በአንዲት ሀገር ላይ
ጨለማና ብርሃን ክፉኛ ተጣሉ
አሸናፊ እስኪለይ ድብድብ ቀጠሉ
የጨለማን ግንባር-አናቱን ሊበሳ ብርሃን ይጥራል
የጨረራ መዓት ጨለማን ለመምታት ተግቶ ይወረውራል
እውሩ ጨለማ መርግ መርግ ፅልመት ከአካሉ ያነሳል
ድቅድቅ አሰልፎ ብርሃን ላይ ያፈሳል
ተው ባይ በሌለበት
ሃይ ባይ በጠፋበት
ጨለማና ብርሃን መስማማትን ስተው
ድቅድና ጨረር በዚህ’ዛ አንስተው
እንደ ሀገሩ ወግ
ጎራቸውን ወደው
ለጎራቸው ሰግደው
ይጠዛጠዛሉ
ጨለማና ብርሃን ቀዬውን ሲመስሉ!
ሰዐቱ ይነጉዳል
ጨለማ ላይ ጨረር
ብርሃን ላይ ፀሊም ሳይፎርሽ ይወርዳል
ከጨለማ ወገን በብርሃን ጨረር እየተከፈለ; እየተላቀቀ
ብዙ አካል ወደቀ
ከብርሃን ወገን-
የጨለማ ድቅድቅ እየዘነበበት
በዛሄ ብርሃን ጠፍቷል የገባበት
ሰዐቱ ይነጉዳል
ጨለማና ጨረር በሁለት ጫፍ ይወርዳል
መደማመጥ የለም
መነጋገር የለም
ያሳብ የእግር ዳና ያልጎበኘው ሀገር
ቅዋንቅዋ አይሰማውም ከመሳሪያ በቀር!
ሰዐቱ እየገፋ ለዐይን እየያዘ
የሁለቱም ወገን ልብ ቂም እንዳረገዘ
የቀውጢዋ ቅፅበት የጦሩን አውድ ያዘ
የሰዐቱ መግፋት
ለጨለማ ብርታት
ለብርሃን መረታት
አምጥቶ አራገፈ
ብርሃን ትከሻ ላይ ጨለማ ገዘፈ::
ትጥቅ የፈታው ብርሃን በእግሬ አውጪኝ ሽሽት ባገኘው ተመመ;
ድል የነሳው ፅልመት ጨለማ እያፏጨ, ጨለማ እያዜመ
በየጥጋጥጉ እግሩን አረዘመ!
የጦር አውዱን ዜና ተራኪ ይፅፋል
ከአውደ ዜናው መሃል ይህም ቃልተፅፏል:
ግዙፉ ጨለማ ሀገሩን ቆልፎ አደረገው ቀንጃ
መጥኔ ለብርሃን መንጋቱንም እንጃ!
ግን ተስፋ መልካም ነው
በረሃ ልብ ላይ ለመብቀል ይዳዳል
ከጨለማ አልጋ ላይ ሕልሙን ይከትባል-
በብርሃን ፀዳል
ይረፍድ እንደሁ እንጂ ሀገሩ ሲነቃ አብሮ ይማልዳል
የጦር አውዱን ዜና ተራኪው ይፅፋል
ከአውደ ዜናው መሀል ይህም ቃል ተፅፏል
‘ቀንቶት ወይ በርትቶ ሃሳብን ከቀማ
ከብርሃን ይልቅ ብርቱ ነው ጨለማ!”