የኛ ሰው ሆዱን በጣም በመውደዱ የሚወደውን ሰው እንክዋ ሲያቆላምጥ “ሆዴ” ብሎ ነው:: ግፋ ካለ “ማሬ” ቢል ነው:: ማርም የሚበላ ነው; ሆድም ምግብ ከታች ነው::
ምሳሌዎቹ እራሱ በሆድ ዙሪያ ድክ ድክ የሚሉ ናቸው::
-የወፍ ወንዱን የሰው ሆዱን አያውቁም!
-ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል
-ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል
-ሆድ ካገር ይሰፋል (እና ሊበላት?)
ብዙ ወዘተ…
ከጉቦ አቅም እንኯ “መብላት” ነው የሚባለው::
“ቡዳ በላው” ይባላል:: ዓይን እና ሆድ ምን አንድ አደረጋቸው??
ሁሉን ነገር “ከመብላት ፖይንት ኦፍ ቪው(ሆድ)” ነው የሚመለከተው::
ልጅ ሆነን ጠጠር ስንጫወት “አይጥ አበላሁት” እየተባለ; ቀማር ብንጫወት “ይሄን ያህል በላሁት” እየተባለ; ሀገሩ የሆድ ሆነ ቀረ::
ጥላሁን ምን አለ? …..”ሆድ ይፍጀው!”
በቀኝም በግራም ሆድ ነው:: ዓመት በዓሎቻችን ከመንፈስ ይልቅ ለሆድ የቀረቡ ናቸው- ሆዳዊ አድርገናቸዋል::
ከዚህ ሁሉ እያዘነ ወደ ቢላ ከሚጋዝ ከብት ቀንሶ ስንቱ ለተራበ ያበላል? አብዛኛው ከግዋዳ ብቅ የሚል ታሪክ የለውም::
ሀገሩ በጣም ሆድ ላይ ከማተኮሩ የተነሳ አብዮት እንክዋ ሲፋፋም ልጆቿን የምትበላ ነው የምትሆነው:: ሆዳም አብዮት! ለነገሩ በማን ትውጣ?
ዶናልድ ሌቪን በ Wax and Gold መፅሐፉ ገበሬዎችን የሕይወት ዓላማቸውን ሲጠይቃቸው ምን አሉ? -“ሰርቶ መብላት!”
ስንፀልይ ከፍ ብላ የምትሰማው ፀሎታችን የትኛዋ ናት?
“የዕለት እንጀራችንን ስጠን”የምትለው!……..