥራቸውን አንድ ሺ የሚያደርሱትም አሉ(የቁጥር ጉዳይ በየቦታው አጨቃጫቂ ነው)

የካቲት 25/1888 እነ ራስ ወሌ፣ ራስ አሉላ፣ ራስ መንገሻ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ አባ ማትዮስ በተገኙበት አፄ ሚኒልክ በኤርትራውያኑ ላይ ፍርድ ለመስጠት ተቀመጡ። በፍርዱ የኤርትራውያኑ ቀኝ እጅ እና ጋራ እግር እንዲቆረጥ ተወሰነ። ከአንድ ሺ በላይ በሚሆኑት ኤርትራውያን ላይ ፍርዱ ተፈፃሚ ሆነ። እጅ እና እግራቸው ተመለመለ። በእርግጥ ዋይልድ ቅጣቱ የተፈፀመባቸው 800 ናቸው ይላል። ይህ ፍርድ በብዙ ኤርትራውዯን ዘንድ ዘላቂ መራራ ቅያሜን አሳደረ። ምን አልባትም ኢትዮጵያ ከኤርትራ ልብ ጋር ተቆራርጣ የቀረችበት አንዱ ክስተት እነዚህ ወታደሮች እጅ እና እግር መቆረጥ ነው! ማለት የሚቻል ይመስለኛል።

ወደ 3000 በሚጠጉት ጣልዯናውያን ወታደሮች ላይ የተወሰደው እርምጃ ግን ከዚህ የተለየ ነበር። ሁሉም ነፃ ተለቀቁ!! ቢያንስ ኤርትራን ለማስለቀቅ መደራደሪያ መሆን አይችሉም ነበር?? ግን በነፃነት ተሰናበቱ።
ጥያቄ አለኝ…. ከሩቅ ሀገር አገራችንን ለመውረር ከመጡት ባዕዳን፣ ከእድዋም ቀድሞ በቅኝ ግዛት ስር የተጣሉት ኤርትራውዯን ድርጊት የከፋ ነበር? ምን የከፋ ቢሆን እንኳ ኤርትራውያኑን በነፃ ከማሰናበት እንዲህ የራቀ ፍርድ ሊፈፀምባቸው ይገባል? አፄ ምኒሊክ ይህን ማየት ተሳናቸው??
የኤርትራ ችግር እዚህ ምዕራፍ ላይ ብቻ የሚጠናቀቅ አይደለም። ኢጣላናውያን ከአርባ ዓመት በኋላ ላሰቡት በቀል ምቹ መሰረትን ጥሏል። ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ለሚፈልጉ ሃይሎችም የታሪክ መሰረት ጥሎላቸዋል። ምኒሊክ ይህን ቀድመው የሚያውቁበት እድል ባይኖርም፣ ችግሮቹን ለማየት ግን የሚሳናቸው አልነበሩም።

…….እንደው ግን እጠይቃለሁ! አንድ በሀገሩ ሉዓላዊነት የሚያምን መሪ፣ በነፃነት የሚያምን መሪ…. የውጫሌ ስምምነትን መፈረም ለምን አስፈለገው? መልሱ ጠፍቶኝ አይደለም። እንዲሁ ጥያቄውን ለማስቀመጥ ከመፈለግ ነው….
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተሻለ የምትለው ዘመናይ መሪ ብትሉኝ ምኒሊክን እጠራለሁ። በኤርትራ ጉዳይ ግን….

በአድዋ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሌሎች ፅሁፎች ይኖሩኛል ብዬ አምናለሁ።

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...